Back to Front Page

ኦህዴድ ከየት ወዴት?

ኦህዴድ ከየት ወዴት?

 

ክፍል አንድ

 

ከኡስማን ሙሉዓለም

ታህሳስ 2012

 

 

ወድ አንባቢዎች! በኢትዮጵያ የቅርብ ግዜ ታሪክ አረመኔው የደርግ ስርዓት ከስልጣን ለማውረድ የትጥቅ ትግል ካከሄዱት አራት ድርጅቶች ውስጥ ሰለሆነው ኦህዴድና ከሱ ጋር ተያየዥ የሆኑትን ጉዳዮች በማነሳት ድርጅቱ ከየት ወዴት እንደተጓዘ በሁለት ከፍል በተከታታይ ለማየት እሞክራሎህ፡፡

 

 

የኦህዴድ አፈጣጠርና ዕድገት

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኦህዴድ ረዥም ዕድሜ ካለው ኦነግ ቀጥሎ የኦሮሞ ጥያቄ ለመመለስ አማራጭ ፕሮግራም ይዞ የተፈጠረና የተደራጀ ድርጅት ነው።ኦህዴድ ደርግ ከስልጣን ለማውረድ በተካሄደው የትጥቅ ትግል ቀድመው ከጀመሩ ድርጅቶች ማለትም ከህወሓትና ከኢህዴን ጋር በመሆን የራሱን ታሪክ ፅፏል፡፡ ኦህዴድ በትግራይ ነፃ በወጡ አካባቢዎች መደራጀት ጀምሮ በሰላሌ አከባቢ ደራ በተባለ ቦታ ህልውናውን በይፋ በማወጅ የኦሮሞ ህዝብን ማደራጀትና ማታገል ጀመረ።

 

ያኔ ኦህዴድ የኢህአዴግ አባል በመሆን ከኢህዴንና ከህወሓት ግንባር ፈጥሮ ትግሉን አጠናከረ።በኢህአዴግ አመራርም በየደረጃው እኩል ተሳታፊ የነበረበት አደረጃጀት ነበረው።በስራ አስፈፃሚም በምክር ቤትም እኩል የሚሳተፍበት ሁኔታ ነበር።ከመጀመሪያው ጀምሮ ኦህዴድ ትንሽና ጀማሪ ድርጅት ነው በሚል አልተገደበም።ጀማሪነቱ፣ በቁጥር ትንሽ መሆኑና የልምድ ማነስ ክፈተቱ በሁሉም የግንባሩ ተሳትፎዎቹ አልገደበውም፡፡ ከነባር ድርጅቶች የተመክሮና የልምድ ልውውጥ በማድረግ አብሮ በመስራት ፈጥኖ ከወቅታዊ ሁኔታ እንዲሄድ የሚያስችለው ብቃት እየገነባና እየተታገለ ደርግን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ በተደረገው ወሳኝ ፍልሚያ ከሱ የሚጠበቀውን ድርሻ የተወጣ ድርጅት ነበር።በጎንደርና በጎጃም ሰፍሮ በነበረው የደርግ ጦር ላይ በተካሄደ የዘመቻ ቴድሮስ ኦፕረሽን ለመጀመርያ ጊዜ ተሳትፎ ጎጃም ውስጥ በነበረው ውግያ ላይ በመሳተፍ ደብረማርቆስን ተቆጣጥራል። ቀጥሎም በዘመቻ ቢሊሱማ በወለጋ፣ በአምቦና በደምቢደሎ በተካሄዱት ውጊያዎች ተሳትፏል። በተለይ ደምቢደሎ ላይ ሰፍሮ በነበረው የደርግ ጦር ከህወሓት እና ከኦነግ ሰራዊት ጋር በመሆን በአጭር ጊዜ በመደምሰስ የመዋጋት ብቃቱን ያሳየበት ሁኔታ ነበር።

 

የኦህዴድ ዕድገት ደርግ ከተደመሰሰ በኃላ

ኦህዴድ ደርግ ከተደመሰሰ በኃላም ከኦነግ ውጭ ለኦሮሞ ህዝብ ሌላ አማራጭ ሆኖ የቀረበ ድርጅት ነበር፡፡ በተለይም በኦሮሞ አርሶ አደር ቀስ በቀስ በከባድ ትግልና መስዋእትነት አለኝታ የሆነበት ሁኔታ ነበር።በወቅቱ ኦነግ በኦሮሚያ ከኔ ውጭ ሌላ ድርጅት ተላላኪ እንጂ ሐቀኛ የኦሮሞ ድርጅት የለም ብሎ ያወጀበት ነበር፡፡ ኦነግ ይህንን ሐሳቡ ለማጠናከር ተሃድሶ ወስደው መልሰው እንዲቋቋሙ የተደረጉትን የደርግ ሰራዊት አባላት የነበሩ ኦሮሞዎችን መልምሎ በአጭር ጊዜ ቁጥሩን ከፍ አደረገ፡፡ ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳና ሐይልም በመጠቀም በሰላማዊ ውድድር እንታገል የሚለውንና የኦሮሞን ህዝብ የሚጠቅም ፕሮግራም የነበረው ትንሹየኦህዴድ ድርጅትን አላንቀሳቅስ በማለት ያዋኩቡት ነበር።ኦህዴድይህን ሁኔታ በከፍተኛ ትዕግስት፣ ቆራጥነትና መስዋእትነት ተወጥቶ ነው የኦሮሞ ህዝብ ሀቀኛ መሪ ድርጅት ለመሆን በቅቶ የነበረው፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መመስረትና በተከታታይም በህዝብ ተመርጦ ክልሉን ለመምራት የቻለው።በገባው ቃል መሰረትም በኦሮሚያ የገጠር ልማት እንዲስፋፋና ሚልዮኖች ከድህነት ወለል እንዲወጡ ከላይ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ያሉት አመራራሮቹና አባላቶቹ ከፍተኛ ድርሻቸውን ተወጥተዋል።የኦሮሞ ህዝብም በኦህዴድ መሪ ድርጅቱ ስር ተደራጅቶና ተንቀሳቅሶ ለዚህ ከፍተኛ ለውጥ ወሳኝ ሚናውን ተጫውቷል።ህዝቡ በዕለታዊ እንቅስቃሴው በቋንቋው በአፋን ኦሮሞ እንዲጢቀምና እንዲማር፣ ባህሉ እንዲያጎለብት እና በሰፊው የኦሮሚያ ምድር የሰፈረው የኦሮሞ ህዝብ ገዥዎች የወለጋ፣ የሀረር፣ የባሌ፣ . . . ወዘተ ብለው እንዲለያይ ያደረጉበትን የአከባቢያውነት አጥር በጣጥሶ አንድነቱ ጠብቆ እንዲገናኝና ትስስሩ እንዲጠነክር ኦህዴድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

 

ኦነግ ከመንግስት ምስረታ ወጥቶ የትጥቅ ትግል በመላው ኦሮሚያ በሚያደርግበት ወቅትም ኦህዴድ የልማትናየፀጥታ ስራው አላስተጓጓለም ነበር፡፡ ህዝቡ ከጎኑ በማሰለፍና ህዝባዊ ሚሊሻ በማደራጀት የተከፈተበት ትንኮሳ እየመከተ የክልሉን ፀጥታ በማስከበርና በልማት ስራውም ውጤታማ ስራ ሰርቷል።ይህ የሆነበት ምክንያት ኦህዴድ ከተመሰረተበት ግዜ ጀምሮ ብዙ ብቁ አመራሮችን እየፈጠረ በመምጣቱ ነበር። በዛው ልክ በስልጣን ያለ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ስልጣንን በአቋራጭ የሚፈልጉም ተቀላቅለውበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በውስጥ ትግል እያጠራ ህዝባዊ ዓላማዎቹን እያሳካ ተጉዟል። በዚህም አሮሚያ ክልል በለውጥ ጎደና እንድትጓዝ ተግቷል፡፡

 

