Back to Front Page

የትግራይ ህዝብ፤ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው

የትግራይ ህዝብ፤ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 12-25-19

ከጥንት ጀምሮ እስካሁን፤ እግዚአብሄር ከፈቀደ ለወደፊትም ቢሆን የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ግን ጊዜው በከፋ ሁኔታ ተለውጧል፤ ሰይጣናዊ አየር ነፍሷል፤ የአላዋቈች አውቃለሁ ባይነት ነግሷል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እየሰፈሩ የሚያድሉና እየቋጠሩ የሚከለክሉ ጉዶች ተፈጥረዋል፡፡ ስለኢትዮጵዊነት በሩጫ ቀድመው የሚጮሁ፤ ኢትዮጵዊ ማንንትን እንደግል ገንዘባቸው ካዝና ውስጥ ያስቀመጡ የሃገር ፍቅር ነጋዴዎች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ የነሱ ጥቅም በተነካ ቁጥር ነኪውን የኢትዮጵያዊነት ክብሩን ይገፉታል፡፡ የግልና የቡድን ቂም በቀል መወጫ ሆኗል፤ ፀረ-ኢትዮጵያ የሚል ሰሌዳም ይለጥፉበታል፡፡ የትም አገር የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት መኖሩ ጤናማ ህብረተሰብ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ የአመለካከት ልዩነት ለማንም ህበረተሰብ ባህሪያዊ ነውና ልነት ካልተንፀባረቀ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ዝምታ ሰላምን አያመለክትም፤ ምናልባት አምባገነንነትን እንጂ፡፡

ምርጫ በወቅቱ ይካሄድ ሲባል ፀረ ኢትዮጵያ!፤ ህገመንግስቱ ይከበር ስርአቱን ተከትሎ እስኪቀየር ድረስ ሲባል ፀረ ኢትዮጵያ!፤ ሊቆይ ስለሚችል የፖለቲካ ውህደት ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሰፈነውና አጣዳፊ ስለሆነው አለመረጋጋት እንነገር ሲባል ፀረ ኢትዮጵያ! ይባላል፡፡የሚገርመውና የሚደንቀው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሰፈነውና አጣዳፊ ስለሆነው አለመረጋጋት እንነጋገር ብላ በግንባር ቀደምትነት የምትወተውተው ፓርቲ ህወሓት ብቻ ናት፡፡ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ሆነ ወረዳ ውስጥ ኮሽ ባለ ቁጥር በመብረቅ ፍጥነት በለኳሽነት ሰሟ የሚነሳው ደግሞ ህወሓት ናት፡፡ መንፈስ ይመስል በመላ ኢትዮጵያ በየሰፈሩ እየገባች ታተራምሳለች እየተባለች በነጋ በጠባ የምትከሰሰው ህወሓት ከማንኛውም ጉዳይ የበለጠ ቅድሚያ ተሰጥቶት ስለሃገራችን ሰላም እንነጋገር ስትል አይሆንም የሚል መልስ የሚሰጣት ህወሓትና ትግራይ በኢትዮጵያ ጉዳይ አያገባችሁም ነው? ወይስ ህወሓትን በአተራማሽነት የመክሰሱ የፖለቲካ ታክቲክ እንዳይከሽፍ ነው? መቸም ኢትዮጵያን ለማፍረስ አቅዳ አገሪቱን እርስ በርስ እያዋጋች ነው የምትባለው ህወሓት ከሆነች አለመረጋጋቱን ተነጋግረን መፍትሄ እናበጅለት አትልም፡፡ የመፍትሄ አካል መሆን የማይፈልግ የችግሩ አካል እንደሆነ እሙን ነው፡፡

