Back to Front Page


Share This Article!
Share
ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ ።

ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ ።

ከ ኣብርሃም 1-17-19

የኣማርኛ ኣስተማሪያቺን የነበሩት ነብሳቸውን ይማርና የሚወድዋት ጥቅስ ይቺ ለዚህ ኣርእስት ትሆነኛለች ብየ የመረጥኳት ጥቅስ ነበረች ። ታድያ ኣንድ ቀን ከጎኔ ይቀመጥ የነበረውን ተማሪ የዚህ ትርጉም እንዲያብራራላቸው በጠየቁት ጊዜ የኔታ ላሟ እኮ እበት እንጂ ኩበት ኣትሰጥም ኩበት የሚሆነው በሰው ተጠፍጥፎ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ከደረቀ በሁዋላ ነው ብሎ ሲመልስላቸው ተናደዱና ቁጭ በል ኣንተ እበት ሲሉት ክዚያ ቀን ብሁዋላ እበት የሚለው ቃል ተቀጥላ ስሙ ሆነ ቀረ ።

Videos From Around The World

ታዲያ የልጁን ትርጉም ሳይሆን ኣርእስቱ እንዳለ ለዚህ ፅሁፍ ይመጥናል ብየ የመረጥኩት በኣሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየታየ ላለው ሁኔታ ይህ ጥቅስ ትርጉም ኣለው ብየ ስለ እምገምት ልጠቀመው ተገድጃኣለሁ ። ኢትዮጵያ ሃገራችን ከምን ጊዜውም በላይ ሰላም የናፈቃት ሃገር እየሆነች እንደመጣች በየእለቱ የምንሰማው ዜና ሆኗል ። ታዲያ ይህ ኣባባል ኢትዮጵያ ከኣሁን ቀደምስ ቢሆን በሰላም ትኖር ነበርን የሚል ጥያቄ እንዳያነሳ ብሰጋም ኣዎ የሚለው መልስ ክብደት ይኖረዋል ብየ እገምታለሁ ። ኢትዮጵያ ትልቅ ኣገር እንደመሆንዋ መጠን በተለያዩ ዘመናትና በተለያዩ ቦታዎች የሰላም እጦት የነበረባት ኣገር ነች ቢባል ኣሌ የማይባል ሃቅ ነው ። ሆኖም እንደኣሁኑ ኣይነት እየታየ ያለው መፈናቀልና መገዳደል ግን በታሪክም ኣልተፃፈም በኣይናችንም ኣላየንም ። ሰው በገዛ ኣገሩ ሲፈናቀልና ሲገደል በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያው ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም ።በዘመኑ ኣምጣሽ የመገናኛ ኣውታሮች ጥላቻና ፕሮፖጋንዳ ሲስበክ ክሩዋንዳው እልቂት ቀጥሎ ሁለተኛው ሊሆን ይችላል ። እሳቱ እየጋየ ያለው በሁሉም ቦታ በመሆኑና እሳቱን ለማርገብ ከመጣር ይልቅ ማርገብገብ ፡ መፍትሄ ከመጣር ይልቅ ጣት መቀሰር ፍቅርንና ኣንድነትን ከመስበክ ይልቕ ሽለላና ቀረርቶ መስማት የተጠመደ ወጣት እያፈራች ያለች ኣገር ሆናለች ። የሰላም መሪ ኣልባ ኣገር ሆናለች ለማለት ያስደፍራል ። ይህ ኣባባል የጠቅላይ ሚኒስተር ኣብይ ኣህመድን ስልጣን በመዘንጋት ኣይደለም፡ በእርግጥ ዶክተር ኣብይ በኣሁኑ ዘመን ይሁን ከቀደሙት መሪዎች ሰዎስት ኣበይት የሃገር ውስጥ ቋንቋዎች ኣቀላጥፈው የሚናገሩ ካርዝማቲክ መሪ ናቸው ሊባል ይቻላል ግን እንደ ኣንድ የኢትዮጵያ መሪ ከክልል ኣስተዳዳሪዎች የተለየና የኣንበሳውን ድርሻ ሃላፍነት ያለባቸው ሰው በመሆናቸው ወቀሳው በኣብዛኛው እሳቸውን ይመለከታል ። ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ከቀያቸው ሲፈናቀሉና ሲገደሉ ኣጥፊዎችን ለፍርድ ማቅረብ ሲገባቸው ፡ ከክልል ክልል የሚያገናኙትን ኣውራ ጎዶናዎች ሲዘጉ ፈጥኖ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ የፖሎቲካ ትርፍ ያገኝልኛል ብለው ኣምነው ይሁን በሌሎች ተገፋፍተው ጣታቸውን ወደ ኣንድ ክልል በመቀሰር ያለፈ የፖሎቲካ ሂሳብ ሲያወራርዱ ስለሚታዩ ፡ የተበደለ ህብረተሰብ ፊቱን ሊያዞርባቸው ይችላል። ከኣሁን በፊት በተናገሩዋቸው ንግግሮች የተከፋ ህብረተሰብ ስለ ኣለ ይቅርታ መጠየቅ የኣንድ ብልህ መሪ ተግባር ሆኖ እያለ ረስተዉትም ይሁን ጊዜ በማጣት እስከ ኣሁን ኣልፈፀሙትም።

