Back to Front Page


Share This Article!
Share
ከአባብያና ከልዑል ጋር የምስማማበትና የምለያይበት

ከአባብያና ከልዑል ጋር የምስማማበትና የምለያይበት

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 2-2-19

ባለፈው ሰሞን በጊዜ ብዙም ሳይራራቁ በአይጋ ፎራም የቀረቡ ሁለት ፅሁፎች ላይ የግል አስተያየቴን ለመስጠት ነው። የሚድያው ብዛት፣ በመልእክቱ መጨናነቅ፣ የሰፈር ለሰፈር ፋይዳ ቢስ የቡና ወሬ፣ በየስራ ቦታው ያለ የስራ ፈቶች ፍረጃና ማግለል፣ የጥቂት አፍራሾች ድምፅ ከሚገባው በላይ እየገነነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ትግራይ ክፉ ክፉውን እንጂ በጎ በጎውን እንዳይሰማና እንዳይረዳ አፍኖ ይዞታል። ለዚህም ነው እኔና እኔን የመሰሉ ፀሃፊዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አካሉ ከሆነው ከሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር፣ በሸረኞች ውስብስብ ሴራ ተታሎ፣ በቀላሉ ወደ ኋላ ሊመለስ የማይችል የጥላቻ ስሜት ውስጥ እንዳይገባ ሃቁን ለማጋለጥ ስንፅፍ የነበርነው። 

Videos From Around The World

ለህዝብ ደህንነት ጠበቃ በመሆንና የፓለቲካ ድርጅት አፈቀላጤ በመሆን መካከል የማይዘለል ሰፊና ጥልቅ ገደል አለ። ለምሳሌ እኔ እንኳንና የህወሓት አባል መሆን ቀርቶ ደጋፊም አይደለሁም። ይህ ማለት ግን ወልዶ ስላሳደገኝ ህዝብ ደህንነት መሟገት የለብኝም ማለት አይደለም። ወልዶ ስላሳደገኝም ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ዛቻ ሆነ ጥቃት ሲደርስበትም አወግዛለሁ፣ እሟገታለሁ፣ እከላከላለሁ።

ኦቦ አባቢያይ በትግራይ ህዝብ ላይ ሴራ እየተጎነጎነ ነው የሚለውን አጣጥለው፣ ሴራ አለ እያልን የምንፅፈውን ደግሞ እባብን አይተው ልጥ እንዳስፈራቸው ህፃናት ቆጥረውናል የሚል ስሜት አድሮብኛል። በርግጥ ጭንቀታችንን እንደሚረዱ ለመግለፅ ለተጠቀሙባቸው መልካም ቃላት ምስጋናየን አቀርባለሁ። ትልቁ የሰው ልጅ ድክመት በሌላው ላይ የሚደርሰው ችግር እራሱ ላይ እንደደረሰ ሆኖ እንዲሰማው የሚረዱ የስሜት ህዋሳትን አምላክ ስላልፈጠረ ነው። ስለዚህ ያፈነገጠ የጫማ ሚስማር ምን ያህል እንደሚያም የሚያውቀው ለባሹ ብቻ ሆነ። ብዙዎቻችን ለእለት ኑሯችን የሚበቃ ሰአት ያጥረናል። ልጥ አይተን 10 ገፅ የምንፅፍ ከሆነ እግዜር አንዱን ቀን 48 ሰአት አድርጎልናል ማለት ነው።

