Back to Front Page


Share This Article!
Share
ጠቃሚና ጎጂ ብሄረተኝነት

ጠቃሚና ጎጂ ብሄረተኝነት

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 1-14-19

"ብሄር" የሚሉት ፅንሰሃሳብ ልክ እንደዝሆን "በአካል" ሲያዩት እንጂ በቃላት ሲገለፅ በቀላሉ የሚገባ አይደለም። የዚህ ፅሁፍ አላማ የብሄርን ትርጉም ለመተንተን አይደለም፣ መገለጫውን እንጂ። የብሄር መገለጫው ብሄረተኝነት ነው፤ አለበለዚያ በቤተመዛግብት ያለ ስታቲስቲክስ ብቻ ነው የሚሆነው። ብሄርተኝነት ብሄሮቹ ራሳቸውን እንዴት እንደሚያዩና ከሌሎች ብሄሮች ጋር ባላቸው መስተጋብር ይገለፃል። ብሄርተኝነት ጠቃሚም ጎጂም ገፅታዎች አሉት።

የብሄረተኝነት በጎ ጎን "ከባለቤቱ ያወቀ... ነው"  ከሚለው ይጀምራል። "የት ላይ እንደሚያምህ የማውቀው እኔ ስለሆንኩኝ መፍትሄውንም የምፈልግልህ እኔ ነኝ" ከሚልህ ሰው ርቀህ የራስህን ህመም ራስህ አዳምጠህ ወደ ፀበል ይሁን ወደ ሃኪም መሄድን የመወሰን መብት ስትጎናፀፍ ነው። የዚህ በጎ ብሄርተኝነት "የራስን እድል በራስ መወሰን" በሚለው ሃይለቃልም ይገለፃል። መልካም አስተዳደርን፣ ትክክለኛ የፍትህ ስርአትን ለማስፈን፣ የትምህርትን ተገቢነት ለማረጋገጥ በራስ ቋንቋ መጠቀምና በራስ ባህላዊ ማእቀፍ ውስጥ ለማስገባት ጥረት የሚያደርግ ብሄረተኝነት ጠቃሚ ብሄረተኝነት ነው። ይህ አይነት ብሄርተኝነት ለሌሎች የነፃነት ፋና ከማብራቱ በስተቀር የሌሎችን ብሄሮች መብት የሚነካ አይደለም። ጣልቃ አትግቡብኝ እንጂ ጣልቃ ልግባባችሁ አይልም፤ እኩል ነን እንጂ እበልጣችኋለሁ አይልም፤ የኔ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋ ከሌላው የላቀ ነው አይልም፤ አገር በማስተዳደር ከሁሉም የበለጠ ጥበብና ልምድ አለኝ አይልም።

 

