Back to Front Page


Share This Article!
Share
ዳንሻ የልማት እንጂ የጦርነት አውድማ አትሆንም ።

ዳንሻ የልማት እንጂ የጦርነት አውድማ አትሆንም

በልኡል  ገብረመድህን (ከአሜሪካ )

የካቲት  29.2011.

        በሁለቱ ሀያል የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች (አማራና ትግራይ ) አዋሳኝ ቦታዎች የተረጋጋ ሰላም የለም ። ለሰላም መደፍረስ የሁለቱ ወንድም ህዝብ ምክንያት አይደለም ። የትግራይ እና ወንድም የአማራ ህዝብ ትስስር ከጉርብትና ያለፈ ማህበራዊ ትስስር አላቸው ። በጋብቻ ዝምድና የተገመደ ህዝብ ነው ። የትግራይ ማህበረሰብ ከወንድም የኤርትራ ህዝብ ባልተናነሰ ከአማራ ህዝብ ጋር በሰጋነ ደሙ የተዋሐደ ህዝብ ነው ። በኢትዮጵያ የመንግስት አሰተዳደር ሰልጣንና ሰልጣኔ አመጣጥ ሂደት ላይም ተመጋጋቢ ፣ ተወራራሽ  ፣ እንዲሁም ተዛማጅነት ያላቸው የመንግስት አሰራርና አካሔድ የነበራቸው ህዝቦች ናቸው ። በእምነቱ በኩልም የሁለቱ ህዝቦች አምልኮተ ሰርአት ተመሳሳይ ነው ። የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት (ክርስትያናዊ ተዋሕዶ ) መሰረትና ምንጭ መሆናቸው ላላቸው እምነታዊ ሆነ ማህበራዊ ትስስር መነሻ ምክንያት ነው ። በኢትዮጵያ የመንግስት አሰተዳደር መዋቅራዊ ቅርፅ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ዘመናት የተሻገሩ የሁለቱ ታላቅ ህዝቦች ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ማህበራዊ መፋለስ የሚያስከትሉ የፖለቲካ አሰተዳደር ችግሮች መታየት ጀምሯል ። ሁለቱም ህዝቦች በመሬት ቆዳ ስፋትና ህዝብ ብዛት ካልሆነ በቀር በአኗኗር ዘይቤ ተመሳሳይነት አላቸው ። የኑሮ መሰረታቸው ግብርና ላይ የወደቀ ነው ። ሌላው የአስተዳደር መብት ጭቆና በሁለቱም ህዝቦች በስፋት የሚታይ ጉዳይ ነው ።

Videos From Around The World

      በኢትዮጵያ ተሳስሮ እና ተሳሰቦ በጋራ ለመኖር የሚያስችሉ በርካታ መስተጋብሮች ቢኖሩም አጠቃቀም ላይ ጉድለቶች አሉ ። የትግራይ ተወላጆች ከጎንደርና አካባቢው ማፈናቀል ታሪካዊ ስህተት ነበር የተፈፀመው ። ጉዳዩ በአፋጣኝ መታረም ሲገባው በማፈናቀል ተግባር ላይ ተሰማርቶ በነበሩ ህግ አልባ የመንደር ቦዘኔዎች ይሁን የክልሉ የመንግስት ሀላፊዎች ላይ የተወሰደ አስተዳደራዊ ሆነ የህግ እርምት በጉልህ አልታየም ፣አልተሰማም ። እንዲሁ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በአማራ ማህበረሰብ ላይ የደረሰው የማፈናቀል ሰብአዊ ጥሰት በቁጥር ሆነ በይዘት የሚቀራረብ የለም ። ከደቡብ ኢትዮጵያ ፣ ከጋምቤላ ፣ ከድሬዳዋ ፣ እንዲሁም ከሌላ ቦታ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጅ ዜጎች ሲታይ የማህበረሰቡ የትዕግስት መጠንና አስተዋይነት እጅግ የሚያስደንቅ ነው ።ህዝቡ ልበ ሰፊ ባይሆን ኖሮ የሚደርሰው እልቂት የከፋ ይሆን ነበር ። በአማራ ህዝብ ላይ ምድራዊ የአስተዳደር ወንጀል ተፈፅሟል ። ህዝቡ ለዘመናት ይኖርበት ከነበረ የመሬት ይዞታው ያለምንም ካሳ በሐይል እንዲፈናቀል ተደርጓል ። ህዝብ በማፈናቀል ተግባር ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የመንግስት ሀላፊዎች ላይ ምንም አይነት ህጋዊ ተጠያቂነት ያለመኖሩ የበለጠ ህመም ነው ። በተመሳሳይ ከአማራ ክልል በሐይል የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጅ ዜጎች ላይ ለተፈፀመው ሀላፊነት የጎደለው እርምጃ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው አሰተዳደር በህግ አግባብ ተጠያቂ መሆን አለበት የሚል የፀና እምነት አለኝ ። በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያ ጉራፈርዳ ላይ በአማራ ተወላጅ ዜጎች ላይ ለደረሰው ሰቆቃ አቶ ሺፈራው ሹጉጤ ላም ተገቢው የወንጀል ምርመራ መደረግ አለበት እላለሁ ።

