Back to Front Page


Share This Article!
Share
የቲም ለማ መገርሳ አመራር ከላይ ዘይት ከታች ወይራ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያሰፈልጋል።

የቲም ለማ መገርሳ አመራር ከላይ ዘይት ከታች ወይራ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያሰፈልጋል።

በልኡልገብረመድህን(ከአሜሪካ )

የካቲት 26/2011.

ታሪክ መሻማት ከነበረበት የትግራይ ህዝብ ነበርበኢትዮጵያ ለነፃነት በተደረጉ እልህ አስጨራሽ ትግሎች የትግራይ ህዝብ ግንባር ቀደም ነው።የውጫሌ፣የመተማ፣የደጔሌ ፣ የአድዋ የነፃነት ተጋድሎ ሲነሱ የትግራይ ህዝብ አሰተዋጽኦ የላቀ እንደነበር መናገር የሚያስፈልግ አይመስለኝም ። ሌላ ቀርቶ ጨቋኙ የደርግ ሰርአት በሐይል ለመታገል የካቲት 11, 1967 ዓ.ም ደደቢት በረሃ ላይ የተለኮሰ የትግል ችቦ ፍሬ አፍርቶ በኢትዮጵያ እኩልነት እንዲሰፍን የአንበሳ ድርሻ የነበረው የትግራይ ህዝብ ድሉ የእኔ ብቻ ነው አላለም ። በኢትዮጵያ የተገኘው ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ድል ነው ነበረ ያለው የትግራይ ህዝብ ። የትግራይ ህዝብ ሁኔታዎች በመርህና በምክንያት የመተንተን ሙሉ አቅም ያለው ህዝብ ነው ።የትግራይ ህዝብ ማንኛውም ጉዳይ በልኩ የሚመዝን ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ ጭቆና ከድህነት በላይ ይጠየፈዋል ፣ ይጥለዋል ። ለኑሮው የሚመጥን የአስተዳደር ለውጥ ሲፈልግም የመንግስትና የግል የልማት ተቋማት በእሳት አያጋይም ፣ እንደ አምቦቄሮቦዘኔዎች የግለሰብ ሆቴል ንብረት አያወድምም ፣ አያቃጥልም። እንደ ፋኖ ጥራዝ ነጠቆች መንገድ አይዘጋም ፣ የሰው ንብረት አይወሰድም ።  በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ በተግባር እንጂ በሸለላና ቀረርቶ ከቶ አያምንም ። አንዳንድ ህዝብ ጤፋቸው የሆኑ የጎሳ አክራሪዎች ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ ስሜት የሚነኩ አስነዋሪ ንግግሮች እንዲሁም አስተያየቶች ሲሰነዝሩ ይስተዋላል ። የአንዳንዶቹ አሰተያየት በገበያ እጦት ውርጭ የመታው ሲሆን ሰዎችም ጤናማ ለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም ። እዚህ ላይየሚያሳዝነኝ በትልቁ  የአገር ግንባታ ወደ ጎን ትተን እርባና በሌላው የጎሳ ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መግባታችን ምንኛ ውድቀት እንደሆነ የሌላው ባላውቅም እኔን ግን ይሰማኛል ።

