Back to Front Page


Share This Article!
Share
አስተማማኝ ሰላም በሌለበት አገር ጤናማ ኢኮኖሚ ሊኖር ኣይችልም

አስተማማኝ ሰላም በሌለበት አገር ጤናማ ኢኮኖሚ ሊኖር ኣይችልም

ፍስሃ መረሳ 02/ 09/19

ባለፈው ሳምንት  በነበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተለመደ የስብከት ስራቸውን ያቀረቡ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ያለውን ተጨባጭ ሃቅ በመካድ የሌለና በፍፁም ሊታመን የማይችል ሪፖርት እንዳቀረቡ ሁላችን ሰምተናል፡፡ከሪፖርቱ አንዱ በአገሪቱ ያለው ኢኮኖሚ ጤናማ እንደሆነና እንድያውም ከማንኛውም ጊዜ በተለየ መንገድ የውጭ እርዳታ እንደተገኘና የኢኮኖሚ ግሽበቱም መቆጣጠር እንደተቻለ ሪፖርታቸው ይገልፃል፡፡አቀራረቡ በዝርዝር በመረጃ የተደገፈ ስላልነበረ በዛ መልክ ለእያንዳዱ በመረጃ የተደገፈ ማብራርያ ማቀረብ ባይቻልም የተወሰኑ ጉዳያች በማንሳት ምን ያክል ሃሰት መሆኑ ማሳየት የበለጠ ነገሩን ግልፅ ሊያደርገው  ስለሚችል አሁን በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታና ራሱ መንግስትም በተለያዩ መድረኮች ይፋ ካደረገው ሪፖርት መነሻ ማድረግ   ማብራራት የተሻለ ይሆናል   ፡፡

ሰላም በሌለበት አገር  ጤናማ ኢኮኖሚ ሊኖር  አይችልም

የአገራችን ሰላም ከደፈረሰ ለብዙ ጊዜ ቆይታል ፡፡ በተለይ ባለፉት 10 ወራት ደግሞ በከፋ መንገዱ ሰላማችን ስለደፈረሰ ግጭትና ትርምስ መለያችን ሆነዋል ፡፡ ከሶስት ሚልዮን በላይ የሆኑ አምራች ዜጋ በየአካባቢው እንደተፈናቀለ ይቅር እኛ አለምም ያወቀውና ብዙ የተነገረበት ጉዳይ ነው  ፡፡ መንገድ መዝጋት መሰረተ ልማት ማውደም የተለመደ በየቀኑ በብዙ አከባቢዎች የሚታይ ክስተት ሆነዋል ፡፡ ሌላው ይቅር መንግስት ባለበት አገር በጠራራ ፀሃይ የመንግስትና የግል ባንኮች ሳይቀሩ ተዘርፈዋል ፡፡ ሰላም በሌለበት ሁኔታ የውስጥም የውጭም ኢንቨስትመንት በፍፁም ሊታሰብ አይችልም ፡፡ በዚህ ምክንያት የአገራችን  ኢንቨስትመንት በእጅጉ እንደተጎዳም ሊካድ የማይችል ሃቅ ነው ፡፡ በኦሮምያ ክልል ብቻ ራሱ ክልሉ ባወጣው መግለጫ እንደሰማነው በኢንቨስትመንት ምን ያክል ጉዳት እንደደረሰ ይታወቃል ፡፡ ሰላም ከሌለ ዜጎች ሰርተው ገቢያቸውን ማሳደግና ራሳቸውን መለወጥ አይችሉም ፡፡ ስለዚ በየትኛው መመዘኛ ነው አስተማማኝ ሰላም በሌለበት ፖለቲካዊ ሁኔታ  ጤናማ ኢኮኖሚ ሊገነባ የሚችለው የሚል መልሱ ለማግኘት ቀላል ነው የሚሆነው  ፡፡

Videos From Around The World

ኢኮኖሚውም እየተዳከመ መሆኑን የራሱ የመንግስት ሪፖርት  ያስረዳል  

እስኪ የተወሰኑትን እንደማሳያዎች እናንሳ - የአገሪቱ የውጭና ገቢ የንግድ ሚዛን /Trade balance/ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ የተዛባ መሆኑን መንግስት ራሱም ያውቀዋል ፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሬ ገቢያችን የ2011 ዓ/ም  የስድስት ወር አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያሳየው ኣንድ ነጥብ ሁለት ቢልዩን ብቻ መሆኑና ይህ ደግሞ ከተያዘው እቅድ 62 ፐርሰንት እንደተፈፀመና  ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀርም ከፍተኛ ቅናሽ እንዳሳየ ሚኒስተር መስራቤቱ ይፋ  አድርጓል፡፡


