Back to Front Page


Share This Article!
Share
ግድቡን ማጠናቀቅ ብሔራዊ ኩራት፤አለማጠናቀቅ ግን ብሔራዊ ውርደት!

ግድቡን ማጠናቀቅ ብሔራዊ ኩራት፤አለማጠናቀቅ ግን ብሔራዊ ውርደት!

በሳምሶን ዮ. 2-27-19

በዓለማችን በትልቅነቱ የመጀመሪያውን ደረጃ የያዘ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡ 22 ሺ 500 ሜጋዋት ሃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር፤ በአካባቢው ስነምህዳር እና በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያመጣል ከሚለው የተቆርቋሪዎች እሮሮ እና ተቃውሞ ጀምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ያደረገ ፕሮጀክት በሚል ዓለም ያወገዘው ግድብ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

አሁን ላይ ይህ ሁኔታው ተቀይሮ በዓለማችን አሉ ከሚባሉ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል በሚሰጠው ከፍተኛ ጥቅም የሚወደስ ግድብ ለመሆን በቅቷል፡፡ይህ ግድብ ስሪ ጎርጅስ በመባል የሚታወቀውና ከ400% በላይ ተጨማሪ ወጪ ወጥቶበት የተጠናቀቀው የቻይና ሃይል ማመንጫ ግድብ ነው፡፡ በዓለም ላይ በርዝመቱ ሶስተኛ በሆነው በያንግዚ ወንዝ ላይ የተገነባው ስሪ ጎርጅ ግድብ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ በቻይና የሀይል አቅርቦት ላይ አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

Videos From Around The World

ስሪ ጎርጅ ግድብን ለማሳያነት የተጠቀምኩት የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በባህሪያቸው ከተያዘላቸው ጊዜና በጀት በላይ ፈጅተው እንደሚጠናቀቁ ለማሳየት ያህል ነው፡፡ ህንዱ ሳርዳር ሳሮቫር 513%፣የማሌዢያው ባኩን 417 %፣ የሩሲያው ሳያኖ-ሹሼንስካያ 353% ፣ የካናዳው ላግራንዴ 246% ተጨማሪ ወጪ ወጥቶባቸው ከተጠናቀቁት የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መጀመሪያ ታሳቢ ሲደረጉ እድገትን የሚያፋጥኑና ለልማት አይነተኛ መንገድ መሆናቸው ታምኖባቸው ቢሆንም በጥንቃቄ ካልተያዙና ካልተመሩ ግን የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድባችንም ያጋጠሙት እንቅፋቶች እና ፈተናዎች በተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ላይ ያጋጠሙ በሌሎች የሰለጠኑ ሀገራትም ቢሆን የታዩ ክስተቶች ናቸው፡፡ዋናው ነገር ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለውጤት እንዲበቃ መደገፍ ከሁላችንም የሚጠበቅ ሃላፊነት መሆኑን መረዳት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ያጋጠሙት ችግሮች በግልጽ የታወቁ በመሆናቸው መንግስት ላለፉት ወራት መፍትሄዎቹን ሲያመቻች ቆይቷል፡፡ችግሮቹ በዋናነት በሀይድሮ ኤሌክትሮ መካኒካል እና በሃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ስራዎች ያጋጠሙ የመዘግየት ችግሮች ናቸው፡፡

ችግሮቹ በዋናነት በሀይድሮ ኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎች የሀገራችን ባለሙያዎች የነበራቸው ልምድ አናሳ መሆን፣ የማምረት፣ የተከላ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ልምድ ውስንነት፣ የፕሮጀክቱን ጥልቀትና ውስብስብነት በትክክል በመረዳት አፋጣኝ መፍትሄ ያለመውሰድ፣ በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰሩ ስራዎች (Bottom outlet, culvert, waterway penstock, gates) ጥራትና ልኬት ፕሮጀክቱ በሚፈልገዉ ደረጃ አለመሆን በዋናነት ያጋጠሙ ችግሮች ናቸው፡፡

መንግስት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምክንያት ናቸው ያላቸውን ችግሮች ገምግሞ ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በተለይም በመስኩ አለም አቀፋዊ ዕውቅና ያላቸውና ኘሮጀክቱን የሚያውቁ የውጭ ኩባንያዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ፤ የግድቡን ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርቡ ቀጥሏል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ግድቡን ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ከፍሬው ለመቋደስ በሚደረገው ጥረት ሁለት ዋና ዋና ተግዳሮቶች የሚያጋጥሙ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ችግሮቹም ፤ በብረታ ብረት ስራዎች ላይ የታዩ እንከኖችን የማረም እና ለቀሪዎቹ ስራዎች ፋይናንስ ማፈላለግ ናቸው፡፡