Videos From Around The World

የኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ሲፈተሽ ትግራይ ሆኖ ይገኛል ። ከግዕዝ እስከ አማርኛ ያለው የጊዜ ሒደትና ተዋረድ ምንጩ ከትግራይ ነገድ ሳባውያን ነው ። ከቤተ ክህነት እሰከ ቤተ ያሬድ ያለው ታሪክ ሲተነተን ምንጬ ከትግራይ ነው ። ከዘመነ አክሱም እሰከ ፍተሐ ነገስት ያለው የመንግስት አሰተዳደር ታሪክ ቢጠና ምንጩ ያው ከትግራይ ነው ። ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪዎች እጅ እንዳትሆን በተግባር የተፈተነ ህዝብ የትግራይ ህዝብ ነው ። በሁሉም መለኪያ ለኢትዮጵያ ግንባታ እና ቅርፅ የትግራይ ህዝብ አሰተዋጽኦ በግንባር ቀደም መነሳቱ ዘላለማዊ ነው ። እዚህ ላይ የትግራይ ምሁራን የትግራይ ህዝብ በሁሉም መስክ ለኢትዮጵያ ግንባታ ያደረገው አሰተዋጽኦ በአግባቡና በወቅቱ ተጠንቶና ተፅፎ ለትውልድ ማስተላለፍ ላይ ክፍተቶችና ድክመቶች ይታይባቸዋል ። የህዝብ ታሪክ በትክክል እና በተገቢው መንገድ ለመጪው ትውልድ መተላለፍ ይኖርበታል የሚል የፀና እምነት አለኝ ። ሰለሆነም ትግራይ ህዝብ ታሪክ በቂ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ተገቢውን ክብርና ቦታ እንዲኖረው የሁሉም የትግራይ ምሁራን የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት ለማሳሰብ እፈልጋለሁ ። በእኔ እምነት የትግራይ ህዝብ ተገቢውን የታሪክ ክብር አግኝተዋል የሚል እምነት የለኝም ። በመሆኑም የህዝቡን የታሪክ ምግባሮች ተገቢው ቦታ እንዲያገኙ የታሪክ ሰነዳ ያሰፈልጋል ። አድዋ ሲነሳ የትግራይ ህዝብ አሰተዋጽኦ አብሮ መነሳትና መዘከር አለበት ።

የጎሳ አክራሪ ጀማሪ ፖለቲከኞች በህዝብ ላይ ያነጣጠረ ትንኮሳ ለማንም እንደማይበጅ መገንዘብ አለባቸው ።ህዝብን ያህል ሐያል ቀርቶ ግለሰብም ቢሆን በሐይልና ጉልበት ማርበድበድ ፈፅሞ የሚቻል አይሆንም ። የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ ያለው ክብር ከማንም ቢበልጥ እንጂ ከማንም አያንስም ። ውስጣዊ ሰላሙንና ልማቱን ለሚፃረር ማንም ሐይል እድልና ፋታ የሚሰጥ ህዝብ አይደለም ። በመሆኑም በድንበር አዋሳኝ አከባቢዎች የሚደረጉ ያላሰፈለጊ የግጭት ትንኮሳዎች ተገትቶ በውይይትና በድርድር እልባት ማግኘት ይኖርባቸዋል ። የትግራይ ህዝብ ለግጭት ጊዜ የለውም ።ወንድም የአማራ ህዝብም እንደዛው ከወንድም የትግራይ ህዝብ ጋር ግጭት ውስጥ መግባት ፈፅሞ አይፈልግም ።የክልል ሆኑ የማዕከላዊ መንግስት አመራር ክፍተት ችግር በመሆኑ በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ ቦታዎች ውዝግብ ተመራጭ መፍትሔ በመቻቻልና በህግ መርህ ላይ የቆየ የጋራ ውይይትና ድርድር ማድረግ ይሆናል ። የጋራ ችግሮች በልዩ ሐይል እንዲሁም በመከላከያ ጣልቃ ገብነት የሚፈቱ አይደሉም ። ክልሎች ልዩ ሐይል የማሰልጠን ህገ መንግሰታዊ መብት የላቸውም ። በትግራይ እና አማራ እየተደረገ ያለ የጦርነት ዝግጅት ዋጋ ቢስ ከመሆኑም በላይ ማን ለማን ይገድላል ?። ከኢትዮ ኤርትራ ግጭት በቂ ተሞክሮ የተወሰደ ይመስለኛል ። የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም በውስጣዊ ግጭቶች የሚዳዳ አይሆንም ።

