Back to Front Page

ጎንደርና ትግራይ ከግጭት ይልቅ በትብብር ይጠቀማሉ

ጎንደርና ትግራይ ከግጭት ይልቅ በትብብር ይጠቀማሉ

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 11-21-19

ጎንደርና ትግራይ እርስበርስ ያላቸው የታሪክና የባህልትስስር የሚያክል ከሌላ ህብረተሰብ ጋር የላቸውም፡፡ በጂኦግራፊም ቢሆን የጎንደር ሰሚናዊ አጋማሽና የትግራይ አብዘሃኛው ቆዳ ስፋት በተከዜ ወንዝ ተፋሰስ ውስጥ ይገኛል፡፡ የወንዜ ልጅ የመባባል ያህል የሚያቀራርብና የሚያዛምድ ነገር አለን?ባለፉት ሁለት አመታት እነዚህ ሁለት እህትማማቾች የፈጠሩት ኢትዮጵያን ያናወጠው ፀብ ለብዙዎቸ ልብ የሚሰብር ሆኑዋል፡፡ ከሁሉም የላቀ የሚያሳዝነው ደግሞ የፀባቸው መነሻ ምክንያት እንኩዋን ለፍልሚያ ለኩርፊያም የሚያበቃ አለመሆኑ ነው፡፡ወልቃይት የጎንደር ሆነ የትግራይ ለሁለቱም የጦርነት አውድማ ከመሆን ይልቅ የጋራ ልማት ውድማ ቢሆን ይመረጣል፡፡ መሬት እኮ ያለ ሰው ዋጋም ትርጉምም የለውም፡፡ ሰውም በመሬት ላይ ሲኖር ተስማምቶ ካልኖረ ኑሮው የምድር ሲኦል እንጂ የምድር ህይወት አይሆንም፡፡

Videos From Around The World

በአለም ታሪክ ውስጥ በትብብርና አብሮ በሰላም በመኖር እነጂ በመሬት ባለቤትነት ፉክክር ተጠቃሚ የሆነ የለም፤ በእልክ ተያይዞ የጠፋ እንጂ፡፡ የመስቀል ጦርነት ተብሎ በሚታወቀውና አውሮፓውያን ጦረኞች ኢየሩሳሌምን ከሙስሊሞች ለማላቀቅ ለበርካታ ምእተ አመታት የተካሄዱት ፍጅቶች እስካሁን ድረስ መቁዋጫ አላገኙም፡፡ ኢየሩሳሌም ለአንድ ሺህ አመታት ያህል በባለቤትነት ጥያቄ እንደታመሰች ትኖራለች፡፡ ለወደፊትም ግጭቱ እየተካረረ እንጂ እየረገበ እንደማይሄድ የሚያሳዩ ግልፅ ምልክቶች አሉ፡፡ የሁለቱ የኔ ናት ባዮች የፍልሚያ አቅም እየጎለበተ በሄደ መጠን አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት የጊዜ ገደቡ የማይታይ ኪሳራ ማትረፍ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ከመስቀል ጦርነቶች ሁሉ አጅግ የከፋ የነበረው በታላቁ የሙሰሊም ጀኔራል ሳላሁዲንና በአንድ የአውሮፓ ክርሰትያን መስፍን መካከል ኢየሩሳሌም ላይ የተካሄደው ጦርነት ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ቀደም ብለው በተደረጉ ጦርነቶች ክርስትያኖች ሰፍረውባት ነበርና ሳላሁዲን ክርስትያኖችን ለማስለቀቅ በመቶ ሺዎች የሚገመት ጦርና በወቅቱ እጅግ ዘመናዊ የነበሩ የጦር መሳሪያዎች ይዞ ኢየሩሳልምን በመክበቡ የደረሰው እልቂት ይህ ነው ተብሎ በቃላት ሊገለፅ የሚችል አልነበረም፡፡ በተከበቡት ክርስትያኖች ዘንድ የነበረው ከፍተኛ ወኔና አልሞት ባይ ተጋዳይነትና የሳላሁዲን ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችየተደገፈ ውጊያ ጋር ተጣምሮ የጦርነቱ ማለቂያው አልታይ አለ፡፡ ሳላሁዲን ጦረኛ ብቻ ሳይሆን ብልህም ነበረና ከክርስታየኖች በኩል የመጣለትን በሰላም ኢየሩሳሌምን የመልቀቅ ጥያቄ ተቀበለ፡፡