በብረታ ብረት ስራዎች ላይ የታዩ እንከኖችን የማረም ሃላፊነትን በዘርፉ የተሰማሩት ኩባንያዎች ቢሆንም፤ የፋይናንስ ምንጮቹ ግን እኛው መሆናችንን መዘንጋት አይገባም፡፡ የፋይናንስ ጉዳይ፤ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ችግር አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን፤ለህዳሴ ግድብ የሚሰስቱት ነገር እንደሌለ በቢሊዮን የሚቆጠር ብሮችን በመስጠት እና በመለገስ አስመስክረዋልና፡፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጓተት ኢትዮጵያውያንን ያስከፋውን ያህል ጉዳዩ ያስደሰታቸውም አልጠፉም፡፡ጉዳዩ በተለይ አንዳንድ ግብጻውያንን ጮቤ አስረግጧል፡፡

የግድቡ ግንባታ የሚጠናቀቅበት ጊዜ በአራት ዓመት መራዘሙ ያስደሰታቸው አንዳንድ ግብጻውያን በተለይም ታዋቂ ጋዜጠኞች በተለያየ መንገድ ደስታቸውን ገልጸዋል፤ ጸሎታችን ሰመረ ያሉም አልጠፉም፡፡ታዋቂው የግብጽ ቴሌቪዥን አዘጋጅ አምር አዲብ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚጠናቀቅበት ጊዜ በአራት ዓመት መራዘሙን ሲሰማ ይህ ከአላህ የተላከ ገጸበረከት ነው፡፡ ነበር ያለው፡፡አምር በዚህ ብቻ አላበቃምኢትዮጵያውያን ወንድሞቼን ልነግራቸው እፈልጋለሁ፡፡ አትቸኩሉ ፣ታገሱ፤የገነባችሁትን በሙሉ አፍርሱና እንደ አዲስ ግንባታውን ጀምሩ ባይሆን መሀንዲሶች እንልክላችኋለንሲል ተሳልቋል፡፡

የዚህ ጋዜጠኛ ንግግር ፤እኛ እንደ ዓይናችን ብሌን በምንሳሳለት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ልማታችንን የማይፈልጉ ሀይሎች ምን ያህል እንቅልፍ አጥተው እንደሚኖሩ የሚያሳይ ነው፡፡በግድቡ ዙሪያ ለደቂቃ እንኳን መዘናጋት እንደሌለብን ይልቁንም አንድነታችንን ማጠንከር እንደሚገባ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ይዘገል መባሉን ግብፃውያን እንደ ፈጣሪ ስጦታ ቆጥረውታል፡፡እውነቱን ለመናገር ለዘመናት በአባይ ውሀ የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብታችንን ሳንጠቀምበት ቆየን እንጂ አባይስ ከማንም በላይ ስጦታነቱ ለኢትዮጵያውያን ነበር፡፡አሁንም ግን አልረፈደም፡፡እናም ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ አጠናቅቀን ጥቅም ላይ በማዋል የጠላቶቻችንን አንገት በማስደፋት ወገንን መካስ ይገባናል፡፡

 

የህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየቱ ኢትዮጵያውያንን ማስከፋቱ ተገቢ ነው፡፡ይህ መከፋት ቁጭት የወለደው ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡ ከድህነት ለመውጣት በምናደርገው ትግል ትልቅ እገዛ ያደርግልናል በሚል በተስፋ ስንጠብቀውና እንደ ዓይናችን ብሌን በስስት ስናየው የኖርን ፕሮጀክት በመሆኑ መከፋታችን ምክንያታዊ ቢሆንም እንኳ እየቆዘምን ልንኖር ግን አይገባም ፡፡ ዳግመኛ በእልህና በወኔ ተነሳስተን ግድባችንን ለማጠናቀቅ መትጋት አለብን፡፡ከፊታችን ሁለት አማራጮች አሉን ህዳሴ ግድብ ተጓተተ፣ተዘረፈ፣ቆመወዘተ እያሉ እና እየቆዘሙ መኖር አሊያም በቁጭት ተነሳስቶ ግድቡን መደገፍ ብሎም ማጠናቀቅ፡፡

