Back to Front Page


Share This Article!
Share
ኢትዮጵያ ታማለች!!!

ኢትዮጵያ ታማለች!!!

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ 1-29-19

በማንኛውም ነጠላና የጋራ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጤናማ መኾንና አለመኾን የነበረ፣ ያለና የሚኖር ተርዕዪ ነው፡፡ ተርዕዮውን ትርጉም ባለው መንገድ እንድናይና እንዳናይ የሚያደርገን ኹኔታዎችን የምናይበትና ዋጋ የምንሰጥበት ልዩነት ነው፡፡ ይህም ቢኾን ዕይታን (perception) ይቀይርና ይለያይ ይኾናል እንጂ ነባራዊ ጥሬ ሃቅን አይቀይርም፡፡

አንድ ሀገር ጤናማ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታዎች ውስጥ ናት ወይስ አይደለችም? ጤናማ ያለመኾን ደረጃው ምን ደረጃ ላይ ነው? አስጊ፣ እጅግ አሳሳቢና የማያሳስብ ነው? ለዚህ ያደረሷት ዐበይት መንሥኤዎች ምን ምን ናቸው? ከምንስ ይመነጫሉ? መፍትሔው ምንድነው? ከማን ምን ይጠበቃል? የሚሉ ሰፋፊ፣ ጥልቀትና ልዩ ትኩረትን የሚሹ በኹለንተናዊ አቅጣጫ ሊታዩ የሚገባቸው ተግባራት ይኖራሉ፡፡

Videos From Around The World

ስለኾነም በዚህ አጭር ጽሑፍ የምንመለከተው የመጀመሪያውን ጥያቄ ብቻ ይኾናል፡፡ ዕውን በተጨባጭ ኢትዮጵያ ምን ላይ ናት? እነዚህ ምልክቶች የጤናማነት ናቸው ወይስ አይደሉም? ዋነኛ የዚህ ሂደት ጉዞ ወዴት ሊያመራ ይችላል? የሚለውን እንመለከታለን፡፡

1ኛ. ጥያቄ ያልኾነው የቱ ነው?

በሀገራችን ቀላል በማይባሉ አካባቢዎች የሰላም፣ የደህንነት፣ ከስጋት ነጻ የመኾን፣ የሕግ የበላይነት፣ የፍትህ፣ የተጠያቂነት፣ ተዘዋውሮ የመስራት መብት - - - አሳሳቢ ጥያቄ ኾኗል?

2ኛ. የገዥው ፓርቲ ሕልውና ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው!

በማንኛውም ሀገር ውስጥ ሥርዓትን የሚመራና የሚመሩ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በሀገራችን ቁልፍ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘ የአባላትና የአጋር ድርጅቶች ግንባር የኾነ ገዢ ፓርቲ እንዳለ ይታወቃል፡፡

የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እርስ በራሳቸው የመንፈስ አንድነት፣ የመስመር ጥራት መተባበርና ሕብረት፣ የጋራ የአካሄድ መስተጋብር መግባባት አላቸውን? እንደሌላቸው በተለያዩ መግለጫዎቻቸው ገልጸዋል፡፡

ታድያ ራሳቸውን አንድ ማድረግ ያቃታቸው አካላት እንደምን ሀገርን አንድ ሊያደርጉ ይችላሉ? በተለያየ መንገድ እየሄዱስ እንደምን ስለጋራ ሀገር ሊያነሱ ይችላሉ? የነሱ ቤታቸውን አለማጽዳት - እንደምን በጋራ በጋራ ስለጋራ ጉዳይ እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል?ሀገር እንኳንስ አንድ ሳይኾኑ አንድ ኾኖ እንኳ ከኹለንተናዊ ችግሮቻችን ለመላቀቅ እጅግ ብዙ ዓመታትን እንደሚፈጅብን ማስተዋል እንደምን አቃታቸው?

እነሱ አንድ ሳይኾኑ እንደምን የሚመሩትን ሕዝብ በጋራ እንዲሰለፍ ማድረግ ይችላሉ?የገዥው ፓርቲ ሕልውና አለ ወይስ የለም? የሚለው በትልቁ በአደባባይ በሚነሣበት ኹኔታ እንደምን ከሕልውና ባሻገር ስላለ ኹለንተናዊ ጉዳይ አጀንዳ ማድረግ ይቻላል?