በዚህ ሁኔታ እያለ በኢህአዴግ አባል ድርጅት የተነሱ ልዩነቶች ወደ ኦህድድም መምጣታቸው አልቀረም፡፡ በ1993 ዓ/ም በህወሓት ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት በህወሓት ብቻ ሳይሆን በሁሉም የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች ተንፀባርቆ እንደነበር ይታወቃል።ኦህዴድ ውስጥም በጥቂቶች ቢሆንም ልዩነቱ ተከስቶ ነበር።ይህ ሁኔታ በተሃድሶ መድረኩ ተፈቶ አልፏል።ከዚህ ተሃድሶ ማግስትም ኦህዴድ በኦሮሚያ ፈጣን ዕድገት እንዲረጋገጥ መላ ህዝቡን ከጫፍ እስከ ጫፍ አንቀሳቅሶ በመምራት አንፀባራቂ ድል ተቀናጅቷል። ለውጡን ለማየት አሁን ያለችው ኦሮሚያ ደርግ ሲገረሰስ የነበረችው ኦሮሚያ ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው። ለዚህም ነው ኢህአዴግም ኦህዴድም ያለፈው ሃያ ሰባት ዓመት የጨለማ ዘመን ነበር ብለው ያልገመገሙት። የአብይና የደመቀ የተጠለፈው ኢህአዴግ ግምገማ ካልሆነ በስተቀር! የኢህአዴግ ግምገማ የተመዘገበው ለውጥ ማስቀጠል እምቢ አለን፣ እኛ አመራሮች ቅድሚያ ለስልጣንና ለራስ ጥቅም በመስጠታችን ለህዝቡ መሆን አቃተን ነበር ግምገማው በአጭሩ።

 

Videos From Around The World

በሌላ በኩል ደግሞ በድል ላይ ድል የተቀዳጁት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በድል መስከር ጀመሩ።ድሉ ገና ሚልዮኖችን ከድህነት ያልወጡ በተስፋ እየተጠባበቁ ያሉን ያላዳረሰ መሆኑን ረስተው የድል በሽታ የሆነውን እርካታ በሁሉም የግንባሩ ድርጅቶች አመራርና አባላት ተስፋፋ።ፈታ ዘና ማለት ተጀመረ።ይህ በሽታ በሁሉም ድርጅቶች በተለያየ ደረጃና መልክ ተንፀባረቀ።በኦህዴድም ይህ በሽታ በከፍተኛ ደረጃ መታየት ጀመረ።

 

የኦህዴድ የዝቅጠት መንገድ

ኦህዴድ የሚመራው ክልል ብዙ ሚልዮን ህዝብ ያለበትና ሰፊ መልከዓምድር የሚሸፍን ነው።በምንም መመዘኛ ቢሰላ ይህ ድርጅት በክልሉ ያስመዘገበው ድል ከፍተኛ ነው።ይህ ከፍተኛ የተመዘገበ ዕድገት ያላዳረሰው ያልሸፈነው ህዝብና አከባቢ መኖርና ራሱ የተመዘገበው ዕድገትም የሚፈጥረው ተጨማሪ ፍላጎት ሟሟላት የሚቻለው ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማረጋገጥ እንጂ በተመዘገበ የአንድ ወቅት ድል ሰክሮና ረክቶ ዘና ማለት ባልተገባ ነበር።ይሁን እንጂ ኦህዴድ ያሁሉ የከፈለው መስዋዕትነት ዘንግቶ ባገኘው ለውጥ መኩራራት በማብዛቱ ችግር ላይ መውደቅ ጀመረ። ይህንን ጉዳይ ተገንዝቦ የእርምት እንቅስቃሴ ለማደርግ ቢውተረተርም እንቅስቃሴው ለታይት ላይ ላዩን በማድረጉ ቆርጦ ከችግሩ መውጣት አልቻለም።

 

በውስጡም ለውጥ አስመዘገብን በሚሉና ኦሆዴድ ደክማል በሚሉ መካከል ልዩነት መፈጠር ጀመረ።የተለያዩ ቡዱኖችም ተፈጠሩ።አንዳንዱ በአካባቢያዊ መልክ፣ አንዳንዱ በዝርፍያና ጥቅም ላይ ተመስርቶ፣ አንዳንዱ ደግሞ ስልጣን የሚፈልግ ቡዱን መልክ የተቀራረቡና መጀመርያ ላይ ላላ ያለ አደረጃጀት የነበራቸው በኃላ ግን እየለዩ ተጠናክረው በመሄዳቸው የኦህዴድ አባል ብቻ ሳይሆን ከኦህዴድ ውጭም፣ የሌሎች እህት ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡና ተቃዋሚ ድርጅቶችም የሚያቁት ሀቅ እየሆነ መጣ።በድርጅቱ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከድርጅቱ ውጭ ከባለስልጣን ተጠግተው እንደመዥገር የህዝብ ሀብትን የሚዘርፉ ጥገኞች በየቡዱኑ ጎራ ለይተው ተሰለፉ።በወለጋ፣ በሃረር፣በሻሸመኔ፣በአዳማና በሌሎች የክልሉ አከባቢዎች መሬት በመቸብቸብ የከበሩ ጥገኛ ባለሀብቶች ብቻ ሳይሆኑ የኦህዴድ አመራሮችም ጭምር ቸርቻሪና አስቸርቻሪ በመሆን ይሳተፉ ነበር።ይህ በግላጭ እየተካሄደ ባለበትም በፍንፍኔም በድብቅ የኦህዴድ ባለስልጣን ሆኖ መሬት ያልሸጠና ሁለት ሦስት ቤት ያልገነባ ማግኘት ከበደ።እነሱ ራሳቸውም በድብቅ ያጋበሱት ሀብት ሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች ጭምር ሁሉም የሚያደርገው እስኪመስላቸው ድረስ ረሱት።ይሁን እንጂ በህወሓት፣ በብአዴንና በደህዴን በጣም ጥቂቶች ከሆኑት እና ከሁለትናከሶስት የማይበልጡ አመራሮች በስተቀር አብዛኛውአመራር መሬትም ቤትም የሌለው ነበር።ጥቂቶቹም በዓሊ አብዶና አርከበ የአዲስ አበባ ከንቲባነት ዘመን ለወታደራዊ መኮነኖችና ውጭ ለተመደቡ አምባሳደሮች (ሁሉም አልወሰዱም) በሚታደልበት ወቅት መሬት ወስደው መኖርያ ቤት የገነቡት ናቸው፡፡ የወታደራዊ መኮንኖቹ መሬት መውሰድና በኃላ የገነቡዋቸው ህንፃዎች ከድርጅቶቹ አመራሮች ተለይቶ የሚታይና የራሱ ታሪክ ያለው ነው።ከአጀንዳዬ ስለሚያስወጣኝ ስለ ወታደራዊ መኮነኖቹ እዚህ ፅሑፌ ላስገባው አልዳዳም።ነገር ግን እዚህ ላይ ሌሎች ድርጅቶች በተለይም ኦህዴዶች በኃላ ላይ እናንተም ሌቦች አሉዋችህ እያሉ ዘር ቆጠራ ውስጥ የገቡት ከመንግስት ለወታደራዊ አዛዦች የተሰጠው መሬትና እሱን ተጠቅመው የገነቡዋቸው ህንፃዎች ሽጠውም አትርፈውም መበልፀጋቸው አስታከው ነው፡፡ ኦሆዴዶች እኛ ብቻ አይደለንም ሌቦች ለማለት አጣቅሰው ይናገሩት እንደነበረ ታሳቢ አድርጎ ማለፉ ብቻ ተገቢ ነው።

 

 

ነገር ግን በኦህዴድ መድረኮች እና በኢህአዴግ ስብሰባም ድርጅታችሁ ውስጥ ቡዱኖች አሉ፡፡ አመራሩ አንድ አይደለም እየተባለ ቢነሳም የኦህዴድአመራሮች ሁሉም በጋራ አንዳንዴ ውሸት ነው ሲሉ አንዳንዴ ደግሞ በዝርዝር ነፃ ሁነን ተወያይተናል መራራቅ የወለደው እንጂ ምንም ተጨባጭ የሚያለያየን እንዳልነበረም አይተናል ብለው የራሳቸውን ካድሬንም እህት ድርጅቶችንም በነጭ ውሸትለማጃጃል ይሞኩሩ ነበር፡፡ ከስብሰባው ወጣ እንዳሉ ደግሞ ተባድነው ውስጥ ለውስጥ መናቆራቸውን ይቀጥሉበት ነበር።

 