ወዳጄ ኦቦ አባቢያ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በፊት ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የመጣበት ችግር ባይኖር ኖሮ የሁላችንም ስጋት ግምት ላይ የተመሠረተ ይሆን ነበር። ይህም ማለት እርስዎም ልክ ሊሆኑ፣ እኛም ልክ ልንሆን እንችል ነበር። እርሶም አሳምረው እንደሚያውቁት ህዝቡ በ1936 ሰኞ ገበያ ላይ በአውሮፕላን ቦምብ ተጨፍጭፏል፤ በራስ አበበ አረጋይና ተባባሪዎቻቸው ጦር አባላት በህዝቡ ላይ የደረሰው እንግልት እናቶቻችን ነግረውናል፣ በደርግ ጊዜም ይህ ሁለ በከፋ ሁኔታ ተፈፅሟል። እባቡን አይተናል። የአሁኑ ስድብና ቀረርቶ፣ መንገድ እየዘጉ ህዝብን በረሃብ ለመፍጀት የሚደረግ የማያባራና ዳኛ የጠፋበት ሙከራ፣ አገራችን ነው ብለው ከሚኖሩበት በማንነታቸው ብቻ የሚባረሩበት ዳኛ ያጣ የአገርና ህገመንግስት ክህደት፣ በየስራ ቦታችን እየገጠመን ያለው መገለልና የተንኮል ድርጊት እንደ ልጥ እንድናየውና በፍርሃታችን ስቀን እንድንተወው ነው ምክሮን የለገሱን? ተረጋጉ ብሎ መምከር ጥሩ ነው። ሆኖም ግን የማያረጋጋ ነገር እያለ ተረጋጉ ማለት ተዘናጉ ከማለት የተለየ ትርጉም የለውም።

እየሆነ ያለው እባብ እንጂ ልጥ አይደለም የሚለውን ስጋት የሚያጠናክር ከታሪክ የተገኘ የራስ ልምድ ከላይ ተገልጿል። በየሰላማዊ ሰልፉ፣ በየፌስ ቡኩ፣ በየክልልና አገር መሪው አፍ፣ በየመንገዱና በየስራ ቦታው  በሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚነገረው ሁሉ ኮሜዲ ከሆነ ሁላችንም አብረን እንስቃለን። ምን ችግር አለው? ድሮ በጉራጌዎች ላይ ሲተረብ በነበረበት ዘመን እኮ ጉራጌዎች አብረው ይስቁ ነበር፤ ትረባው በህዝባቸው ላይ የጦርነት ነጋሪት ድምፅ አለመሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ። በሙሴ ዘመን  ታላቁ ፈርኦን የስጋ ልጅ የነበረው ራምሲስ የፈርኦኑ ተወዳጅና የጉዲፈቻ ልጅ የነበረውን ሙሴን ሲከታተል ቆይቶ አይሁድ ባሮችን ከግብፅ የሚያስወጣው መሪ ሙሴ ራሱ መሆኑን ደረሰበት። ይህንን ዜና ራምሲስ ለፈርኦኑ ሲነግረው ፈርኦኑ የመለሰለት እንዲህ ብሎ ነበር፦ "የምትነግረኝ ነገር ተረት ከሆነ በጠርሙስ ሞልተህ፣ እውነት ከሆነ በሰንሰለት አስረህ አምጣልኝ"። ፈርኦኑ ሙሴን ከልቡ ይወደው ስለነበር ተረት ሆኖ በጠርሙስ ቢመጣለት ተመኘ። ይህ ግን አልሆነም ሙሴ በሰንሰለት ታስሮ ከፊቱ ቀረበ። እንደፈርኦኑ ሁላችንም የምንመኘው የወረራ ስጋቱ በጠርሙስ እንዲቀርብልን ነው። ሃቁ ምን እንደሚሆን ግን ኦቦ አባቢያ ከኛ የበለጠ እርግጠኛ መሆን አይችሉም። በሱ ላይ አስተያየት መስጠት ባልፈልግም ፅሁፍዎ በስፋት ወገናዊነትን የሚያንፀባርቅ መሆኑ እርሶም አይክዱትም። እኔና እኔን መሰሎች የህወሓት አመራርና አባላትን መልካም አልስሩም ብለን ባመንበት ላይ ያለ ርህራሄ እያወገዝን ፅፈናል። እኛ ላልበላው ዳዋ እንጂ ለበላው አይጥ አልቆምንም፤ ያሳደገን ባህል ስለማይፈቅድልን። እርሶ ግን ገና ከእንቅብ ቃላት በስተቀር እፍኝ ተግባር ያላየንበትን ሲያሞጋግሱ ብዙ ቃላት ተጠቅመዋል። "ምኒሊክን ለማወደስ የትግሬ ህዝብ መሰደብ የለበትም" አሉ ገ/ህይወት ባይከዳኝ።

