Back to Front Page

በተመጣጣኝ ውክልና ስም መንግስት አነስተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎችን እንዳይደፈጥጥ እንዴት እንከላከለው?

 በተመጣጣኝ ውክልና ስም መንግስት አነስተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው

ክልሎችን እንዳይደፈጥጥ እንዴት እንከላከለው?

 

ባህሩ ተገኘ

11/27/2019

 

የፌደራል ስርዓት በዓለማችን ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ በመሄድ ላይ ያለ ስርዓት ነው። ይሁን እንጂ

በማእከላይ መንግስትና በክልሎች እንዲሁም በክልሎች እርስ በራሳቸው በእኩልነት የተገነባ ስርዓት

እንዲመሰርቱ ካልተደረገ አደጋው ከባድ ነው። በተመጣጣኝ  ውክልና ስም የህዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎች

በድምጽ ብልጫ አነስተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎችን መጉዳታቸው የማይቀር ነው። እንዲህ አይነት

ችግር እንዳይከሰት ለማድረግ ከፍተኛ ትግል አድርገው አመርቂ ውጤት ካስመዘገቡ አገሮች ጎልታ

የምትጠቀሰው አሜሪካ ነች። ስለሆነም የአሜሪካን ተሞክሮ  ላካፍላችሁ። ይህን ተሞክሮ  ከአገራችን ሁኔታ

ጋር አጣጥመን መፈጸም ከቻልን ስጋቱን ሊቀርፍልን ይችላል ብየ አምናለሁ።   

አሜሪካን የመሰረቱ ቀደምቶቹ አስራ ሶስት ክልሎች [ስቴትስ] ከፍተኛ ትግል አካሂደው የእንግሊዝ ቅኝ

ግዛትን አሸንፈው ነጻ ከወጡ በኋላ ከፍተኛ ጥያቄ ሆኖ  የመጣው መንግስታችንን እንዴት እንመስርት የሚል

ጥያቄ ነበር። ከአስራ ሶስቱም ክልሎች የተውጣጡ ተወካዮች ፊላደልፍያ ከተማ ተገናኝተው ሕገ

መንግስታቸውን ሲያረቁ ከፍተኛ መወያያ ያደረጓቸው ጉዳዮች እንዴት መተዳደር አለብን ?ምን ዓይነት

ሕገ መንግስት ይኑረን? ምን ዓይነት መንግስት እንመስርት የፌደራሉ መንግስት ክልሎችን እንዳይደፈጥጥ 

ምን እናድርግ? የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ። በዚህ ከመይ 25 እስከ ሰብተምበር 17/1787 በተካሄደው የሕገ

መንግስት ጉባኤ አማራጮቹን አንድ በአንድ ፈትሸው እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ሕገ መንግስት ለማጽደቅ

ችለዋል።   

ይህን የአገሪቱ ከፍተኛ ሕግ የማጽደቁ ሂደት ቀላል ኣልነበረም። መንግስት እንዴት ይመስረት በሚል ጥያቄ

ዙርያ ሲወያዩ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት በነበራቸው ክልሎች እንዳይዋጡ ከፍተኛ  ስጋት ስለነበራቸው የተለያዩ

ፕላኖች ለውይይት እንዲቀርቡ ተደርጓል። እንደተፈራው የቨርጂንያ ተወካይ ያቀረበው የቨርጂንያ ፕላን

እየተባለ የሚጠራው በህዝብ ብዛታችን ኣንጻር ተመጣጣኝ ውክልና ይኑረን የሚል ሃሳብ ይዞ ቀረበ። ይህ

ተመጣጣኝ ውክልና በሚል ስም የቀረበው በውጭ ሲታይ ዴሞክራሲያዊ ቢመስልም ውጤቱ ሲታይ ግን

በተመጣጣኝ ውክልና ስም የህዝብ ብዛታቸው ኣነስተኛ የሆኑትን ክልሎች የሚደፈጥጥ ስለሆነ ተቀባይነት

አጣ። ተከታትሎ የመጣው ከኒውጀርሲ ተወካይ የቀረበው የኒውጀርሲ ፕላን የተባለው ነበር። ኒውጀርሲ

ትንሽ የህዝብ ብዛት ስለነበራት ሁሉም ክልሎች እኩል ውክልና ይኑራቸው የሚል ሃሳብ ይዘው ቀረቡ። ይህ

ፕላንም ክፍተኛ የህዝብ ብዛት የነበራቸው ክልሎችን የሚያስከፋ ሆነ። ተመጣጣኝ  ውክልና ደፍጣጭ

መሆኑንና እኩል ውክልና የሚል ሃሳብም ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸውን ክልሎች ጥቅም እንደማያስከብር 

