Back to Front Page


Share This Article!
Share
በሪፎርም ስም የመከላከያ ሃይላችንን ጀግንነት ፣ወኔና ዝነኛነት በ ኢ - ሪፎርም ቁልቁል ሊወርድ ኣይገባም

በሪፎርም ስም የመከላከያ ሃይላችንን ጀግንነት ወኔና ዝነኛነት በ ኢ - ሪፎርም ቁልቁል ሊወርድ ኣይገባም

Tignen Tidmek  1-22-19

እንደሚታወቀው ባለፈው ዓመት ወደ ስልጣን የመጡትን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዓብይ ኣሕመድ ስልጣን ከያዙ ከጥቂት ሳምንታት በሃላ የመከላከያ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ኣዛዦችን ሰብስበው በመከላከያ ሃይላችን ከፍተኛ የሆነ ሪፎርም መካሄድ እንዳለበት ፣ ኣሁን ካላበት ኣወቃቀር በተለየ መልኩ በዓለም ላይ ካለው ቴክኖሎጂ የሚራመድ ፣ በኣገራችን ላይ ለሚቃጣ የውጭ ጥቃት ገና በርቀት እያለ የሚያስቀር ፣ በፊት ለፊት ውጊያ ያልታጠረና በቴክኖሎጂ የታነጸ መከላከያ ሰራዊት እንዲኖረን ማድረግ የሚሉ ነጥቦች ያካተተ ንግግር ሲያደርጉ በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን ተመልክተናል : :

ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወደፊት ኣቅጣጫ በንጹህ ኢትዮጵያዊ ኣእምሮ ሲታይ በእውነት የሚደገፍና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው : : ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ያዳመጠ ኢትዮጵያዊ በመከላከያ ላይ የተነገረው ረዕይ በርግጥ የኢትዮጵያን የደህንነትና ጸጥታ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲገነባና ሰላምዋም በከፍተኛ ደራጃ የተጠበቀ ፣ ለጠላቶችዋ ደግሞ የማትገበር የኣፍሪካ ኩራት የሆነች ኣገር ሊያደርጋት እነደሚችል የሚያሳምን ነበር : :

Videos From Around The World

ራዕዩን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ብዙ በርካታ ስራዎች እንደሚጠብቅ የታወቀ ነው : : ለኣብነት እንኳን ለመጥቀስ ያክል ራዕዩን ዕውን ለማድረግ በ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ና በኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕውቀት ያለው የመከላከያ ሰራዊት ለማፍራት ከሚያስፈልጉ ነገሮች ኣንኳር ኣንኳር የሆኑትን ጥቂቶቹን ለመጥቀስያክል እንደሚከተለው ቀርበዋል: :

1    በቅድሚያ ጦርነትንና ውግያን በሩቁ እያለ ሊያስቀር የሚችል የመከላከያ ሰራዊት የመፍጠር ፍላጎት ለሟሟላት ይሄንን በተመለከተ የሚያስፈልግ ዕውቀትና ክህሎት የሚሰጥ የስልጠና ተቋም ፣ ኮሌጅ ወይም የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋም ያስፈልጋል : : ይህንን ለማሳካት በኣገሪቱ ያለውን የመከላከያ ኮሌጆች መጠቀም ስለሚቻል ይህንን የትኩረት ኣቅጣጫ እንደ ኣውራ ግብ ይዘው ቢንቀሳቀሱ ቢያንስ ስልጠናው ለመጀመር 6 ወራት ለዝግጅት ያስፈልጋል : :

2    ይህንን ዕውቀትና ክህሎት ያለው የመከላከያ ሰራዊት ለማብቃት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣ በኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂና ተዛማጅ የሆኑ ኮርሶች የተካተቱበት የስልጠና ካሪክለም መቅረጽ የግድ ይላል : : ይህንን ለመፈጸም ቢያንስ 6 ወራት ለዝግጅት ያስፈልጋል : :

