Back to Front Page


Share This Article!
Share
አራምባና ቆቦ፦ፓለቲከኞችና ህዝባዊ አላማ በኢትዮጵያ

አራምባና ቆቦ፦ፓለቲከኞችና ህዝባዊ አላማ በኢትዮጵያ

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 3-3-19

በንጉሱ ዘመን ነበር ከአድዋ ከመጡ አንድ ሰው ጋር ገዳም ሰፈር አካባቢ በአጋጣሚ የተገናኘነው። ከአድዋ አዲስ አበባ ድረስ ያመጣቸውን ጉዳይ ምን እንደሆነ ስጠይቃቸው ለመሬት ክርክር ይግባኝ ብየ መጥቼ ነው አሉኝ። ስንት ጊዜ እንደቆዩ ስጠይቃቸው 18 ዓመት እንደሆናቸው ነገሩኝ።   መሬቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ይከታተላሉ ወይ ብየ ሰጠይቃቸው የመለሱልኝ መልስ አፌን ያስያዘኝ ነበር፤ እንዲህ አሉኝ፦ "ሄጄም አላውቅ፣ ጠይቄም አላውቅ!" እግዚአብሄር ያሳያችሁ ከአድዋ 1000 ኪ.ሜ. ያህል ተጉዘው የመጡበት ዋናውን ጉዳይ ረስተው ዋና ጉዳያቸው መሬታቸውን ለማግኘት የተጠቀሙበት ሙግቱ ብቻ ሆኖ ቀረ።

Videos From Around The World

የፓለቲካ መሪዎች ዋና ግብ ምንድነው ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ ግልፅና የማያከራክር ነው። ወደዱትም ጠሉትም የፓለቲካ መሪዎች ዋና ግብ የህዝቡን አካላዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነትን ማረጋገጥ ነው። አሁንም በፊትም እየተስተዋለ ያለው ግን ይህ አይደለም። ፓለቲካው ለህዝብ ኑሮ እድገት መሆኑ ቀርቶ የፓለቲካ ሽኩቻው ዋናው ግብ የፓለቲካ ሽኩቻው ራሱ የሆነ ይመስላል። ይህ እውነታ መሬት እንዲረግጥ በማድረግ የሚረዱኝ የአራት ታላላቅ አሜሪካውያን ጥቅሶችን ከዚህ ቀጥሎ አስፍሬአለሁ፦

1. "ፓለቲካ ፅዱ ሆኖ እንዲቆይ የሚያደርገው አላማ ቢኖር ለአገርና ለህዝብ የሚበጅ ጥሩ ነገር የመስራት አላማ ብቻ ነው።" (ሄነሪ ፎርድ- ታላቁ የፎርድ መኪናዎች አምራች ኩባንያ ባለቤት )

2. "ፓለቲካ የመጨረሻ ግብ ሳይሆን ወደ ህዝባዊ ግብ የሚደረስበት መሳርያ ነው። ሲሆን የሚስተዋለው ግን ፓለቲካ ግልፅነትና ሃቀኝነት ያለበት የህዝብ አገልግሎት ሳይሆን በሸርና በራስ ወዳድነት የተሞላ ሂደት ነው።" (ካልቪን ኩሊጅ-- የአሜሩካ ፕሬዚዳንት የነበሩ)

3. "አንድ የፓለቲካ ፓርቲ መሠረቱን በሃቅና በሞራል ላይ ካልገነባ የፓለቲካ ፓርቲ ሳይሆን ስልጣን ለመያዝ የተዋቀረ ሴራ ነው።" (ድዋይት አይዘንሃወር-- የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና በሁለተኛው የአለም ጦርነት የህብረቱ ጦር ዋና አዛዥ የነበሩ)