ይህን ረዢም ታሪክ የምተርክላችሁ ኢየሩሳሌምን ለመቆጣጠር የተካሄደው ደም መፋሰስ ምንም እርባና ለሌለው ነገር መሆኑ ሳላሁዲን የተናገረውን ለመጥቀስ ነው፡፡ ድርድሩ ከተጠናቀቀ በሁዋላ የክርስቲኖቹ የጦር መሪ ሳላሁዲንን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- ኢየሩሳሌም ምን ያህል ታወጣለች?” የሳላሁዲን መልስ ታሪካዊ ነበር፤ እንዲህም አለ፡- ምንም!ጥያቄው ይህ ሁሉ እልቂት ለምን ነበር ለሚለው አግራሞት መልስ ለማግኘት ነበር፡፡ ይቀል የነበረው ክርስትያኖቹና ሙስሊሞቹ ኢየሩሳሌምን በየራሳቸው ርስተ መዝገብ ለማስገባት፤ ያውም አንዳቸውም ላይሳካላቸው፤ ከሚፋለሙ የሁለቱም አብራሃማዊ ሃይማኖቶች ቅድስት ከተማ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን በሰላምና በጋራ ቢኖሩባት ነበር፡፡

ህንድና ፓኪስታን ሁለቱም ከድሆች ተርታ የሚሰለፉ አገሮች ናቸው፡፡ እነደሃብታሞቹ አገሮች ግን ሁለቱም ኒዩክሌር ታጥቀዋል፡፡ አንዳቸው ሳት ቢሉ ይችን አለም ፍፃሜዋን ሊያቃርቡ ይችላሉ፡፡ ይሀ ሁሉ መፋጠጥ የመጣው እንግሊዞች አወሳስበውት በሄዱት የካሽሚር ግዛት ጉዳይ ነው፡፡ ህንድና ፓኪስታን ካሽሚርን ለሁለት ተከፋፍለው የተቆጣጠሩ ቢሆንም ፓኪስታን ሁለቱም ባብዛኛው የሙስሊሞች መኖሪያ ስለሆኑ ከሂንዱዎች መላቀቅ አለባቸው ባይ ናት፡፡ህንድ ደግሞ እንግሊዞች አስረክበውኝ የሄዱትን መሬት አለቅም ባይ ናት፡፡ ይህ ችግር መፍትሄ ሳያገኝ፤ ሁለቱም አገሮች ድህነታቸውን በጋራ ለመቅረፍ እድል ሳይኖቸው፤ ከሃያላን አገሮች ዘመናዊ የጦር ማሳሪያ ሲሸምቱ ይኖራሉ፡፡ የሁለቱም አገሮች ግጭት ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረለት አለም አቀፍ ሽብርም በተለይ ለፓኪስታን ቤተኛ ነው፡፡ እኒህ በቅኝ ግዛት ማክተሚያ ሁለት የሆኑት አገሮች የጥንቱ የኢንዳስ ወንዝ ስልጣኔ ምድር ነበሩ፡፡ ጥንተ ታሪካቸው የጋራ ከመሆኑም በላይ ልሳናቸው ሆነ ሌላው ባህላቸው ብዙም የሚራራቅ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያና ኤሪትርያ መቶ ሺህ ያህል ህዝብ ያለቀበት ጦርነት ከተካሄደ በሁዋላ ለ20 አመታት ያህል በድንበር ላይ ተፋጠው ኖሩ፡፡ አሁንም ለውጥ የለውም፤ ችግሩ መቼ እንደሚፈታም አይታወቅም፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ድንበር አካባቢ ያሉት ህዝቦች የስጋት ህይወት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የባድመ ጉዳይ ለአምባገነንነት መስፈን እንደሰበብ እየተቆጠረ የኤሪትርያ ህዝብበባይተዋርነት አገር ላገር እየተንከራተt፤ ውሃ እየበላው፤ እድሜውን በካምፕ እየፈጀይገኛል፡፡ በዚህ ድህነት ላይ ሁለቱም አገሮች ዘመናዊ መሳሪያ ግዢ ላይ ተጠምደው ቆይተዋል፡፡ የኤሪትርያና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ከእልክና የመሪዎች የግል ፉክክር ነፃ ሆኖ በድርድረሊፈታ ይችል ነበር፡፡ ከድንበሩ ወዲያና ወዲህ ያለው ህዝብስ የት ላይ ነው መስመር የሚሰመርበት፤ አንድ አይነት ህዝብ አይደል? እንዲህ አይነት ማህበራዊ መሰረት የሌለው ድንበር እኮ በጦርነት አይፈታም፡፡ የበሬ ግንባር በሚያክሉ መሬቶች የሁለቱ ወንድማማች አገሮች ህዝቦች በጠላትነት አይን እየተያዩ ለጦርነት ይፈላለጋሉ፡፡ ጥያ፡-ባድመ ምን ያህል ታወጣለች?”  መልስ፡- የመቶ ሺህ ዘመዳሞች ሞት!ጎንደርና ትግራይ ሁለቱም በተፈጥሮ ሃብት የበለፀጉ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በሁለቱም ዘንድ የተንሰራፋውን ድህነትን ቀንሰው ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ግንባር ቀደም ተግባራቸው መሆን አለበት፡፡ በወልቃይት ጉዳይ በተነሳ አለመናበብ በጎንደርና በትግራይ ውስጥ ካቅም በላይ የሆነ የመሳሪያ ዝግጅትና ህዝቡን ለዘለቄታ የሚቃቅር የቃላት ጦርነት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ መካረሩ ተባብሶ ግጭት የተጀመረ እንደሆነ ደም ደምን እየወለደ ወደማያባራና ወልቃይት ይህን ያህል ታወጣ ነበር?” ወደሚያሰኝ መተላለቅ ሊከት ይችላል፡፡

ካሽሚር ውብ የሆነ ተራራማ ምድር ነው፡፡ ለቱሪዝም፤ ለፊልም ስራ፤ ከሃሩራማና ወበቃማ ከሆነው የሁለቱ አገሮች አካባቢ ቀዝቃዛ ትንፋሽና  እረፍት ለማግኘት የሚጎርፈው ህዝብ ቁጥሩ ቀላል አይባልም፡፡ ሆኖም ግን ይህ የተፈጥሮ ሃብት ከሁለቱ አገሮች ለአንዳቸውም አገልግሎት ላይ ሊውል አልቻለም፡፡ የትም ቦታ ድንገት ቦምብ የሚፈነዳበትና ሳይታሰብ የመሳሪያ ግጭት የሚቀሰቀስበት ስፍራ የኢኮኖሚ ጥቅም ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ ሲሆን የኖረው ለ70 አመታት ያህል ነው፤ በትንሹ ለሌላ 70 አመት መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ወልቃይትም ቢሆን መሬቱ ምንም ውሃማና ለም ቢሆንም እህል ሳይሆን የሰው አጥንት ከተዘራበት ለማንም ጠቃሚ አይሆንም፡፡በትግራይና በጎንደር ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ ይህ ማለት በዛ መጠን ችግርን በጦር ሳይሆን በእውቀትና በውይይት ሊፈታ የሚችል ከፍተኛ የሰላም ሃይል አለ ማለት ነው፡፡ የሚታየው አዝማሚያ ግን ወይ ዝምታ ነው ወይ ከምሁራን ጭንቅላት የማይጠበቀው ግፋ በለውነው፡፡ የምሁራን ዋና ተግባር ህዝብን እስከወዲያኛው የሚያለያይ ለፍጅትም የሚዳርግ ግዴለሽነት ሳይሆን በሰላም አብሮ ለመኖር የሚስችል መላ ማበጀት ነው፡፡