3    የተቀረጸው ካሪክለም መሰረት ያደረገ የመማር ፣ የማስተማር ፣ የማሰልጠን ስራ ለማካሄድ በሙያው የሰለጠኑ መምህራን ወይም ኣሰልጣኞች መቅጠር ኣስፈላጊ ይሆናል : : ይህንን ለመፈጸም ቢያንስ 2 ወራት ያስፈልጋሉ : :

4    ለመማር ማስተማር ፣ ለስልጠና ኣስፈላጊ የሆኑ የህንጻ ስራዎች ፣ የመማሪያ ቁሳቁሶች ወዘተ ሟሟላት ኣንድ ራሱ የቻለ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ስራ ነው : : ይህንን ለመፈጸም የራሱ ጊዜ የሚወስድ ሲሆን በቁጥር 1 ከተመለከተው የስራ ኣይነት ኣብሮ ጎን ለጎን ሊተገበር ይችላል : :

5    ራዕዩን ለማሳካት መሰልጠን ያለባቸው ሰልጣኞች ለመመልመል ኣስፈላጊ መስፈርቶች በዝርዝር እንዲዘጋጅ ማድረግ : : ለምሳሌ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣ በኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ገብተው የፕሮግራሚንግና የኮምፒዩተር ቋንቋ ዘርፍ ለመማር ቢያንስ የዕድሜ ጣራ ፣ በመልቀቂያ ፈተና ጥሩ ነጥብ ያለው ወይም ያላት ወዘተ ተዘርዝሮ መዘጋጀት እንዳለበት የግድ ይሆናል : : ይህንን ለመፈጸም ቢያንስ 1 ወር ለዝግጅት ያስፈልጋል : :

6    ሰልጣኞችን ለመመልመል መስፈርቶች ከተዘጋጁ በኃላ በመስፈርቱ መሰረት ሰልጣኞችን የመመልመል ስራ ይሰራል : :

7    የተመለመሉ ሰልጣኞች በቲዎሪና በተግባር ሰልጥነው የበቁና የተካኑ እንዲሆኑ በየዘርፉ እየተማሩ ከቆዩ በኃላ ተመርቀው በሰራዊቱ በሚመለከታቸው ዘርፍ እንዲገቡ ማድረግ የግድ ይላል : : ይሄንን የመማር ማስተማር ወይም የማሰልጠን ስራ ለመከወን ቢያንስ 4 ዓመት ይፈጃል : :

ከላይ የተጠቀሱት የስራ ሂደቶች ለማስፈጸም ቢያንስ ከ 4 ዓመት በላይ እንደሚወስድ መገንዘብ ይቻላል : : በተለይ የሰው ልጅን በዕውቀትና ክህሎት ኣንጾ ላማውጣት በኮሌጆች ፣ በዩኒቨርሲቲዎችና ተመሳሳይ ተቋማት እንደምናየው የስልጠና ሂደቱ ጊዜ የሚወስድ ጉዳይ ነው : : እንደ የምርት ዕቃ ማምረቻ ወይም ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሳይሆን የሰው ኣእምሮ የሚገነባበት ተቋም ስለሆነ የራሱ የሆነ ተፈጥሮኣዊ ኣካሄድ ያለውና በይድረስ ይድረስ የሚፈበረክ ምርት ኣይደለምና : :

ከዓለማዊ ጉዳይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ነጂነት የምትሽከረከር ዓለማችንና ግሎባላይዜሽን የሚሄድ የሰራዊት ሃይል መገንባት ማለት እንዲሁ በቀላሉ የሚገነባ እንዳልሆነ በጥቂቱ ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ለመፈጸም እንኳን የሚወስደው ጊዜ ማየቱ ቀላል እንዳልሆነ ኣመላካች ነው : :