Videos From Around The World

ህወሓት የብሄሮች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ህገመንግስት ውስጥ እንዲገባ በማስደረጓና የብሄር የራስ አስተዳደር ክልሎች በመፈጠራቸው "የኢትዮጵያን ህዝብ ክፉ ትምህርት አስተማረችው" እየተባለች ለሦስት አስርት አመታት ተተችታለች። በተግባር ያየነው ግን ማንም ህዝብ የማይፈልገውን ነገር በግድ ተምሮ እንዳልተገበረ ነው። ለአቅመ መለየት ያልደረሰ ህፃን ላይ ብቻ ነው ክፉ ሆነ በጎ አስተሳሰብ ጭንቅላቱ ውስጥ መጎስጎስ የሚቻለው። አንድ መሆን ጥሩ ነው። ሆኖም ግን የህዝብ ራስን የማስተዳደር መብት በእኔ አውቅልሃለሁ የሚሻር ከሆነ ህዝቡ የህወሓትን አስተማሪነት የሚጠብቅ አይመስለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ብሄረተኝነት በህወሓት የተፈፀመ የግዴታ ስልጠና ውጤት ቢሆን ኖሮ እንደ ከባድ ሰቆቃ ተቆጥሮ አቃቤ ህግ ወፍራም ፋይል ይከፍትበት ነበር። የህወሓት መሪዎች ስልጣን ሲለቁ የኢትዮጵያ ህዝቦች ብሄራዊ ክልሎችን ንደው ጠቅላይ ግዛቶችን ይመልሱ ነበር። ብሄረተኝነት በኢትዮጵያ የሰፈነው በህወሓት ተፅእኖ ሳይሆን ህዝቡ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ የማወቅ አቅም ስላለው ነው። ድህረ ህወሓት ብሄራዊ ክልሎች የበለጠ ተጠናከሩ እንጂ የህወሃት ቅሪቶች እንደሆኑ አይነት ሆነው አልኮሰሱም። እንዲያውም ብሄረ ሲዳማ ከነበረው ከፍ ያለ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እየጠየቀ ነው። በመሠረቱ ብሄረተኝነትን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተማረችው ህወሓት አይደለችም። ብሄራዊ ጭቆና ያስመረራቸው የኦሮሞ ብሄርተኞች፣ ገና ህወሓት ሳትታሰብ፣ በሜጫ ቱለማ ተደራጅተው እንደታገሉ በታሪክ ተመዝግቧል። እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው አሁን በሚንቆለጳጰሰው የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት ተገድለዋል በእስር ተሰቃይተዋል። ደርግም ቢሆን ያልማረው ጄኔራል ታደሰ ብሩ የዚህ ትግል ቁንጮ ነበር። ብሄረተኝነትን ለኦሮሞ ህዝብ ማስተማር የሚችል ሊቅ የለም፤ የደረሰባቸው አስከፊ ጭቆና የወለደው ነውና። ህወሓት የሠራችው ዋናና በጎ ተግባር ከመጠን በላይ ገሮ አገሪቱን ሊጎዳ ደርሶ የነበረውን ትጥቅ ያነገተ ብሄረተኝነት ማለሳለስ ነበር።

ጎጂና ሊወገዝ ብቻ ሳይሆን አምርረው ሊታገሉት የሚገባ ብሄረተኝነት አለ። ይህ አይነት ብሄረተኝነት ቢያንስ ሁለት ገፅታዎች አሉት። አንደኛው "ሃርድ ብሄረተኝነት" ሊባል የሚችለው ሲሆን ጦረኛ የሆነ ብሄርተኝነት ነው። ሆኖም የራስን መብት ለማስከበር ብረት አንስቶ መታገልን አያካትትም፤ የሌሎችን መብት ለመጨፍለቅና የተወሰነ ብሄር ገናናነትን ለማስፈን የሚደረግ ግፍ እንጂ። በሰይጣናዊ ብሄረተኝነት አለም እስካሁን ተወዳዳሪ ያልተገኘለትን የናዚ ጀርመን ብሄረተኝነት ነው። ጀርመን ከሰው ፍጡር ሁሉ የላቁ እንደሆኑና    አይሁዶች ግን ከሰው  በታች እንደሆኑ ሰበኩ። ይህ በዚህ አላበቃም፤ እያሰሩ፣ በጋዝ እያፈኑ፣ በጥይት እየደበደቡ ከምድረገፅ ለማጥፋጥ ሞከሩ። እንግሊዞች ከሰው ፍጡር በታች ያሏቸውን የአውስትራሊያ ባላባት ህዝቦች (አቦርጂንስ) ከምድረገፅ ለማጥፋት ትንሽ ነበር የቀራቸው። ስፓኛውያን በአሜሪካ ህንዶች ላይ የፈፀሙት ደግሞ ከሁሉም የከፋ ነበር። አንድ ብሄር ከሁሉም ልቄ የሰለጠንኩ ነኝ፣ መልከኛ ነኝ ባይ ከሆነ እንደ "እንሰሳ" የሚቆጥራቸውን ሌሎችን ማጥፋት፣ ካካባቢው ማባረርና፣ በባርነት መግዛትን ይመርጣል። በበርማ በሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የተፈፀመው ግፍም በቡዲዝም ሃይማኖት የተደገፈ የማይናማር ጭፍን ብሄረተኝነት ያጋጋለው ጥላቻ ነበር። በሩዋንዳም ሁቱዎች ቱትሲዎችን ከበረሮ ጋር እያመሳሰሉና ከሌላ አገር ተሰደው የመጡ ባእዶች ናቸው እያሉ ነበር በቆንጨራ የፈጇቸው። በሃገራችን ታሪክ አልፎ አልፎ ከታዩት ወደዚህ አይነት ብሄረተኝነት ሊመነዘሩ የሚችሉ ውስን ክስተቶች በስተቀር ከላይ በምሳሌነት የጠቀስኳቸው ስፋት የነበራቸው አይነት ብሄር ተርኮ ግፎች አልተፈፀሙም። በርግጥ እስካሁን ድረስ የብሄሮችን ግንኙነት ብልሹ እንዲሆን ያደረጉ ግዛት በማስፋፋት ሂደት ላይ፣ ግዛት በመቀራመት ላይ፣ በንግስና ውድድር ላይ፣ መሬቴን አትሻሙ በሚል የኔ ነው ባይነት ላይ፣ አያቶቻችሁ ወይንም ወገኖቻችሁ ለፈፀሙት ግፍ እናንተው ክፈሉ በሚል ትውልድ ተሻጋሪ እዳ ላይ፣ እንዲሁ የበላይ ሆኖ የመገኘት ትግል ላይ የተለያዩ ብሄር አባላት በአጥቂና በተጠቂ ወገን ሆነው ኖረዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል።