Videos From Around The World

ትርምሱን ለማንኛውም የፖለቲካ ሽግግር ባህርያዊ ነው እያሉ ለስልጣን ማደላደያ ጊዜ በመግዛት ላይ ያሉት ባለስልጣኖች አለመረጋጋቱንና የህወሓት ውንጀላን እንደ የጢስ-ቦምብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ እዚህ ላይ ለህሊና ፍርድ እናቅርበው፡- እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የሆነው የትኛው ነው? አገሪቱ ውስጥ ስለሰፈነው አለመረጋጋት እንነጋገር የሚለው ነው ወይስ ሕወሓትን እየወነጀለ ህዝቡን አስተሳስሮት የኖረው ማህበራዊ ድርና ማግ ተበጣጥሶ እስኪያልቅ ድረስ ሽግግር ነው እያለ የሚጠብቀው ነው? ሁሉም የውይይትና የድርድር በሮች በፀረ ኢትዮጵያ! መዝጊዎች ተቀርቅረዋል፡፡ ቀርቃሪዎቹ አዎ እናንተ ናችሁ ልክ ብሎ የምርኮ ቃል ለሚናገር ካልሆነ በሮቹን አይከፍቱም፡፡ ሕዝብ ፊት ቀርበው እስኪለኩ ድረስ ሃሳቦች ሁሉ እኩል ናቸው፡፡ አገራችን የቤት ልጅና የእንጀራ ልጅ የሚባል አታውቅም፤ የቤት ልጅ ነኝ ባዩ መጨማለቅና የእንጀራ ልጅ ነህ ታባዩ ልመናን አታስተናግድም፡፡

የበኩር ልጅ የሆነው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ በርግጥ የትግራይ ህዝብ የገጠመው ፈተና በአይነቱ የተለየ ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ አስቦና ተጨንቆ ከችግሯ እንዳይታደጋት ኢትዮጵያን ከስልጣን ጥማቸው በታች እንጂ ከጥቅማቸው በላይ አድርገው ማየት የተሳናቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና፤ ማህበራዊ ጫና የራስዋን ህልውና በመጠበቅ ላይ ብቻ እንድትጠመድ አድርገዋታል፡፡ በረቀቀ ስልትና በተከታታይነት እየተፈፀመ ያለው ይህ ከኢትዮጵያ ጉዳዮች ህዝቡንና ህወሓትን የማግለል ድርጊት ብዙ ቅን ኢትዮጵያ ወዳድ የትግራይ ተወላጆችን እያሳዘነ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ወደ መቁረጥ እየነዳቸው ነው፡፡

