Back to Front Page

‘የጤዛ ፖለቲካ እና አኗኗራችን’

 የጤዛ ፖለቲካ እና አኗኗራችን

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ  12-28-19

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

   በተፈጥሮ ሂደት ውስጥ ከምናያቸውና ለሁላችንም ግልጽ ከኾኑ ከማያከራክሩ ልዩነት ከማይታይባቸውና ሊታይባቸው ከማይችሉ ጉዳዮች መሐከል ጤዛ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጤዛ ጠዋት ላይ የሚገኝ ብዙም ሳይቆይ የሚጠፋ ስለመኾኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ጤዛ ታይቶ የሚጠፋ የቆይታውም ጊዜ እጅጉን ያጠረ በመኾኑ በብዙ የአኗኗር ምሳሌዎች ውስጥ ወካይና ገላጭ ተደርጎ ሲቀርብ መመልከት የተለመደ ነው፡፡

   የሀገራችን ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ነባራዊ ኹኔታዎችን  ስንመለከት ጤዛዊ ባህሪያትና ጠባያት በእጅጉ ይበዛበታል፡፡ በዕለት ተዕለት ኹለንተናዊ እያንዳንዷ በሀገራችን የተፈጸመችና በመፈጸም ላይ ያሉ ኹነቶችን ስንመለከት፡-

Videos From Around The World

      1ኛ. ቶሎ አዳዲስ ነገሮች ይከሰታሉ ሳይቆዩ ይከስማሉ፤

      2ኛ. ሥር ስለማይሰድ ይረሳል፡፡

      3ኛ. ለንጽጽር እንኳ የማይበቃ ኾኖ ይገኛል፡፡

  ይህን ጥቅል ነጥብ በዝርዝር ከኾኑና በመኾን ላይ ካሉ ነገሮች ጋር አስተሳስረን ስንመለከተው በየወቅቱ ብዙ እጅግ ዘግናኝ፣ አሳፋሪ፣ አሳዛኝና አስፈሪ ኹነቶች ተከስተዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቀሉ አንድ ሰሞን ብዙ ተባለ - ጠያቂም ኾነ ተጠያቂነት ትርጉም ባለው መንገድ ሳይኖር አለፈ፡፡ ተፈናቃዮች ግን ጠባሳውን እድሜ ልካቸውን በማይረሱት መንገድ በልባቸው አትመው ይኖራሉ፡፡

  ብዙዎች በግጭቶች ንብረታቸው ወደመ፣ ሀብት ንብረታቸው የማንም መጫወቻ ኾነ፣ አካላቸው ጎደለ ከኹሉ በላይ ህይወታቸውን አጡ - በአንድ ሰሞን ብዙ ተባለ - ከዛ ተረሳ - እነኾ እኛም ምንም እንዳልተፈጠረ እንኖራለን - የደረሰበት ግን ከዛ ለማገገም ብዙ ጊዜያት እንደሚወስድበት እሙን ነው፡፡

  በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እንኳ ያሉ ሀገራት ሶሪያ፣ ሊቢያና የመን ውስጥ በቀን ከሚሞተው ጋር ሲተያይ የበለጠ ብዙ ሰው ስለመሞቱ እርግጥ ቢኾንም - ምንም እንዳልተፈጠረ ማን - ምን - ስለምን - በነማን ተፈጸመ? የሚለውን ሰሞነኛ አጀንዳ ከመኾን ሳይዘል ታልፎ - እኛም ረስተነው መደበኛ ሕይወት በመምራት ላይ እንገኛለን፡፡

  በርካታ ቦታዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የሚተዳደሩ ስለመኾናቸው በአደባባይ የሚታወቅ ቢኾንም ለምን? እንዴት? በማን? ማን ነው ተጠያቂው? የሚለው ጥያቄ የአብዝሃ ቢኾንም - ጥቂቶች ብቻ ዘወትር እያነሱት - አብዝሃ የራሱ ጉዳይ እንኳ መኾኑን ረስቶት ይኖራል፡፡ በአንድ ወቅት እዛም እዚም በተከሰቱ ኹነቶች አጀንዳ ኾኖ ነበር:: ከዛ በመግለጫ ጋጋታ ተድበስብሶ አለፈ:: በቃ - አለቀ - ከዛ በኃላ ማን ዞር ብሎ ያያል? ጤዛን ከረፈደ ማን ዞር ብሎ ይፈልጋል? ከረፈደ በኃላ ጤዛስ ቢኾን ከወዴት ይገኛል? ኑሯችንና አኗኗራችን የጤዛ ኾኖ የለምን?

   በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል፣ ብዙዎች ተጎድተዋል - ቀላል የማይባል የሰው ሕይወት አልፏል - እኛ ግን እንደጤዛ የአንድ ወቅት ኹነት ብለን አልፈነዋል፡፡ ኹነቱ ግን ብዙ ወላጆችን ያለልጅ ስለማስቀረቱ፣ ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ወላጆች ከዛ ተጽዕኖ ነጻ እንዳልወጡ - የአካባቢው ማሕበረሰብም በቁጭት ውስጥ ገብቶ እድሜ ልኩን የማይረሳው ተጽዕኖ እንዳሳረፈበት ዘንግተናል፡፡ ስለዘነጋንም ሊደረግ የሚገባውን የመከላከል ሥራ ሳንሰራ በቀትር አንቀላፍተን እንገኛለን፡፡ ለምን ይኾን የዘነጋነው? ለምን ይኾን በባለቤትነት ስሜት ትርጉም ባለው መንገድ ከዳር ያላደረስነው?

   በአንድ ወቅት ሰው በአደባባይ እጅግ በአሰቃቂ ኹኔታ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንኳንስ ሊደረግ ሊታሰብ በማይችል በሚባል ደረጃ ቁልቁል ተዘቅዝቆ ተገደለ፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የደቦ ፍትህ ተሰጠ፤ ሰው በድንጋይ ተወግሮ ተገደለ - አንድ ሰሞን ብዙ ተባለ - ከዛ ተረሳ - ወላጆችና ወዳጆች ግን ከዛ ለማገገም ችለው ይኾን? ብሎ አጥብቆ የጠየቀ ማን ይኾን?

   በሀገራችን በሥልጣን ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ትላንት ሌላ ይሉ የነበሩ ሰዎች ዛሬ ደግሞ እጅግ ተቃራኒ ነገር ሲናገሩ አብዝሃ ዝም ይላል - እነሱም ሳያፍሩበት ያለ ይሉኝታ መዋሸትና ማስመሰልን ከማንነታቸው ጋር ስላዋሃዱት ምንም ሳይመስላቸው ደረታቸውን ነፍተው ተራ የቃላት ድርደራ ውስጥ ሲገቡ፤ ክህደትን ዋነኛ መለያቸው ሲያደርጉና የኖሩበትን በርካታ ጊዜ ሲኮኑኑ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ጤዛዊ ባህሪና ጠባይ እንደምን እንደባሕል ስር ሰደደ? ስለምንስ ወጊድ ማለት አቃተን?

  እነኾ ፖለቲካችን እንደጤዛ አጀንዳ በየጊዜው የሚቀያይር፣ ዛሬ የተባለው ነገ የማይደገም፤ ዛሬ ይደረጋል የተባለው የማይደረግ፤ ይሰራል የተባለው የማይሰራበት፤ ይኾናል የተባለው የማይኾንበት፤ ትላንት ሌላ ዛሬ ሌላ - እጅግ በጣም የሚቃረንና ተቃራኒ የኾነ ነገር እንኳ ሲደረግ ለምን? የማይባልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

  በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ ብዙ መድረኮች ላይ በጣም ብዙ እጅግ ብዙ ብዙ ነገር ይባላል - የተባለው መሬት ሳይነካ እዛው ባየር ላይ የማህበራዊ ሚድያ ፍጆታ - የብሽሽቅ ማራገቢያ - የሥነ ልቦና ጦርነት ማካሄጃ ንጣፍ በመኾን ከፍ ካለ ደግሞ የሌላ ሚድያ (ሬድዮና ቴሌቪዥን) ማድመቂያ በመኾን ጊዜ ያጣብብና ይረሳል፡፡ ደሞ ሌላ ይመጣል - ከዛ ደሞ ያ ይረሳል - በተራው ደሞ ይሄ ሲሄድ ሌላ ደሞ ይመጣል፡፡ ስለዘር ስለዘር ማፍራት ማን ትርጉም ባለው መንገድ ያስባል?

  ጤዛ ጠዋት ታይቶ ረፋድ ላይ እንደሌለው ኹሉ - ለፍሬና ለፍሬያዊነት እንደማይበቃው ኹሉ ዘወትር ጨልሞ እስኪነጋ የሚጠብቅ እንደመኾኑ ኹሉ ፖለቲካችን በመግለጫ፣ በመድረክ ዲስኩር፣ በዶክመንተሪ ጋጋታ፣ በኢንተርቪው ጨዋታና በጉብኝት ትያትር የተሞላ ስለመኾኑ ማንም አይስተውም፡፡ አብዛኛዎቹ ነገሮች ጤዛና ጤዛዊ ባህሪያትና ጠባያትን የተላበሱ ስለመኾናቸው እጅጉን አጉልተንና ትኩረት ሰጥተን ባንናገርም፣ ባንጽፍም ኾነ ባንጮህለትም ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡

   ዛሬ ዛሬ በሀገራችን አንድ ደፋር የተገኘ እንደኾነ ብዙ ይባልለትና - ደግሞ ይጠፋል፤ እሱም ከጊዜያት በኃላ የአብዝሃ ማህበርን ይቀላቀልና ወደ ነበርነት ይቀየራል፡፡ ስለአመክንዮ፣ ስለእውቀትና ስለነጻነት አብዝተው ቀን ከለሊት ሲተጉ የነበሩ ሰዎች ለሴራ፣ ለሥልጣን፣ ለውግንናና ለፍላጎታቸው መሟያነት የኾነ ነገር ሲያጋጥማቸው እጅጉን ይምሉና ይገዘቱበት ከነበረው እምነት፣ እውቀት፣ ነጻነትና አመክንዮ እጅጉን ርቀው ኸረ እንዲያውም ተጠይፈው የተገኙ ብዙዎች አይደሉምን? እንደጤዛ በአንድ ወቅት ብዙ ተብሎላቸው ገና ሳይረፍድ ስብዕናቸው የጠፋ በርካቶች አይደሉምን?