ሁለተኛው የብሄረኝነት አይነት"ሶፍት ብሄረተኝነት" ብለን መጥራት የምንችለው ነው።  ይህ አይነት ብሄርተኝነት ብረት ሳያነሳ ፍላጎቱን ለመፈፀም የሚፈልግ ነው። "ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው" የሚለው ተረት ሌላው ህዝብ ጥይት ሳይመታው፣ ቦምብ ሳይፈነዳበት፣ የመሸነፍ ስሜት እንዲያድርበት የማድረግ ዘዴ የበለጠና ዘላቂ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ያመለክታል። የማያቋርጥና በስልት የተቀነባበረ የውሸት ዜና፣ የሌላውን ብሄር ስብእና የሚያኮስስና እውነታነት ያለው የሚመስል ፕሮፓጋንዳ፤ በየስራ መስኩ የሌላ ብሄር ልሂቃን ስራ እንዳያገኙ፣ ቢያገኙም በአድማና በሸር ታዋቂነትና እድገት እንዳያገኙ በማድረግ ሞራላቸውን ማላሸቅና ሊጠቃ የተፈለገው ብሄር የረባ ውክልና እንዳይኖረው አድርጎ ማዳከም፤ ሚድያውንና የባህል ተቋማትን በማራባትና በመቆጣጠር የአንድ ብሄር ቋንቋና ባህል የበላይነትን አግንኖ የሌሎችን ብሄሮች ቋንቋና ባህል እኩል አገራዊ ተወዳጅነት ወይንም የሚገባው እኩል ተሰሚነት እንዳይኖረው አድርጎ ማጣበብ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።

ሰፊና ጥልቀት ያለው ትርጉም እያለው እንደ ተራ ቀልድ ሆኖ የሚነገር አንድ አባባል አለ፦ "ኢህአዲግ በ1983 የባህል ሚኒስቴርን አልተቆጣጠረም" የሚል። ይህ ማለት መስሪያቤቱ ውስጥ የደርግ ሚኒስትር ቢሮው ውስጥ እንደተቀመጠ ቀረ ማለት አይደለም። ብዙዎች ይህን አባባል የሚጠቀሙበት ኢህአዴግ የተቃዋሚዎቹን በፓለቲካ አቅሙ ሊያዳክማቸው ቢሞክርም በስነፅሁፍ፣ በድራማ፣ በሌሎች በህዝብ ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው የባህል ዘርፎች አማካይነት እየተፈታተኑት መሆኑን ለማመልከት ነው። እኔ የምረዳውና ሌላውም ይጋራኛል ብየ የማምነው ግን ይህ አባባል ኢህአዲግ የብሄሮች እኩልነትን በዘላቂነት የሚያረጋግጥበት ዋናውን ቁልፍ አላገኘውም ለማለት ነው እላለሁ።