ይህ በእንዲህ እያለ በኦሮሚያ ክልል ተጀምረው የነበሩ የልማት እንቅስቃሴዎች እየቀነሰና እየተቀዛቀዘ መሄድ ጀመረ።የኦሮሞ ህዝብ የመሰለውን ሃሳብ በነፃነት የመግለፅና ሂስ የማቅረብ ሁኔታ እየተገደበ ሄደ፡፡ ከላይ መበስበስ የጀመረው የኦህዴድ አመራር ታች ያሉት ሁኔታዎች የሚከታተል፣ የህዝቡን ድምፅ የሚሰማና የሚያዳምጥ ስላልነበረ የኦሮሚያ ሁኔታ ከመጥፎ ወደ ከፋ ሁኔታ እያደጉ ክልሉ ወደኃሊት ጉዞ ይጀምራል።እዚህ ላይ አንድ ጥሩ ምሳሌ ላንሳ።በኢህአዴግ ስብሰባስራ አጥነት በተመለከተ መፍትሔ ይቀየሳል።ይህን ለመተግበር የየአካባቢው ስራ ፈላጊዎች መዝግቡና እንደየፍላጎታቸው ይደራጁ፣ ስልጠና ይሰጣቸውና ብድር ይመቻችላቸው በዚህም ስራ አጥነትን መቅረፍ ይቻላል ተባለ።የኦህዴድ መንግስት ይህን ዕቅድ ይዞ በየዞኑ አወረደ።ወጣቶቹ ተመዝገቡ ተብለው ተመዘገቡ።እንደየፍላጎታቸውም መስራት በሚፈልጉበት ዘርፍ መርጠው በቡዱን በቡዱን ተደራጁ ተብለው ተደራጁ።ከዛ ስልጠና ይሰጣቹሃል ተብለው ቢጠብቁ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ ስልጠናው።በየአካባቢው ያሉ አመራሮች ይህን ያህል አደራጀን፣ ይህን ያህል ስልጣና ሰጥተን ስራ አስጀምረናል፣ ይህን ያህል ደግሞ ተደራጅተው ስልጠና እየተጠባበቁ ነው አሉ።ነገር ግን በጀት ስላነሰን ብናሰለጥናችሁም ወደ ስራ ማስገባት አይቻለንም ብለን ጠብቁ ብለናቸዋል ብለው ሪፖርት አደረጉ።በእርግጥምበኃላ ሲታይ የሰለጠኑም ብድርም አግኝተው ስራ የጀመሩ ነበሩ።ይሁን እንጂ እውነታው ሌላ ነበር፡፡ ስራ ጀመሩ የተባሉትምበአድልዎና በወገንተኝነት ነበር፡፡ አመራሮቹ የየራሳቸው ቤተሰቦችን አደራጅተው ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ዓይነት በጥቅምና በወገንተኝነት ስራ ያገኙ ነበሩ፡፡ ብዙሃኑ ስራ ፈላጊ ወጣት ተደራጅቶ ስልጠና አግኝቶ በከፍተኛ ትዕግስት ስራ ለማግኘት ሲጠባበቅ የነበረ ነው።

 

ኦህዴድ ራሱ አደራጅቶ ያለ መፍትሔ ቁጭ ብለው የሚጠብቁትን ወጣቶች የሚሰማ ጆሮ አልነበረውም።የስራአጥ ሠራዊት ተፈጠረ።ይህ በኃላ የተደራጀ ተቃውሞ እንዲፈጠር አስችሏል።የቄሮ መሪዎች እነዚህ ግፍ የተፈፀመባቸው ወጣቶችን ይዘውነበር ተቃውሞውን ሲያሰሙ የነበሩት።እስክንድር ነጋ እነዚህን ምስኪኖችና አሁንም ጥያቄያችን ይመለስ የሚሉትን ስራአጥ ወጣቶች ነው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ እየከሰሰ ያለው።አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ነው ነገሩ።ይህም ሆኖ በኦሮሚያበጣም ጥቂት አካባቢዎች ቢሆንም የኦህዴድ ቅን ካድሬዎች ብዙ ሺ ወጣቶችን ስራ አስይዘዋል።የነዚህ ህዝባውያን ካድሬዎች ተሞክሮ ማስፋፋት በተቻለ ነበር ነገር ግን አመራሩ ሌላ ሁኔታ ውስጥ ስለነበረ ጥሩ ተሞክሮው መጠቀምና ማስፋፋት ሳይቻል ቀረ።ለዚህም ነው በኦሮሚያ ተቃውሞው በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ደረጃ ያልነበረው።

 

ሌላ ጥሩ ምሳሌ በፍንፍኔ ዙርያ የነበረው ሁኔታ ነው። በሁሉም የፍንፍኔ መውጫዎች በቡራዩ፣ በሰበታ፣ በሱሉልታ፣ በለገጣፎና በብሸፍቱ ለትላልቅ ኩባንያዎችና ኢንቨስተሮች የተሰጡ መሬቶች ከገበሬው ተወስደው ነበር። ለገበሬው ተለዋጭ መሬት ወይም ኑሮውን ማስቀጠል የሚችል ካሳ መክፈል ይገባ ነበር። ካሳ ከተከፈለ በኃላም መንግስት ክትትልና ድጋፍ አደርጎ ገብሬው መልሶ መቋቋም እንዲችል የማድረግ ሃላፊነት ነበረው። የሆነውግን የተገላቢጦሽ ነበር። አርሶ አደሮቹ ካሳ እንዲከፈሉ የፌደራል መንግስት በቂ ባጀት መድቦ የነበረ ቢሆንም የክልሉ መንግስት ግን ክፍያው ለመፈፀም ጊዜ በመውሰድና ባለመክፈልም ጭምር ገበሬው ቅሬታ እንዲስማውና እንዲከፋ አደረገው።በዚህም በኦሮሞ አርሶ አደር ዘንድ ተወዳጅና አለኝታ ተደርጎ ይታይ የነበረው ኦህዴድ ከህዝቡ መነጠል ጀመረ። በተለይም ህዝባዊ መሰረቴ ከሚለው አርሶ አደሩ አመኔታ አጥቶ ቅራኔው እየበረታ መጣ። አርሶ አደሩ ለልጆቹ ስራ ዕድል የሚፈጥሩትን ኩባንያዎችና ኢንቨስትመንት መሬቱን የሚቀሙ ጠላቶች አድርጎ እንዲያያቸው ኦህዴድ አስገደደው። ይባስ ብሎ በነካው እጅህ የተባለ ይመስል በፍንፍኔ ዙርያ መሬት ለአዲስአቤቤዎች መቸብቸብ ጀመረ።ኦህዴድ የገበሬው መሬት ቀምቶ ያለ በቂ ካሳ እና ካሳ ትከፈላለህ ብሎ ለረጅም ግዜ እንዲጠባበቅ በማድረጉ አርሶ አደሩ በድርጅቱ ላይ እንዲያመር አደረገው። እንደ ኢንቨስትመንቱና እንደ ኩባንያዎቹም አዲስአበቤንም ወራሪ አድርጎ እንዲመለከተው አደረገ። መራሹ ኦህዴድ እነዚህ ችግሮች መቅረፍ አልቻለም። እንዳውም ሲጨንቀው በአንድ ወቅት እነዚህ ፍንፍኔ ዙርያ ያሉት የከተማ ከንቲባዎችን ማሰር ጀመረአለማየሁ አቶምሳ። ብዙ ሳይቆይ አለማየሁም አሟሟቱ ሳይመረመር ሞቶ ቀረ። የኦህዴድ ፀረ ሙስናውም ትግል አብሮ ተቀበረ። የታሰሩት ከንቲባዎችም ሁሉም ተፈቱ። በኃላምብዙዎቹ የለውጥ ሃዋርያ ሁነው የኦሮሚያ ጠበቆች ነን ብለው ሲፎክሩ እየታዩ ነው።

 

ለኦሮሞያና ለኦሮሞ ህዝብ ይጠቅማል ተብሎ የተነደፈው ማስተር ፕላንም ተቃውሞ የገጠመው ካለምክንያት አልነበረም፡፡ የኦህዴድ አመራርናየአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩበትና በኦሮሚያ ፕሬዝደንት የሚመራ የማስተር ፕላን ኮሚሽን የተረቀቀው ፕላን በህዝብ ተቃውሞ የገጠመው በይዘቱ አልነበረም፡፡ በፍንፍኔ ዙርያ የተካሄደውን የመሬት ዝርፍያና በህዝቡ የተፈፀመው በደል የሚያስቀጥል ይሆናል በሚል ህዝቡ በኦህዴድ አመራር ላይ አመኔታ በማጣቱ ነበር።አርሶ አደሩ መሬቱ ያለካሳ ወይም ደግሞ ካለ በቂ ካሳ የተነሳና መሬቱ መዘረፉ ሳያንሰው የማህበራዊ ቀውስ ሰለባም በመሆኑ ነው፡፡ ሦስት አራት ልጆቹ አስረኛ ክፍል ጨርሰው ነጥብ አልመጣላቹሁም ተብለው፣ በኃላ ደግሞ ዩኒቨርስቲ ተመርቀው ስራ ፈተው በወላጆቻው ቤት ያለ ምንም ስራ ቁጭ ሲሉና ቀጣይ ህይወታቸው መተንበይ የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ ወላጆች ሲገቡና ሲወጡ ከጎረምሳ ልጆቻቸው ግልምጫ ሲደርስባቸውና ኑሮም ከብዷቸው ወላጅም ልጅም መፈጠራቸውን መጥላት ጀመሩ። የሚወዱት ኦህዴድ ለምን እንደጨከነባቸው ማወቅ ተሳናቸው። በሰላማዊ መንገድ በየስብሰባው ችግራቸው እንዲፈታ ቢጠይቁም ኦህዴድ ብቃት ያለው መልስና መፍትሔ ሊሰጣቸው አልቻለም። በተደጋጋሚ እንፈታለን ብሎ ቃል ከመግባት በዘለለ በተግባር ምንም የተጨበጠ ነገር ሳይሰራ ቀረ። ኦህዴድ ተደጋጋሚ ቢጠይቅም የህዝቡ ጥያቄ መመለስ አልቻለም። የህዝቡ ችግር ጥልቀቱን የመረዳት አቅም ያነሰው ኦህዴድ አትጨቅጭቁን ማለትም ጀመረ።