3ኛ. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዘጋት፤

ሁለት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዩኒቨርስቲዎች በይፋ ተዘግተዋል፡፡ እንግዲህ በውስጣቸው የሚማሩ ብዙ ሺ ተማሪዎች ብቻ ሳይኾን በቀጣይ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ የሥነ ልቦና ጫና፣ የገጽታ ኹኔታ እንዲሁም አብሮነት ላይ የሚሳድረው አሻራ ቀላል እንደማይኾን እሙን ነው፡፡

4ኛ. ፍጹም በተቃርኖ የቆሙ ኃይሎች ሕብረት የይስሙላ ወይስ መርህን መሰረተ ያደረገ ነው?

የሀገራችንን ነባራዊ ወቅታዊ ኹኔታ መኾን ካለበትና ሊኾን ከሚገባው ይልቅ እየኾነ ካለው ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ አንጻር ስንመለከት እጅግ በጣም የተለያየ፣ ፈጽሞ ሊቀራረብ የማይችል፣ አብሮ ሊያሰራ የማይችል፣ ፍጹም ተቃራኒ ሀሳብና አቋም ያላቸው ኃይሎችና አካላቶች ሕብረት ፈጥረውና ሕብረት ፈጥረናል ብሎም ተስማምተናል ሲሉ መስማት የተለመደ ኾኗል፡፡

ሀገራችን ዛሬ ያለችው እጅግ የተለያየ ፍላጎትና አቅም ያላቸው ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በለውጥ አስፈላጊነት ላይ የተስማሙ ቢኾንም ምን አይነት? አድማሱ እስከምን የደረሰ? በማን የሚመራ? በምን ዓላማ? ለምን? የሚለው ላይ ትርጉም ባለው መንገድ የጋራ መግባባት የላቸውም፡፡

መግባባት ያለ ሚመስለው በስሜት (Emotion) እና በአስተያየት (Opinion) እንጂ ትርጉም ባለው ሀሳብ (Idea)፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) ላይ እንዳልኾነ ግልጽ ነው፡፡

ይህም ይኾን ዘንድ ያደረጉ ብዙ ውስብስብና ሰፊ ጉዳዮች መኖራቸው ጥሬ ሃቅ ቢኾንም ከማዕቀፍ አንጻር ባሕሪያዊና ጠባያዊ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ኾነው ከጊዜ ማዕቀፍ አንጻር፡-

አንደኛ፡- በኹለንተናዊ (ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ሀገራችን ትላንት ምን ላይ ነበረች? መኾኗንንስ የተለያዩ ኃይሎች እንዴት ያዩታል?

ሁለተኛ፡- በኹለንተናዊ (ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ሀገራችን ዛሬ ምን ላይ ነች? የተለያዩ ኃይሎች ይህን ነባራዊ ኹነት እንዴትያዩታል?

ሶስተኛ፡- በኹለንተናዊ (ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ጉዳዮች ሀገራችን ነገ ምን ላይ እንድትኾን እንሻለን?

ይህም የዕይታ፣ የትንታኔ፣ የትርጓሜ፣ የአቀማመጥ፣ የግንዛቤ - - - ልዩነቶች እንደተጠበቁ ኾነው ቢያንስ መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ ያደረጉት ሀሳብ ባይኖር እንኳ በጋራ ለመወያየትና ለመረዳዳት የሚያስችል ምቹ ኹኔታ ከመፍጠር፣ ከመጠቀምና ከማስተናገድ አንጻር ምን ላይ ናቸው ያልን እንደኾነ ምግባራቸው ፍጹም በተቃርኖ ውስጥ ያለ እንደኾነ ዐቢይ ምስክር ነው፡፡

5ኛ. ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና አለመግባባቶች ተበራክተዋል፤

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በሚሊዮን የሚቆጠር እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በግጭቶችና በአለመግባባቶች እየወደሙ ያሉ ንብረቶች፣ እየተጎዱ ያሉ ሰዎች፣ ሕይወታቸው እያለፉ ያሉ ዜጎች የእርስ በርስ ጦርነት ካለባቸው ሀገራት ጋር ሲነጻጸር የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡

ከኹሉ በላይ ፡-

5.1 ችግሮች ይከሰታሉ - ተጠያቂነት ግን የለም፡፡

5.2 ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶችና ከመከሰታቸው በፊት እንዳይከሰቱ የማድረግ ጥረቶች እጅግ ደካማ ናቸው፤

ለአብነት፡- በክልሎች መሐከል ለሚፈጠሩ ችግሮች የሚሰጡ ምላሾች - እስካሁን የተዘጉና መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ የማይከናወንባቸው አካባቢዎች አሉ ነገር ግን እስካሁን እሱን ወደነበረበት ነባራዊ ኹለንተናዊ ነባራዊ ኹኔታ ለመመለስ የሚደረግ ጥረት እምብዛም ነው፡፡

6ኛ. ኢኮኖሚያዊ መዋዠቆችና የመንግሥት መዋቅሮች መናበብ ምን ላይ ነው?

