Back to Front Page


Share This Article!
Share
በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ በአዋጅ መታገድ አለበት ።

በኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ በአዋጅ መታገድ አለበት ።

        ፀሐፊ ። ልኡል ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

ቀን ፣ ጥር 14/2011

 

             በኢትዮጵያ ህዝብ በድለናል የሚል መሪ አልነበረም ። ህዝብ በተለያዩ ጉዳዮች በመንግስት በደል ሊደርሰበት ይችላል ። የፍትህ እጦት ፣ የመብት ፣ እንዲሁም የሐሳብ ነፃነት ያለመኖር በድህነት ከረጢት ውስጥ  ለመኖር የሚሰገድዱ ሰዉ ሰራሽ  ጋሬጣዎች ናቸው ። እነዚህ ጉዳዮች መንግስት ሳይመራባቸውና ሳያከብራቸው ሲቀር ማህበራዊ ህውከቶች ማስከተላቸው ማይቀር እውነታ ነው ። ለህዝብ ቅርብ ያልሆነ ስርአትና የመንግስት አሰተዳደር ሰሩ እንዳረረ ተክል ነው ። ለህዝብ የቀረበ መንግስት ሲባል ቀለል ባለ አገላለፅ ህዝብ የሚቆጣጠረው መንግስት ማለት ነው ። በኢትዮጵያ የሰነ መንግስት ጥናት መሠረት ለህዝብ የቀረበ መንግስት የለም ።  መንግስት ህገ መንግስት አርቃቂና አፅዳቂ  በመሆኑ የሰከነ ዲሞክራሲ ሊሰፍን አልቻለም ። ህገ መንግስት መንግስት መስራች እንጂ መንግስት ህገ መንግሰት መሥራች ሊሆን ፈፅሞ አይችልም ። በኢትዮጵያ ህገ መንግሰት የመሰረተው መንግስት አልነበረም ፣ አሁንም የለም ። ኢትዮጵያዊያን መሪዎች የነበረው ማፍረስ እንጂ የነበረው የማስቀጠል ልምድም ሆነ ፍላጎት የላቸውም ።የንጉሡ ወታደርና ሰርቶ አደር በደርግ ሲበተን በተራው የደርግ ሰራዊትና ጥሮ አደር በኢህአዴግ መር ሰርአት ፈርሰዋል። ይህ መሆን ያልነበረበት ታሪካዊ ስህተት ነበር ። የነበረው አቀናጅተህ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ዜጎች ለአደጋና ሰቃይ ማጋለጥ ጠላትነት ካልሆነ እድገትና ሰላም አይመጣም ።