 

ለጥልቅ ችግር ጥልቅ ተሃድሶ

በሃይለማርያም የሚመራው ኢህአዴግ በህዝቡ፣ በድርጅቱ ውስጥ ባሉት ህዝባውያንና ከአዲሱም ከነባሩም አመራር ግፊት ምክንያት መፍትሔ ተብሎ የጥልቀት ተሃድሶ የመጨረሻ የሙከራ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በተካሄዱት በሁሉም የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ እና የምክር ቤት ስብሰባዎች የኢህአዴግ ደካማ ጎን ተብሎ በግልፅ ይገመገም የነበረው ኦህዴድ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል እየታመሰ የኦህዴድ አመራር የዝሆን ቆዳ የለበሰ ያህል ምንም የማይሰማው ፍጡር ነበር። የኦሮሚያ ህዝብ በክልሉ አጋጥመውት በነበሩት ሁኔታዎች ጨንቆት አንዴ አምቦ አንዴ ሌላ ቦታ ሁከት ቢፈጠርም ኦህዴድ በሃይል ለመጨፍለቅ ከመውተርተር ውጭ ምንም አልተንቀሳቀሰም፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሲያስቀምጠው የነበረውን የፖለቲካ መፍትሔ ተጠቅሞ ለመፍታት በአደራሽ ይስማማና ወጣ ሲል ማእከላይ ኮሚቴውን ሰብስቦ በየዞኑ ሂዳቹሁ ህዝቡ አረጋጉ ብሎ አመራሩን ከመበተን በላይ ያደረገው ነገር አልነበረም። የተበተኑት አመራሮችም በየዞኑ ሄደው መፍታት የሚችሉትንም የማይችሉትንም እንፈታለንብለው የማያልቅ ቃል ገብተው፣ ይመለሳሉ። ምንም መፍትሔ ሳያደርጉ ሲቀሩ ህዝቡ ጊዜ እንስጣቸው እሰቲ ብሎ ትንሽ ለመረጋጋት ሲሞክር እነሱ ህዝቡ ተረጋግቷል ብልው ችግሩን ሳይፈቱ ይተኙበታል። የችግር እሽክርክሪቱ ይቀጥላል፡፡ ሻሸመኔ፣ ነቀምት እና ሌሎች አከባቢዎች ተመሳሰይ ሁከት ይፈጠራል። የኦህዴድ አመራርም ያለፈው ረስተው ሌላ የማእከላይ ኮሚቴ ስምሪት ያደርጋል።

 

በዚህም ምክንያት ይህ መንገድ አያዋጣም በዚህ ሁኔታ መቀጠሉም አግባብ አይደለም ተበለ፡፡ በአጠቃላይ በኢህአዴግ ደረጃ ጥልቅ ግምገማ ተደርጎ ተሃድሶ ይደረግ ተባለ። ሁሉም ተስማማ።

 

የየድርጅቶቹ ማእከላዊ ኮሚቴ ሰብሰባ ተቀመጡ፡፡ ህወሓት 35 ቀናት የፈጀ ጥልቅ ግምገማ አካሄደ፡፡ ደህዴንም ለሁለት ሳምንት ያህል በጥልቅ ገመገመ፡፡ ዱላ ቀረሽ ግምገማ ጀምሮ የከሸፈበት ብአዴንም ለሳምንት ግምገማ አካሄደ፡፡ ኦህዴድ ግን የተለየ መንገድ ተከተለ። ኦህዴድ አጭር መንገድ መረጠ፡፡ ምንም ሳይገመግም ይህ ሁሉ ችግር በክልላችን እያጋጠመ ያለው በእኛ የአመራር ችግር ነው የምትለውን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ግምገማ መዞ ይዞ፡፡ በክልሉና በፌደራል ባለው ሚና እያንዳንዱ አባል ምን ችግር ነበረው ብሎ ሳይዘረዝርና ሳይገመግም እና እያንዳንዱ አመራር ሂስና ግለሂስ ሳያደርግ ሙክታርንና አስቴር (በወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል የነበሩት) ዋና ተጠያቂዎች በማድረግ ሐላፊነት ወስዳቹህ ውረዱ ተባሉ፡፡ በጥድፊያም ማእከላይ ኮሚቴ ሰብስበው እንዲወርዱ አደረጉ። የሚተካቸው እንምረጥ ብለው ለማን በሊቀመንበርነትና ወርቅነህ ገበየሁን በምክትልነት ተመረጡ አሉ። ሁለቱም እንዲመረጡ ጥቆማ የጠቆሙት ሰዎችም ቆጣሪ ሁነው ተመረጡ አሉ፡፡ በአጭሩ የወረዱትም የተሾሙትም ሳይገመገሙ ወረዱ ተሾሙ። ሁሉም ነገር በጥድፍያ ሆነ። ጥልቅ ተሃድሶ አደረግን ብለው ፎከሩ። በኦህዴድ ካድሬዎች ይህ የጥድፍያ ስራ ግልፅነት የሌለው አካሄድ ነው ተባለ። አብዛኛዎቹ ኩዴታ ኩዴታ ይሸታል ብለው ኮነኑት። አንዱ ቡዱን ሌላውን ቡዱን አጥቅቶ ስልጣን ተቆጣጠረ እንጂ ጥልቅ ተሃድሶ አላደረጋቹሁም ብለው ማብራርያ እንፈልጋለን የሚል ካድሬ በዛ። ስልጣን የያዘው ቡዱን በካድሬው ውስጥ ያሉትን ደጋፊዎቹን አደራጅቶ ስብሰባ ጠራ። የወረደው ቡዱን ደጋፊዎችን የሚያሸማቅቅ ዝግጅት አድርገው በመግባት ለውጥ ያስፈልጋል አሉ፡፡ ችግሩ የአመራር ነው ከተባለ መቀየራቸው ትልቅ እርምጃ ነው ከአሁን በኃላ ሁሉም ችግር ፈጥኖ ይፈታል አሉ፡፡ይህ ወጣት አመራር መደገፍ አለብን የሚሉ ዲስኩሮች በደጋፊዎቻቸውም በራሳቸውም አስተጋቡ። ይህንን የሚቃወሙ ካድሬዎችማ እነሙክታር ራሳቸው ሐላፊነታችን አልተወጣንም፣ ራሳችንን ተጠያቂ እናደርጋለን ብለው ወርደው እናንተ ምን ባዮች ናቹህ ተብለው እንደ ቤተክርስትያን/መስጊድ የገበ ውሻ አካላብዋቸው። ግምገማ፣ ሂስና ግለሂስ ብለን እንደሌሎቹ ድርጅቶች ቁጭ ለማለት ጊዜ የለንም። አንዳንዶቻቹሁ ደግሞ ምን እንዳደረጋቹህ እናውቃቹህ የለም እንዴ! በማለት በማሸማቀቅ ዝም አስኛቸው።

 

ቀጥሎ ከእህት ድርጅቶች የሚመጣው ተቃውሞ አሰቡ፡፡ ሂደቱን አልተከተላቹሁም የሚል ወቀሳ እንዴት መመከት እንችላለን ብለው አቅደው ተንቀሳቀሱ። የፓርቲው አመራር በሁለት ተከፈለ የሚል ወሬ በአባላችን፣ በህዝቡም፣ እና በሌሎችም ስላለ እነ ሙክታርን ራሳችን ነው የለቀቅነው ብላቹሁ አሳምኑ ተባሉ። ለዚህም ተግባራዊነት ኦሆዴድ ዱላም ካሮትም ተጠቀመ።