ቃላት ከጦር የበለጠ የሾሉ መሆናቸው የሚያስረግጥ የአበው ተረት አለ፦ "ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው"። አንድ ጦር ተወርውሮ የሚገድለው አንድን ሰው ነው፤ አንድ ጥይትም እንዲሁ። ስድብና ዛቻ ግን በአንድ ጊዜ የሚልዮኖች ቅስም ይሰብራል። ይህ ደግሞ ከሞት አያንስም። ወሬ በኖ ይቀራል የሚባለው የአዘናጊዎች ስልት ወይንም የየዋሆች ተረት ተረት ነው።  የ6 ሚልዮን አይሁዶች ፍጅትና የ50 ሚልዮን ህዝብ ሞት ካስከተለው ሁለተኛው የአለም ጦርነት ዋዜማ ጀርመኖችን ወደ እብድነት የቀየሩ ቃላት ነበሩ።  የአንድ ሚልዮን ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች እርድን ቀድመው የመጡት አክራሪ ቱትሲዎችን ወደ አውሬነት የመቀየር አቅም የነበራቸው ቃላት ናቸው። የማያሻማ ዛቻ እየተሰማ በተግባርም በህዝብ ላይ መንገድና ኬላ እየተዘጋ መሪዎችም ዝም፣ ጠቅላይ አቃቤ ህጉም ዝም፣ ፓሊሱም ዝም ካለ የትኛው ህዝብ ነው በወረቀት ላይ ያለው ህገመንግስት እጅና እግር አውጥቶ ይጠብቀኛል ብሎ ተስፋ በማድረግ የሚረጋጋውና እኛም ወደ ሌላ ስራችን የምናተኩረው?

ይህ ሁሉ ስጋት የተፈጠረውና ተቆጣጣሪ ያጣው የብሄር ፓለቲካ አገሪቱን በታጋችነት ሰንጎ ስለያዛት ነው። የብሄር ፓለቲካ ጠቃሚና ጎጂ ገፅታዎች እንዳሉት ቀደም ብሎ በዓይጋ ፎራም ላይ የወጣው ፅሁፌ ላይ አብራርቻለሁ። በብሄር መመዘኛ ክልሎች ሲሸነሸኑ ነበረ ብየ የማስበው እምነት ክልሎች የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዲወስኑ የሚፈቅደው የብሄረተኝነት በጎ ጎኑ በተግባር ሲተረጎም ነበር። በጊዜ ሂደት ግን ይህ የራስን እድል በራስ መወሰን ከፌደራል መንግስት ተሸርፈው የሚሰጡና ባካባቢው አቅም፣ ችሎታና ባህል ቢሰሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ለታመነባቸው ጉዳዮች ብቻ መሆኑ ተዘንግቶ ክልሎቹ ራሳቸውን የቻሉ ሉአላዊ መንግስታት ሆኑና ፌደራል መንግስትን እንደ ተባበሩት መንግስታት ወይንም እንደ አፍሪቃ ህብረት ሳይቆጥሩት አልቀሩም። ነገሩን ያወሳሰበውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ያሉት በፌደራል መንግስቱ ውስጥ የሚሰሩ ግለሰቦች በየብሄር ፓርቲያቸው የኮታ ውክልና የተመለመሉ ስለሆኑ አባል በሆኑባቸው የብሄር ፓርቲዎቻቸው አመራሮች ከሆኑት የክልል ፕሬዚደንቶችና ሌሎች ባለስልጣናት ፈቃድ ሳያገኙ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሠሩት አገርን የማዳን ስራ አለ ብየ አላምንም። አገሪቱ ከፌዴሬሽንነት ወደ ኮንፌደሬሽንነት የተቀየረች ትመስላለች። የክልል መሪዎች ሲጀመር የሚያጣላቸው ነገርም የለም፤ ካለም ለፌደራል ስልጣን አካላት በማመልከት የሚፈታ እንጂ ፌደራል መንግስትን ወደ ጎን ትተው የሚቆራቆሱበት ህጋዊ መነሻ  የላቸውም። የሚታየው እውነታ ግን እንደዘመነ መሳፍንት ለፌደራል ህግ አልገዛ ያሉት የክልሎች መሪዎችን ለማስታረቅ አዛውንትና የሃይማኖት መሪዎች በየክልሉ መንከራተታቸው ነው። ይህ ክስተት በየራሳቸው ህግ የነበሩት  ፊታውራሪ መሸሻንና ፊታውራሪ አሰግድን "እግዚኦ"ብሎ ለማስታረቅ ከመንበሩ የተነሳው የዲማ ጊዮርጊስን ታቦት የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ ያስታውሰኛል።

