Back to Front Page


Share This Article!
Share
ኢህአዴግ የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነት ሰበቡን ያቁምና መደበኛ ሃላፊነቶቹን በሚገባ ይወጣ

ኢህአዴግ የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነት ሰበቡን ያቁምና መደበኛ ሃላፊነቶቹን በሚገባ ይወጣ

ከእውነቱ ይታያል 1-24-19

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 27 አመታት ብዙ የልማት ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ተጥሰዋል። እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀሙ የነበረው በተለመደው መንገድ ብቻ ሳይሆን አውሬ ካልሆነ በስተቀር የሰው ልጅ ያደርገዋል በማይባል አግባብ ጭምር እንደሆነም ታዝበናል። በሙስና ረገድም ኢትዮጵጵያን አጥንቷ እስኪቀር ድረስ የጋጡ ከሃዲ ልጆቿ እንደነበሩ እያየን መጥተናል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችም መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያስብል ሁኔታ እግር ከወርች አስረው አላንቀሳቅስ ያሉበት ደረጃ ደርሰው እንደነበር ለማንኛውም ሰው ግልፅ ነው። ለነዚህ ሁሉ ችግሮች መፈጠርና እየተባባሱ መምጣት የህወሓት ሰዎች ጉልህ ድርሻ የነበራቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ማለት ግን የብአዴን፣ የኦህዴድና የደኢህዴን አባላትና አመራሮች ከደሙ ንፁሃን ነበሩ ማለት ሊሆን አይችልም። ከነዚህ ድርጅቶች አባላትና አመራር ውስጥ ከፊሎቹ አሁን የለውጥ ሃይል ነን የሚሉትን ጨምሮ ልክ ህወሓት ውስጥ እንዳሉ ሰዎች የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ፣ በሙስና የተጨማለቁና አስተዳደራቸውም ፍትሃዊነት የጎደለው የነበሩ ናቸው። በዚህ የማይካተቱት ደግሞ ሆዳችውን በመምረጥ በአድርባይነት አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ የነበሩ ስብስቦች ናቸው። ይህ ሲባል ግን ከህወሓትም ይሁን ከሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል በንፅህናና በቅንነት ሲንቀሳቀሱና ጥፋቶችንም ለህዝብ ካላቸው ተቆርቋሪነት የተነሳ በፅናት የታገሉ አባላት አልነበሩም ማለት አይደለም።

Videos From Around The World

ከዚህ በላይ የተገለፁ መረን የለቀቁ ችግሮችን በመረዳትም ይመስላል ኢህአዴግ ለ17 ቀናት ካደረገው የተሃድሶ ግምገማ በኋላ በሊቀመንበሩ ዶ/ር አብይ አህመድ አማካኝነት ከላይ እስከታች በችግር ተዘፍቂያለሁና የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ያድርግልኝ ብሎ የጠየቀው። ይህን ተከትሎም ዶ/ር አብይ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ባለፉት 27 አመታት የጠፉ ጥፋቶች በይቅርታ እንደሚታለፉና አገሪቱና ህዝቦቿ በአዲስ መንፈስ መቀጠል እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ መሆኑ ይታወሳል። በወቅቱ ለኔ የተረዳኝ ይህ የዶ/ር አብይ ገለፃ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ የፖለቲካ አቋም፣ ሃይማኖትና የመሳሰሉ ባህሪያትን ግምት ውስጥ ሳያስገባ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል በሆነ መንገድ ይቅርታ የሚደረግ እንደሆነ ነበር። መሆን የለበት ከዚህ ውጭ አልነበረምና። በመግለጫና በንግግር የተሰማው ከላይ በተቀመጠው መንገድ ይሁን እንጅ በተግባር እየታየ ያለው ግን አሻንፌ ወጥቻለሁ ያለው አካል አሳዳጅ ተሸንፏል የተባለው አካል ደግሞ ተሳዳጅ ሆኖ ነው። እየሆነ ያለውን በሌላ አነጋገር ለመግለፅ አሸንፌያለሁ ያለው አካል የትኛውንም አይነት ጥፋት ያጠፋ ቢሆንም የማይነካ ተሸንፏል የተባለው አካል ደግሞ ለተጠያቂነት የሚያደርስ ጥፋት ባይፈፅምም ምክንያት እየተፈለገ ተጠያቂ እንዲሆን ማድረግ ጎልቶ እየታየ ነው።