 

የኢህአዴግ አመራር ከስብሰባ በፊት ምን አስተያየት እንዳለው ለማጥናት ሰው መድበው አንተ እንትናን አግኘው የሚለው ጭዋታቸው ይዘው ተወራጩ። በተናጠል ሁሉንም ሊባል በሚችል ሁኔታ በአጭር ጊዜ አግኝተው በቂ መረጃም ሰበሰቡ። በሚድያም ጫወታ ጀመሩ። በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም ራሳቸው እነ ሙክታር አስቴርና በክር እንዲናገሩ አስደርገው የእህት ፓርቲዎች መግቢያ አሳጥተው የለማ ቲም (ቡዱን) የመጀመርያ ምዕራፍ የስልጣን ፍላጎቱን በድል አጠናቀቀ። የክልሉን ችግር ቅንጣት ታክል ግን መፍታት ሳይችል ቀረ።

 

የችግሩ ሁሉ ምክንያት የውጭ አድርገው ማቅረብ ተያያዙት።የህዝቡንና የቄሮ ጥያቄ ቀምተው የራሳቸው አድርገው አነገቡት። ለናንተ ነው የመጣንው አሉ።መፈክራችን መፈክራቹህ ነው ብለው ማስጨብጨብ ጀመሩ። ከሶማሊ ክልል ጦርነት ስለጀመርን መሪያችን ኦቦ ለማ ጦር ግንባር ላይ ነው ያለው። በጀግንነት ጦር እየመራ ነው በሱ ፋንታ ንግግር ሳደርግ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል ብሎ አብይ በአዳማ ለተሰበሰበ ህዝብየሂትለር ሽታ የሚሸት የመጀመርያው ንግግር ለህዝብ አደረገ። ተንጨበጨበለት። ቀጠለ ኮነሬል አብይ ከአሁን በኃላ ኦሮሚያ በአካባቢዋ ባሉ ትናንሽ ክልሎች አትደፈርም፣የድሮ አመራር ነው ለዚህ ሁሉ ጭቆና ያደረሳቹህ፣ እኛ ልጅቻቹህ መጥተናልነፃ እናወጣቹሃለን፣ አፋን ኦሮሞ የፌደራል ቋንቋ ይሆናል፣ ማስተር ፕላን ይቀደዳል፣ የኢኮኖሚ አብዮት እናካሂዳለን፣ የፊንፍኔ የሰፈሮች ስያሜ በድሮ የኦሮምኛ ስያሜያቸው ይጠራሉ፣ በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይረጋገጣል፣ ስራ አጥነት በፍጥነት ይፈታል፣ ከሶማሊያ፣ ቤንሻንጉል፣ ደቡብ ህዝቦች እና ከሌሎችም ክልሎች ያለን የወሰን ጥያቄ በፍጥነት ይመለሳልብሎ ደሰኮረ። የማይነጋ መስሎት አስጨበጨበ። እንደገና አስጨበጨበ። ኦህዴዶች ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስተር እንዲሆን እንታገላለን አሉ። ይህችን ዋናው አላማቸውን ጊዜ ወስደው አስተዋወቁ።የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ ዋናው ችግር የስልጣን አተያይ ችግር ነው ይላል።ስልጣን ህዝብን ለማገልገል ሳይሆን ራስን ለመጥቀም፣ ራስን ለማገልገል እና ስልጣንን እንደርስትነት ይዞ ለመቆየት ነው ዋናው ችግራችን ይላል።በሌላ በኩል ደግሞ ኦህዴድ ይህንንየግምገማ አተያ መገምገሚያው ሳያደርግ አይኑን ጨፍኖ ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስተር መሆን ካልቻለ ይህ ስርዓት የኦሮሞ አይደለም ይላል። ኦህዴዶች የህዝቡ ዋናው ጥያቄ ይህ ስርዓት የኛ የምንለው ኦሮሞ ጠ/ሚኒስተር ሲሆን ካየን ብቻ ነው። አለ ብለው በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ባልተለመደ ባህል ሞገቱ።

 

ኦህዴድ በዚህ ሁኔታ እያለ ደህዴን ደግሞ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝን በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ መሰረት ሂሳዊ ግምገማ ተካሄደበት፡፡ መምራት አልቻልክም፣ ወላዋይ ነህ፣ መወሰን አትፈልግም፣ ሁሉንም ልታስደስት ብለህ አገር ትርምስ ውስጥ አስገበሃት፣ የተረከብካትን አገር ትርምስምሷ ሲወጣ አትጨነቅም፣ የምትጨነቀው ለስልጣንህ ነው እና ብዙ ሌሎች ነገሮች ያሉበት ሂስ ቀረቡለት። የአልሞት ባይ ታጋዳይ ክርክር ቢያደርግም የደህዴን ማእከላይ ኮሚቴ በዋዛ አልተረታም፡፡ ክልላችን አዋረድክ ዓይነት የተቀላቀለበት ተጨማሪ ሂሶች ሲቀርቡበት ሃይለማርያም ማምለጥ እንደማይችል ሲያውቅ የቀረቡለትን ሂሶች ተቀበለ። ከስህተቴ እማራለሁ ቢልም ቤቱ መውረድ ነው ያለብህ ብሎ ይሞግታል። እንዲወርድም ይስማማሉ። እዚህ ላይ ትልቅ ስህተትና ቅጥፈት ተሰራ፡፡ ደህዴኖች ተከፋፈሉና ተጣሉ ብሎ ህዝቡ እንዳይደነግጥ (እዚህ ላይ ሲደርሱ የህዝብ ተቆርቃሪ ይመስል) በሚል ራሱ ሁኔታው ከባድ ነው ከስልጣኔ እወርዳለሁ እንዲል ተደረገ። ይህም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሃይሌ በኢህአዴግ የመጨረሻ ዕድሉን ሊሞክር አሰበ። ቢያንስ ህወሓቶች ይውረድ ብለው ጨክነው አይወስኑም የሚል ተስፋ ይዞ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ጠራ።

 

በተጠራው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ የደህዴን ማእከላይ ኮሚቴ በጣም ዲሞክራሲያዊ የሆነ፣ ነፃና ግልፅ ትግል ተካሂዶ ሁሉም ነገር ፍርጥርጡ (የተስፋዬ በልጂጌ ማጋነን ተጨምሮበት) ወጥቶ ተገማገምን ነው የመጣነው አሉ፡፡ ከህወሓት ቀጥለው ጥሩ ግምገማ አደረጉም ተባለ። ሁለተኝነታቸውን አግኝተው ሲያበቁ ሃይለማርያም ስልጣኔን ልለቅ ነው ብሎ ወስኗልና ቤቱ ይወያይበት ተባለ። ሃይሌ ለምን እንደወሰነ እገልፃለሁ ብሎ መግለፅ ጀመረ። ከልቡ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጣሉብኝ አደራ በላሁኝ ሳይሆን ጥሩ ሰራሁኝ የሚለውንም እያጎላ (ቀረባቹህ ዓይነትም የተሞላበት እና የስልጣን ወንበር ምን ያህል እንደምትወደድ በሚያሳይመልኩ) የጎደሉትንም ምክንያቶች እየደረደረ አቀረበ። ቤቱ በአብዛኛው በሃይሌ ልፍስፍስ አመራር አምርሮ የቆየ ስለነበረ የሃዜነታ ውዳሴ እየደረደረ ምን ይደረግ ልልቀቅ ካልክ ጥሩ ነው እንዲያውም ባህል ሆኖ ይለመዳል ተቀብለንዋል! ብሎ መልቀቅያውን ተቀበለው። የህወሓትም አመራሮች ሃይልዬ እንደጠበቀው ሳይሆኑ መልቀቅያውን ተቀበሉት። የግልግል ዓይነት ቤቱ እረፍት ወጣ።

 

በዚህ አጭር ግዜ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፡፡ ሃይለማርያም ከስብሰባው አደራሽ አንድ ደቂቃ ወደ ምትወስደው ቢሮው ተጣድፎ ሄደ፡፡ ቢሮ እንደገባበግምገማው ወራት የታመቀ ትንፋሹን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ ስሜቱ ፈንድቶ አምርሮ አለቀሰ። የቅርብ ጠባቂዎቹና የግል ፀሓፊዎቹ ይታዘቡኛል ሳይል ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። ህወሓቶች እንዴት እንዲህ ይጨክኑብኛል ብሎ እየየውን አስነካው፡፡ የእረፍት ሰዓቱ በማብቃቱ አጠገቡ የነበሩ ሰዎች እንደምንም አባብለው ፊቱን ታጥቦ ይዘውት ወደ አደራሹ ተመለሱ። ሲጠቃለል ይህ አጭር ፈታኝ ግዜ ለሃይለማርያም ጨለማ ለኦህዴድ ስልጣን ጥመኞች ብርሃን ለብአዴኑ ደመቀ ተስፋን ፈጥሮ ስብሰባው አለቀ።