  ስንቶች ናቸው - የብዙዎችን አፍ አስከፍተው - የስንቶችን ወኔ ቀስቅሰው - የስንቶችን ስሜት ገዝተው - የስንቶችን ድጋፍ በቀላሉ አግኝተው - ብዙ ከተባለላቸው በኃላ ስለእውነት፣ ስለነጻነት፣ ስለፍቅር፣ ስለተስፋ፣ ስለምህረት ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ እንዳልጮሁ  የሚፈልጉትን ካገኙ በኃላ በጓዳ ሌላ በአደባባይ ሌላ የኾኑ ጤዛዎች በርካቶች አይደሉምን? እንኳንስ በአቋም ጸንተው ሊቆዩ ማርፈድ እንኳ የማይችሉ በርካቶች አይደሉምን?

     ሌላው የጤዛዊነት ባሕል ስለማዳበራችን አንዱ ማሳያ - በርካቶች በመድረክ ብዙ ብዙ ይላሉ - ህዝቡን እጅጉን ያወድሳሉ - ያወድሳሉ - ይፎክራሉ - ይፎክራሉ - ደሞ መልሰው ያቅራራሉ - ደሞ ሌላ ቦታ ላይም ሲሄዱ የተጠየቁትን ትተው ያልተጠየቁትን ይመልሳሉ፤ የሚታየውን ትተው የማይታይና ሊታይ የማይችል ነገር በማንሳት ብዙዎችን ይሸውዳሉ፤ ከሚያስፈልግ ይልቅ ይፈለጋል ተብሎ የሚታሰብን ነገር በማንሳት ሰዎችን ግራ ያጋባሉ - ያወናብዳሉ - በግልጽ ቋንቋ ይስፈር ከተባለ ያጭበረብራሉ፡፡ ከነሱ በላይ ተጭበርባሪው መጭበርበሩን ሳያውቅም ኾነ አውቆ ያራግባል - ያ ጊዜ ሲያልፍ ማን ምን እንዳለ የሚያስታውስ ስለሌለ - ጊዜው አብዝሃ ሳያስተውለው ያልፋል - ጊዜ መግዛት የፈለጉ ጥቂቶች ብቻ ጊዜ ይገዛሉ፡፡

   ጤዛዊነት በዓለም ላይ አንድን ሰው መዋሸት ነውር - ቡድኖችን መዋሸት ታክቲክ - ብዙሃንን መዋሸት ትራጄዲ - ሚሊዮኖችን መዋሸት ቁጥር፣ ተራ ብልጠት፣ የላቀ ዝቅጠትና የዘመኑ ‘ሥልጣኔ’ መኾኑን ያመላክታል፡፡ ‘ድራማ’ የተበራከተው ከ‘ተዋናዩ’ ይልቅ የ‘ድራማ’ ተከታይ፣ አድናቂና አማኝ እጅጉን በመበራከቱ ስለመኾኑም በትልቁ ይመሰክራል፡፡ ያስመሰክራል፡፡

  ጤዛዊነት የበላይነት በያዘበት ማሕበረሰብ ውስጥ ይብላኝ ለቁመ ቀር ህጻናት ‘ተዋንያኖች’ - ጊዜ እንደኾነ ይሄዳል፤ ታሪክ እንደኾነ ይፈርዳል፤ ስካርም እንደኾነ ጊዜ ይወስዳል እንጂ ይጠፋል፡፡ በመሐከል ግን ትውልዶች ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ ትውልዶች ኹለንተናዊ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ መተኪያ የሌለውን ጊዜ፣ ሃብትና ዕውቀታቸውን በአግባበቡ ባለመጠቀማቸው - ባለመጠቀም የሚገኝ መራራ ፍሬ በማግኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

   እንደሀገር ከጤዛዊ ባህሪያትና ጠባያት ወደ ተላቀቁ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርጉም ያላቸው እንቅስቃሴዎች ካልገባን በቀር በመጣንበት መንገድ በመቀጠል መሠረታዊ ለውጥ - በዚሁ ቀጥለን የምንፈልገው ነገር ይመጣል - ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጦችን እናያለን ማለት ዘበት ነው፡፡

  ዓለም ካለማወቅ ይልቅ ያወቁትን ባለመተግበር ብዙ እንዳጣች ከታሪካችንና ከአኗኗራች በላይ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ ጤዛዊ እንቅስቃሴ ከጤዛዊ ፍሬዎች የተለየ ነገር እንደማያመጣ ማወቅ ብልህነት ብሎም ማስተዋል ነው፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

 

 

Back to Front Page