በተለይ ለነበሩት ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂዎቹ ህወሃትና የብአዴን የተወሰኑ ነባር አመራር አባላት ናቸው የሚል ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲደረግና በነሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ላይም ርምጃ ሲወሰድ ይታያል። ባለፉት 27 አመታት ለጠፉት ጥፋቶች ይቅርና አሁን ለምናያቸው ብጥብጦችና ትርምሶችም ጭምር ህወሃት ላይ ጣት መቀሰር የተለመደ ተግባር ሆኗል። አሁን ባለው የዶ/ር አብይ አስተዳደር ግልፀኝነት መጓደል ከኦነግ ጋ ባለ አተካሮ ምክንያት እየደረሰ ላለው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ተጠያቂው ህወሃት፤ በቅማንትና በአማራ አካባቢዎች እየተከሰቱ ላሉ ትርምሶች ተጠያቂው ህወሃት፤ ፀጉረ ልውጥ ብለው ዶ/ር አብይ በመናገራቸው አሶሳ ውስጥ ተፈጥሮ ለነበረ ምስቅልቅል ተጠያቂው ህወሃት፣ አፋር ላይ ላሉ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂው ህወሃት፣ አዲስ አበባ ላይ ለነበረው የቦምብ ፍንዳታም የግድ ተለጥጦም ቢሆን ተጠያቂው ህወሃት፤ ሃዋሳ ላይ ለሚታየው ስርዓት አልበኝነት ተጠያቂ ህወሃት፤ ድሬዳዋ ላይ ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂው ህወሃት፣ አንድ ቦታ ኮሽ ባለ ቁጥር ተጠያቂው ህወሓት፤ በአጠቃላይ በሁሉም ክልሎች እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች ተጠያቂው ህወሃት ነው የሚል አሰልችና የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ አይነት ሰበብ በዝቷል። የሚገርመው ይህ ሰበብ የሚቀነቀነው በመንጋ አስተሳሰብ በሚነዳው ሃይል ብቻ ሳይሆን በመንግስት አካላትም ጭምር መሆኑ ነው።

በዚህ ረገድ በአንክሮ ሊጤን የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ተጨባጭ ርምጃ እየተወሰደባቸው ያሉ ሰዎች በብዛት ያንድ አከባቢ ሰዎች መሆናቸው ነው። በርግጥ ረዘም ላሉ ጊዚያት የህወሃት ሰዎች የፌዴራል መንግስት ተቋማትን በመምራት ሰፋ ያለ ሚና የነበራቸው በመሆኑ ከተጠያቂነት አንፃርም ቁጥራቸው መብዛቱ ተፈጥሯዊ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጅ እየተወሰደ ያለው ርምጃ አጠቃላይ ትኩረት በህወሓት ሃይሎችና ከነሱ ጋ ቀረቤታ ነበራቸው ተብለው በሚታሰቡ ሰዎች ላይ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም። እንዲያውም ሰሞኑን እያየን እንዳለነው አንዳንድ የፈጠራ ክሶች እየተዘጋጁ የቀድሞ ኢህአዴግ አመራሮች ለእስር ሲዳረጉ ኢህአዴግና ህዝቡ በትግላቸው ገርስስው የጣሉት ደርግ ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ አገር እየመራ የበቀል እርምጃ መውሰድ ጀመረ እንዴ የሚል ጥያቄ ማስነሳት ጀምሯል።

ከዚህ ሁሉ ይልቅ የህወሓትን ሰዎች እጀ ረጅምነትና የበላይነት ዝንባሌ በተመለከተ ምሁራን አጥንተው ለታሪክ እንዲያስቀምጡት እንተወውና ኢህአዴግ በሚከተሉት ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሃላፊነቶቹን በሚገባ እንዲወጣ ሁላችንም የበኩላችን ጥረት ብናደርግ ተመራጭ ይሆናል ብየ አስባለሁ።