            በኢትዮጵያ የመንግስት ምስረታ ችግር ለምን ዘመን ተሻጋሪ እንደሆ ሳይነሳዊ ጥናት የሚያስፈልገው አይሆንም ። የችግሩ ምንጭ  ለመጪው ትውልድ የሚያስብ እንዲሁም የሚተጋ የፖለቲካ ሰርአትና መሪ እጦት ነው ። ብሔርና ዘር የሚቆጥር ሰርአት በምን ስሌት አንድ ልአላዊ አገር ሊያሰተዳድር ይችላል ? ። የኢትዮጵያ ዋናው የድህነትና የደህንነት ችግር ቤተ መንግስት የሚገባ መንግስት ነው ። ህዝባዊ ስልጣን እርስት አይደለም ። ሰልጣን የህዝቦች ብቸኛ የጋራ ሀብት ነው ። በህዝብ ፍቃድና ፍላጎት ላይ ያልተመሠረተ መንግሰታዊ አሰተዳደር መግዛት እንጂ ህዝብ ማስተዳደር ከቶ አይሆንም ። አድሮ ጥጃ ባይሆኑ ኖሮ ቅሉ  በኢትዮጵያ ውስጥ መልካም ሰብዕና እንዲሁም ህዝባዊ ተቀባይነት የተቸራቸው በሳልና አርቆ አሳቢ ፖለቲከኞች ነበሩ ። በሌላ ጎን ደግሞ ከአገርና ህዝብ ጋር የተጣሉ ፖለቲከኞችና መሪዎችም ነበሩ ። በኢትዮጵያ የመንግስትነት በትረ ሰልጣን የሚይዙ ሰዉ መሳይ መሪዎች ተመሳሳይ የመንግስት አሰራርና አመራር አላቸው ። በእኔ እይታ መሪዎች ሥራ አጥ ቦዘኔዎች ይመስለኛል ። ጭቆናና አፈና ፣ መግደልና ማሰር ፣ መሰረቅና የአገር ሐብት ማሸሽ  የቅድሚያ ተግባሮቻቸው ናቸው ። ለአብነት ያህል የሰንት ባለስልጣን ልጆች ኢትዮጵያ ውስጥ ይማራሉ ቢባል መልሱ በጣት የሚቆጠሩ ይኖሩ ይሆናል ። አብዛኛዎቹ  የባለስልጣን ልጆች ትምህርታቸው የሚከታተሉ ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ አህጉሮችና አገሮች ውስጥ ነው ። ባለስልጣኑ ልጁን ውጭ አገር ለማስተማር የሚያስችል የገንዘብ አቅም ከየት አመጣ ?።  ለዛም በውጭ ምንዛሪ ። ምን ያህል የአገር ሀብት በየዓመቱ ከአገር ይሸሻል በእነማንሰ ይሸሻል ቢባል መልሱ በአገርና ህዝብ የሚነግዱ የመንግስት ሀላፊዎችና የፖለቲካ ነጋዴዎች መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ የለውም ።              በሰኔ 16 , 2011 ዓ.ም የግድያ ሙኮራ እንዲሁም በመሰከረም ወር 2011 ዓ.ም የመፈንቅለ ሰልጣን ሙኮራ የተፈፀመባቸው ጠቅላይ ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ መሪ ቢሆኑም በህዝብ የተመረጡ አይደሉም ። ከአንድ ጣምራ የፖለቲካ ፖርቲ በሽግግር የመሪነት ስልጣን የተረከቡ በመሆናቸው የህዝብ ሙሉ ውክልና የላቸውም ። በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ብሔር ተኮር ከሆነ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ ፖርቲ መሥራችና ሊቀመንበር በመሆናቸው የአገር መሪ አድርጐ ለማየት ብዙ ያልተሟሉ መስፈርቶች አሉ ። ኢትዮጵያ ብሔር መሠረት ያደረገ ምግባረ ሰናይ እንጂ ብሔር መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ድርጅት በጭራሽ አያስፈልጋትም ፣ አይመጥናትም።  የአንድ አገር ህዝቦች ገጀራ አንሰቶ ወንድም እህቱን ሲገድል ፣ ከቀየው ሲያፈናቅል ፣ ሀብትና ንብረት ሲዘርፍ ከማየትና መሰማት ውጭ የሚሰቀጥጥ ጉዳይ ምን አለ?። በአንድ ልአላዊ አገር የመኖሩ ዜጎች በአብሮነት መልካም ፍቃድ ላይ የተመሰረተ የጋራ ብልጽግና ላይ የተመረኮዘ ህገ መንግስት አርቅቆና አፅድቆ ሰላማቸው ጠብቆና አስጠብቆ ለመኖር የሚያስችላቸው ህዝባዊ መንግስት መምረጥ ይኖርባቸዋል ። የኢህአዴግ ሰርአት ሆነ መንግስት ከመንቀዙም አልፎ በሰብሰዋል። ከኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ለቆ ወጥተዋል ። ስርአቱ በህዝብ አሰተሳሰብ ውስጥ የለም ። በህግም እንዲታገድ የበርካቶች ጥያቄና ፍላጎት ነው። ምክንያቱም የኢህአዴግ መር መንግስት በጋህድ ሆነ በህቡዕ ሰብዓዊና ቁሳዊ ወንጀሎች ፈፅመዋል። የአገር ሐብት መዝብረዋል። ስርአቱ ለዜጐች መፈናቀል አብይ ምክንያት ሆነዋል ።

