Back to Front Page

ሲዳማ - አስረኛዋ ‹‹ክልል››፤ ወደ ብልፅግና? ወይስ…?

ሲዳማ - አስረኛዋ ‹‹ክልል››፤ ወደ ብልፅግና? ወይስ…?

 (ሢሣይነሽ መንግሥቴ) 11-24-19

የሲዳማ የ‹‹ክልል››ነት ጥያቄ ከተነሳ፣ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የተለያዩ ዕውቅ ግለሰቦች እና ‹‹የሲዳማ አርነት ንቅናቄ/ ሲአን›› ጥያቄውን አንግበው ከ‹ክልሉ›› ገዢ ፓርቲ - ደኢህዴን ጋር ግብግብ ፈጥረው ከርመዋል፡፡ አንዴ የደኢህዴን ሃይል በርትቶ ሲጨፈልቃቸው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አነርሱ ሃይል አግኝተው ሲገዳደሩት እንደሚያነሱት ጥያቄ ዕድሜ ረዥም ዘመናት አልፈዋል፡፡ ነገር ግን እንዳለፈው ሁለት ዓመት ጥያቄው ጎልቶ በሁሉም ጎራ ታውቆ የተስተዋለበት ጊዜ አልነበረም፡፡

በ2011/12 ወቅት በዩቲዩብ የሚተላለፍ አንድ የቴሌቪዥን አገልግሎት ላይ እሰራ ነበር፡፡ ይዘቱ የውይይት እና የዜና ትንታኔ የሆነ ዝግጅት በዋና አሰናጅነት አቀርብ ነበር፡፡ በምሰራበት ጊዜ የሲዳማ ጥያቄ (11/11/11ን ልብ ይሏል፡፡) ገንፍሎ ፍጅት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህንን ፍጅት በዜና መልክ ከመሸፈን ባሻገር፣ የውይይት ፕሮግራሞችን እንቀርፅ ነበር፡፡ የትኩረት ማዕከላችን ሲዳማ ነበረች፡፡ ቢያንስ፣ ስምንት ፕሮግራሞችን በዚሁ ላይ ተንተርሰን ቀርፀናል፤ የሲዳማ ጉዳይ የደቡብ ‹‹ክልል››ን ህልውና - በተለይም የደኢህዴን በህይወት የመኖር እና ያለመኖር ዕጣ የሚወስን ስለሆነ!...

በርግጥ፣ በስራ ብቻ ሳይሆን በትውልድም ሲዳማ ትቀርበኛለች፡፡ አባቴ ከቅድመ-አያቴ እስከ እናት እና አባቱ ድረስ፣ ተወልዶ - ተዛምዶ ያደገው እዛው ሲዳማ ነበር፡፡ አያቶቼ፣ አጎቶቼ እና አክስቶቼ ከአለታ ጩኮ እስከ ወንዶ፣ ከሃዋሳ እስከተለያዩ የሲዳማ የገጠር ቀበሌዎች ዘልቀው ኖረዋል፤ እየኖሩም ነው፡፡ ጥያቄው ካሳሰበኝ፣ አንድም በሚዲያ ሰውነቴ፣ ሁለትም በቤተሰቦቼ ምክንያት ነው፡፡

ህዝቡ ተወስኖ የሚደግፈው የ‹‹ክልል››ነት ጥያቄ፤ መነሻ ሰበቦች ሁለት ናቸው፤ የህዝቡ የመልማት ፍላጎት እና የልሂቃኑ የስልጣን ጥም! ሁለቱ ሲታዩ ‹‹አይጠጌ - አይነኬ›› ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን አይደሉም፡፡ ህዝቡ እርሻውን አጎልብቶ በኢኮኖሚ የማደግ የወል ህልም አለው፡፡ ከጓሮ አትክልቱ ጋር ቀን ከሌሊት ሲፋለም የሚውለው ለዕድገት ነው፤ መቆፈሪያውን ይዞ፡፡ ሲዳማ ‹‹ክልል›› ከሆነች፣ የዕድገት ፍላጎቱ በአንዴ እንደሚሟላ፣ ፖለቲከኞች በድርሻቸው ይሰብካሉ፡፡ ህዝቡ ቶሎ አማኝ ነው፡፡ አምኖም ይከተላቸዋል፡፡