በቲም ዶክተር ለማ መገርሳ እየተመራ ያለ አገር በለውጥ ላይ መሆኑ ባያነጋግርም ወጣ ገባ የበዛበት አመራር እንደሆነ የሚያሳዩ ሁኔታዎች በመከሰት ላይ ናቸው ። ቲም ለማ አመራር በህዝብ ላይ በሚደርሱ ተገቢ ያልሆኑ ችግሮች ላይ አልሰማንም ፣ አላየንም የሚሉ የውሰለታ አካሄዶች እያየን ነው ። በለገጣፎ የተፈፀመ ህዝብ የማፈናቀል ተግባር በቀጥታ ቲም ለማ የሚመለከት ጉዳይ ነው ። የለገጣፎ ከተማ አሰተዳደር ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ ቤት የፈረሰባቸው ሰዎች ጣምራ ብሔር ያላቸው በመሆኑ ተገቢ ያልሆነ ወቀሳ እየደረሰብን ነው ሲሉ መሰማት ምንኛ ያሳፍራል ። እኝህ ሴት የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባል ናቸው ። ህገ ወጥ ቤቶች ናቸው በሚል ምክንያት ከ3000 ቤቶች በላይ የማፍረስ እርምጃ በወይዘሮ ሐቢባ ሲራጅ ሲወሰድ በቂ የቅድሚያ ጥናትና ዝግጅት አልተደረገም ። ህገ ወጥ ሰፈራ ለማንም አይበጅም ። ቢሆንም የመሬት ህገ ወጥ ወረራ ሲፈፀም ድርጊቱ በህግ አግባብ ማስቆም ሲቻል የመሬት ወረራ ሲደግፍና ሲያሰፈፅም የነበረ የመስተዳድር አካል ተገቢው ህጋዊ ቅጣት ሳያገኝ ቤት ገንቢዎች ላይ ያለበቂ የማስጠንቀቂያ እንዲሁም ዝግጅት  እንዲፈናቀሉ መፍቀድ ለዜጎች ያለን እይታ የተሸረሸረ ይሆናል ። የቲም ለማ አመራር ውሰጠ ንፅህና ጉዳት አለበት ። የለውጥ ሐይል በሚል እንቅስቃሴ የጀመረ ቲም ለማ በውስጡ በወንጀል የሚጠረጠሩ አመራር ሰጪ ሰዎች ያሉበት ሰብሰብ ነው ። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የለውጥ አካል አድርጎ ማሰብ ሸፍጥነት ነው ። የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን ሀላፊ በነበሩት ወቅት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል ። ዶክተር ወርቅነህ በተፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አሰፈላጊ ምርመራ እንዳይደረግ እንቅፋት ነበሩ ። ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ላይ ተገቢው ምርመራ መከናወን ይገባል የሚል እምነት አለኝ ። አቶ ደመቀ መኮነን ለውጥ አራማጅ መሆናቸው መልካም ቢሆንም የሜቴክ ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩ አመራር ሰጪ ሰው ናቸው ። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የሚያውቁት ይኖራል የሚል እምነት አለኝ ። ሰለሆነም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ደመቀ መኮነን ላይ ተገቢነት ያለው ምርመራ መደረግ አለበት ። የኢትዮጵያ ህዝብ እውነታውን የማወቅ መብት አለው ። ሌሎችም የዳበረ የሙስና ልምድ ያካበቱ የቱም ለማ ሙሰኞች ላይ ህጋዊ የፍትህ ምርመራ መከናወን ሒደት መፋጠን ይኖርበታል ።