      በኢትዮጵያ የፖለቲካ አሰተዳደር የህዝብ ፍላጎት ያማከለ ባለመሆኑ ተደጋጋሚነት ያላቸው ማህበረ ኢኮኖሚ አገራዊ ውስጣዊ ችግሮች ጥልቀት ሰፊ ነው ። የችግሮች መፍትሄ ደግሞ በህግ ልዕልና ላይ የቆመ የፖለቲካ መዋቅር ነው ። ህግን መሰረት ያደረገ የመንግስት ሰርአት ህዝባዊ መሠረት ይኖረዋል ። ፍትሀዊ የህዝብ ይሉኝታ ያላገኘ የፖለቲካ ሰርአት የህዝብ መሰረታዊ መብቶች ያከብራል ተብሎ አይታሰብም ። የብሔር ጣምራ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በርካታ ህገ መንግሰታዊ የመብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ ህጋዊ እርምጃዎች መውሰድ ባለመቻሉ የህዝብ ፍትህ ጥያቄዎች መመለስ ባለመቻሉ አሁን የደረሰበት ሁኔታ ላይ እንዲያበቃ በህዝብ ፍላጎት ተገደዋል ። ድርጅቱ ካጋጠመው ውስጣዊ ቀውስ ለማዝገም የሚያስችል ድርጅታዊ ተሐድሶ ግምገማ ቢያደርግም ግምገማው የህዝብ ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ ባለመኖሩ ከድርጅቱ ውሰጥ የለውጥ ሐይል የሚል አካል ተፈጠረ ። ይህ የለውጥ ሐይል መሠረቱ የኢህአዴግ የፖለቲካ መሰመር ቢሆንም በለውጡ ውሰጥ ማካተት አልተፈለገም ።