ልሂቃኑን አምኖ በመከተሉ፣ የ‹‹ክልል››ነት አምሳያውን - ‹‹ሻፌታ››ን መረጠ! (እዚህ ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ የ‹‹ጎጆ›› {በ‹‹ክልል››ነት የመቀጠል} ድምፅ እንደምን ሊታፈን ቻለ? በተለመደው የማጭበርበር ስልት?)

ህዝቡ በሃቀኛ የድምፅ አሰጣጥ መምረጡ ላይ - እንዲሁ - ብንተማመን፣ አዲሲቱ - አስረኛዋ ‹‹ክልል›› መፃዒ ዕድሏ ምን እንደሚመስል በአጭሩ እንገምት፡-

ቢሆን-1፡- ‹‹ክልሉ›› የተወሰነ ዕገዛ ከቀድሞ እናት ‹‹ክልሉ›› ያገኛል፡፡ በድጋፉም እየተጠናከረ ይመጣል፡፡ ባለሚዲያ (‹‹ሲዳማ ሚዲያ ኔትወርክ››ን ያስተውሏል፡፡) እና ባለ‹‹ኤጄቶ›› ልሂቃን የዘመናት የስልጣን ፍላጎታቸውን በመጪው ምርጫ ላይ ያሳካሉ፡፡ የተስፋፊነት ህልማቸውን ለማጠናከር ልዩ ሃይል ያቋቁማሉ፡፡ መሃል ላይ ለኦሮሚያ እና ለሲዳማ ቅርምት የተተወችውን - ጌዲዖን ይጠቀልላሉ፡፡ ለምለሟን ምድር የስልጣናቸው መደላደያ ያደርጓታል፡፡ ህዝቡ ሲመኘው የባጀበትን ምኞት ያኮላሹታል፡፡ እንደቀድሞው ድህነት ይባባሳል፤ የልሂቃኑ ሰውነት አየሞላ፣ ገፃቸው እየቀላ ይመጣል፡፡ ‹‹ክልሉ›› በአስከፊ አዙሪት ውስጥ ይላቁጣል፡፡

Videos From Around The World

ቢሆን-2፡- ‹‹ክልሉ›› ይጠናከራል፡፡ ልሂቃኑ ይለዝባሉ፡፡ ከኦሮሞ ፅንፈኛ ልሂቃን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያርቃሉ፡፡ ጌዲዖን ከመቀራመት ይልቅ የህዝቡ የልማት ጥያቄ ላይ ቀልባቸውን ሰብስበው ይሰራሉ፡፡ በመጪው ምርጫ እስኪወዳደደሩ ድረስ፣ ከዞኑ መዋቅር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመመካከር ይሰራሉ፡፡ ልዩ ሃይል የማቋቋሙ ሃሳብ ውድቅ ይሆናል፡፡

ሁለቱን ‹‹ቢሆኖችን›› ስናመሳክር፣ የሁለተኛው ‹‹ቢሆን›› ተመራጭነት አያጠራጥርም፡፡ ሰላም ማጣትን፣ መራብን፣ መታረዝን፣ መጠማትን የሚሻ ወገን የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ካለም፣ ልበ-ድንጋይ ፍጡር መሆን አለበት፡፡ ግን ነገሮች ተገልብጠው፣ ‹‹ቢሆን-1›› ካየለ፣ የማያባራ የዕልቂት ቃጣና ይሆናል - ሲዳማ፡፡ ዘመዶቼ የዕልቂቱ ተካፋይ ከመሆን የሚያግዳቸው ሃይል አይኖርም፡፡ ስለዚህ ሲዳማ ወደ ብልፅግና እንድታመራ (እንደአምራች አካባቢነቷ) ልሂቃኑ አደብ ገዝተው እንዲንቀሳቀሱ ማሳሰብ አስፈላጊ ነው፡፡

Back to Front Page