ኢህአዲግ በፓለቲካዊ አስተዳደር ዘርፍ የብሄሮችን እኩልነት ያረጋግጥልኛል ብሎ ያሰበውን ብዙ ተግባር አከናውኗል። ለምሳሌ ከህገመንግስቱ ቀጥሎ ፓሊሲዎች፣ አዋጆች፣ መመሪያዎች፣ የህዝብ ተወካይ ምርጫዎች፣ ተዋፅኦአዊ ሹመቶች፣ ብሄራዊ ክልሎች፣ ወዘተ። እነዚህ መንግስትን ማእከል ያደረጉ ፓለቲካዊ እርምጃዎች የብሄሮች እኩል አገራዊ ተሳትፎና ውክልና፣ እንዲሁም የውስጥ የራስ አስተዳደርን በማመቻቸት ፍትህና ትምህርት ባካባቢ ቋንቋ መሆኑ ለብሄረሰቦች እኩልነት የማይናቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ቢሆንም ዘላቂ እኩልነት ያለው ከመንግስት ቢሮዎችና ምክር ቤቶች ውስጥ ሳይሆን በህዝብ ጭንቅላት ውስጥ ነው። የቢሮ ውስጥ አሰራር የሚቀየረው በ"ቃለ አጤ" ደብዳቤ ነው። የህዝብ አስተሳሰብ/አመለካከት ግን የሚቀየረው ማህተም ባረፈበት ወረቀት አይደለም። የህዝብ አስተሳሰብ የሚቀየረው የባህል ለውጥ ሲኖር ነው። የባህል ለውጥ የሚመጣው ደግሞ በባህላዊ ተቋማት ነው።

በህንድ አገር ህግ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ህዝቦች ሁሉ እኩል ናቸው፤ የተወሰነን ህዝብ ዝቅ አድርጎ በማየት መብት መከልከል ሆነ ማዋረድ በህግ የተከለከለ ነው። ይህ ህግ ነውና ያስከስሳል ያስፈርዳል። ሆኖም ግን የሂንዱ ምርጥ ዘር ነን ባዮች "ዳሊት" የሚባሉትን ህንዳውያን እንደውሻ እያዩ ሲያራክሷቸው መመልከት ህግ ለእኩልነት ምንም ዋስትና እንደማይሆን ያረጋግጣል። የአሜሪካ ጥቁር ህዝብ መብቱ በህግ የተጠበቀ ይሁን እንጂ፣ ጥቁር ፕሬዚዳንት ይመረጥ እንጂ፣ የኮንግረስ ግማሹ ጥቁርም ቢሆን አንድ ጥቁር አሽከርካሪ ምንም ሳያጠፋ በነጭ ትራፊክ ፓሊስ ከመያዝ አያድነውም። ለነጭ ፓሊስ ጥቁርና ወንጀል አንድ ናቸው። በአሜሪካ ሰክሮ ማሽከርከርና ጥቁር ሆኖ ማሽከርከር እኩል ወንጀል ናቸው እየተባለ ይቀለዳል። ፓሊሶችን ለምንድነው ህጉን የማያከብሩትና ጥቁሮቹን እንደእኩል የማያያዋቸው? ዋናው የባህል ለውጥ ስለሆነ፣ ግን ይህን የሚያስተካክል ሳይሆን የሚያባብስ የባህል ዘመቻ በመኖሩ።

