Back to Front Page


Share This Article!
Share
ፖለቲካዊ ቀውሱ እንደቀጠለ ነው

 

ፖለቲካዊ ቀውሱ እንደቀጠለ ነው

ፍስሃ መረሳ

02/02/19

 

ባለፉት 10 ወራት የአገራችን ፖለቲካዊ ይዘትና ገፅታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል ማለት ይቻላል ፡፡ ፅንፈኛው ስልጣን የተቆጣጠረው ቡዱን የመጀመሪያ ስራውን ያደረገው ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማፍረስ ለሱ የተመቸና ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን ያለውን ፍላጎት ለማሟላት የሚያችላቸውን መደላድል ለመፍጠር ሲል  የአገሪቱን ፖለቲካዊ ችግር ከግዜ ወደ ጊዜ እንዲባባስና አገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስ እንድትገባ የመሪነቱን ሚና በመጫወት እነሆ በዚህ አጭር ጊዜ በፖለቲካም በኢኮኖሚም በሰላም እጦትም የቆየ ገፅታችን እንዲቀየርና እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ ህልውና ላይ ስጋት እንዲኖረው የሚያደርግ አዲስ ፖለቲካዊ ክስተት እንዲፈጠር አድርጓል ፡፡

Videos From Around The World

ትናንት የነበረው የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ በአጠቃላይ የጀመርነው የተስፋና የእድገት ጉዞ ቆሞ በአንፃሩ ዜጎች ሰላም የሚናፍቁበት ተስፋቸው ጨልሞ የቀጣይ ሂወታቸውን ከማሰብ ይልቅ ነገ ምን ይከሰት ይሆናል በሚል የዕለት ተዕለት ኑራቸውን በቅጡ መምራት የማይችሉበት አሳሳቢ ፖለቲካዊ ሁኔታ ተፈጥሯል ፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያለበት ሁኔታ ለመመዘንእንዲመች ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች እንደመነሻ መውሰድ የበለጠ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ግልፅ እንዲሆን ያደርገዋል ፡፡

 

መንግሥት ራሱ ሰላም እንዳይኖር እያደረገ ነው

 

በየትኛውም አገር በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በተለይ በህዝብ ምርጫና ውሳኔ ወደ ስልጣን የመጣ ሃይል ተቀዳሚ ተግባሩ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በማክበርና በማስከበር የአገሪቱ ሰላምና ድህነትን አስጠብቆ መሄድ የግድ እንደሆነ የማያከራክር ጉዳይ ነው ፡፡ እንደ መንግሥት ያለው ህግና ህግን የማስከበር ሃላፊነት የተሰጣቸውን ተቋማት በመምራት የዜጎችን ድህነትን ማስጠበቅ ካልቻለ መንግሥት አለ ማለት አይቻልም ፡፡ አሁን በአገራችን በተግባር እየታየ ያለው ችግር በስልጣን ያለው ቡድን ይቅር ስርዓት ሊያስከብር ሁሉም የሰላም ፀር የሆኑ እንቅስቃሴዎች መነሻቸው ራሱ በስልጣን ላይ ያለው ሃይል መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ግጭትና ህገመንግስታዊ ጥሰት የደቡብ ክልል መፍረስ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ከሌሎች ክልሎች እንዲጋጭ ማድረግ የአማራ ክልል መንግሥት በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ማወጅና በትግራይ በቅማንት ተወላጆች ዘር የለየ ጥቃት እንዲፈፀም የማድረግ እንቅስቃሴና በፈዴራል ደረጃ ብሄር የለየና ወደ ግጭት የሚያነሳሳ በሚድያ የታገዘ ዘር የለየ የጥላቻ ቅስቀሳዎች ስናያቸው ሁሉም አራት ኪሎ መዳረሻው ያደረገ ጥገኛው ሃይል በእሱ አስተባባሪነት የሚፈፀሙ ፀረ ሰላም ዘመቻዎችና ድርጊቶች እነሆ አገሪቷን ወደ መውጫ የሌለው ቀውስ እንድትገባ አድርጓታል ፡፡

 

የአገሪቱ ኢኮኖሚም በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው

 

ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር እንደሚቆም ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው ፡፡ በየቀኑ የዜጎች ሞትና መፈናቀል ዜና የሚሰማባት አገር እስከሆነች ድረስ የውጭም የውስጥም ኢንቨስትመንት ይኖራል ተብሎ የማይታሰብ ነው ፡፡ በተግባር በዚህ አጭር ጊዜ እየሆነ ያለውም ይህን ችግር እንዳለ በየጊዘው ይፋ ከሚሆኑ አንዳንድ መረጃዎችን እንኳ በማየት መረዳት አያስቸግርም ፡፡ ግብር መሰብሰብ በአብዛኛዎቹ ክልሎችና ፌደራል መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ ዛሬ ብዙ ሜጋ ፕሮጀክቶች ሳይቀሩ በበጀት እጥረት ግንባታቸው እንዲቆም ተደርገዋል ፡፡ ይቅር አዳዲስ ፕሮጀክቶች ሊሰራ የተጀመረውንም ማስቀጠል እንካ  አልተቻለም ፡፡ የኤክስፖርት ገቢ ከባለፈው ጊዜ ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል ፡፡ ማንኛውም እቃ ከውጭ ለማምጣት የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ብዙ ወራት መጠበቅ የግድ ሆነዋል ፡፡ የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከባለፈው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ የመንግሥት ሪፖርት ይፋ አድርጓል ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ስራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ በተለይ በከተምች አከባቢ ዝርፍያና ሌብነት እየተስፋፋ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው ፡፡ የዚህ ድምር ውጤት አገሪቱ ወደ ውጭ ሃይሎች የልመና እጇን እስከ መዘርጋት የደረሰችበት ሁኔታ እየተፈጠረነው ፡፡ ይህም ራሱ መንግሥት የፈጠረው ችግር መሆኑ ግልፅ ነው ፡፡

 

የጥላቻ ፖለቲካ አሁንም እንደቀጠለ ነው

 

በህግ የሚመራ መንግሥት እስከሌለ ድረስ በአገሪቱ ያሉ ዜጎችን በማቀራረብ አንድ የጋራ ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ሊፈጠር እንደማይችል የታወቀ ነው ፡፡ በተለይ አገራችን የብሄርና የብሄረሰቦች አገር እንደመሆንዋ የነዚህ ህዘቦች ጥቅምና መብት አስከብሮ መሄድ እስካልተቻለ ድረስ ማንኛውም በሃይልና ከመተማመን ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ውጤቱ ምን እንደሚሆን የቅርብ ጌዜ በደርግ ስርዓት የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ በቂ ማሳያ ነው የሚሆነው ፡፡ በዚህ አንፃር አሁን የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥፋት እስከ ዘር የለየ የጥላቻ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር እየተመራ በሚድያዎች እየታጀበ ወደ ግጭትና ብጥብጥ የሚወስድ ከፍተኛ ቅስቀሳ በመካሄድ ላይ ይገኛል ፡፡ ሌላው ይቅር ክልሎች መምራት ሲያቅተው ይህ ፀረ ዴሞክራሲ ሃይል የፌዴራል ስርዓት ለማፍረስና ክልሎችን በበጀት ለመያዝና ለመቆጣጠር እንደማስፈራሪያ መሳርያ እየተጠቀመበት ይገኛል ፡፡ ስለዚህ በፖለቲካ ረገድም ሲታይ በመከባበርና በመቻቻል ህዝቦች ተቀራርበው በእኩልነት የሚኖሩባት አገር መፍጠር ሳይሆን በሚረጨው ዘረኛና የጥላቻ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ከጊዜ ወደ ጊዚ መቃቃርና አለመተማመን እንዲነግስ በማድረግ የአገሪቱ ህዝቦች ቀጣይ ህልውና አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል ፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህ ከላይ ያየናቸው ችግሮች ብቸኛው መንስኤ በስልጣን ላይ ያለው ቡዱን ወደድክም ጠላህም ተደመር በሚል ፀረ ዴሞክራሲ አካሄድ ሰላም ዲሞክራሲና ልማት እንዲጠፋ በማድረጉ ውጤቱም ወደ የማያቋርጥ ቀውስ እንድንገባ በማድረጉ አሁን ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመምጣቱ ዞሮ ዞሮ ይህ ሃይል ራሱ በፈጠረው ችግር የኣገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ አሁንም እንደቀጠለ ነው ፡፡

 

Back to Front Page