አስተውሎ የመጣው ሚስተር ሮጀር ሸርማን የተባለ የከነትኬት ተወካይ ነበር። ይዞት የመጣው ሃሳብም

ኮንስቲትዩሽናል ኮምፕሮማይዝ ይባላል። ሕገ መንግስታዊ ሽምግልና እንደማለት ነው። ይህ ፕላን ሁለት

ምክር ቤቶች እንዲኖሩ ያደርጋል። አንደኛው ምክር ቤት በህዝብ ብዛት መሰረት የሚዋቀር የተወካዮች    

ምክር ቤት [ለወር ለጂስለቲቭ] ነው። በዚህ ምክር ቤት ክልሎች ያላቸውን የህዝብ ብዛት ግምት ውስጥ

ያስገባ የተወካዮች ብዛት እንዲወክሉ ያደርጋል። ሁለተኛው ምክር ቤት ደግሞ ሰኔት [አፐር ለጅስለቲቭ]

እየተባለ የሚጠራው ምክር ቤት ነው። የሰኔት ምክር ቤት የሚቋቋመው ከሁሉም ክልሎች በእኩልነት ሁለት

ሁለት ተወካዮችን በማቀፍ ነው። ህግ ሲጸድቅ ደግሞ በሁለቱ ምክር ቤቶች ተቀባይነት ያለው መሆን

ኣለበት ተባለ።

 

ይህ ፕላን ክልሎች እንደ ያዙት የህዝብ ብዛት ተወካዮቻቸውን ወደ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመርጡ

ሲያስችል አነስተኛ ብዛት ያላቸው ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ባላቸው እንዳይደፈጠጡ ዋስትና የሚሰጥ የሰኔት

ምክር ቤት ደግሞ ሁሉም ክልሎች እኩል ሁለት ሁለት ተወካዮችን እንዲወክሉ በማድረጉና ህግ ሲጸድቅም

የሁለቱ ምክር ቤቶች ይሁንታ ማግኘቱ የግድ ስለሚል የሁሉም ክልሎች ፍላጎት እንዲሳካ አደረገ። 

ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎችም ያላቸው የህዝብ ብዛትና ድምጽ እየተጠቀሙ ሌሎችን

እንዳይደፈጥጡ ከፍተኛ ተቋማዊ መከላከያም ሆነ። ይህን በምሳሌ ለመመልከት እንሞክር። አሁን እስከ  39

557 045 የህዝብ ብዛት ያላት ካሊፎርንያ፣ 28 701 845 የህዝብ ብዛት ያላት ቴክሳስና 21 299 325

የህዝብ ብዛት ያላት ፍሎሪዳ  ስቴት 557 737 የህዝብ ብዛት ካላት ዋዮሜ፣ 626 299 የህዝብ ብዛት ካላት

ቬርሞንትና 737 438 የህዝብ ብዛት ካላት አላስካ እኩል እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ተወካዮችን ወደ

ሰኔት ምክር ቤት ይወክላሉ። ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ ባላቸው የህዝብ ብዛት መጠን ስለሚወክሉ

ካሊፎርንያ 53 ፍሎሪዳ 27 እና ቴክሳስ 36 ሲወክሉ ዋየመ፣ ቬርሞንትና አላስካ አንድ አንድ ተወካዮች

ብቻ ይወክላሉ። 

 

ከውስጣቸው የተለያዩ ብሄረሰቦችን በማቀፋቸው ምክንያት በተገቢ መንገድ ብዛታቸው ተለይቶ  ባይታወቅም

እስከ አሁን ድረስ በሚነገረው ግምት ከተሄደ  በኢትዮጵያም ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎች

ኦሮምያ 35 467 001 ፣ አማራ 21 134 988 ፣ደቡብ 19 170 007 ሲኖራቸው አነስተኛ የህዝብ ብዛት

ያላቸው ደግሞ ሃራሪ 246 000፣ ጋምቤላ 435 999፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ 1 066 001 እና ዓፋር 1 812

002 የህዝብ ብዛት አላቸው። በኢትዮጵያ መንግስት ሲመሰረት ተመጣጣኝ  ውክልና የሚባለው አሰራር

ብቻ ተግባራዊ ከተደረገ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎች በርካታ ተወካዮችን አስመርጠው በድምጽ

ብልጫ እየተባለ  ዝቅተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸውን ክልሎች እንዳይደፈጥጡና አነስተኛ የህዝብ ብዛት

ያላቸው ክልሎች በአገራቸው ጉዳይ የመወሰን አቅም እንዳያጡና የክልላቸው ህዝብን ጥቅም ማስከበር

እንዳይሳናቸው ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ አብይ ጉዳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። አለማዊ ተመኩሮውን

እናጢነውና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምደን እንዴት መተግበር እንደሚችል እንነጋገርበት።

ዘመናዊ ዴሞክራሲ የብዙሃን ድምጽና የውሁዳን መብትን አጣጥሞ እንዲሄድ የግድ ይላል። 

Back to Front Page