4. "ፓለቲከኞች ከመመረጣቸው በፊት ሁሉም ነገር ለህዝብ ይላሉ፤ ተሳክቶላቸው ከተመረጡ በኋላ ግን ሁሉም ነገር ለራሳችን ይላሉ። ለመነሳት ህዝቡን ይጠቀማሉ ልክ ፈረስን እንደሚያደርጉት። ከፈረስ ኮርቻ ላይ ዘለው ከመውጣታቸው በፊት ፈረሱ ጆሮ ላይ የቁልምጫ ቃላት ሹክ እያሉ አንገቱን ይዳብሱታል። ኮርቻው ላይ ወጥተው ከተደላደሉ በኋላ ግን የሚከተለው  አለንጋና እርግጫ ነው።"  (ክርስትያን ኔስቴል ቦቪ--አሜሪካዊ ደራሲ)

የፓለቲካ አመራር ለውጥ ማለት በመሰረቱ ህዝባዊውን አላማ (ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትና ደህንነት) ከበፊቱ አመራር በበለጠ ሁኔታ ማሳካት ማለት ነው። አሁን በኢትዮጽጵያ እየታየ ያለው ግን መሻሻል ሳይሆን መባባስ ነው። "አዲሶቹ" መሪዎች ድሎቻቸውን ሲቆጥሩ የህዝቡ ደህንነት በከፋ ሁኔታ አደጋ ላይ ወድቋል፤ የህዝቡ ኑሮ የቁልቁለት መንገድ ጀምሯል፤ ስራ አጥነት ብሶበታል፤ በተለያዩ ክልሎች ህዝብና ህዝብ ለልማት ትብብር ሳይሆን ሳንጃ ለሳኝጃ ለመሞሻለቅ አሰፍስፏል፤ ህዝብ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከቀየው እየተፈናቀለ ዋናው የኢኮኖሚ ዋልታ ግብርና እየተስተጓጎለ ነው፤ ህዝብ በመንፈስ እየተራራቀ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ሲፈልጉ የሚያነሱት ሳይፈልጉ እንደአሮጌ ቁና የሚወረውሩት ማንነት ሆኗል፤ ፓለቲከኞች በርስበርስ ውድድርናና ፉክክር ላይ ተጠምደው የአገሪቱን የቁልቁለት ጉዞን ለማስተዋልና የፓለቲካ ጥቅማቸውን ወይንም ስልጣናቸውንም ቢሆን መስዋእት አድርገው ይህን ጉዞ የመቀልበስ ስሜት ብዙም አይነበብባቸውም። ብዙ ወጪ አውጥታ አዲስ አበባ ብትሞሸር ለድሃው አዲስ አበቤ እራት ሆና በሳህን አትቀርብም። መጠለያ ለተቸገረው ህዝቧ ጣርያና ግድግዳ ብትሆንለት ግን ባይበላም በጅብ ከመበላት ከሃሩርና ቁር ይድናል። በኢትዮጵያ ውስጥ ፓለቲካ እያገለገለ ያለው ፓለቲካውን ራሱን እንጂ ዋና አላማው የሆነው ህዝቡን ሊሆን አልቻለም።