1.      ከሁሉም ጉዳዮች በላይ ኢህአዴግ በሚከተለው ርዕዮተ-አለም ላይ የጠራ አቋም ሊወስድ ይገባል። የእኔ አሳቤ የነበረው ሰሞኑን አድርጎት በነበረው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ወቅት በርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ ያለውን ውዥንብር አጥርቶ ይወጣል የሚል ነበር። ይህ ግን አልሆነም። እንዲያውም ከሪፖርቱ የተረዳሁት ፍሬ ነገር ቢኖር ችግሮችን አለባብሶ የማለፍ ሙከራ ነው። ሁላችንም እንደሰማነው ርዕዮተ-ዓለምን በተመለከተ በአባል ድርጅቶች ውስጥ ወጥ የሆነ የአመለካከትም ሆነ የአቋም አንድነት የለም። አንዳንዶቹ በተለይም ህወሓት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ፈቀቅ የሚያደርገኝ የለም የሚል አቋም ሲያንፀባርቅ ሌሎች በተለይም ደግሞ አዴፓ (የቀድሞው ልበለውና-ብአዴን) ደግሞ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያለንበትን ዘመን የዋጀ ስላልሆነ ከሱ ውጭ ያሉ እንደነ ለዘብተኛና ማህበራዊ ዴሞክራሲ የመሳሰሉትን እናማትር የሚል ሃሳብ እያራመደ ይገኛል። የዚህ አይነት የርዕዮተ-ዓለም አንድነት በጠፋበት ሁናቴ የተግባር አንድነት ይኖራ ማለት ዘበት ነው። የአመለካከትና የተግባር አንድነት ከሌለ ድግሞ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ድርጅቶቹ መበተናቸው አይቀርም። ይህ እንዳይሆን ኢህአዴግ እከተለዋለሁ በሚለው መርሃግብርና ርዕዮተ አለም ላይ ሁሉም አባል ድርጅቶች እንዲያምኑበትና እንዲቀበሉት ማድረግ ይጠይቀዋል።

 

2.      ኢህአዴግ የነጠረ አቁም ይዞ መውጣት ያለበት በመርሃግብሩና በሚከተለው ርእዮተ-ዓለም ላይ ብቻ አይደለም። ከነዚህ በተጨማሪም አባል ፓርቲዎች የሚገዙበት ህገደንብ ላይም የማያሻማ ስምምነት ሊደርስ ይገባል። ስምምነቱ መደረግ ያለበት ደግሞ በሁሉም አባል ፓርቲዎች መሆን ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ሲታይም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የመፈራቀቅ አዝማምያ እየታየባቸው እንዳለ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል ሁሉም ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ዙሪያ አንድ አይነት አቋም የላቸውም። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ለህወሓት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። ለአዴፓና ለኦዴፓ ደግሞ እንደጦር የሚፈራ የህገ ደንቡ አካል እየሆነ መጥቷል። በዚህ ረገድ መስማማት ላይ ካልተደረሰ አሁንም ኢህአዴግ አለ ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። እንደኔ እንደኔ ከሆነ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነፃነትን የሚጋፋ ኢ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ አሰራር ስለሆነ ከምድረገፅ ቢጠፋ እመርጣለሁ። ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ የኢህአዴግ በመሆኑ ዴሞክራሲያዊ ማዕካላዊነትም ሆነ ሌላ በአባል ድርጅቶች ስምምነት ላይ የተደረሰበት ህገ ደንብ ማስፈለጉ አጠያያቂ አይደለም።

 