     በኢህአዴግ ፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የፈለቀው የለውጥ ሐይል የሁለት ታላላቅ ማህበረሰብ በሚወክሉ የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ፖርቲዎች የተቀናጀ ጥምረት ነበር ። በዚህ ወቅት አንጋፋው የህወሓት ፖለቲካ ፖርቲ ከፖለቲካ ጨዋታ ውጭ ሆነ ። ድርጅቱ ለማስተዳደር ዶክተር አብይ አህመድ ለመምረጥ በተካሄደው የምርጫ ሒደት ላይ ህወሃት ለዶክተር አብይ ይሉኝታ ነፍገዋል ። በመሆኑም የለውጥ ሐይሉ በህወሓት ላይ የበለጠ መጠራጠር አሳደረ ። የኢህአዴግ ጣምራ የብሔር ፖለቲካ  ድርጅቶች የህወሓት የበላይነት አለ ሲሉ የከረሙ በኢህአዴግ ድርጅት ላይ ፅኑ እምነት አልነበራቸውም  ። የዶክተር አብይ መመረጥ ለኢህአዴግ ድርጅት የደም ያህል ያስፈልገው ነበር ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጥ ጥያቄዎች ማዕበል ኢህአዴግን ጠራርጎ ለስደት አልያም ለእስር ያበቃው ነበር ። በመሆኑም ዶክተር አብይ በኢህአዴግ ሰዎች ቢመሰገኑ ቢያንስ እንጂ አይበዛባቸውም ። ህወሃት ክህነትና ደባ ተፈፅሞብኛል የሚል ስሞታ አሰምተዋል ። ህወሃት ለማዳከም በውስጥ እና በውጭ ፖለቲካዊ ሴራ (political conspiracy ) ተፈፀመብኝ ፣ የህገ መንግስት ጥሰትም እየተፈፀመ በሚል ፖለቲካዊ ሰልት ህወሓት ራሱን ለመከላከል የትግራይ ልዩ ሐይል የማሰልጠንና የማደራጀት ትግበራ ውሰጥ ገባ ። በተመሳሳይ ለህወሓት ዘራፊ ብዱን እያለ የሚጠራው የድሮ ብአዴን የአሁኑ አዴፖ የክልሉ ልዩ ሐይል የማሰልጠን ፣ የማደራጀት ፣ እንዲሁም መሳሪያ የማስታጠቅ እንቅስቃሴ እያደረገ ቆይተዋል።  ክልሎች ከፖሊስ ውጭ ሌላ ልዩ ሐይል የማሰልጠን የህግ መሠረት የላቸውም ። ነገር ግን በሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውር ሲደረግ የማዕከላዊ መንግስት ያለው ነገር የለም ። በትግራይ  እንዲሁም  በአማራ አዋሳኝ ቦታዎች ብረት ያልታወቀ ሰው የለም ። ወንድም ወንድሙን ለመግደል በተጠንቀቅ ላይ ነው ። ዳንሻም እንደ ባድመ የጦርነት ግንባር ለመሆን የተመረጠች ትመሰላለች ።

         እውን ትግራይ የአማራ ህዝብ ላይ አማራ የትግራይ ህዝብ ላይ ውስጣዊ ወረራ ይፈፀማል ?። የትግራይ እንዲሁም የአማራ ህዝብ በድህነት ወለል ላይ የሚገኙ ህዝቦች በመሆናቸው ጦርነት የሚያስብ አዕምሮ ፣ መጥፎ የሚሰማ ጀሮ የላቸውም ። በአለም ባንክ (World Bank ) መረጃ መሠረት ከጠቅላላው የትግራይ ህዝብ 32 % በቀን ከአንድ ዶላር በታች ገቢ ያለው ህዝብ ነው ። በተመሳሳይ ከጠቅላላው የአማራ ህዝብ 31 % ከአንድ ዶክተር በታች በቀን ገቢ ያለው ህዝብ ነው ። ገጠሩን ሳያካትት በአማራ ከተሞች ከ 360,000በላይ ሥራ አጦች ያሉበት ክልል ሲሆን በተመሳሳይ ገጠሩን ሳይጨምር በትግራይ ከተሞች ከ 140, 000 በላይ ሥራ አጦች ያሉበት ክልል ነው ።  የህዝብ ብዛት የወሰድን እንደሆን የትግራይ ህዝብ ከወንድም አማራ ህዝብ በአራት እጥፍ ያንሳል ። ሁለቱም ህዝቦች የጦርነት አስከፊነት በሚገባ የሚገነዘቡ ታላቅ ህዝቦች ናቸው ። ከጦርነት የሚገኝ አንዳች ትርፍ እንደሌለ ለሁለቱም ህዝቦች ነጋሪ አያስፈልጋቸውም ። በሁለቱም ህዝቦች መሐል ግጭት እንዲነሳ ፍላጎት ያላቸው ሀይሎች አሉ ። አንደኛ የወልቃይት እንዲሁም የራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሚያራምደው በሚገባ ያልበሰለ ሓሳብ ሲሆን ሌላው የአዴፖ እና የህወሓት የፖለቲካ ጡዘት ነው ። የወልቃይትና ራያ ጉዳዮች አራማጅ ኮሚቴዎች የሚያነሱት የማንነት ሆነ ወሰን ነክ ጉዳዮች ህግና ሰርአት የተከተለ መሆን ሲገባው አጀንዳው በሌሎች የውስጥና የውጭ ሀይሎች በመጠለፉ ትክክለኛ መፍትሔ እንዳያገኝ ሆነዋል ። የወልቃይትና ራያ ማንነት ጉዳይ አራማጅ ሰዎች ላይ በትግራይ ክልል መስተዳድር ወከባና ጫና እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል። በምዕራቡ ቀመር 1994 ብሔር መሠረት ያደረገ ዘጠኝ ክልሎች ያቀፈ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሰርአት ውይይት ሆነ ማስፈፀም ላይ የነበረ የቀድሞ ብአዴን የአሁኑ አዴፖ የአማራ ግዛት ቦታዎች በህወሓት አሻጥር ምክንያት ተወስዶብኛል ፣ የህዝቤ ደህንነትም አደጋ ላይ ነው ሲል ስሞታ ያሰማል ። በነሐሴ ወር 1995 (በምዕራቡ ዘመን ) የፀደቀው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ህገ መንግስት የዘጠኝ ክልሎች ብሔር ተኮር አወቃቀር ላይ የሐሳብ ሆነ የውሳኔ ልዩነት ያልነበረው የአሁኑ አዴፖ እንዴት የክልል አወቃቀር ችግር ነበር ይላል ?። ይህ በራሱ ክህነት እና አገራዊ ወንጀል ነው ።  