ታድያ የሪፎርም ጉዳይ ይህ ሆኖ ሳለ ባልተጠበቀና ባልተገመተ ጊዜ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ለ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በ 6 ወራት በተሳካ ሁኔታ የመከላከያ ሪፎርም ሰርተናል ብለው ንግግር ሲያደርጉ ነጻ ህሊና ላለው ሰው ግርምትና ጥርጣሬ በመጫር ውሃ የሚቋጥር ስራ እነዳልተሰራ ያስተዋለበት ጊዜ ይመስለኛል: : ተሰራ የተባለው ሪፎርም በተጨባጭ የጉዳዮችን ኣፈጻጸም ብንመረምረው ከእውነት የራቀና ኣሁን እየመራ ያለው ኣመራር ስለ ሪፎርም በውል ያልተገነዘበ መሆኑን የሚያሳይና በማከላከያም ሆነ በኢኮኖሚ ፣ በዴሞክራሲ ፣ በፍትህና በሌሎች ዘርፎችም ኣገሪቱን ወደ ከፍታ ሊያሸጋግራት የሚችል የዕውቀት እጥረት እንዳለው በግልጽ ያሳያል : :

እናማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፎርም ኣድርጌኣለሁ ብለው የተናገሩት በመከላከያችን እያየነው ያለው ነገር ለውጥ ከተባለ የሚከተሉትን መዘርዘር ይቻላል

         በከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና በዘመናዊ ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት የታነጸ ሰራዊት በበለጠ ሊተካ የሚችል የሰው ሃይል ሳያዘጋጁ በተለያዩ የኣመራር እርከን የነበሩትን ኣካላት ያለበቂ ምክንያት ማሰናበት

         በከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና በዘመናዊ ወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት የታነጸ ሰራዊት በበለጠ ሊተካ የሚችል የሰው ሃይል ሳያዘጋጁ በተለያዩ የኣመራር እርከን የነበሩትን ኣካላት ከብርጌድ ብርጌድ ፣ ከክፍለጦር ክፍለጦር ወዘተ ማዘዋወር

         የትግራይ ተወላጆችን እየለዩ ከሰራዊቱ በሰበብ ኣስባብ መቀነስ ከሆነ ሪፎርም ሊሆን ኣይችልም : : ምናልባት በውል ያለተገነዘቡት ጉዳይ ቢኖር በመከላከያ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ኣገርን ከማገልገል እንጂ ውትድርናን የሙጥኝ ብለው ይዘውታል ብለው ያመኑ ከሆነ በጣም በጣም ተሳስተዋል : : እንዲያውም የትግራይ ተወላጆች በእንደዚህ ኣይነት እይታ ከሚታዩ መልቀቅ የሚፈልጉ በርካታ እንደሚሆኑ እገምታለሁ : :

         ራዕይ በሌለው መንገድ መከላከያ ሰራዊቱ መበወዝ

         ትርጉም የለሽ የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ቦታ ማንገዋለል

         የኣገሪቱ ጥቅም መሰረት ያላደረገ ሹምሽርና የማዘዋወር ስራ የሰራዊቱ ወኔና እምነት እንዲሸረሸርና ለጠላት ተጋላጭ የመሆን ሁኔታ እየጨመረ መሄድ

         እስከኣሁን ድረስ ታፍራና ተከብራ የኖረች ኣገር በኣሁኑ ጊዜ ለኣሸባሪዎች ምቹ የመሆን ሁኔታን የተፈጠረባት ለመሆንዋ በሶማሊያ ኣከባቢ በመከላከያ ሰራዊታችን እየደረሰ ያለውን ጥቃት ማሳያ ነው

         ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ተጋላጭ የሆነ ሃይል እንዲሆን ማድረግ

         ወዘተ

አረ ሪፎርም ሪፎርም ስንል በርግጥ በመከላከያ ሰራዊታችን ይህ ነው የሚባል ችግር ነበርን ? በቅጡስ ተገምግመዋልን ? ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብና መላው የዓለም ህዝብ እንደሚያውቀው ከሆነ መከላከያ ሰራዊታችንተልዕኮው ጠንቅቆ የሚያቅ በኣገር ውስጥም ከኣገር ውጭም በድል ላይ ድል እየተጎናጸፈ የመጣ፣የኣገር ኣለኝታ ፣ የኣፍሪካ ብሎም የዓለም ኩራት የሆነ መከላከያ ሰራዊት እንደሆነ ነው : :