ልኡል ገብረመድህን (አቶ ልበል?) በዚች አገር የታለመለትን መስመር በሳተው የብሄር ፓለቲካ የተነሳ አገሪቱ ለመበታተን አደጋ ሊዳርግ በሚችለው አገር አቀፍ ስርአት አልበኝነት የተበሳጩ መሆንዎ ግልፅ ነው። መበታተንን ሸጦ ገንዘብ የሚያገኝ አገር ከሃዲ ባንዳ ካልሆነ በስተቀር ማን ያልተበሳጨ አለ ብለው ነው ልኡል ወንድሜ? ብዙ ሰው እንደሚያደርገው ብስጭትዎን አምቀው ሳይዙ አደባባይ በማውጣትዎ አክብሮቴ የላቀ ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ አንድ ተረት አለ። ይህን ተረት ነፍሳቸውን ይማር አቶ መለስ ዜናዊ ፓርላማ ላይ እንስተውት ነበር። ሁለት ጓደኞች ሲጓዙ ውለው ሲመሽባቸው ድንኳን ተክለው መንገድ ላይ ያድራሉ። ድንኳንዋ ከማጠርዋ የተነሳ የሁለቱም እግሮች ወደ ውጭ ወጥተው ነበረና ጅብ መጥቶ የአንደኛውን እግር መቆርጠም ይጀምራል። የሚቆረጠመው ሰው ጓደኛ በድንጋጤ ከእንቅልፉ የነቃው በጓደኛው የስቃይ ጩኸት ሳይሆን በቁርጠማው ድምፅ ነበር። ምንድነው የምሰማው ድምፅ ሲባል ተቆርጣሚው "ዝም በል እንዳይሰማን፣ የኔን እግር እየበላ ነው" ብሎ መለሰ አሉ። አገር ስትጠፋ የሚጎዳው ሁሉም ነው። አገሪቱ በጥፋት ጎዳና ላይ እየሄደች እያየ ህዝቡ ከሃገር መጥፋት የባሰ ነገር ያለ ይመስል "የባሰ አታምጣብን" እያለ የዛሬ የዛሬን ብቻ ይኖራል። የሃገር ጉዳይ የሚመለከተው ጥቂት ምሁራንን ብቻ ይመስል ህዝቡ ጥቂቶች የሚፅፉትንና በሚድያ የሚናገሩትን ብቻ በማንበብና በማዳመጥ ብቻ ተወስኗል። ዩጎዝላቪያ ስድስት ትንንሽ የሆነችው እንዲህ እንደዋዛ "ጅቡ እንዳይሰማ" እየተባለ ነበር። የክሮሽያ ተወላጅ ሆኖ ግን አገራዊ እንጂ የብሄር ስሜት ያልነበረው ማርሻል ብሮዝ ቲቶ የሪፓብሊኮቹ ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በተጠናከረ የፌደራል መንግስት አስተዳደር ታላቅ አገር አድርጎ ሲያስተዳድር ቆይቶ አለፈ። የቲቶ አስተዳደር ግን በግለሰብእናው ግርማ ሞገስ እንጂ ዘላቂ ስልትና ስርአት ስላልፈጠረለት ከሱ ህልፈት በኋላ ፕሬዚደንትነት የክልል (ሪፓብሊኮች) በዙር የሚሰየሙበት ሆነና በድርድር የሚሰሩ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ተፈጠሩ። ነፃነት እያወጁ ለመገነጣጠል የቀለላቸውም እንደ ካርኒ መቁረጫ በስፒል የተበሱ ነጠብጣብ ድንበሮች ዝግጁ ስለነበሩ ነው። ዋና ከተማዋ ዙሪያ ያለችው የሰርቦች ክልልም ዮጎዝላቪያ አትፈርስም በሚል ከንቱ ወኔ ጄኔራሎቿ ብዙ ግፍ ሰርተው የአለም ፍርድ ቤቱን በስራ ከመወጠር በስተቀር አገሪቱን ማዳን አልቻሉም። "ቀድሞ ነበረ እንጂ መጥኖ መደቆስ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ" ይላል ያገራችን ሰው።