        የወልቃይት እንዲሁም የራያ ማንነት ሆነ ተዛማጅ ጉዳዮች አንቀሳቃሽ ኮሜቴ አጀንዳ ተሸጠዋል ። የቀድሞ ብአዴን የአሁኑ አዴፖ የክህደትና ውሰለታ አጀንዳም አያዛልቅም ። አሁን ጉዳዩ ማን ቀድሞ ጥይት ይተኩስ ሳይሆን ማን ቀድሞ ሓሳብ ያመንጭ የሚል ይሆናል ። በወልቃይት ሆነ በራያ በአብዛኛው የትግራይ እና የአማራ ማህበረሰብ የሚኖሩባቸው ቦታዎች ናቸው ። የወልቃይት እንዲሁ የራያ የማንነት ሆነ የወሰን ጥያቄ ሁለቱ ህዝቦች ለግጭት የሚዳርግ አይደለም ።ሁለቱም ህዝቦች ጦርነት የሚገጥሙበት መነሻ ምክነያት የለም ። ያለው የክልል ፖለቲካ ፖርቲ አመራሮች የለበጣ ጦርነት (proxy war ) ነው ። መፍትሄው ደግሞ የቆሰሉ የክልል አመራሮች ማሰወገድ ቀጥሎም በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ህግና ደንብ የተከለ ጤናማ ህዝባዊ ውይይቶች ማካሄድ ተመራጭ አካሔድ ነው ። ወልቃይት ሆነ ራያ በሐይል መውሰድ ሆነ ማስመለስ ለመገመት የሚታክት ዋጋ ያስከፍላል ። የወልቃይት ሆነ የራያ ውስጣዊ ችግሮች በመሆናቸው ለችግሮቹ መፍትሔ ማመንጨት ላይም ውስብስብነት የላቸውም ። የማንነት ጥያቄዎች ተገቢ በመሆናቸው ተገቢው ህጋዊ ውሳኔ ላይ ማረፍ አለባቸው ። ማንነታችን ይከበር የሚል መሰረታዊ መርህ የማንነት ጠያቂዎች ሙሉ መብት ባካተተ መልኩ የህዝብ ውሳኔ ይሉኝታ ማግኘት ይኖርበታል ።  በሁሉም ክልል ህዝቦች ተሰባጥረው በሚኖሩ አናሳ ጎሳዎች ሙሉ የፖለቲካ ውክልና ተሳትፎ እንዲኖራቸው ፣ እንዲሁም ባህላቸውና ቋንቋቸዉ በተግባር በክልል ምክር ቤቶች መተግበር ይኖርበታል ። ከራያ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሚሰማ አንዱ ጉዳይ የአማራ ተወላጅ ልጆች በትግራይ ክልል በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አልቻሉም የሚል ነው ።