ሃያ ሰባት ኣመት ሙሉ ከቁሻሻ በቀር ኣንድም የተሰራ ነገር የለም ብሎ መናገር የኣፍ ወለምታ ሊሆን ስለሚችል መለስ ቢያጠኑትና ይቅርታ ቢጠይቁበት ከኣንድ ብልህ መሪ የሚጠበቅ ነው ። ኣንዳዶች ኣባባልዎን የምንቃወመው ለሃያ ሰባት ኣመታት ብስልጣን ላይ የነበረውን መንግስት በመደገፍ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ልግል ጥቅማችን ሳይሆን ለኣገር ብልፅግና በጉልበታችንና በገንዘባችን ስንታገል የነበርን በሙሉም ሳይሆን በከፊል ኣንዳንድ ኣመርቂ ለውጦችም ማየት ስለ ቻልን ደስተኞች ነበርን ። ሆኖም በእርስዎ ኣንደበት ምንም ኣልተሰራም ሲሉ ስንሰማ ልፋታችን የውሃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱ ከልብ ኣዝነን ነው ። ለኣገር ልማት ያዋጡ ፡ ለኣባይ ግድብ ቦንድ የገዙ በኣገራቸው ልማት የተሳተፉ ተረስተው ኣፍራሽ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ሲወደሱ በማያታችን እነሱ ለኣፍራሽ ኣላማቸው የሚጠቀሙት ቃላት ብእርስዎ ሲደገም በመስማታችን ከልብ ማዘናችንን ሊገነዘቡት ይገባል ። ኣሁንም ወጣት መሪ ነዎትና ብወጣትነት ብስሜት ተገፋፍቶ የማይሳሳት መሪ ስለ ማይኖር የተናገሩትን ያርሙታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በኣገራችን ሰላምና ፍቅር ነግሶ ዜጎችዋ በእኩል ሲተናገዱ ለማየት የምንጓጓ ብዙዎች ነን ። በሃይማኖት ኣባቶችና ታዋቂ ግለ ሰቦች የተጀመረው የእርቀ ሰላም ጅማሮ የሚደገፍ ነው። የሃይማኖት ኣባቶች የመጀመርያ ተግባራቸው እርቅንና ሰላምን ማውረድ ነው ቢባል ሁሉንም የሚያጠቃልል ነው ፡ ምክንያቱም ሁሉም ሃይማኖትች በኣንድ ቃል መናገር የሚችሉትና የሚሰብኩት ፍቅርንና ሰላምን ስለሆነ ። ፍቅር ካለ ሁሉም ነገር ኣለና ። ፍቅርንና ሰላምን የምንፈልጋቸው ግን ከቦታቸው ስናጣቸው ነው። ሰላም የሚፈልግ ህብረተሰብን ሰላም ተቀበል እያልክ ብትወዘውዘው ትርጉሙ ጭቅጭቅ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው ። ሰላምን ኣምኖና ተቀብሎ በተግባር እያስተናገደ ላለ ህብረተሰብ ሰላም ፍጠር ማለት እጅና እግርህን ኣጣምረህ የሚሰጥህን ትእዛዝ ከመቀበል የዘለለ ስልጣን የለህም እንደማለት ይቆጠራል። የዚህ ፅሁፍ ኣቅራቢ ግራ ያጋባው ለእርቅና ሰላም ብለው ሁለት ጊዜ የተመላለሱት የሃይማኖት ኣባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ነው ። በእርግጥ ወደ መቐለ መምጣታቸው በኣንድ በኩል ሊመሰገኑ የሚገባቸው ቢሆንም በሌላ በኩል ሊጠየቅ የሚገባው ይዘዉት የመጡት ኣጀንዳ ነው ።