የብሄሮችን እኩልነት ዘላቂ ለማድረግ ኢህአዴግ ከተጠቀመባቸው የባህል ተቋማት አንዱ በየአመቱ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ነው። ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተውጣጡ በየአመቱ ዙር በተመረጡ ከተሞች የባህል ትርኢቶች ሲያሳዩ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ይታያሉ። ምን ያህል ህዝብ ይከታተለዋል? ምን ያህል ውጤታማ ነው? በምን ያህል በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የብሄሮች እኩልነት ስሜት አሳድሯል የሚል የተፅእኖ ጥናት ተካሂዶ የሚያውቅ አይመስለኝም፤ ከአንድ ሳምንት ደመቃ ባለፈ።

ሌላው በየክልሉ የቴሌቪዥን ጣብያዎች ማቋቋም ነው። ይህ ብዙ ጥቅም አለው፣ በተለይ ለአካባቢ ልማትና ባህል ማዳበር። ወላይታው ከአማራው ጋር እኩል ነኝ ብሎ ማሰቡ አይደለም ወሳኝ የሚሆነው። እኩልነት የሚለው ፅንሰሃሳብ ስለ አንድ ሳይሆን ከአንድ በላይ የሆኑትን የማወዳደር ጉዳይ ነው። አንዱ ራሱ ለራሱ እኩል ነኝ ብሎ ቢያምን ጥቅም የለውም፤ ሌላው እኩል መሆኑን እስካላመነለት ድረስ። ወላይታው ከአማራው ጋር እኩል ነኝ ብሎ ሲያስብ አማራውም ወላይታው ከኔ እኩል ነው ብሎ አምኖ ከተቀበለ እኩልነቱ ዘላቂነት አለው። የክልል ቴሌቪዥን ጣብያዎችን የሚከታተለው የክልሉ ህዝብና ከክልሉ ውጭ ያሉ የክልሉ ተወላጆች ናቸው። ይህ የሆነው ከደቡብ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል (?) በስተቀር ሌሎቹ በየቋንቋቸው ስለሚያስተላልፉ ነው። የክልል ተወላጆች የራሳቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ልማት፣ ተፈጥሮ ሃብት በስፋት ቀኑን ሙሉ መመልከት የእኩልነት ስሜትና እርካታ እንደሚሰጣቸው እሙን ነው።ይህ ግን በራሳቸው ተወስኖ የሚቀር ነው። ሌሎች ህዝቦች እያዩላቸውና እየሰሙላቸው የእኩልነት ስሜታቸውን የሚጋሩበት እድል ቢኖር የተሟላና ዘላቂ ይሆናል በአንድ አገር ውስጥ የምትኖር እስከሆንክ ድረስ።

የክልል ቴሌቪዥን ጣብያዎች በመላው ኢትዮጵያ ብዙም ተመልካች የማያገኙበት ሌላው ምክንያት በርካታ የተደራጁና ተመልካች የሚስቡ ፕሮግራሞች የሚያቀርቡ የአማርኛ ቴሌቪዥን ጣብያዎች ስርጭት በመጀመራቸው ነው። እነዚህ በመላ ኢትዮጵያ ብዙ ተመልካች ያላቸው ጣብያዎች በአማርኛ ቋንቋ ማቅረባቸው የክልል ቴሌቪዥኖች ያለባቸውን የቋንቋ ተደራሽነት ችግር በከፊል የሚቀርፍ ቢመስልም የብሄሮችን እኩልነትን ለማስፈን በሚረዳ መልኩ የተራጁ አይደሉም። እንዲያውም በተቃራኒው የአንድ ብሄር የባህል የበላይነት በሁሉም ብሄሮች ህዝብ ዘንድ ለማስረፅ ዘመቻውን የተያያዙት ይመስላሉ።