ድህነት ጦርነትን ይወልዳል፤ ጦርነትም መልሶ ድህነትን ያባብሳል፡፡ ይህ አዙሪት አገር እስኪወድም ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ ሊቆም የሚችለው ሁለቱንም በማስወገድ ነው፡፡ ድህነትን ሳይቀርፉ ጦርነትን ለማስቆም መሞከር ከባድ ነው፡፡ ጎንደርና ትግራይውስጥ የሰፈነው ድህነት እንኩዋንና ተለያይቶና በግጭት ተጠምዶ ክንድን አጣምሮም በቀላሉ የሚወጡት ፈተና አይደለም፡፡ ሰሞኑን ለማስተማር ስራ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተጉዤ በሰነበትኩበት ወቅት የተገነዘብኩት ቢኖር ጎንደር ሰላማዊ ብትሆንም እጅግ ተቀዛቅዛ ከብዙ አመታት በፊት ከማውቃት ብዙም የተለየች ሆና አላገኘሁዋትም፡፡ ሰላም በሌለበት ልማት የለማ! ሕዝብ ተረጋግቶ ስለ ነገ ሕይወት ማሰብ ከቻለ ነው ልማትና መሻሻል የሚኖረው፡፡ ለልማት መሳካት ወዳጅ እንጂ በጠላት ፍለጋ መቸገር እጅግ ይጎደል፡፡ እርግጥ ነው፤ በሁለቱም በኩል ያሉት አመራሮች ላለመግባባት የተግባቡ ይመስላሉ፡፡ ለፍቅር የምታወጣው ለፀብ ከምታወጣው ወጪ በእጅጉ ያንሳል፡፡ የጎንደርና የትግራይ አለመግባባት ህዝባቸውን ከመጉዳቱ በስተቀር የሚስገኘው አንዳች ትርፍ የለም፡፡ ስለዚህ የልዩነቱ ገደል ሰፍቶ ሞልቶ ለመደልደል የማይቻል ደረጃ እሰኪደርስ ድረስ ዝም ብሎ ማየቱ የሁለቱንም የወደፊት የሰላምና የብልፅግና እድል ማበላሸት ነው፡፡ እኔ በተለይ የሁለቱም ወጣቶች መምከር የምፈልገው ሆድ የሚሻክሩ ቃላት እርስ በርሳቸው ላይ ከመወራወር እንዲቆጠቡ ነው፡፡

እርግጥ ነው ከጎንደር ብዙ የትግራይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ ተጎድተዋል፡፡ ይህን ጥፋት የምንፈታው ግን ተጨማሪ መካረር በመፍጠር አይደለም፡፡ ዘመዶቻችንን (የኔን አያትና አጎቶቼን ጨምሮ) የፈጀችው ኢጣልያ እኮ አሁን ወዳጃችን ናት፡፡ አሜሪካ እኮ ሁለት መቶ ሺህ ጃፓናውያን በአቶሚክ ፈጀታ አሁን የጀፓን ሸሪክ ሆናለች፡፡ ለመቶ አመታት የተዋጉት እንግሊዝና ፈረንሳይስ አሁን ጥብቅ ጉዋደኞች አይደሉ፡፡ ነገርን እንደክርብናከረው ይበጠስና መስፊያ እናጣለን እንጂ የሚፈይደን ነገር የለም፡፡ ሁለት ፅኑ ክርስትያን ህዝብ ለፀብ መፈላለጉ እግዚአብሄር የሚወደው አይደለም፡፡ 

Back to Front Page