 

ከስብሰባው በኃላ ከህወሓት በስተቀር ሌላው ድርጅት ስለ ስልጣኑ የሚያስብበትና ወደ ስልጣን የሚወጣበት ስትራተጂ የሚቀይስበት ሁኔታ ላይ ተጠምዶ ቀጠለ። ሁሉም ስልጣን ለመያዝ የሚቋምጥ እንደ ዕንቅፋት የሚቆጥረው ህወሓትን ነበር። ህወሓትን ዝም ማሰኘትና ሌሎችም ስልቶችም መንደፍ እንደሚገባ አስቦ መሯሯጥ ተያይዘው፡፡ የኦህዴድዱ የለማ ቲም ከውጭ ረዳቶቻቸው ጋራ ስትራተጂ ነድፈው ጨርሰዋል። ደመቀም ዕድል ካለው ለማየት ብአዴን ውስጥና የህወሓት ስዎችን በተናጠል ማግኘትና በግልፅ እኔ ብሆንስ ሃይሌን የምተካው ባይልም ዳር ዳሩን ማሰስ ጀመረ፡፡ ዳሰሳው እንደየሰው ሁኖበት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ተስፋ ሲጭሩበት አንዳንዶቹ ደግሞ ዘንድሮ ሃይሌን የሚተካው ኦሮሞ ቢሆን ይሻላል ብለው ተስፋውን ያጨሉሙበታል። ደመቀ ግን እስከመጨረሻው ተስፋ ሳይቆርጥ ዘልቃል የሚሉ ሰዎች አልጠፉም። እንደነሱ አገላለፅ ደመቀ የወሰነው መጫረሻ ላይ ነው ይላሉ። ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት የስራ አስፋፃሚው ያለፈው ውሳኔ ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፋፃሚ መለስ ድንገት ሲሞት ምክትሉ የነበረው ሃይለማርያም ይተካው ብለው ወስነው ሰለነበር ነው፡፡ ሰለዚህ በተመሳሳይ አካሄድ ሃይለማርያም ተርሙ ሳይጨርስ ስልጣኔን እለቃሎሁ ካለ ምክትል ስለሆንኩኝ እኔ መተካት አለብኝ ብሎ ሂሳቡን አሰልቶ እየጠበቀ ሰለነበር ነው ይላሉ። ደመቀ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዳልሆን የማይፈልጉት እነዚህ የብአዴን ሽማግሌዎች እና ህወሓት ናቸው ቢልም መጨረሻውን ግን ለማየት በጉጉት እየጠበቀ ነበር ብለው ያምናሉ። ለኔ ይህ ሐሳብ ብዙም ክብደት አልሰጠውም፡፡ ደመቀ ቀደም ብሎ እንደማይሆን ገምቶና በውጭ ሃይሎችም መመርያ አግኝቶ ከኦህዴድ ስልጣን ጥመኞች ጋር መተባበር ከጀመረ ቆይቷል ባይ ነኝ።

 

ሃይለማርያም ውስጡ እርር ድብን እያለ የመጀመርያ የአፍሪካ መሪ ስልጣን በፍቃዱ እለቃለሁ ያለ! የምትል ስም በማግኘቱ ከላይ መኩራራት ጀመረ፡፡ እዚህ ላይ ለዚህ ዝናና መኩራራት የውጭ ሐይሎች በየሚድያው ሲያራግቡለት ስያስጮሁለት እሱም በፊናው ደግሞ የሚፈፅመው ግዳጅ ተሰጥቶት ነበር። የተሰጠው ግዳጅ ከቅሬታውም ተነስቶ የሚፈልገው ነገር ነበር። አንደኛው ደህዴኖች ውስጥ ሰዎች እንዲመለምልና እሱን ይተካሉ የተባሉትናከህወሓት ጎን ይሰለፋሉ ተብለው የተፈረጁት ላይ ስም ማጥፋት፡፡ ሁለተኛ ከደህዴን ውጭ ህወሓትን በማጥቆር እኔ ስልጣን አልነበረኝም ሊያሰሩኝ አልቻሉም በማለት በኦህዴድና በብአዴን የተጀመረው የኦሮማራ ስውር ደባ በህወሓትና በደህዴን እንዳይፈርስ የማድረግ ተልእኮ ነበር የተሰጠው። ተልእኮው ከከፍተኛ የስልጣን ፍላጎቱ ያደናቀፉኝ ብሎ የሚያስባቸውን ሁለቱ ድርጅቶች ላይቂሙን ሊወጣ ስራዬ ብሎያዘ፡፡ የመልቀቅያው ጥያቄ እስኪፀድቅለት ድረስ ለጊዜው የያዘውን ስልጣን ተጠቅሞ ተንቀሳቀሰ። እንደሰሩልኝ እሰራባቸዋለሁ! የሚል መፈክሩን አንግቦ በሙሉ ሐይሉ ጥረት አደረገ። ስልጣን ከያዘበት ቀን ጀምሮ እንደዚህ በንቃት ሰርቶም አያቅም ይላሉ ሁሉም ጓዶቹ። የተሳካ ስራም ሰራ። ሌላ ጊዜ ሃይለማርያም ማን ነበር? የሱ ጉዞ ከየት ወዴት (እስከ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ጉሩፕ ቦርድ አባልነቱ)? በሚል እግዛብሔር ከፈቀደ እፅፋለሁ። አሁን ግን ወደ ዋናው አርእስቴ ልመለስ ወደ ኦህዴድ።

 

ከኢህአዴግ ስራ አስፋፃሚ ስብሰባ በፊትም በኃላም የኦህዴድ ሰዎች በድብቅ የውጭ ጉዞዎች ነበሩዋቸው (አሁን ለህዝብ ግልፅ የሆኑትም ለህዝብ ይፋ ያልሆኑትም ጭምር)። እንደ አንድ የኦሮሚያ ዞን የሚያዩት ደቡብ ኮርያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ አገር አድርገው አሜሪካም ይመላለሱ ነበር። ተጀንጅነውና እቅድ ይዘው ይመጣሉ። በእቅዱ መሰረት በፌደራል ስርዓቱ ግርግር ይፈጥራሉ። ተመልሰው ፌዴራል መንግስት ባጀት ብቻ ይመድብልን እንጂ ግርግሩ እናስቁመዋለን ብለው መሐላ ቀረሽ ሀተታ ያቀርባሉ። ለወጣቱ ስራ ለማስያዝ ዕቅድ አቅደናል፣ በኦሮሚያ በኢኮኖሚ አብዮት (እንደመደመር ምንነቱ የማይታወቅ) መሰረት ኢንቨስት ያደረጉና ትርፍ መሬት የያዙት (ለማስፋፍያ ብለው) ቀምተን ለወጣቱ እናድለዋለን፣ በኦሮሚያ ኢንቨስት ያድረጉ ባለሃብቶች ለወጣቱ ስራ መስጠት ሰለአለባቸው ከሌላ አከባቢ የመጡ ሰራተኞች አባርረው የአካባቢውን ወጣት ስራ ይስጡ አሉ። ከሌላ የመጡት የተባሉት ከሌላ የኦሮሚያ ዞኖችም የመጡትን ኦሮሞዎች ጭምር ይውጡ በመባላቸው ቀውስ ተፈጠረ። በዚህ ብዙ ፋብሪካዎችና የአበባ ግሪን ሃውሶች እንደ ችቦ በእሳት ተቀጣጥለውና ተዘርፈው ኦና ሆኑ። በክልሉ ስርዓተ አልበኝነት ነገሰ። የክልሉ ፀጥታ ራሳችን እንፈታዋለን አሉ፡፡ መከላከያ እና ፌዴራል ፖሊስ ከክልላችን ይውጡ ብለው ወተወቱ። የለማ ቲም ይህን ዓይነት ግርግር ደስ ይለዋል።

 