Videos From Around The World

          አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንጂ የኢህአዴግ ሰርአት አይደግፍም ። በመሆኑም ዶክተር አብይ በአስቸኳይ የህገ መንግስት ማሻሻያ አዋጅ በማውጣት ደም የሌለው ፖርላማቸው መበተን ይኖርባቸዋል ። የህዝብ ወኪል የፖርላማ ስብስቦች አይደል የወከላቸው ህዝብ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ይቅርና የራሳቸው መብት ያላሰጠበቁ አድርባዮች ናቸው ። የአገር ሐብት ሲባክን ፣  የውጭ እዳ ሲቆለል ፣ ዜጋ ፍትህ አጥቶ ሲሰቃይ ፣ ዜጎች ሲፈናቀሉ የኢትዮጵያ ፖርላማ የከተሙ ሰው መሳይ ግን በተግባር አሻንጉሊቶች መንግስት የፈፀማቸው የፍትህ ጉድለቶች ተከታትሎ ማረምና ማስቆም ሳይችሉ ቀርተዋል ። የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአዋጅ መፍረስ ይኖርበታል ። የሰብአዊ መብት እንዲሁም የእንባ ጠባቂ ተቋማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በአዋጅ ማፍረስ ይኖርበታል ። በብሔር የተዋቀሩ ውይም የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች በአዋጅ መበተንና መፍረስ ይኖርባቸዋል ። ለኢትዮጵያ የሚበጅ አገራዊ ራእይ ያለው የፖለቲካ ፖርቲ እንጂ የብሔር ራእይ ያለው የፖለቲካ ድርጅት አይደለም ። የብሔር ድርጅት አገርና ህዝብ ሊያሰተዳድር የሚያሰችል መርህ አይኖረውም ። በህዝብም ቅቡልነት አይኖረውም ።የብሔር ፖለቲካ በትልቁ አገር አፍራሽ ነው ። የብሔር ነፃነት ከብሔር ፖለቲካ ድርጅት ጋር የሚያስተሳስረው ጉዳይ የለውም ። 

          በኢትዮጵያ በ 2012 ሊካየድ የታሰበው አገራዊ የስልጣን ምርጫ መዘግየት የሚያስፈልግበት በርካታ ምክንያቶች አሉ ። 80 የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች ይዞ ህዝባዊና አገራዊ ምርጫ ማስፈፀም የቆዩ ችግሮች እንደነበሩ ይቀጥሉ እንደማለት ይታሰባል ። በዲሞክራሲ መርህ መሠረት አገር ሊኖራት የሚችል አንድ መሪ ፣ አንድ የፍትህ ተቋም  ፣ አንድ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሲሆን ሁለት መሪ ወይም ሁለት የታጠቀ ሐይል ሊኖራት አይችልም ።  የመከላከያ ሰራዊት ተልእኮ ማደናቀፍ ኢህገ መንግሰታዊ ከመሆኑም በላይ ወንጀል ነው ። በኢትዮጵያ በአንዳንድ ክልል ቦታዎች እየታየ ያለ ከመከላከያ ጋር የሚደረግ ሰጣ ገባ መልካምነት የለውም ። በአሻጥር የመከላከያ ተግባሮችና ተልዕኮዎች ማስተጓጎልና ማደናቀፍ የሚያስከትለው አደጋ ከግምት መግባት ይኖርበታል ። መከላከያ እንዳይንቀሳቀስ መንገድ ምንም በማያውቁ ህፃናት መዝጋት በመከላከያ ስርአቱ ላይ እምነት ማጣትን ያሳያል ። ከሆነ መከላከያ ማስከበር ነው ከሆነም በአዋጅ ማፍረስ ነው ። ከነዚህ ውጭ አማራጭ አይኖርም ። የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋም በችሎትና አቅም ላይ እንጂ በብሔር ተዋህዶ /ተዋፅኦ /ላይ ያተኮረ መሆን የለበትም ። አገር መከላከያ በብሔር ተመጣጣኝ ሆኖ ሊገነባ ፈፅሞ አይችልም ። ተሞክሮ አለም ላይም የለም ። ለኢትዮጵያ የሚመጥን በብቃትና ችሎታ ላይ የተመሰረተ መከላከያ ተቋም ነው ። የብሔር ተመጣጣኝ መከላከያ ተቋም የሚባል ክሰተት አይኖርም ። የደርግ ሰርአት ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በብቃታቸውና ችሎታቸው የሚያገለግሉበት የአገር መከላከያ ተቋም ነበር መከላከያ ተቋሙ የተገነባው በብሔር አለነበረም ። የሆነ ሆኖ በሚቀጥለው ዓመት ሊካሔድ የታሰበው አገራዊና ህዝባዊ ምርጫ መዘግየት አለበት ።  ምርጫ ለማከናወን ሰላምና መረጋጋት መኖር የግድ ይሆናል ። በአሁኑ ወቅት ብዙ አካባቢዎች ሰርአት አልባ የሰፈር አለቆች ህገ ወጥ መሳሪያ ይዞ ስርቆትና ግድያ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ ። የጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ መንግሰት ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር መቆጣጠርና ማስቆም ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ ። በመንግሥት በኩል የአቅም ውስንነት እንዳለ የሚያሳዩ ጠቃሚ መረጃዎች አሉ ። በሌላ ሁኔታ ደግሞ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ አቅጣጫዎቻቸው በውል አይታወቅም ። ከፊሎቹ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው በመሆናቸው ለምርጫ መቅረብ አይችሉም ። ህገ መንግሥቱም አይፈቅድም ። ሌለው ደግሞ የዲሞክራሲና የፍትህ ተቋማት ገና የመዋቅር ለውጥ አላደረጉም ።