3.      ሌላው ኢህአዴግ ትኩረት ሰጥቶ ሊቀርፈው የሚገባው ትልቅ ችግር በየስብሰባ ደረስኩባቸው በሚላቸው ስምምነቶችና በዶ/ር አብይ በሚፈፀሙ ተግባራት መካከል ያሉትን ከፍተኛ ተቃርኖዎች የተመለከተውን አብይ ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ይሁንና ለጊዜው የተወሰኑትን በመጥቀስ ብቻ የችግሩን አሳሳቢነት ለማስየት እሞክራለሁ። አንዳንዴ ኢህአዴግ ይሰበሰብና አገሪቱ በምትከተለው የኢኮኖሚ አቅጣጫ ላይ ተስማምቸ ወጥቻለሁ የሚል መግለጫ ይሰጣል። መግለጫው ከወጣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ደግሞ እየተወሰደ ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ በስብሰባው ወቅት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አይደለም የሚል ተቃውሞ የሚያነሳ አባል ድርጅት ይነሳል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢህአዴግ እንዲሁ ይሰበሰብና ከግንቦት 30/2010 ዓ.ም በፊት ወንጀል ለፈፀሙ ሰዎች ምህረት ለመስጠት የሚያስችል አዋጅ እንዲወጣ ተስማምቻለሁ የሚል ማብራሪያ ይሰጣል። አዋጁ ከወጣ በኋላ ደግሞ መመዘኛው ምን እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ የቴሌቪዥን ዘገባ በማሰራጨት ጭምር በተወሰነ ቡድን ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሲያስር ይታያል። ሲፈልግ ደግሞ ህገመንግስታዊ ስርዓቱና የህግ የበላይነት እንዲከበሩ የማያወላዳ ውሳኔ አሳልፌያለሁ ይልና የውሳኔው መግለጫ የተፃፈበት ቀለም ሳይደርቅ በዶ/ር አብይ የሚመራው የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጉዳይ ህገወጥ የሆነ ጣልቃ ገብነት ሲፈፅም ይታያል።

ከዚህ አለፍ ሲል ደግሞ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይሰባሰብና ኢኮኖሚው እየተዳከመ፣ ሰላምና ፀጥታን የሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች እየተበራከቱና በአባል ድርጅቶች መካከል መጠራጠር እየጎላ እንደሆነ መግለጫ ይሰጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ዶ/ር አብይ የተለያዩ መድረኮች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ የሳቸው አመራር በጣም የተዋጣለትና አለም ሳይቀር እያደነቀው እንደሆነ ያለምንም ማመንታት ሲገልፁ ይሰማሉ። በነገራችን ላይ ዶ/ር አብይ ለውጥን የሚመዝኑት ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እይታ አንፃር ሳይሆን ስብዕናቸውን ሊያጎሉላቸው ይችላሉ ብለው ከሚያስቧቸው አለማቀፍ ማህበረሰብ፣ የድሮው ኢህአዴግ ምቾት ከማይሰጣቸው ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፤ የመገናኛ ብዙሃን አባላትና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍና ተቃውሞ አንፃር እየቃኙ እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ይህ አይነት መሳከር ባስቸኳይ እስካልታረመ ድረስ አሁንም የኢህአዴግ አንድ ሆኖ የመቀጠል ሁኔታ አጠያያቂ ነው።

4.   ኢህአዴግ የግለሰብ መሪን ተክለሰውነት ለመገንባት ጥረት ከሚያድረግ ይልቅ ትኩረቱን በተቋማት ግንባታ ላይ ቢያዞር ለሃገር ግንባታና ለህዝቦች አንድነት የሚጠቅም መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል። ከዚህ በፊት የአቶ መለስን ተክለ ሰውነት ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ አይተናል። አሁን ላይ ደግሞ የዶ/ር አብይን ተክለሰውነት ለመገንባት ሸብ ረብ ሲባል እየተመለከትን ነው። ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ የዶ/ር አብይን አምባገነንነት ይፈጥር እንደሆነ እንጅ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊያመጣ የሚችል ሂደት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊጎለብት ይችል ዘንድ የግለሰብ መሪን ተከለሰውነት ከተቋማት አስበልጦ ማየት እንዲቀርና በምትኩም ያሉ ተቋማት ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆኑ ሌሎች የሚያስፈልጉ ተቋማት ደግሞ እንዲፈጠሩ ማድረግ የህዝብ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል።

 