ግድቡን ገንብቶ ማጠናቀቅ አማራጭ የሚቀመጥለት ጉዳይ አይደለም፡፡ ግድቡን ማቆም መሸነፍ ነው! ሽንፈትን መቀበል ደግሞ የኢትዮጵያውያን ባህል አይደለም፡፡ ግድቡን አለማጠናቀቅ በኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረውን የይቻላል መንፈስ በማኮላሸት ዳግም ወደ ነበርንበት የጭለማ ዘመን ለመመለስ መፍቀድ ማለት ነው፡፡ ይህ የማይሆን ነገር ነው፡፡ማንም ሰው ከብርሀን ጨለማን ሊመርጥ አይችልም፡፡ማንም ሰው እናቱና እህቱ በኤሌክትሪክ እጦት ምክንያት ለዘመናት በጭለማ ውስጥ እንድትዳክር ፤ በኩበት ጢስ እየተጨናበሰች እንድትኖር አይፈቅድም፡፡ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበር አለብን፡፡በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግድቡን መደገፍ አለባቸው፡፡

እርግጥ ነው በሀገር ውስጥ ካለው ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ አንጻር ሲታይ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ድጋፍ ውስን ነው ማለት ይቻላል፡፡ በዳያስፖራውና በመንግስት መካከል የነበረው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት የዳያስፖራውን ተሳትፎ እንዲያንስ አድርጎታል፡፡በሀገር ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊ ዘር ፣ቋንቋ፣ሃይማኖት ሳይለየው ድጋፉን የለገሰ ቢሆንም ቁጥሩ 3ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ በሚታሰበው ዳያስፖራ ማህበረሰብ ዘንድ የነበረው ድጋፍ ግን የሚጠበቀውን ያህል ካለመሆኑም በላይ በተቃውሞም ጭምር የታጀበ መሆኑ ሲያስተዛዝበን ቆይቷል፡፡ በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች የፖለቲካ እስረኞችን የማትፈቱ ከሆነ የህዳሴ ግድብን አንደግፍም በማለት ህዳሴ ግድብን እንደመደራደሪያ ያቀረቡበት ሁኔታ ሌላው አሳዛኙ ክስተት ነበር፡፡ ዳያስፖራው በፖለቲካ ልዩነት ብቻ ፖለቲካን ከህዳሴ ግድብ ነጣጥሎ ባለማየቱም የህዳሴ ግድብ ቦንድ ሺያጭ በአሜሪካ እንዲስተጓጎል አድርጓል፡፡ መንግስት የታላቁ ህዳሴ ግድብን የሚገነባው የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ብሎም የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ህይወት የተሻለ ለማድረግ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ከዚህ አንጻር ዳያስፖራው የቀጣዩን ትውልድ መጻኢ ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋፅኦ የማድረግ ሀገራዊ ግዴታ እንዳለበት ሊረዳ ይገባል፡፡

በአሁኑ ወቅት ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ዳያስፖራው በተለያዩ አህጉራት ጠንካራ ኮሙዩኒቲዎች ያሉት በመሆኑ መንግስት በተለይም የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት እነዚህን ኮሙዩኒቲዎች በስፋት በመጠቀም ዳያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግ መስራት አለበት፡፡

ዳያስፖራው በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በቂ መረጃ የሌለውና ከፖለቲካዊ ፋይዳው ይልቅ በቀጣይ ለሀገራችን የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያልተረዳ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በዳያስፖራው ማህበረሰብ ተደማጭ የሆኑ መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅሞ ህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ግልፅ፣ወቅታዊና እውነተኛ መረጃዎች ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚቀርብበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡

ያለብንን የሀይል ችግር በመቅረፍ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በኢኮኖሚ ለመተሳሰር ያስችለናል ብለን የጀመርነውን የህዳሴ ግድብ ብናጠናቅቀው ብሔራዊ ኩራታችን እንደሚሆን ሁሉ የሚጠበቅብንን ድጋፍ ባለማድረጋችን ምክንያት ግድቡ ሳይጠናቀቅ ቢቀር ዕድሜ ልካችንን የምንሸማቀቅበት ብሔራዊ ውርደት መሆኑን ለአፍታም እንኳን ልንዘነጋ አይገባም፡፡

 

 

Back to Front Page