አማርኛ የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ አማርኛንና የአማራ ብሄር ባህልን ማለያየት አልተቻለም። ያልተቻለው መለየት ስለሚያዳግት ሳይሆን የአማራ ብሄር ተወላጆች ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ይህ እንዳይሆን በከባድ እየታገሉ በመሆናቸው ነው። የመንግስት ሆነ የግል ሚድያዎችን በመቆጣጥር፣ በማራባትና፣ በማጨናነቅ በከፍተኛ እውቀት፣ ክህሎትና፣ የፈጠራ ችሎታ ተመልካቹንና አድማጩን በማማለል የአማራን ባህል የበላይነት በህዝብ ዘንድ፣ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ዘንድ፣ በማስረፅ የብሄሮች የእኩልነት ስሜት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንደ አገር አፍራሽነትና አስፈላጊ ያልሆነ ልዩነት ፈጠራ ተደርጎ እንዲተረጎም ምክንያት እየሆነ ነው።

በርካታ ቋንቋዎች በሚነገርበት አገር የአንዱ ብሄር ቋንቋ በታሪክ አጋጣሚ የሃገር የሥራ ቋንቋ ቢሆን ቋንቋው የተገኘበት ባህልም አብሮ የሃገር ባህል ይሆናል ሌሎችን ባህሎች አክስሞ የሚል ግዴታ ሊኖር አይችልም። ኢንግሊዝኛ ብዙ የአለም አገሮች በሥራ ቋንቋነት ቢጠቀሙበትም የራሳቸውን ጠብቀው እንጂ የእንግሊዛውያን ባህል ተቀብለው አይደለም። ይህ ከቋንቋ ጋር ባህልንም አብሮ የመቀበል ግዴታ ሳይኖር ሲቀር በተለያየ የባህል ወረራ ስልቶች ለመተግበር የሚደረጉ ዘመቻዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ እንግሊዞች "ብሪቲሽ ካውንስል" የሚል ተቋም መስርተው የእንግሊዝን ባህል በኢንግሊዝኛ ቋንቋ ጠቅልለው ለማጉረስ ይሞክራሉ።

የቋንንቋና የባህል ቁርኝት ማስፈፀሚያ ዋናው ዘዴ የሆነው ሚድያውን መቆጣጠር ነው። በኢትዮጵያ በአማርኛ የሚሠራጩ ሚድያዎች ውስጥ በብዛት የሚቀጠሩት የአማራ ትውልድ ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም ጥርት ያለ አማርኛ የሚናገሩት እነሱ በመሆናቸው። አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ከሌላ ብሄር የተገኘ ሰው ለሚድያ የሚመጥን የአማርኛ ቋንቋ ችሎታ አይኖረውም። ችግሩ ለምን አገራዊ የስራ ቋንቋ የሚጠቀሙ አገራዊ ሚድያዎች ለምን አማሮችን በብዛት ቀጠሩ አይደለም። ችግሩ አገራዊ ሚድያዎችን በአማርኛ ቋንቋ እየተጠቀሙ ለአገራዊው የብሄሮች እንኩልነት ማንፀባረቂያነት ከመጠቀም ይልቅ የአንድ ብሄር ባህል የሚገንባቸው መድረኮች እየሆኑ መምጣታቸው ነው። የሌሎች ብሄሮች ባህልና አኗኗር የሚቀርበው አልፎ አልፎ በሚዘጋጁ መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ነው። በተረፈ ግን ማስታወቅያውም፣ ድራማውም፣ ዘፈኑም፣ ሌሎች መዝናኛዎችም፣ የህፃናት ፕሮግራምም፣ የሚቀርቡት በአማራ ባህላዊ እሴቶች ተቀምረው ነው። የሌሎች የሚቀርብ ሲሆንም "ሌሎችም አሉ" የሚል ስሜት ባዘለ መንፈስ የሚቀርብ ይመስላል። የአማርኛ ኢቲቪና የአማራ ክልል ቴሌቪዥን የዘፈን አመራረጥ ልዩነታቸው የት ላይ እንዳለ የሚያውቅ ሰው ካለ ቢነግረኝ። ልዩነታቸው ባህርዳርና አዲስ አበባ መሆናቸው ብቻ ነው። ለተመሳሳይ ሥራ ወጪ ከማብዛት አንዳቸውን መዝጋት አይመረጥም ትላላችሁ?

 

 

Back to Front Page