             በኢትዮጵያ ከምርጫ በፊት መቅደም ያለበት አብይ ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት  ነው ። ይሄ ለማድረግ ደግሞ እርቀ ሰላም መካሔድ አለበት ። እርቀ ሠላም ለማስፈን ደግሞ የእርቀ ሰላም ኮምሽን መመሰረት ይኖርበታል ። በዳይና ተበዳይ በህግ የበላይነት መዳኘት ይኖርባቸዋል ። ተበዳዮች የበደል ካሳ (Compensation ) ማግኘት ይኖርባቸዋል ። ዜጎች ለደረሰባቸው ጉዳት መንግስት ካሳ መክፈል አለበት ። ዜጎች ያለምንም ምክንያት ለዘመናት ከሰፈሩበት ቦታ በሐይል ተፈናቅለዋል ። ኢሰብአዊ ጥቃት በዜጎች ላይ ተፈፅሟል ። ለጥቃታቸው አብይ ምክንያት የብሔር ፖለቲካ ሲሆን ከፊል ጥቃቶች የተፈፀሙት በመንግሥት ባለስልጣናት ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በስርአት አልበኞች የተፈፀመ ነው ። አሁንም ድረስ ሰለ ብሔርተኝነት ትርጉም የለሽ ቀረርቶና ሸለላ የሚያቅራሩ ሰው መሳይ ጅሎች የመኖራቸው ያህል ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የላቀ ክብር ያላቸው የግራ ፖለቲከኞች አሉ ።  ለኢትዮጵያ ቀረርቶ አያስፈልጋትም ። ገና በቅጡ ከኑሮ ጋር ያልተዛመደ ህዝብ ባለበት አገር ህዘብ የሚያጋጭ ተግባር ላይ ጊዜና ገንዘብ ማጥፋት ለማንም አይበጅም ። የሚበጀው የተጀመረው የዲሞክራሲ ሒደት በፍጥነትና በጥራት ማስቀጠል ብቻ ነው ። ይህ ሲሆን መጪው ትውልድ በዲሞክራሲ የተገነባ አንዲሁም ቀጣይነት ያለው እድገትና ሠላም የሚሳካው ። ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ህግና ሰርአት መሠረት አድርጐ የሚያስተዳድር ባለራዕይ መሪ እንጂ አፋኝና ሰብዓዊ መብት ረጋጭ መንግስት አይደለም ።  የአገር ውስጥ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ከማንም ጋር መደራደር አያስፈልግም ። በማንኛው ጊዜ ህዝብ በሰላም እንዲኖር የመንግስት የቅድሚያ ቅድሚያ ሐላፊነት ነው ።