የቲም ዶክተር ለማ መገርሳ አመራር በአገረ አሜሪካ ሚኖሶታ ግዛት ላይ ዘንድሮ የተከበረው 123ተኛ አመት የአድዋ ድል አጥቢያ ላይ ተመርቆ የተከፈተው የኢትዮጵያ ቆንፅላ መስሪያ ቤት መርቆ የከፈቱት የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳድር ክቡር ዶክተር ለማ መገርሳ ነበሩ ። ለመሆኑ የዶክተር ለማ መገርሳ የስልጣን ሀላፊነት ምን ድረስ ነው ?።  ዶክተር ለማ መገርሳ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተግባር ደርቦ እንዲሰሩ ሰልጣኑ ማን ሰጣቸው ?። አገር እየተመራ ያለው በህግ አግባብ ነው ወይስ በግለሰቦች ፍቃድ ?። በእኔ እምነትና እይታ የአንድ ክልል ሀላፊ ብቻውን የአንድ አገር ልዕልና መገለጫ የሆነ ኢምባሲ መርቆ የመክፈት ሰልጣን ያለው አይመስለኝም ። ከሆነም የሁሉም ወይም የተወሰኑ ክልል ርዕስ መስተዳድሮች በጉዳዩ ላይ መሳተፍ ነበረባቸው ። የዶክተር ለማ መገርሳ ሰርአት አልባ አሰራር ከትዝብት በላይ ህገ ወጥ አሰራር ነው ። ይህ ህገ ወጥ አሰራር አስተዋዩ የኦሮሞ ህዝብ የሚወክል አይመስለኝም ። ዶክተር ለማ መገርሳ ሚኖሶታ ላይ የፈፀሙት ስህተት ማብራሪያ እንዲሰጡበት በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ ። በሌላ ጉዳይ ደግሞ ክቡር ዶክተር ለማ መገርሳ በኦሮምኛ እና በአማርኛ የሚሰጧቸው ፖሊሲ ነክ አስተያየቶች ግልጽነት የላቸውም ። ሰለሆነም በርካታ ህዝብ በቲም ለማ ላይ እምነት የማጣት አዝማሚያ ይታያል ። በመንግሥት አመራር ጉድለት በሒደት ማህበራዊ ግጭቶች የመከሰታቸው አዝማሚያ ሰፊ ነው ። በመሆኑም መንግስት ስህተቶች በቶሎ ማረም ይኖርበታል ።

        የቲም ዶክተር ለማ መገርሳ አመራር አዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት ላይ ያለው ውሳኔ ግልጽ አይደለም ። በእኔ እይታ ይህ ቦታ ያ ቦታ የማን ነው የሚል ንግግር ሰሰማ ያቅለሸልሸኛል። ምክያቱም ወሃ የማይቋረጥ የወደቀ ሓሳብ ሰለሆነ ነው ። መነጋገር የሚገባው በልማትና የማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል ላይ መሆን ሲገባው በቦታ ሰያሜና ይዞታ ላይ ጊዜ ማባከን የደንቆሮዎች አሰተሳሰብ ከመሆን አያልፍም ። በኢትዮጵያ ምድር በከተሞች ሰያሜና ይዞታ ምንነትና ማንነት መነጋገር አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የድንቁርና ምልክት ነው ። መቀሌ የኢትዮጵያ ከተማ ነው ። የሚገኘው ግን በትግራይ ክልል ነው ። አዋሳ የኢትዮጵያ ከተማ ነው ። የሚገኘው በደቡብ የኢትዮጵያ ቦታ ነው ። ባህር ዳር የኢትዮጵያ ከተማ ነው ። የሚገኘው በአማራ ክልል ነው ። መቀሌ ሆነ አዋሳ ፣ ባህርዳር ሆነ አዳማ የብሔር ከተሞች አይደሉም ። የኢትዮጵያ ከተሞችና ቦታዎች ናቸው ። አዲስ አበባ የኦሮሞ ዋና ከተማ ናት የሚሉ ብቅል አውራጃዎች ምን እያሉ እንደሆኑ የሚገባቸው መስሎ አልተሰማኝም ። የትግራይ ህዝብ መቀሌ የትግራይ ናት ብሎ አያቅም ። የትግራይ ህዝብ በመቀሌ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጥላቻ ሆነ በምንም ምክንያት አፈናቅሎ አያውቅም ። በባህር ዳርም አልታየም ። አዲስ አበባ የኦሮሞ ዋና ከተማ ናት የሚሉ የኦሮሞ ፖለቲካ ተዋናዮች መነሻ ምክንያቶች ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቢሆኑም ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው እየተደረገ ያለ እሩጫ ለማንም አይበጅም ። አዲስ አበባ የማንም ብሔር ዋና ከተማ አይደለችም ። አዲስ አበባ በታሪክ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ትቀጥላለች ። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ አጎራባች ቦታዎች ለአዲስ አበባ ቅርበት ስላላቸው የተለየ ጥቅም የሚያገኙበት አንዳች አሳማኝ ምክንያት የለም ። እንዲያውም ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርበት ስላላቸው ከሌሎች ቦታዎች የተሻለ የገበያ ግብይት ስለሚኖራቸው ከሌሎች ቦታዎች የተሻለ ተጠቃሚ ናቸው ።አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ህዝቦች መናገሻ ዋና ከተማ ናት ። በአጠቃላይ አዲስ አበባ ጨምሮ የሚነገሩ እንዲሁም የሚሰጡ አስተያየቶች አሳዛኝ ናቸው ። ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ ማሰብ የተሳነን ደረጃ ላይ መድረሳችን ቢያሳዝን እንጂ የሚያስደስት አይደለም ። እንደ አንድ አገር ህዝብ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ እድገት ፖሊሲ ላይ መነጋገር ሲገባን ራያ ወልቃይት ፣ አዋሳ ሲዳማ ፣ አፋር ኢሳ ፣ ኦሮሞ ሱማሌ ፣ አዲስ አበባ ድሬዳዋ እያልን መናቆር እንደ አገር ምንኛ ያሳፍራል ። አዲስ አበባ የኦሮሞ ሆነ አልሆነ የሚገኘው ፋይዳ ምንድን ?። በአዲስ አበባ የሚኖሩ ዜጎች ለማፈናቀል ወይሰ ለጋራ እድገት ? ። አሳዛኝ ዘመን ላይ ነው ። አስተሳሰባችን ሆነ ተግባራችን የአንድ አገር ዜጎች አንመስልም ። የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ በታሪካዊቷ ትግራይ መቀሌ ቢሆን ተመራጭነት ነበረው ።