የሀገራችን ኢኮኖሚ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ መለኪያዎች የሚታይ ነው፡፡ የመንግሥት መዋቅሮች ከላይ እስከ ታች ተናበው፣ ጥንካሬያቸውን ጠብቀው፣ ሕዝብና የተለያዩ ኃይሎችን መምራት ብሎ አቅጣጫ መስጠት በሚችሉበት ቁመና ላይ እንዳልኾኑ ሥራቸውና እንቅስቃሴያቸው ምስክር ነው፡፡

7ኛ.ከትርጉም ያለው ነገሮች ይልቅ ጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ሠልጥነዋል፤

እንደሀገር በተራ ትርጉም አልባ ወሬዎች፣ ንግግሮች፣ ጥቅሶች፣ መወድሶችና የአደባባይ ፍሬ ከርስኪ የፎቶ ትርዒት እንጂ ትርጉም ባለውና መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ተግባራት እጅግ ዝቅተኛ ናቸው፡፡

8ኛ. አስጊ ነባራዊ ጥሬ ሃቆች፤

-   እንደሀገር ራስን ባለማረም በዘፈቀደ የሚደረጉ ንግግሮች ተበራክተዋል፤ የጦር መሳሪያ ንግድ ዕለታዊ ዜና ኾኗል፤ በአደባባይ ዝርፊያዎች ይከናወናሉ፤ ግጭት ብቻ ሳይኾን በመጠንና በይዘት ከዛ የዘለሉ ጦርነቶች እዛም እዚም ይታያሉ፤ የውጭ ጣልቃ ገብነት ተበራክቷል፤ ሀሰተኛ የፕሮፕጋንዳ ሥራዎች - የሴራ መጫወቻ የኾኑ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፡፡

-   የጦርነት ወሬዎች እዛም እዚም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመባባሳቸው ባሻገር - ዝግጅቶችም ጭምር በአደባባይ ይስተዋላሉ፤ ስለሰላም አባቶችና ሽማግሌዎች በየከተሞች ይዞራሉ ነገር ግን መኾን ያለበትን ከመደስኮር በዘለለ ማን ምን አደረገ? ለምን? የሚለውን ትርጉም ባለው መንገድ አይፈትሹም፡፡

-   ጥላቻና የጠላትነት ስሜት እጅጉን በመንሰራፋት ላይ ይገኛል፤

9ኛ. ስሜት የዋጠውና አስተያየት የበላይነት የያዘበት ጉዞ፤

ከኹሉ በላይ ስሜት (Emotion)፣ አስተያየት (Opinion)፣ ሀሳብ (Idea)፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) በአንድ ሀገር ኹለንተናዊ ያለፈ፣ ያለና የሚኖር እንቅስቃሴ ውስጥ የማይነጣጠል፣ ተያያዥና ተደጋጋፊ ሚና ያላቸው ቢኾንም በስሜት (Emotion) እና በአስተያየት (Opinion) የምትገዛ ሀገር ወደ ኃላ እንደምታመራ - አርቴፊሻልና የማስመሰል ስራዎች እንደሚበራከቱባት! ሴረኛነት እንደጥበብ ተቆጥሮ እንደሚከበርባት! ከኹሉ ጭራ እንደምትኾን! ዘወትር ለተከታይነት እንደምትሰራ! ባርነት እንደነጻነት ባደባባይ የሚሰበክባት እንደምትኾን!!!

በአንጻሩ ትርጉም ባለውና ዘመኑን በዋጀ ሀሳብ (Idea) ፣ ዕሳቤ (Thought) እና ርዕዮት /ርዕዮተ ዓለም/ (Ideology) ከርዕዮተ ሀገር ጋር የምትመራ ሀገርወደ ፊት እንደምትጓዝ! - መሠረታዊ ለውጥም እንደምታመጣ! - ተወዳዳሪ እንደምትኾን! - ለቀዳሚነትም እንደምትሰራ የታወቀ ቢኾንም በተግባር የምናየው ከሀሳብ ይልቅ ስሜት፤ ከዕሳቤ ይልቅ አስተያየት የበላይነት የያዘበትን ኹኔታ ነው፡፡

10ኛ. የኹለንተናዊ ቀውሶች ድምር ወደ የበለጠ ኹለንተናዊ ቀውስነት ይሻገራል!!!