             ኢትዮጵያ የተቋም መዋቅር ሽግግር ላይ ነች ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንግስት ለውጥ አሸጋጋሪ መሪ ናቸው ። የኢትዮጵያ ህዝብም የሚረዳው ባልኩት መልኩ ነው ። ዶክተር አብይ በሁለት የሐሳብ ጠጎች መሐል ላይ ይገኛሉ ። አንደኛው ሓሳብ የፌደራል ብሔርተኝነት ሲሆን ሌላኛው ሓሳብ ደግሞ ፌደራላዊ የዜግነት ሰርአት መመሰረት ነው ። በአጭሩ የዘር ፖለቲካ (ብሔርተኝነት ) እና የዜግነት (አንድነት )ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ደረቅ ሀሳቦች ናቸው ። በሁለቱ ሃሳቦች መካከል ተዛማጅነት ቢኖራቸውም ተቀራርቦ ለመወያየትም ሆነ ለመስራት በፖለቲከኞች መካከል ያለው ስምምነት የተቀዛቀዘ ነው ። ለ27 አመት ያህል በክልል ታጥራ የቆየች አገር ወደ ዜግነትን ፖለቲካ ለማዞር ጊዜና ብቃት ይጠይቃል ። ክልሎች የኢትዮጵያን እድገት በሚያፋጥን መሰመር ውስጥ አልነበሩም ። ህዝብ እያፈናቀሉ እንዴት እድገትና መረጋጋት ይመጣል ?። አለም ላይ በአገር ፅንስ ሓሳብ እንጂ በክልል (በዘር )የተሰራ የመንግስት መዋቅር የተለመደ አይደለም ። ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ በአግባቡ ተግባር ላይ ካልሆነ ህዝብ ሰርአት ያፈርሳል ። በመሆኑም በኢትዮጵያ የቆየ ችግር አሁንም ያለ ህዝብ የስርአት ለውጥ በሚሻበት ወቅት አገርኛ ሊሂቃኖች በውይይትና ድርድር ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥን ዲሞክራሲያዊ ሰርአት መትከል ያሰፈልጋል ። የፖለቲካ ልዩነት ሃሳብ መቻቻል እንዲኖር መነጋገርና መወያየት ያሰፈልጋል ። በድሃ አገር ለስልጣን ላይ ለመንቆናጠጥ የሚደረግ የፖለቲካ ቁማር ወንዝ አያሻግርም ። በኢትዮጵያ የመቻቻል ዲሞክራሲ ገና አልተለመደም ። የተለመደው ጭንቅላት ሲለግም እግር መጎተት ነው ። ባንክና ታንክ ያለው አካል ተቀናቃኙን ያስራል ፣ይገድላል ፣ አልያም አገር ለቆ እንዲሰደድ ይደረጋል ። የፖለቲካ በላይነት / Political superiority / በአደጉ የአለም አገሮች አይሰራም ። በታዳጊ ግን የስርአቱ የምዝበራ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ። የፖለቲካ በላይነት የመንግስት ብልሹ አሰራርን እንዲሸፈን /Cover up tool/ ሆኖ ያገለግላል ። የዜጎች ሰብአዊ አይከበርም ። የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አይሆኑም ። 

         በፖለቲካ መዋቅርና ለውጥ ወቅት የሚያጋጥሙ ማህበራዊ እንዲሁ የኢኮኖሚ ችግሮች ይኖራሉ ። በኢትዮጵያ  በዲሞክራሲያዊ ውድድር የመንግስት ስልጣን ርክክብ የተደረገበት ዘመን የለም ። አንድ ትውልድ ገድሎ ያጠፋ የደርግ ሰርአት ከንጉሱ ሰልጣን የተረከበው በህዝባዊ ምርጫ አልነበረም ። ሌላ ቀርቶ ንጉሡ በወጉ አልተቀበሩም። በደርግ ሰርአት የደረሰው ሰብአዊ ግፍ ለመግለጽ ያስቸግራል ። የደርግ ስርአት በኢህአዴግ ሰርአት ሲተካ የደርግ ተባዮች ላይ የተወሰደ ተመጣጣኝ የፍትህ እርምጃ አልነበረም ። የደርግ ሰርአት ቁንጮ ሆኖ አገር ሲያምስ የነበረ መንግሥቱ ሐይለማርያም ላጠፋው ጥፋት ፣ለበደለው በደል በአግባቡ አልተጠየቀም ። ያ ሰው በላው መሪ (መንግሥቱ ሀይለማርያም ) ዜጎች በድሎ አሁንም በህይወት አለ። ጥገኝነት ከጠየቀበት አገረ ዙምባቡዌ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በሰላም እንዲኖር በአንዳንድ ሰዎች ስሰማ ያመኛል ።በሰው ቁሰል እንጨት ሰደድበት መሆኑ ነው ። አሁንም ድረስ የደርግ ሰርአት አፍቃሪዎችና ናፋቂዎች እንዳሉም እገምታለሁ ። በእርግጥ መንግሥቱ ሀይለማርያም ማሞካሸት መብታቸው ቢሆንም በጤናቸው ግን አይመስለኝም ። መንግሰቱ ሀይለማርያም የሚያሞግሰ ሰው ካለ የታመመ ወይም የደነቆረ መሆን አለበት ። መንግሥቱ ሀይለማርያም ታሪክ አልባ መሪ ነው ። ገዳይ፣ አብዮተኛ ፣ እንዲሁም አምባገነን መሪ እንጂ ልማታዊ መሪ አልነበረም ። ተወዳዳሪ ያልነበረው ጨካኝ ሰው በላ መሪ ነበር ። ኢትዮጵያን ቁልቁል የሰደዳት ይህ ጨካኝ መሪ ነበር ። ጥይት እንጂ መደራደርና ችግሮች በውይይት የሚፈታ መሪ  አልነበረም ። 