የቲም ዶክተር ለማ መገርሳ አመራር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤተ እምነት ፖትርያርክ ላይ እየደረሰ ያለው ህገወጥ ወከባ ማስቆም አለበት ። በለውጥ ምክንያት የቤተ እምነት ደንብ ባልጠበቀ ሁኔታ እየተካሄደ ያለው የሥራ ጫና ብሎም ፖትርያርኩ ከቦታ የማስነሳት እቅድ አገራዊ ችግር ከማስከተሉ በፊት መጠንቀቅ የሚበጅ ይመስለኛል ። ፖትርያርኩ እያካሄዱት ያለው ለውጥ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል ፣ የደህንነት ጥበቃም ያስፈልጋቸዋል ። በእምነት ሸፋን የፖለቲካ ጨዋታ የሚያካሔዱ አክራሪ ጳጳሳት ሰርአት አደብ እንዲያደርጉ ፣ ለህግ እንዲገዙ መደረግ አለባቸው ። በቤተ እምነት የሚደረጉ ውስጣዊ የአስተዳደር ለውጦች የቤተ ክህነቱን ቀኖና የተከተሉ መሆን ይኖርባቸዋል ። ከዚህ በፊት የተፈፀመ ስህተት አሁንም መደገም የለበትም የሚል አሰተያየት አለኝ ። ፖትርያርኩ ላይ እየተፈጸመ ያለ ወከባ በቶሎ ካልቆመ የቤተ ክህነቷ ቀጣይ እጣፈንታ አደጋ ላይ ይወድቃል ። በለውጥ ሰም የሚፈፀም ወንጀል መቆም ይገበዋል ። አሁን በቤተ ክህነት እየተፈጸመ ያለ ሰርአት አልባ የጥላቻና ህርፈተ ሰልጣን  የፖትሪያርኩንህልውና የሚፈታተን በመሆኑ ለችግሩ እልባት ካልተበጀለት ፖትርያርኩ በቦታው የሚቆዩ አይመስለኝም ። አገሪቷም ዝቅጠት ውስጥ የመግባት እድል የሰፋ ይሆነናል ። ብጥብጥና ሰርአት አልበኝነት ይስፋፋል ። ለውጭ ጣልቃ ገብነት ይጋብዛል ። እልቂት ይከሰታል ። ቲም ለማ የጎሳ አክራሪዎች ላይ ክትትል ማድረግ የግድ የሚልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል ። በቤተ ክህነት የብሔር ጥላቻ በፊት ከነበረው ጨምሯል ። ይህ ሁኔታ በአጭሩ መፍትሔ ካላገኘ ለኢትዮጵያ ህልውና አስጊ መሆኑ አይቀርም።

 

 

 

Back to Front Page