ባጠቃላይ በሪፎርም ስም በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ያገሪቱን ጥቅም መሰረት ያደረገ ነው ለማለት በጣም ያስቸግራል : : እንዶውም የሚመስለው ያገሪቱን ጥቅም ተረግጦ የግለሰብ ፍላጎት ጣራ የነካበት ሁኔታ ነው ያለው : : በተለይ በስልጣን ለመቆየት የሚደረግ እንቅስቃሴ ስለመሆኑ ሚዛኑ የደፋ ይመስላል : : በኣንድ ኣገር ደግሞ የፈለገ ቢከሰት የኣገር ጉዳይ በምንም መልኩ ሊጣስ ኣይገባም : : ሁሌም የኣገር ጉዳይ ቀዳሚውን ስፍራ መያዝ ኣለበት እንጂ የግለሰቦች ፍላጎት በኣገር ጉዳይ እየገባ መረማመድ ሊፈቀድለት ኣይገባም : :

በብዙ ጥረት ፣ ከፍተኛ ወጪና እጅግ ሰፊ ጊዜ ተወስዶ የተገነባ መከላከያ ሰራዊታችን እኔ ኣውቅልሃለሁ በሚል ግለሰብ ፣ በወታደራዊ እርከኑ ኣገሪቱን ከሚመሩ ከፍተኛ የጦር ኣዛዦች በእጅጉ የወረደ ወታደራዊ ችሎታ ባለው ግለሰብ ፣ ያለምንም በቂ ጥናት እንዲሁ በድፍረት ጠንካራውን የኣገር ኣለኝታው መከላከያ ሰራዊታችን በኣፍሪካና በዓለም የጀግንነት ክብር የተጎናጸፈው መከላከያ ሰራዊታችን በድፍረት በሪፎርም ስም ምስቅልቅሉን እነዲወጣ የማድረጉ ኣካሄድ ኣየመራሁኝ ነኝ ለሚለው የግለሰቡ ጥቅም እንጂ ለኣገር ጥቅም ሆኖ የሚታይ ኣይደለም ያለው : : ስለዚህ ማንኛውም በሪፎርም ስም በመከላከያ ሃይላችን የሚካሄድ ተግባር በፍጥነት መቆም ኣለበት : :

ሪፎርምም መደረግ ካለበት ኣሁን በተጨባጭ ለኣገራችን የሚስፈልጋት ሰላምና መረጋጋት እንጂ ሪፎርም ኣይደለም : : ይህንንም ጉዳይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋና የመከላከያ ሰራዊት ኣባል በውል የሚገነዘበው ይመስለኛል : : ስለዚህ በኣገር ስም የግለሰቦችን ጥቅም ፣ የግለሰቦች የስልጣን ጥማት ማርኪያ ሲባል መከላከያ ሰራዊቱ እንደ ኣሻንጉሊት እንደፈለጉት ሪፎርም ምንትሴ እየተባለ ባይቀለድበት : : መከላከያ የሁላችን ነው ኣገራችንም የግለሰቦች ሳትሆን የሁላችን ናትና : : በእውነት ጦርነትን ከርቀት ማስቀረት የሚችል መከላከያ ሃይል እነዲኖረን ከተፈለገ ቅድሚያ ሰላምና መረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ ማስፈን ከዛ በመቀጠል ደግሞ ጥናት መሰረት ያደረገ የሪፎርም ሂደት መጀመርና መተግበር ነው : : ከዚህ ውጪ የሚሰራ ሪፎርም ግን ላገራችን ጥቅም ሳይሆን በስልጣን ላይ ተቆናጦ የመቆየት ህልምና ፍላጎት ለማሳካት የሚደረግ ሽርጉድ እንጂ እውነተኛ ሪፎርም ከቶ ሊሆን ኣይችልም : : በስልጣን ለመቆየትም ኣርቆ የማያይና የማያስብ ኣመራር ካልሆነ በስተቀር ጤነኛ ህሊናና ኣስተሳሰብ ያለው ኣመራር ይህንን መንገድ እንደ ኣማራጭ ኣይወስድም : : ምክንያቱም ለግል ጥቅም ብሎ ለሚተጋና ለሚቋምጥ ኣመራር የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስት የለውምና : :

ቸር እንሰንብት !

tidmektignen@gmail.com

 

 

Back to Front Page