         ኢትዮጵያ ብዙ ፀጋ እያላት ትግበራ ላይ ግን ችግር አለ ። ነዳጅ በዚህ በዛ ተገኘ ይበላል ። ማምረት ጀምረናል ይባላል ። አንድ ሊትር አገልግሎት ላይ ሳይውል ደግሞ ነዳጅ ማምረት አቁመናል ይባላል ። ችግሩ ነዳጅ መገኘቱ አለመገኘቱ አይደለም ። ችግሩ በየትኛውም ቦታ ፍትሀዊ የመንግስት አሰተዳደር ሆነ አመራር የለም ። እንደ እኔ ምልከታ በኢትዮጵያ የነዳጅ ሐብት መጠቀም መጀመር የኢትዮጵያ ህዝብ በቁሙ ማፋጀት መስሎ ይታየኛል ። እንካን ነዳጅ ማምረት ጀምረን አፈር ላይ ስምምነት የለንም ። ነዳጅ ካለም እሱም በብሔር የተከለከለ ነው ። በሱማሊያ ክልል ነዳጅ ከተገኘ የክልሉ ተፈጥራዊ ሀብት ተደርጎ ይወሰዳል ። ግን ጅጅጋ የኢትዮጵያ ቦታ መሆኑ ከግምት አይገባም ። በወሎ ቦታዎች ነዳጅ ከተገኘ የኢትዮጵያ ነዳጅ ሀብት ሳይሆን የወሎ ተደርጎ ይወሰዳል ። በአፋር ክልልም እንደዛው ነው ። ብሔር ተኮር የመንግስት መዋቅር የአገር ሀብት ብክነት መነሻ ምክንያት ነው ። ሁሉም ዜጎች ከሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ የሚያደርግ አይደለም ። በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ መጠቀም አለመቻል ለውሰጣዊ ግጭት ይዳርጋል ። የሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ይሆናል ።የኢትዮጵያ ህዝቦች በብሔር ተከፋፍሎ ምድራዊ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ፈፅሞ አይችሉም ። ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጅ ህዝባዊ መንግስት መመስረቱ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ። የኢትዮጵያ አንዱ የድህነት ምንጩ ህዝባዊ መንግስት ያለመኖሩ ነው ። የብሔር ፖለቲካ አድላዊ ተግባር ለመፈጸም በር ከፋች ከመሆኑም በላይ የግጭት መንስኤ ነው ። አንዱ አንዱን ተጠቀመ በሚል መንፈስ ለግጭት ይነሳሳል ፣ ለዜጐች መፈናቀል ምክንያት ይሆናል ። ህዝቡ የእኔ የሚለው መንግስት የመመስረት ግዴታ ይሆናል ። አለበለዚያ መነቋቆሩና መጠላለፉ ይቀጥላል ። ኢትዮጵያ ውስጥ ቀጣይነት ያለው መረጋጋትና የውስጥ ሰላም ካልሰፈነ ፣ የህግ በላይነት ካልነገሰ ፣ የብሔር ሰሜት በሸታ ካልታከመ፣ መከባበርና መቻቻል ካላሸነፈ ፣ የሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ መርህ ካልተከበረ ፣ ዜጎች እንደ አንድ አገር ዜጋ ካልታዩ ፣ በአገራቸው ውስጥ የሰላምና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ ሰርአት የማፍረስ ተግባር ይቀጥሉበታል ። 