በክልሉ ስለ ኣለው ሰላምና የሰው ኣያያዝ በመረዳት ሊያመሰግኑ ቢሆን ኖሮ የሚያስመሰግናቸው ነበር ። ወይስ እነሱም በኢትዮጵያ ለሚነፍሰው ንፋስ ሁሉ ተጠያቂው የትግራይ ህዝብ ወይም ህወሓት ነው ብለው ኣምነው ይሆን የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል ። ይህንን በምልበት ጊዜ ከብዙ ኣመታት በፊት ሳቅ በሳቅ የሚል መፅሃፍ እንዳነበብኩ ትዝ ይለኛል ። ከዛ መፅሃፍ ውስጥ ያሳቀኝ ኣንድ የሰከረ ሰው በጨለማ እየተወላገደ ሲሂድ ከኪሱ ዝርዝር ሳንቲሞች ወልቆው ስለ ጠፋበት መፈለግ ይጀምራል ፡ ሌላ ሰው ሲያልፍ ያየውና ኣንተ ሰውየ ምን ትፈልጋለህ ብሎ ሲጠይቀው እቃ ጠፍቶብኝ ነው ይለዋል ፡ የት ኣካባቢ ነው የጠፋብህ ብሎ ሲጠይቀው የጠፋብኝ እዛ እጨለማው ነው ብሎ ሲመልስለት ታድያ እዚያ ከጠፋብህ እዚያው ትፈልጋለህ እንጂ እዚህ ምን ታደርጋለህ ብሎ ሲጠይቀው እዚህ የተሻለ ብርሃን ስለ ኣለ ለማየት ይሻላል ብየ ነው ብሎ ሲመልስለት ሰውየው የዚህ የሰካራም ነገር ግራ ገብቶት በል እንግዲህ እግዚኣብሄር ካንተ ጋር ይሁን ብሎት ሄደ።

ከላይ ለፅሁፌ ኣርእስት የሰጠሁትም የዚህ ተመሳሳይ ይመስለኛል ። ሰላምን መፈለግ ኣስፈላጊ ቢሆንም ከትግራይ በፊት ብዙ ኣካብቢዎች በሰላም እጦት የሚታመሱ እንዳሉ በየዕለቱ የሚሰማ ዜና ከሆነ ቆይቷል ።ታዲያ ትግራይ መጥቶ ስለ ሰላም መጮህ ለምን ኣስፈለገ ሌላ ኣጀንዳ ከሌለው በስቀር ። በጣም ከሚገርመው ኣንዲት የዋህ እናት እባካችሁ ስለ እናቶች ብላችሁ ሰላም ፍጠሩ ብላ ዶክተር ደብረፅዮን እግር መውደቅዋ ሌላ ኣጠያይቂ ነገር ነው ። ሴትየዋ የትግራይ እናቶች ስለ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንደከፈሉና የሰላምን ዋጋ ምን ያህል እንደ ሆነ እንደሚያውቁ ቢረዳት ኖሮ ዶክተር ደብረፅዮን እግር ባልወደቀች ነበር ። መለመንም ሆነ ማልቀስ ኣይገባትም ነበር ። ሰላም ለትግራይ ህዝብ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ። ለዚሁ ነው ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ያልኩት።

ያም ኣለ ያም ኣለ በኢትዮጵያ ሰላም የሚወርደው ሁሉም ድርሻውን ሲያበርክት እና ግዴታውን ሲወጣ ነው ። ሰላም ተለምኖ የሚመጣ ሳይሆን ለሰላም የሚያደናቅፉትን ኣስተሳሰቦች ስናስወግድ ብቻ ነው ። ሽለላና ቀረርቶ ሰላም ከማምጣት ይልቅ ደም ያፋስሳሉ እንጂ ሰላምን ኣያወርዱም ። ኣገሪቱ ብህገ መንግስት ስትገዛና የውጭ ጣልቃ ገብነት ሲቆም በነዳጅ ቦቴዎች ከሱዳን በመተማ ደንበር በኩል የገባው ጠመንጃ ወደ ማረሻ ሲቀየር ወይም በምርኮ ተሰብስቦ ሲቃጠል ብቻ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች ። በሁሉም ኣካባቢዎች ለጊዜው የሚመጥኑ መሪዎች ሲገኙ ኣሁንም በኢትዮጵያ ሰላም ይሰፋናል. ኣመሰግናለሁ ።

 

Back to Front Page