ሕወሓትንና የትግራይ ህዝብን የሚመለከት ጉዳይ ሲተነትኑ የሚያሾፉና ኮሜዲ በሚመስል መልኩ የሚያቀርቡ ሰዎች እጅግ ተበራክተዋል፡፡ ለሰሚው አንጀት ያሳርራል፤ ያሸፍታል! ይህም የትም አትደርሱም ያሰብላል፡፡ የትግራይ ህዝብ ህወሓት የኔናት የሚል መብቱም ሊጠበቅለት አልቻለም፤ ኦሮሞው ኦዴፓ የኔ ናት፤አማራው አዴፓ የኔ ናት እንዲል እየተጠበቀና እየተቀሰቀሰ ባለበት ሁኔታ፡፡ የትግራይ ህዝብ የሚበጀውንና የማይበጀውን የማያውቅ የጨቅሎች ስብስብ አድርገውታል፡፡ የጨቅሎች ስብስብ ካልሆነም ህወሓትን ካቀፈ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት ካባ ያከናንቡታል፡፡ ሁሉም በጃቸው ሁሉም በደጃቸው ሆኗል፡፡ ይህ በሃገሩ ጉዳይ ገብቶ የመፍትሄው አካል እንዳይሆን፤ አገርን የሚያበጣብጥ ፖለቲካና ሃገርን ጥገኛ የሚደርጉ ዲፐሎማሲያዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ የሚያቀርበው ሃሳብ ዋጋ በማሳጣት፤ ራሱን አልምቶ እኩልነቱን እንዲያረጋግጥ የሚያደርገውን ጥረት በማሰናከል መቆሚያ መቀመጫ እንዲጠበው በማድረግ በኢትዮጵያዊነት ማንነቱ ላይ ግራ እንዲጋባ እያደረጉት ነው፡፡ ይህን ያህል ይገፉትና ውስጡ አምፆ እገነጠላለሁ የሚል የተስፋ መቁረጥ ድምፅ ሲያሰማ በድንጋጤ የትግራይ ህዝብ ፅኑ ኢትዮጵያዊነት የሚመሰክርና፤ ለትግራይ ህዝብ ለራሱ ሳይቀር የሚነግር፤ አርበኛ ይበረክታል፡- የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ምሶሶ ነው!፤ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ወርቅ ነው!፤ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ መነሻ ነው! የሚሉ በማር የተሸፈኑ ውስጠ መርዝ ቃላት በባለስለጣኑም በተራውም ሰው አፍ ይዥጎደጎዳሉ፡፡ መቐለ ውስጥ አንድ የሰፈር ተረት አለ፡- አንቲዐናኻስ ሽንጉርቲ ይብላኻ (ትርጉሙ፡- እነሱ ራሳቸው ፈንክተውህ እነሱ ራሳቸው ነጭ ሽንኩርት አምጡለት ይላሉ፤ ለማለት ነው)፡፡ ሲጀመር እኮ ሰውየውን ባይፈነክቱት ደሙን እያፈሰሰ ፖሊስ አይጠራባቸውም ነበር፤ ፖሊስ ሲመጣ ፈንካቾች ሳይሆኑ አካሚዎች መስለው መታየት ፈለጉ!

ያለ ይሉኝታ፤ ያለ ሃፍረት፡ በማናለብኝነት፤ በህገወጥነት፤ የኢትዮጵያዊነት የዜግነት ክብሩን ሲገሱ ኖረው፤ ህዝቡ ያመረረ ጊዜ ምርጥ ኢትዮጵያዊኮ ነህ ብሎ ማለት ከማላገጥ ብዙም የራቀ አይደለም፡፡ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው የሚባለው ይህ ነው፡፡ አንድ ህዝብ ሆኖ በግማሽ ጭንቅላቱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀን ተሌት የሚታክት፤ በሌላው ግማሽ ጭንቅላቱ ደግሞ ለኢትዮጵያ አንዴ ወርቅ አንዴ ምሶሶ መሆን የቻለ ህዝብ ምድር ላይ ያለ ፍጥረት ነው ወይስ ከሌላ ፕላኔት መጥቶ ትግራይ ላይ የሰፈረ? አንድ ህዝብ በአንድ ጊዜ ሁለቱም (የአገር አፍራሽና የአገር ምሶሶ) ሊሆን አይችልም፡፡ የትግራይ ህዝብ አገር አፍራሽ ሲባል በኔ እጅ አትፈርስም፤ ሲያፈርሷት ግን ተቀምጬ አላይም ብሎ መገንጠልን ሲሻ አይ አይሆንም፤ የትም አትሄድም አንተኮ የኢትዮጵያ ምሶሶ ነህ ይባላል፡፡ ምሶሶስ ይሁን እሺ፤ በገዛ እጃቸው ምሶሶውን ቅንቅን ካስበሉት ሁሉም ተያይዞ መፍረሱ መች ይቀራል፡፡