ይህ ሁሉ እየሆነ እያለ ፓለቲከኞች ተጨንቀው የሚያወሩት ስለምርጫ ነው። ይህ ምርጫ፣ ያውም ተስማምተው በሰላም የሚያከናውኑት ከሆነ ነው፣ የሚካሄደው ከአንድ አመት በኋላ ነው። በየቀኑ አስጨናቂና አሳዛኝ የሆነ አዳዲስ ክስተት በሚከሰትበት አገር አንድ አመት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግሁድ ነው፤ የበለጠ ድህነት፣ የበለጠ ግጭት፣ የበለጠ መፈናቀልና በቀላሉ የማይቀለበስ የህዝብ መቃቃርና መራራቅ። "እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ ላሜ የምትወልደው ለፍልሰታ" የሚለው የአበው ተረት እውን እየሆነ ነው። ህዝብ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የደህንነት ችግሩ እንዲፈታለት የሚፈልገው ዛሬ እንጂ ነገ አይደለም። የህዝቡ መሠረታዊ ችግር ክልል መሆን አለመሆን አይደለም፣ ህዝብ በልቶ ለማደር ወረዳነት፣ ዞንነት፣ ክልልነት አይወስነውም። አዲስ አበባ የአማራ ትሁን፣ የትግሬ ትሁን የኦሮሞ ትሁን ለፓለቲከኞች ሹካና ማንኪያ ከመሆን አልፎ በህዝቡ የኖሮ እድገት ላይ የሚያመጣው ልዩነት የለም። ለተራው የኦሮሞ ህዝብም ቢሆን አዲስ አበባ በኦሮሚያ ርስተ መዝገብ ላይ ስሟ ቢፃፍ ከኑሮው ላይ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም። የወልቃይት፣ የመተከል፣ የራያ ህዝብ ከአማራ ጋር ሲቀላቀል ገነት ከትግራይ ጋር ሲሆን ሲኦል ፣ እንዲሁም በግልባጩ፣ የሚሆንበት ምክንያት የለም። የትም ቢሆን "ያው በገሌ" እንዳለችው ድመት ነው። ኑሮው የሚመስለው ማሳውን እንጂ መቐለን ወይንም ጎንደርን አይሆንም።

ለመደምደም ያህል፣ የሃላፊነት ስሜት የሚሰማቸው ኢትዮጵያዊ ፓለቲከኞች ካሉ ህዝቡን መርዳት ያለባቸው አሁን ነው። ዋናው አላማቸው ህዝብ ከሆነ ሽኩቻውና ፍጥጫው ባስቸኳይ ማቆም አለባቸው። ችግሮች ከምርጫ በፊት በበቂ ሁኔታ በጋራ ምክክር ሳይፈቱ፣ በእንዲህ አይነት ፍጥጫ፣ ወደ ምርጫ መግባት የባሰ አደገኛ የሚሆን ይመስለኛል። የምርጫ ውጤት በፀጋ የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ የሚወሰነው ከምርጫው ቀደም ብሎ መተማመን ሲፈጠር እንጂ ልዩነቱና ፍጥጫው እንዳለ ሆኖ ወይንም ተባብሶ ወደ ምርጫ ከደረስን እሳት ላይ ጋዝ ማርከፍከፍ እንደሚሆን እሙን ነው። አፍሪቃ ውስጥ ተጣልተው የቆዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁ እንደተጣሉ ወደ ምርጫ ሲገቡ ከምርጫ በኋላ አውራ መንገድ ላይ የምናየው ጎማ ሲቃጠል እንጂ ተፎካካሪዎቹ "እንኳን ደስ አላችሁ፣ ወሳኙ የአገር ጉዳይ ነውና እንረዳችኋለን" ሲባባሉ አይደለም። አምላክ ልብ ይስጠን!! ለዚች አጭር ህይወታችን አገር ቀድማን እንድትሞት አንፍቀድ። ኢትዮጵያ የዚህ ትውልድ ብቻ ንብረት አይደለችም። ያለፈውም ያሁኑም የወደፊቱም ትውልድ ንብረት ናት። ማንም ቢሆን በአገሪቱ ህልውና ላይ የመወሰን ስልጣን የለውም። ሚናችን ደቀደምቶቹ ካስረከቡን ኢትዮጵያ አጉድለንና አሰናክለን ሳይሆን አገሪቱን አሻሽለንና አጎልብተን ለወደፊት ትውልድ የማቀበል ብቻ ነው። የያንዳንዱ የዱላ ቅብብሎሽ አትሌት ስራ በተቻለው መጠን በመሮጥ ለሚቀጥለው አትሌት ማቀበል እንጂ ዱላውን ይዞ ቁጭ የማለትና ውድድሩን የማሰናከል መብት የለውም።

Back to Front Page