5.      ኦዴፓ (ኦህዴድ) ታግየና አታግየ ገረሰስኩት ያለውን የሌላ ቡድን የበላይነት ዝንባሌ ራሱ እየደገመው እንደሆነ የሚያስመስሉ ሁነቶች ስላሉ ኢህአዴግ አደገኝነቱን ተረድቶ ችግሩ ከወዲሁ እንዲስተካከል ጠንካራ ትግል ሊያደርግ ይገባል። በዚህ ረገድ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው በአቶ መለስ ጊዜ ብዙዎቹን የፌድራል ተቋማት እንዲመሩ የተደረገው በህወሓት ሰዎች ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ በኦዴፓ (ኦህዴድ) ሰዎች እየሆነ ነው። ለምሳሌ ያህል ጠቅላይ ሚንስትር አብይንና በጽህፈት ቤታቸው ዙሪያ ያሉትን ተሿሚዎች ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ የሆኑ የፌዴራል መንግስት ተቋማት ማለትም የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የገቢዎች ሚ/ር፣ የግብርና ሚ/ር ፣ አየር ሃይል፣ በምክትልነት ቢሆንም የደህንነት መስርያ ቤቱና ሌሎችም እየተመሩ ያሉት በኦዴፓ (ኦህዴድ) ሰዎች ነው። በምክትልነት ቢሆንም አሁን አሁን ጎላ እያሉ የመጡት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ እታማዦር ሹም የኦዴፓ ሰው ናቸው። በተለይ ደግሞ የውጭ ግንኙነትን (Foreign Relations) የተመለከቱ ስራዎች ሲኖሩ የምናየው የሰዎች ፊት የዶ/ር አብይን፣ የዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁንና የአቶ ሽመልስ ጋቢሳን ሆኗል። ሶስቱም ደግሞ የኦዴፓ ከፍተኛ አመራር አባላት ናቸው።

 

የሚገርመው ነገር ይህ የኦዴፓ ሰዎች መብዛት ለፌዴራል ስርዓቱ መጎልበት ጥሩ እንደምታ የለውም ተብሎ አስተያየት ሲቀርብ የሚሰጠው መልስ በህወሓት ላይ ይነሳ ለነበረ ጥያቄ የሚሰጥ አይነት መልስ እየተሰጠ ያለ መሆኑ ነው። ቀደም ብሎ የህወሓት አመራሮች በፌዴራል ደረጃ መብዛት ያንድ ቡድን የበላይነት ሊያመጣ ይችላልና ይስተካከል የሚል አስተያየት ሲነሳ ችግሩ መኖሩንና አለመኖሩን ጥናት አድርጎ አስፈላጊውን ማስተካከያ ከማድረግ ይልቅ ለአንድ አላማ የምንታገል ስለሆነ ቁጥራቸው መብዛቱ ችግር የለውም የሚል መልስ ነበር የሚሰጠው። አሁን ደግሞ በቅርብ ጊዜ አቶ ገዱ አሜሪካን አገር ሰዎች ሰብስበው በሚያናግሩበት ወቅት የኦዴፓ ሰዎች በፌዴራል መንግስት ደረጃ አግባብ ባልሆነ መንገድ እየበዙ ነውና መስተካከል አለበት የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው የመለሱት መልስ እኛ የምንቆጥረው ስላጣን ሳይሆን ትኩረታችን ለውጡ በትክክለኛ መንገድ መሄዱ ላይ ነው የሚል ነበር። ይህ መከራከሪያ ግን ውሃ አይቋጥርም። አንደኛ ነገር የሃገሪቱ አወቃቀር ማንነትን መሰረት ያደረገ ስለሆነ የሁሉም ማንነት ባለቤቶች በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ ተመጣጣኝ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል። ሁለተኛ ብቃት ያላቸው ሰዎች ያሉት አንድ ቡድን ውስጥ ብቻ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

 

ሁለተኛው መከራክሪያ ደግሞ ኦዴፓ የወጣው ሰፊ ቁጥር ካለው የኦሮሞ ህዝብ ስለሆነ የሱ ሰዎች ብዙ ቦታ ላይ ቢቀመጡ ፍትሃዊ አይደለም ተብሎ ሊወሰድ አይገባም የሚል ነው። ይህ መከራከሪያ እውነታነት ቢኖረውም በሁለት ምክንያቶች ዝንፈት እንዳለበት ማሳየት ይቻላል። የመጀመሪያው የኦዴፓ ሰዎች በዛ ያለ ቁጥር እንዲኖራቸው መደረጉ ችግር ነው ባይባልም ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ ቦታዎችን እንዲይዙ መደረጉስ ምን አመክንዮ ሊቀርብለት ነው? መመጣጠን ያለባቸውስ እነሱ ብቻ ናቸው ወይ? ሌሎች ብሄር ብሄርሰቦችስ ለነሱ በተደረገው መልክ እንዲመጣጠኑ እየተደረገ ነው ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ያስነሳል፤ ምን አልባት "ዘመኑ የነሱ ነው" የሚል የወረደና ፀረ ዴሞክራሲ፣ ፀረ እኩልነት፣ ፀረ እድገትና ፀረ አንድነት የሆነ አድሃሪ አስተሳሰብ የበላይነት ካላገኘ በስተቀር።