እነዚህ በትግራይ ህዝብ ላይ የተነሱና ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብን በትግራይ ህዝብ ላይ ለማነሳሳት እየታገሉ ያሉት ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች፤ ፖለቲካን በተገቢው እውቀትና ክህሎት ማራመድ ያልቻሉ የስሜት ፈረስ ጋላቢዎች፤የትግራይ ህዝብ ስሜት ሲቀየር የሚደነግጡት ቢያንስ በሁለት ምክንያት ነው፡- አንደኛው/ የሚያራምዱት ፖሊቲካ በግብታዊነትና በስሜታዊነት የሚነዳ በመሆኑ፤ የአጭር ጊዜ የጎን ጉዳቱን ሆነ የረዥም ጊዜ አደገኛ ውጤቱን የሚያሰላ አይደለም፡፡ከዚህም የተነሳ በራሳቸው ላይ ተመልሶ ችግር የሚፈጥር መሆኑን የሚረዱት ኢላማ የሆነው ህዝብ የማይመቻቸው አይነት ግብረ መልስ መስጠት ሲጀምር ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛ/ የትግራይ ህዝብ በነሱ ለከት ያጣና ዘመን የማይሽረው ንቀት፤ ዘለፋና ማግለል ተመሮ እገነጠላለሁ ሲል ጥርግ በል፤ ግልግል ነው! ብለው እጃቸውን ማወናጨፍ እንደማይሞክሩየታወቀ ነው፡፡ የስድቡ ቃላት ሁሉ ጠፍቷቸው የኢትዮጵያዊነትን የፍቅር ዜማ ለትግራይ ህዝብ የሚያዜሙት አጥንተ-ስጋችንየሆነው የትግራይህዝብ ተለይቶን እንዳይሄድ በሚል ስጋት ሳይሆን የትግራይ መገንጠል በቀሪው ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው አደገኛ ተፅእኖ ሙሉ ተስፋ በሚደረግበት በኦሮማራ ህብረት ብቻ ሊፈታ እንደማይችል ውስጣቸው ስለሚረዳ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ መገንጠል እያለቀሰ የሚወስደው የመጨረሻ እርምጃ ነው፡፡ ከዛ በፊት በብዙ ግንባሮች ከመሰል ወገኖቹ ጋር በማበር የኢትዮጵያዊነት ክብሩን ለማስጠበቅ ይታገላል፡፡ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ክብሩን መልሶ የሚጎናፀፈው አንዳንዶቹ እንደሚመቻቸው እያምታቱ እንደሚተረጉሙት ህወሓትን ወደ ፌደራል ስልጣን በመመለስ አይደለም፡፡ ይህ ችግሩን አይፈታም፡፡ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ክብሩን መገሰስ የጀመረው እኮ ህወሓት ፌደራል ስልጣን ላይ እያለች ነው፡፡ ነገሩ መሰረታዊና የተወሳሰበ ነው፤ የብዙ ዘመናት የማናለብኝነት ድምር ውጤት ነው፡፡ የህዝብ በጎ መንፈስና ከልብ የመነጨ ይቅር መባባል እንጂ በፖለቲከኞች ድርድር የሚፈታ አይደለም፡፡ ፖለቲከኞቹ በትግራይ ህዝብ ላይ ያለው የጥላቻና ማግለል ስሜት ዘላቂ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በተለያየ መንገድ እየሰሩ ነው፡፡ ካርል ማርክስ በሰፊው ህዝብ ዘንድ የሰረፀ አስተሳሰብ የማይበገር ቁስ አካላዊ ሃይል ይሆናል ብሎታል፡፡ይህ ለራሳቸውም የማይበጃቸው የጥላቻ አስተሳሰብ መልሶ ራሳቸውን እንዳይበላቸው መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በሌላ ህዝብ ላይ ጥላቻን የሚሰብኩ ለራሳቸው ህዝብ ጥሩ አስተዳዳሪዎች ይሆናሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ህዝብ ጥቃት በዝቶበት ባመረረ ቁጥር ይቅርታ የሚመስል የልእለ ኢትዮጵያዊነት ሙገሳ ማላበስ የውሸት ጊዜያዊ ማረጋጊያ እንደሆነ ማንም አይስተውም፡፡

ቂምን በሆድ ይዞ መታረቅ፤ ይቅርታ እያሉ መራቀቅ፤ አጉል ነው ከንቱ መበሻሸቅነፍስሄር ጥላሁን ገሰሰ

 

 

 

?

 

 

Back to Front Page