           በአንድ አገር የሚኖር ህዝብ መካለል የለበትም ። ሆኖም ተገቢ የአስተዳደር መዋቅር መሰየም ይኖርበታል ። ማንኛውም ዜጋ በሚኖሩበት ቦታ በአገሩ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መሳተፍ የሚያስችል የህገ መንግስት ጥበቃና ከለላ ያስፈልጋቸዋል ። የአንድ አገር ህዝቦች ብዙ የጋራ ተግባሮች ይኖራቸዋል ። አገርን የውጭ ሆነ የአገር ውስጥ ባላንጣ መከላከል ፣ ታላላቅ አገር በቀል ህዝባዊ በአላት በጋራ ማክበር ፣ በችግርና ተድላ መገናኘትና መረዳዳት ፣ በጋብቻ መዋሀድ እና በመሳሰሉ ማህበርና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች መተሳሰር የአንድ አገር ህዝቦች የጋራ እሴቶች ናቸው ። በመሆኑም የአንድ አገር ህዝብ የውስጥ ግጭቶች እንደ ቤተሰብ ግጭት ተደርጎ ይወሰዳሉ ።ምክንያቱም ህዝቦች በደም ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በኢኮኖሚ የተሳሰሩ በመሆናቸው ነው ። በኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ችግር አልነበረም ፣ የለም ፣ በቀጣይም አይኖርም ። ችግር የሆነው የፖለቲካ ቁማርተኛች አለመግባባት ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ህርፈተ ሰልጣን ወይም ሰልጣን ይገባኛል የሚል እንደምታ ያላቸው በሽተኛ ፖለቲከኞች ቁጥር አናሳ አይደለም ። ሁሉም ፖለቲከኛ ሰልጣን አፍቃሪ የሚሆንበት ምክንያት ለህዝብ ፍትሀዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን የመንግስት ሰልጣን ብቸኛ የሀብት ማስገኛ ምንጭ በመሆኑ ብቻ ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ አብዛኛው በድህነት ሳጥን የሚኖር ህዝብ ነው ። የመንግስት ስልጣን ላይ የሚወጡ መሪዎች ከዚህ ድሃ ህዝብ የተገኙ በመሆናቸው የአገር ሀብት ለመስረቅ በፍፁም ወደኋላ አይሉም ። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የመንግስት ሰልጣን የሀብት ምንጭ ነው ። ይህን አሰራር የሚንድ ተቋም ያሰፈልጋል ። ካልሆነ አንዱ ሌባ ሰልጣን ሲለቅ ሌላ ሌባ መንግስት በቦታው ይተካል ። ልዩነቱ የሚሰረቀው የአገር ሀብት መጠን ካልሆነ ጉዳዩ አልሸሹም ነገር ነው ። 

           አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለ ለውጥ እጅግ አበረታች ነው ። ግን ደግሞ ቅልቅልና ስንክሳር የበዛበት ነው ። የፖለቲካ ገመድ ጉተታ በግልጽ ይታያል ። አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በብሔር የተዋቀሩና የተጠመቁ በመሆናቸው በቂ አገራዊ ራእይ እቅድ የላቸውም ። ሌላው ደግሞ ሰልጣን አጣን የሚሉ የብሔር ፖለቲካ ፖርቲዎች አሉ። ስጋትም አላቸው ። ሆኖም የሚሻለው በመቀራረብና በድርድር ፍላጎታቸውና ስጋታቸው መቅረፍ እንጂ በሽሽት አይሆንም ። ለማይቀረው ለውጥ የለውጡ አካል ሆኖ መዝለቁ የሚያዋጣ ይሆናል ። በኢትዮጵያ የሚደረገው የዲሞክራሲ ሽግግር የመቀልበስ አቅሙ የተመናመነ ነው ። ምክንያቱም የመከላከያ አቅም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ ቁጥጥር ሰር ነው ። ስብጥሩ ተሰተካክለዋል። በትልቁ ደግሞ ለውጡ የገነፈለው ከህዝብ ነው ። በመሆኑም የለውጡ አካል ከመሆን ውጭ ሌላ መንገድ የለውም ። ህዝባዊና ፍትሀዊ መንግስት እንዲኖር የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች መታገል ይኖርባቸዋል ። አለበለዚያ ወደ አገራዊ ራእይ በፍጥነት መሸጋገር አለባቸው ። ካልሆነ ግን የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ የሚሆኑበት ጊዜ እጅግ አጭር ነው ። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አማካይነት ኢትዮጵያ ሰበአዊ መብት የሚከበርባት ፣ ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት ፣ የዲሞክራሲ ፍላጎት የሚያንሰራራባት፣ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚታይባት ፣ ፍትህና የህግ በላይነት የሚነግሰባት አገር እንደምትሆን ግምትም ተሰፋም አለኝ ።

Back to Front Page