 

እንዴውም መሆን አለመሆኑ ወደፊት የሚታይና የሚለይለት ጉዳይ ሆኖ አንዳንድ ሰዎች አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲገመግሙ ኢትዮጵያን ኦሮሟዊ የማድረግ (Oromisation of Ethiopia) የሚል ፕሮጀችት (Project) ተይዞ እየተሰራ ነው ይላሉ። የጃዋር መሃመድን ሰፊ የሆነ የፖለቲካ አቅንቃኝነትና በሚዲያ ላይ ያለውን ከፍተኛ እንቅስቃሴም ከዚሁ ፕሮጀክት ጋ የሚያያይዙት ሰዎች አሉ። በተጨማሪም አሁን አሁን እየሰማንና እያየን እንዳለነው ዶ/ር አብይና ሌሎች የኦዴፓ ሰዎች በሶማሊ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላና በአፋር ብሄራዊ ክልሎች ጣልቃ በመግባት መሪዎቻቸንውን እንዲቀይሩ እስከመግፋት የደረሱት የዚሁ ኢትዮጵያን ኦሮሟዊ የማድረግ ፕሮጀክታቸው አካል እንደሆነ የሚያመላክት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህ የሚሆን ከሆነ አገሪቱ ወደ ሌላ ቀውስ ልትገባ ስለምትችል ኢህአዴግ የችግሩን አደገኛነት ተረድቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅበታል። እኛም እንዲሁ የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበን አስፈላጊውን ግፊት ማድረግ ይጠበቅብናል።

 

6.      በመንግስት ባለቤትነት ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ከድሮ ስርዓቶች ወቃሽነት ወጥተው ለህዝብ ጥቅም መቆም ያለባቸው ጊዜ አሁን እንደሆነ ኢህአዴግ በደንብ መገንዘብ ይኖርበታል። አሁን ላይ ያሉት የነዚህ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ዶ/ር አብይን የሚክቡና አናዳንዴም ፈጣሪ ናቸው ብለው ለመስበክ የሚዳዳቸው ናቸው። እነዚህ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዶ/ር አብይ የሚመሩት መንግስትና ባጠቃላይም ራሱን የለውጥ ሃይል ነኝ ብሎ የሚያውጀውን ሃይል ማሞገስ እንጅ ጥንካሬዎች እንዲጎሉ ድክመቶች ደግሞ እንዲስተካከሉ የሚያደርግ አቅጣጫን እየተከተሉ አይደለም። ስለ ኢህአዴግ ድክመቶች የሚያነሱ ከሆነም ዶ/ር አብይ ሃላፊነት ከመያዛቸው በፊት ስለነበረው ኢህአዴግ እንጅ አሁን ስላለው ኢህአዴግ አይደለም። በዚህም የተነሳ ስንትና ስንት ሊዘገቡና ለህዝቡ ጀሮዎች ሊደርሱ የሚገባቸው ሁነቶችን ነው እንዳላዩና እንዳልሰሙ አስመስለው ያለፏቸውና በኋላም አንድም በውጭ የመገናኛ ብዙሃን ካልሆነም በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች ለመስማት የምንበቃው። ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በሰው ሃይል የብቃት ማነስ፣ የጠራ አደረጃጀት ባለመኖር እንዲሁም ግልፅና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሰራር መጓደል ሊሆን ስለሚችል ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የሁኔታውን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ጊዜ ሳይሰጥ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅበታል። ካለበለዚያ እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን የመንግስት ፕሮፖጋንዳ ቱቦ ሆነው መቀጠል እንጅ የህዝብን ጥቅም ሊያስከብሩ የሚችሉ ተቋማት ሊሆኑ አይችሉም።

 

ቸር ይግጠመን!

 

Back to Front Page