በሀገራችን ውስጥ የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች፣ ማሕበራዊ መስተጋብር መቆራረጦችና ማሕበራዊ ዕሴቶች መደብዘዝ፣ ኢኮኖሚያዊ መዋዠቆች፣ የፖለቲካ ቀውሶች፣ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች፣ የማይግባቡና ሊግባቡ የማይችሉ የፖለቲካ ኃይሎች ያለ ሀገራዊ ማዕቀፍ በሥልጣን ፖለቲካ ፍትጊያ ውስጥ መግባታቸው፣ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ የውስጥ የዜጎች መፈናቀል፣ ግጨቶችና ከዕርስ በርስ ጦርነት ያልተናነሱ ውጊያዎች በተለያዩ ኃይሎች በሚደረግበት፣ በክልሎች መሐከል ያሉ ግንኙነቶች በተቋረጡበት፣ የፀጥታ ስጋት እጅጉን እንደሀገር አሳሳቢ በኾነበት - ለዚህም ሲባል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀባቸውና ኮማንድ ፖስት የተቋቋመባቸው ቦታዎች እያሉ፣ ኢኮኖሚያዊ ኹኔታዎች እንደሀገር እጅግ በሚያሳስብ ደረጃ ላይ ባለበት፣ ሥራ አጥነት አፍ አውጥቶ በአደባባይ በሚናገርበት ሀገር ላይ ተኩኖ ብድሮች ማብዛትና የልማት ድርጅቶችን ስለመሸጥ ማሰብ እንደምን ይቻላል? ጤናማነትስ ነው?

"No nation ought to be without a debt" (PP. 24: THOMAS PAINE: COMMON SENSE) ነገር ግን ብድር ለምን? እንዴት? በማን? መቼ? - - - ወዘተ የሚሉ ትርጉም ያላቸው ጥያቄዎችን ትርጉም ባለው መንገድ በኹለንተናዊ አቅጣጫ ትርጉም ባለው መልኩ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

በተለይም ሀገራችን መድረስ ከምትፈልግበት ግብ (የአጭር የመካከለኛና የረዥም ጊዜ) ብሎም ከራዕያችን አንጻር ማስተሳሰርን የግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ብድር በቀጣይ ትውልድ ላይ ውሳኔ ማሳለፍ በመኾኑ ትልቅ ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡ በዚህም ዛሬ ብድር በገፍ ስንወስድ ዝም ብለው የሚመለከቱትና ደጋፊ የሚመስሉት የተለያዩ አካላቶች ወሳኝ ሰዓት እየጠበቁ መኾኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

እንደቬንዙዌላ (2000 2002) አርጀንቲና (2001 - 2002) ግሪክ (2014/2015) ዛምቢያ (1998 - 1999) ደቡብ ኮርያ (1997) ሲንጋፖር - - - ወዘተ ቀውስ (Crisis) እና "በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ - ብራዚል አርጀንቲና ሜክሲኮ እና ሌሎች የላቲን አሜሪካ ሀገሮች መክፈል ከሚችሉት በላይ መበደራቸው በዚህም ውጤት በ1980ዎቹ ከባቢው በብድር ቀውስ (Debt Crisis) መሰቃየታቸው፤ በህዳር 1994 በደቡብ ሜክሲኮ ቺያፓስ (Southern Mexican State of Chiapas) የጦር እንቅስቃሴ መነሣት፤ የዓለም ነዳጅ ዋጋ መውረድ፤ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና ሜክሲውያንን ወደ ተሳሳተ ፖሊሲ አዘቅጥ እንደከተታቸው፡፡"(Pp 26፡ IAN BREMMER: EVERY NATION FOR ITSELF)ይታወቃል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሱት ሀገራት በታሪካቸው እንዳጋጠማቸው ወሳኝ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያጋጥመን (እንዲያጋጥመን ኹለንተናዊ ሴራ ሲሰራብን) ዛሬ የመደራደር አቅም ያለን የመሰለን ነገር ያን ጊዜ ባዶ መኾኑ ይገባናል፡፡ አይቀሬነቱ የጊዜ ጉዳይ ካልኾነ በቀር መኾኑ መሠረታዊ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ዕውቀት ላለው ሰው ግልጽ ከመኾኑም ባሻገር በሀገራችን በአደባባይ እያየን ያለናቸው የአሽከርነት፣ የገረድነትና የሩጫ የሥልጣን ፖለቲካ ጠባያት ትልቅ ማሳያ ናቸው፡፡