በአደባባይ የዚህ ሁሉ ተጠያቂ ፌደራል መንግስት ነው ይልና በሌላ መንገድ ደግሞ የወያኔ መንግስት ነው ብሎ እህት ድርጅት ላይ ያላክካል። ግርግሩ ለማስቀጠል ምንጩ ያልታወቀ ብር ይበተናል። የለማና የአብይ ፎቶግራፎች በየከተማው በየመኪናው ተለጥፏል። የኦሮማራው ሌላው ቡዱን ደግሞ በግላጭ የተቀመጠውን የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ መድረክን ሸሽቶና በግንባር ላይ ግንባር ፈጥሮ እያለ በጥልቅ የታደሰውንና የዋሁን ወያኔን ይከሳል። እየተቀባበሉ ስልጣን ላይ እኛ ለይስሙላ እንጂ ወያኔ ነበር አገሪቷን ሲያስተዳድራት የቆየው ብለው ለፈፉ፡፡ በየክልላቸው ላለው ችግር እኛ ሳንሆን የምንጠየቀው ወያኔ ነው ብለው የደርግ ርዝራዦችና የኢሳያስ አፈወርቂ ተላላኪ ድርጅቶች የግንቦት ሰባትን ዘመቻን በገሃድ ተቀላቀሉ። ተሳካላቸው።

 

ወያኔ የሁሉ ችግር ምንጭና ተጠያቂ ተደርጎ ተወገዘ። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በተቀመጠ ቁጥር የህንን ያስረግጥልናነል የሚሉት ነገር ሁሉ ይወረውራሉ፡፡ መከላከያ በትግሬዎች ተሞልቷል፣ የአዲስ አበባ ፎቆች የትግሬዎች ናቸው፣ ህወሓት አባዱላን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሊያደርግ እየተዘጋጀ ነው ብለው አስወሩ፡፡ በኦህዴድ ጉዳይ ምንም አያገባቹሁም አሉ። ይህንን የማጥቆር ሂደት ያልተገነዙቡት ደግሞ ከየት አመጣቹሁት ብለው ቢሞግቱ የለማ ቲምና ግበረአበሮቹ ተወራ የሚል መልስ ይሰጣሉ። ጉዳዩ ይጣራ ሲባል ይህ ያለው ህወሓት እንዳልሆነና አባዱላ ቢሆን ያለው ሃይለማርያም መሆኑ ተጣራ። ሐቁን ሲያቁ ደግሞ ነገሩን አድበስብሰው ዝምታን መረጡ። በኦህዴድ ስብሰባ ግን አባዱላን ለምን ከኦህዴድ ፍቃድ ውጭ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን ተንቀሳቀስክ ብለው አባዱላ ላይ አብይና ለማ ዘመቱበት። በተጨማሪም አባዱላን ማሽከርከር ስለሚችሉ ነው ወያኔዎች አባዱላን ዕጩ ለማድረግ የፈለጉበት ምክንያት ብለው አባዱላ ላይ በሌለበት የማጥቆር ዘመቻ አጠናክረው ቀጠሉ። በዛን ወቅት አባዱላ በጤና እክል ውጭ ሄዶ በህክምና ላይ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ግልፅ ያልሆነውና በውቅቱ ብዙ ውዥንብር ፈጥሮ ያለፈው የአባዱላ ከፓርላማ አፈጉባኤነት እለቃለሁ የመንግስት ቤትም አልፈልግላቹሁም የሚል ውሳኔ ነበር። አብይ አባዱላ ከተወገደ ለማ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን እንደማይችል ገብቶታል። አባዱላን ከጭዋታው ውጭ ካደረገ በኃላ እንዴት ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም ቀይሷል ወይም ተቀይሶ ተግቶታል። ለማ በነበረው አጭር ጊዜ ለአገር ፓርላማ ተወዳድሮ መምጣት እንደማይችል የጊዜው ሁኔታ ያሳያል። አብይ የፓርላማ አባል ነው። የአብይ ጭንቁ የኦህዴድ ድርጅት ሊቀመንበር አይደለህም ተብሎ እንዳይቀር ነው። ከለማ እግር እግር እየሄደ ለማ የድርጅት ሊቀመንበርነቱን ቦታ እንዲሰጠው መለማመጥ ሆነ ስራው። አቶ ለማም ይሁን ብሎ ፈቅዶ አስረከበው። ምክትል የነበረው ወርቅነህ ገበየሁ ደግሞ በመሃል ሜዳ ለለማ ቦታ ለቆ ይወጣል። ስልጣን ከኦሮሞ መውጣት የለባትም በሚል መፈክር የሚታወቀው አብይ አህመድ የኦሮሞ ሊቀመንበር ሆነ። የኦህዴድ።

 

አብይ ራሱ በአብይ የሚመራው የኦህዴድ ድርጅት ዕድለኛ እንደሆነ አድርጎ መስበክ ጀመረ። ካድሬ ሰብስቦ ስለራሱ ወታደርነት ጉራውን ለቀቀ። በነገራችን ላይ በቤተመንግስቱ ውስጥ ከወታደሮቹ ያደረገው ፑሽ አፕ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ፑሽ አፕ አደራሽ ውስጥ በመስራት ምን ያህል ወጣትና ጎረምሳ መሪ እንዳገኙ ትያትር ለመጀመሪያ ግዜ የሰራው ለኦህዴድ ካድሬዎች ነው። ካድሬዎቹ አለምብሰሉንና ህፃንነቱን አይተው ብልባቸው ዘንድሮ ደሞ ምን ሊያሳየን ነው ብለው ፑሽ አፑን ተከታተሉ፡፡ ከስብሰባ ወጣ ብለውም ምኑ ቅሌታም፣ ፈጣጣና ደፋር ደግሞ አመጣብን ብለው አሙ። ብዙዎቹ የኦህዴድ ካድሬዎች እሳክሁን ድረስ በእርገጠኝነት አብይ ከመከላከያ እንዴት ወጣ? እንዴት የኦፒዲኦ አባል ሆነ? እንዴት በአንዴ ወደ ማእከላይ ኮሚቴ ተሰቀለ? እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች አያውቁም።

 

አብይ አህመድ በኔትዎርክ ያደራጃቸውን ካድሬዎች ተጠቅሞ ስለሱ ልዩ ብቃት ማስወራት በሰፊው ተያያዘው። ከኦህዴድ ውጭም ስራዬ ብሎ የኢህአዴግን ስራ አስፈፃሚ አባላትና የሁሉም ድርጅት አመራር አንድ በአንድ በግል እያገኘ ቅስቀሳ አድርጓል። ተሰሚነት አላቸው የሚላቸውን የማእከላይ ኮሚቴ አባላትን ጭምር እየቀጠረ አነጋግሯል። የመከለካያ ጀነራሎች የነበሩት በሙሉ የቀረው የለም። ከማግኘቱ በፊት ስለሚያገኛቸው ሰዎች ጥናት አድርጎ ነው የሚቀርባቸው፡፡ ምን ታሪክ አላቸው? ምን ይወዳሉ? ምን ይጠላሉ? ከዚህ በፊት የተዋወቃቸውና የሚያቃቸው ከሆነም ስለሱ ያላቸው አስተሳሰብ ምን እንደሆነ አስጠንቶና አውቆ ነበር የሚያገኛቸው። ሲያገኛቸው መጀመርያ ስለነሱ ያለው አስተሳሰብ እያደነቀና እየካበ ያዋዛቸዋል።ከዛም ስለራሱም ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት ባለው መንገድ ሐሳቡና ቀጣይ ዕቅዱን ሊማርካቸውና ሊስባቸው በሚችል መንገድ ይተርክላቸዋል።ስለሱ የተሳሳቱ ሐሳቦችና ግምቶችም የሚላቸውን በዘዴ በማንሳት ትክክል እንዳልሆኑ ለምን እንደዛ እንደተባለ ማስተባበያ በመስጠት ያለው አስተሳሰብ በጣም የተለየና ብቃቱም ከፍተኛ እንደሆነ ይደሰኩራል፡፡ ምስክሮች በመደርደርም መለስ እንዲህ አለኝ፣በረከት ስለኔእንዲህ ብሎ ነበር፣ ሳሞራ (ጀነራል አይልም ቅርበት እንዳለው ለማሳያት) እንዲህ ነው የሚለኝ በሚል ራሱን በሌሎች አንደበት ተጠቅሞ ክቦ ያቀርባል። የማይደብቃት ነገር አንድ ነገር ብቻ ናት። ለስልጣን ያለው ፍቅር! ጠቅላይ ሚኒስተር እንደሚሆንም ያለምንም ጥርጣሬ ይነግራቸው ነበር (ራሱ እንዳለው)።

 