         የትግራይ እና የአማራ ክልል አመራር ሀላፊዎች ከአጉል ትንኮሳ ተወስኖ በአዋጪ የመፍትሔ ሀሳቦች ዙሪያ ላይ መወያየት ይኖርባቸዋል ።  ይህ አይነቱ አካሔድ የፖለቲካ ብስለት ተመራጭ አካሔድ ነው ። ከየክልሉ መሪዎች በተደጋጋሚ የሚቀርቡ ውንጀላዎች ማብረድ ተገቢ ነው ። የአማራ ክልል መስተዳድር ትግራይ የቅማንት ማንነት ምክንያት በማድረግ የክልሉ ህዝብ ሰላሙን እንዲደፈርስ ሆኖዋል ይላል ። በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ መስተዳድር የአማራ አክራሪ ብሔርተኞች በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ዛቻና ትንኮሳ ተፈፅሞብኛል በማለት ችግሩን ይጠቅሳል ። ያም ሆነ ይህ ልዩነቶች ከማስፋት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ በህግና መርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ መሪዎች በሳል ውይይት ያሰፈልጋል ። ግጭትና ጦርነት ጉዳት እንጂ የሚያመጣው ማህበራዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የለውም ። የወልቃይት እና የራያ መነሻ ምክንያቶች የዘር ጥላቻና የስልጣን ፍላጎት ምንጭ ናቸው ። በጥላቻና መናናቅ መንፈስ የጋራ ጉዳዮች ብሎም ችግሮች መፍታት አዳጋች ነው ። በመሆኑም የትግራይ እና የአማራ ክልል መስተዳድር ሀላፊዎች ለህዝቡ የሚመጥኑ የአስተዳደር ክህሎት ዘይቤዎች አንጥሮ መጠቀም ይኖርባቸዋል ። ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጠብ ቀስቃሽ ቃላቶች ከመለማመድ መቆጠብ ብልህነት ይመስለኛል ። ዘመን የጣላቸው ውዳቂ ቃላቶች ከመጠቀም መቆጠብ ለተሻለ መግባባት መንገድ ይከፍታል ። ወንበዴ ፣ ዘራፊ ፣ ፀረ ለውጥ ፣ ፀረ ሰላም ፣ ፀረ አገር ፣ ፀረ ህዝብ ወዘተረፈ የመሳሰሉ የቃላት አጠቃቀም ህዝብና አገር ከሚያሰተዳድር መሪ የሚጠበቅ አይሆንም ። የመሳሰሉ ቃላቶች አዘውትሮ ማስተጋባት የግብዝ ፖለቲከኞች መለያ ባህሪ ነው ። ለመጪው ትውልድ ሰላምና ብልጽግና እንጂ ዋልጌነት ማስተማር ከአገር መሪዎች አይጠበቅም ።

          የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች በጋራና በሰላም መኖር ለኢትዮጵያ ቀጣይ ህልውና የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው ። በሌላ በኩል የሁለቱ ህዝቦች ሰላም መደፍረስ በኢትዮጵያ የሚያስከትለው ውስጣዊ ቀውስ መገመቱ ያዳግታል ። የትግራይ ክልል መስተዳድር የአማራ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሐይል ወረራ የሚፈፅም ከሆነ በቀጥታ ጦርነት ውስጥ የመግባት እድል የሰፋ ይሆናል ። ግጭት ውስጥ መነከር የትግራይ ክልል ለሚመራ የፖለቲካ ድርጅት አዋጪ አይሆንም ።  ፍትሐዊነት የሌለው ( unjustifiable war) ጦርነት ውስጥ ከተገባው በቀጥታ ትግራይ ከኢትዮጵያ መገንጠል እውን ይሆናል ። ይሁንና ትግራይ የሚያስተዳድር የፖለቲካ ድርጅት ራሱ ከመከላከል አልፎ ግጭት ውሰጥ ይገባል የሚል እምነት የለኝም ። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት እንጂ ጦርነት አይፈልግም ። የአማራ ህዝብም እንደ ትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት እንጂ ህውከት የሚመኝ ህዝብ አይመስለኝም ። በመሆኑም የሁለቱም ክልል የበላይ አካል ሥራ አመራሮች በጥይት ከመተማመን ይልቅ በአመራር ክህሎትና በመርህ ላይ የተቃኘ የጋራ የውይይት መድረኮች ማካሄድ ተገቢ ይሆናል ። በጋራ ጉዳዮች ተቀራርቦና ተከባብሮ መነጋገር ለተፈጠሩ ችግሮች አይነተኛ መፍትሔ ይሆናል ።  የሴራ አካሔድ ለማንም አይበጅም ። ችግሮች በዳበረ የውይይት ባህል መፈታት እንዳለባቸው አምናለሁ ። የትግራይ እንዲሁም የአማራ ወጣቶች የሚያስተምር የፖለቲካ በሳል አመራር ከሁለቱም ክልል የበላይ አመራሮች ይጠበቃል ። ወጣቶች ለጦርነት ከማዘጋጀት ይልቅ በአገር ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ ይጠበቃል ።