11ኛ. ካለፈውና ካለው ትውልድ የሚቀጥለው ትውልድ መራራቅ እጅጉን ያሰጋል፤

አሁን በተጨባጭ ከላይ በተጠቀሱ 10 ዋነኛ ነጥቦችና በሌሎችም በርካታ ማሳያዎች ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው ራሱን ካልካደ - ለራሱ ፍላጎት ባሪያ በመኾን የሚፈልገውን ብቻ በማየትና በመስማት ዐይነ ልቦናውን ካልታወረና የሌሎች ፍላጎት አሽከርና ገረድ በመኾን የራሱ ህልውና የሌለው በቁሙ የሞተ ካልኾነ በቀር ኢትዮጵያ መታመሟ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

ከኹሉ በላይ እጅግ አሳሳቢው ከመቼውም ጊዜ በላይ አለመተማመንና መጠራጠሮች ከመበራከቱ፣ ጥላቻዎችና ሽኩቻዎች በአደባባይ ከመስተዋሉ፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ - ከአብሮነት ይልቅ መለያየት - ከግልጽነት ይልቅ አስመሳይነት - ከዐብይ ነገሮች ይልቅ በጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች መጠመድ - ከዘላቂ ይልቅ በጊዜያዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር - ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅ - ከወደፊት ይልቅ ወደኃላ መመልከት - ከመሠልጠን ይልቅ ሴረኛነት - ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነት - ከመሪነት ይልቅ ገዢነት - ከዕድገት ይልቅ ዝቅጠት - ከክብረት ይልቅ ውርደት ከማየሉ በላይ የትውልዶች እጅጉን በዕምነት (አስተሳሰብና አመለካከት)፣ በእውቀት (ስልት፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም) እና በተግባር (በድርጊት) መለያት እጅጉን አስፈሪና ከምንም በላይ አሳሳቢ ነው፡፡

በየአካባቢው የምናየው አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚሸፍነው - ቀጣይ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እያሳየ ያለው ጫፍ የወጣ ራስን ብቻ የማድመጥ፣ ራስን ብቻ የመመልከት፣ ከጋራ ይልቅ የተናጠል ጉዳይ ላይ ማተኮሩ፣ ከአብሮነት ይልቅ መለያየትን ማጉላቱ - ዕውን የአንዱ ክልል ከሌላው ክልል ወጣቶች ጋር እንደትውልድ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ቁመና አለው ቢያንስ ሀገርን ሕልውና ውስጥ የማይከት አካሄድ አለውን?

ካለፈውና ካለው ትውልድ ኹለንተናዊ የዕምነት (አስተሳሰብና አመለካከት)፣ የእውቀት (ስልት፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም) እና የተግባር (የድርጊት) ልዩነት፣ መስተጋብር፣ ስምነቶችና ግጭቶች በላይ የቀጣዩ ትውልድ በየአካባቢው የሚስተዋለው የዕምነት (አስተሳሰብና አመለካከት)፣ የእውቀት (ስልት፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም) እና የተግባር (የድርጊት) ልዩነቶች ብሎም ሊታረቁ የማይችሉ ሕልውናን የሚፈታተኑ ተቃርኖዎች እጅግ አሳሳቢና አስፈሪም ጭምር ናቸው፡፡

በዕውነት ስለዕውነት ለዕውነት በማስተዋል ከተመለከትነው ኢትዮጵያ ታማለች፡፡ መታመሟም ከላይ ባሉ ምልክቶች የሚገለጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ምልክቶች የራሳቸው ኹለንተናዊ መንሥኤ እንዳላቸው አያጠራጥርም፡፡ ወደ መፍትሔ የሚወስደው አንደኛውና ዋነኛው መንገድ መታመሟ ላይ መግባባት ላይ መድረስ - በዚህም ቁጭት መፍጠር ሲቻል ብሎም የባለቤትነት ስሜትን ከትጋት ጋር ማስተሳሰር ሲቻል ብቻ ይኾናል፡፡ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Back to Front Page