እስከ ምርጫ ወቅት በኢህዴግ ምክር ቤት ስብሰባም ይሁን በኃላም ስራ አስፈፃሚ ከሆነ በኃላ አብይ ከስብሰባ በፊትና በእረፍት ወቅት አቅዶ መጥቶ እያንዳንዱን ሰው እያገኘ ራሱን ይሸጥ እንደነበር ሁሉም የሚያውቀው ነው። አይደክመውም። ትልቁ ስራው ራሱን ማስተዋወቅ ነው። በስብሰባም ወቅት የቤቱን (ተሰብሳቢው) አዝማሚያ አይቶ የሚያምሩ ቃላቶች፣ ጥራዝ ነጠቅ ሃሳቦችና ጥቅሶችን በመደርደር አስታራቂ የሚመስሉ ባዶ ሃሳቦችን ያቀርብ ነበር። ጮክ ብሎ ቤቱን እየተቆጣጠረ ይናገራል። ነገር ግን በፍፁም ከቤቱም ከግለሰብም የሚያጋጭ አንድም ነገር አይናገርም። ውጭ እንደወጣም ያቀረበው ሃሳብ ምን ያህል ተፅእኖ ፈጥሯል ብሎ ሰዎችን እያገኘ ይገመግማል።

 

ኢህአዴግ የሃይለማሪያም መልቀቅያ ተቀብሎ ሊቀመንበሩና ለአገራቸንም ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥ ነበረበት፡፡ እናም የምርጫ ቀን ደረሰ። ከህወሓት በስተቀር ሁሉም ምርጫው እንዴት እንደሚሆን አቅዶው ጨርሷል። ከመደበኛው (ፎርማሉ) ስብሰባ በፊት ምርጫው አልቆ ነበር። ነገር ግን የህወሓትና የተወሰኑ የብአዴን እና ጥቂቶችም ከደህዴን በጣም ተጨባጭ ማስረጃ እያቀረቡ የአብይን መመረጥ በፅኑ ለቤቱ (አሁን ለቤቱ ማለት ለህንፃው ማለት ነው) ተቃወሙ። የሰማቸው አልነበረም፡፡ አብይ ማምሻውን ተመረጠ። ሌሊቱን ዜና ሆነ።

 

የተዘጋጀው የምርጫ ውጤት አዲስ ዜና ተደርጎ በተዘጋጁ ሚዲዎችን ሰዎች ዜናውን ሲቀባበሉት አደሩ። አዲስ ኦሮሞ የሆነ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስተር ከኦህዴድ ተገኘ ተባለ። ፌስታ በፌስታ ሆነ። የስልጣን አተያይ እናሻሽል ያለው የኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ በስልጣን መርካት የሚያስደስተው መሪ ወለደ። ፍቅር፣ አንድነት፣ እርቅና ኢትዮጵያውነት ተሰበከ። ከሱሰኛው ኢትዮጵያዊ በላይ ኢትዮጵያዊነት ያነደደው መሪ እንደሆነ ከቀን አንድ ጀምሮ ለፈፈ። ከፍ ያለ ታዋቂነት አተረፈ። በአጭር ጊዜ ስሙ ገነነ። ሁሉን ነገር ያቀናል ተባለ። አብይም ነብይም ተባለ፡፡ በየሄደበት ጭብጨባ ሆነ። መቐለ፣ ባህርዳር፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ ህዝባዊ ስብሰባ አደረገ። የእያንዳንዱ አካባቢ ታሪክ በመተረክ ስሜትን ለሞከርከር ጥረት አደረገ። ተሳካለት። እግዛብሄር ይጠብቅህ! ይርዳህ! ተባለ። እንደ ንግግርህ ተግባርህም ይሆን ዘንድ እንመኛለን ተባለ።

 

አብይ ይህ የህዝቡ ድጋፍ ከባድ አደራ መሆኑን ረሳ። ብቻውን ለውጡን ለማስኬድ የሚችል አድርጎ ራሱን አስቀመጠ። ኦህዴድን ረሳው፡፡ እዚህ የተሰቀለበት ቦታ የሰቀለውን ኢህአዴግ ዘንግቶ ለውጡ እሱና ጥቂት የህገወጡ ቡዱኑ አባላት ብቻ እንዳሳኩት አድርጎ በጠራራ ፀሓይ አወጀ። ፍቅር፣ አንድነት፣ መደመር፣ ይቅር ባይነት ወዘተ ተረስቶ እኛና ለውጡን ያልተቀበሉ ማለት ተጀመረ። ዛሬ ሞተር የተባሉት በነገታው የቀን ጅብ ይሆናሉ። ሁላችን ተደምረናል ይባልና ብዙ ሳይቆይ ያልተደመሩ ይባላል። የሰኔው አስራ ስድስት የመስቀል አደባባይ (ራሱ ያቀነባበረው ድራማ ነው ይባላል) ክስተት አስታኮ ምርመራ ያልተደረገበት ነገር በብርሃን ፈጥነት የለውጥ መሪያቹህን ሊያጠፉ የተነሱ የቀን ጅቦች ናቸው የፈፀሙት በሚል በትግራይ ህዝብና በህወሓት ላይ ጣቶቹን ቀሰረ።

 

የለውጡ መሪዎች ለመጀመሪያ ግዜ ከአገር ውጭ ወደ አሜሪካ ተሰባስበው ሄዱ፡፡ ወያኔን በውስጥ ትግል በከፍተኛ መስዋእትነት አሸንፈን ከስልጣን አውርደን ድል አስመዘገብንላቹህ ብለው ምድረ ደርጎችን አስጨፍረው ተመለሱ። በአገር ውስጥ ግን በጠራራ ፀሐይ የአገሪቱ አደባባይ በሆነ ቦታ የታላቁ ህዳሴ ኮከብ ሰው ኢንጂነር ስመኘው ሙቶ ተገኘ ተባለ። ይባስ ብሎ በአብይ አንድ ሰው የተባለው የስመኘው የአገዳደል ሴራ ተጠያቂ የሌለው ሆኖ ምርመራም ሳይደረግበት ቀረ። የአገሪቱ ሚድያዎች የለውጡ መሪዎች በአሜሪካው ጉብኝት ወቅት ወያኔን በግልፅ አወርድነዋል የሚለው ዜና አስክሯቸው ያኔ በደጉ ዘመን አስር ጊዜ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ህዳሴው ግድብ ግለፅልን ሲሉት የነበረውን እውነተኛ የኢትዮጵያ ገንቢ መሃንዲስን አሟሟት በወጉ ለመዘገብና የፈፀመው አካል ለማጣራት ሳይችሉ ቀሩ።

 

የለውጡ መሪዎች ነን የሚሉት ኦሮማራዎች ወያኔን ለማናደድ ብለው ብቻቸውን አስመራ ተሰባስበው ሄዱ። ለሻዕብያም ከወያኔ ጋር ነው የተጣላቹሁት እንጂ እኛማ መወሰን አንችልም ነበር ዓይነት እርቅ አካሄዱ። ሁሉም ነገር በችኮላ ሆነ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም የኤርትራ ባለስልጣኖች ራሳቸው በድንገት የመጣብንና ያልተዘጋጀንበት እርቅ እያሉ የሚገልፁት። የነቶሎ ቶሎ ሆኖ እርቁም አልረጋም፡፡ ድንበሩ ዛሬ ተከፈተ፣ ነገ ተዘጋ፣ ደግሞ ተከፈተ የሚባልበት የእቃ እቃ ጭዋታ አደረጉት።

 

ለማጠቃለል በግልፅ ኦህዴድ የሚመራው ኢህአዴግ የኢትዮጵያ መንግስት ተባለ። ቆየት ብለውም ኦህዴድ የሚለውን ትተው ለማ ቲም የሚመራው ለውጥ ሽግግር ተባለ። ሰንበትበት ብሎም አብይ አሻጋሪያችን መሪ መባል ተጀመረ። ቀጥሎም ኦህዴድና ለማ መገርሳ በእውቀት ይሁን በስሕትት ስማቸው ተረሳ፡፡ ኮነሬል አብይ ከጎናቸው ምህረት ደበበና ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ሁሌም አስከተሉ፡፡ ቆይቶም ብርሃኑ ነጋ ተቀላቀላቸው፡፡ ብርሃኑም ቤተመንግስት ላይ ጠዋት ወይ ቀን ወይ ደሞ ወደ ማታ አይጠፋም ይባላል።

 

በክፍል ሁለት የኦህዴድ ጉዞ ሊቀመንበሩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስተርነት ካደረሰ በኃላ ያለውን ሁኔታ እንቃኛለን።

 

ቸር እንሰንብት!

 

Back to Front Page