ሌላው የ2011 ዓ/ም  ገቢ የመሰብሰብ አቅማችን ሲታይም በዚህ ስድስት ወር ፌደራል መንግስት ይሰበባለ ብሎ ከያዘው እቅድ ከ28 ቢልዮን ብር በላይ ኣልተሰበሰበም ይላል የራሱ ይህን ስራ የሚከታተል ሚኒስተር ሪፖርት፡፡ የክልሎች የግብር አሰባሰብ ስራ ስታይም በተለይ በዚህ አመት ከትግራይ ውጪ ከ30 ፐርሰንት በላይ መሰብሰብ እንዳልቻሉና አንዳንድ ክልሎች ጠቅልለው እስከ መሰብሰብ ያቆሙበት ደረጃ እንደደረሱ  ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ የአገሪቱ የትላልቅ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ሲታይም በተለይ የመንገድ  ፕሮጀክቶች  ከባለፈው አመት አፈፃፀም ሲታይ ዝቅተኛ እንደሆነ ይታወቃል  ፡፡

ሌላው የኢንዳስትሪና የሰርቪስ ሴክተሩ የግብርናውም  እድገት ሲታይም ከዚህ የተለየ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ታድያ  በየትኛው መመዘኛ ነው ጤናማ ኢኮኖሚ እየገነባን ነው ማለት የሚቻለው የሚል ጥያቄ በመንግስት በኩል  ምላሽ ሊያገኝ የማይችል ተገቢ ጥያቄ ነውማለት ይቻላል፡፡ በተለይ በአሁኑ ሰዓት የነዚህ ያየናቸው ድምር ውጤት ስራ አጥነት በአገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደመጣና  አንዱ የሰላም እጦትና የግርግር መነሻ መሆኑም የሚታወቅ ጉዳይ ነው ፡፡

 እንደ ትልቅ ድል ተብሎ በሪፖርቱ የቀረበው ጉዳይ የኢኮኖሚ ግሽበት 13 ፐርሰንት ደርሰዋል የሚል ነጠላ ዜማ ብቻ በመውሰድ ኢኮኖሚውን ጤናማ ነው ለማለት ብዙ ትንተና እንደቀረበም ሰምተናል ፡፡ በጣም የሚያሳፍርና የሚገርም ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ለመሆኑ ግሽበት ብቻ በመውሰድ እንመዝን ከተባለም በየትኛውም አገር  ከአንድ አሃዝ በላይ ግሽበት ከተመዘገበ  ኢኮኖሚው ችግር ላይ እንዳለ የሚየሳይ እንጂ የኢኮኖሚ ጤንነት መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢንቨስትመንት በተዳከመበት አገር ያለው ገንዘብን በመገደብ በሌላ አገላለፅ ኢንቨስትመንትን በመገደብ ግሽበት መቆጣጠር ቀላልና የደካማ መንግስት የሞኒተሪ ፖሊሲ መሳርያ መሆኑም  ይታወቃል ፡፡ ስለዚህ አሁን በአገሪቱ እየታየ ባለው ከፍተኛ ቀውስ ምክንያት በሁሉም ዘርፍ እድገት ሳይሆን ማሽቆልቀል እየታየ እንዳለ ለመረዳት ብዙ የሚያስቸግር ጉዳይ ኣይደለም ፡፡ መንግስት ይህ መሆኑን እያወቀ ግን ይህን ሃቅ በመደበቅ ሓላፊነት በጎደለው መንገድ ህዝብን ለማታለል በሌለና ባልመጣ ለውጥ ለውጥ ተመዝግበዋል በማለት በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርገው የስብከትና ለጊዝያዊ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ታሰቦ የቀረበ ካልሆነ በስተቀር በቀውስ በምትታወቅ አገር ከጥፋት ውጪ ጤነኛ ኢኮኖሚ ሊኖር ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሆነው ፡፡

 

Back to Front Page