        በትግራይ እንዲሁም በወንድም የአማራ ህዝብ መሐል መሠረታዊ ቅራኔ የለም ። ሁለቱም ህዝቦች ለግጭት የሚያበቃ ፍትሀዊ ምክነያት የለም ። በመሆኑም ትግራይ ሳይሆኑ በትግራይ ስም እንዲሁ አማራ ሳይሆኑ በአማራ ሰም ህዝቦች በጥላቻ አይን እንዲተያዩ የሚደረግ የሚዲያ ጥሞራ መቆም ይኖርበታል ። የሁለቱ ክልል አመራሮች ከጥላቻ ፖለቲካዊ አባዜ ወጥቶ መልካም ጉርብትና በሚጠናከርበት ሁኔታ ህግን ማዕከል ባደረገ አሰራርና አመራር በጋራ ችግሮች ላይ መወያየት የሁሉም ህዝቦች ፍላጎት ነው ። የወልቃይት ሆነ የራያ ሰው ሰራሽ ችግሮች በሁለቱም ህዝቦች ሙሉ ተሳትፎ እንዲሁም ህግና ሰርአት መሰረት ባደረገ መፍትሔ እንዲመጣ የሁለቱም ህዝቦች ፍላጎት ነው ። የትግራይ ህዝቦች ሆነ የአማራ ህዝብ በጥርጣሬ መኖርና ጥላቻ ለመጪው ትውልድ ማውረስ ፈፅሞ ፍላጎት የለውም ። በመሆኑም በሁለቱም ህዝቦች ቀጣይነት ያለው ማህበራዊ ትስስር ለማስፈን ከአማራ ክልል በሐይል የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆች ወደ ነበሩት የቀድሞ ቦታቸው እንዲመለሱ የዶክተር አምባቸው መኮነን አመራር እንዲያስብበት እሻለሁ ። ቤት ንብረታቸው የወደመባቸው የትግራይ ተወላጆች ያፈሩት ንብረት ዋጋ ግምትና የሞራል ካሳ እንዲሰጣቸው ለማሳሰብ እፈልጋለሁ ። በትግራይ ተወላጆች ላይ የህግ አልበኝነት ተግባር የፈፀሙ በግልጽ ችሎት በህግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ የአዲሱ ዶክተር አምባቸው መኮነን አሰተዳደር ሳሳሰብ ተፈፃሚነት እንደሚኖረው በመተማመን ይሆናል ።

         በመጨረሻም የሁለቱ ክልል አመራሮች ከአንጀት ይሁን ከአንገት ከዚህ ቀደም የጀመሩት የመነጋገርና የመወያያ እቅዶች ከጥላቻ በፅዳት መንገድ ለጋራ ብልጽግና በመሠረታዊ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የጋራ በሳል ውይይቶች ማካሄድ ይኖርባቸዋል ። ከግጭትና ጦርነት የሚገኝ ትርፍ አካላዊ እንዲሁም ቁሳዊ ውድመት ከመሆኑም በላይ ማህበራዊ ጥላቻ በህዝቦች እንዲያገነግን ምክንያት ይሆናል ። የትግራይ ህዝብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ መጠቃቀምና መግባባት ላይ ያተኮረ ማህበራዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲኖረው የፀና እምነት አለው ። ይህም ለማሳካት የዘውትር አገራዊ ግንባታ ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል ።

      

 

 

     

Back to Front Page