ድስት ጥዶ ከማልቀስ የሚገላግለን አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ስንወስድ ብቻ እንደሆነ ልኡል ገብረመድህን በአፅንኦት አሳስበዋል። ፓም ወይንም አፕል በጥንቃቄ ከተያዘ ጤናማ ምግብ ነው፤ ከተበላሸ ግን ከመጣል በስተቀር ምንም አማራጭ የለም። ሆድ ውስጥ ገብቶ መርዝ በመሆን ሞትን ያስከትላል። የብሄር ፓለቲካም እንደዛው ነው። ለህዝቦች ነፃነትን ያጎናፅፋል የተባለለት የብሄር ፓለቲካ የጋራ አገራዊ ራእይ በሌላቸው ጠባቦች ተጠልፎ አገሪቱን በማመስ ወደ ገደል አፋፍ የሚመራት ከሆነ ህዝብ መምረጥ ያለበት ወይ ሃገሩን ወይ ብሄሩን ነው፤ እንደተመኘው ሁለቱንም አንድ ላይ በጤንነት ሊያገኛቸው ስላልቻለ። ልኡል ገብረመድህን የጠየቁት እርምጃ የብሄር ፓለቲካ በአዋጅ እንዲታገድ የሚል ነው። ይህ እርምጃ እሳቸው እንዳሰቡት ቀላል ቢሆን ኖሮ የሚበቃው አንድ ማርሽ ብቻ ነበር። አንድ ቀን ምሽት በኢቲቪ ዜና ሰአት ከ"ኢፌዲሪ መንግስት የወጣ አዋጅ" ፤ "ከዛሬ ጀምሮ የብሄር ፓርቲዎች ታግደዋል፤ የብሄር ፓለቲካ ሲያካሂድ የተገኘ ምንም ሰው በህግ ይጠየቃል" ቢባል አዋጁን ያወጀው ክርስቶስ ራሱ ወርዶ በቴሌቪዥን ስቱድዮ ውስጥ በሃይለ ስልጣኑ ገብቶ ነው ብየ እደመድማለሁ እንጂ ሌላ ምድራዊ ሃሳብ በጭንቅላቴ ዝር አይልም። በኢንግሊዝኛ ቋንቋ ተረትና ምሳሌ የሆነ አንድ የአይጦችና ድመቶች ታሪክ አለ። ድመት ድንገት እየደረሰ ያስቸገራቸው አይጦች ጉባኤ ተቀምጠው ሲመክሩ አንዱ አይጥ ብድግ ብሎ አስደናቂ መፍትሄ አቀረበ። ወንድሜ ልኡል ምሳሌየን እንደስድብ እንዳይቆጥሩት አደራ እላለሁ። የቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ድመቱ አንገት ላይ ቃጭል እንዲታሰር ነው። በሃሳቡ ሁሉም በአድናቆት ተስማሙና ጭፈራ ተጀመረ። ከንቱ ጭፈራውን ታግሰው ማሳለፍ ያልፈለጉት አዛውንት አይጥ "ሃሳቡ ምርጥ ነው፤ ግን ማነው ድመቱ አንገት ላይ ቃጭል የሚያስረው?" ብለው ሲጠይቁ ጉባኤው ድምፅ አልባ ሆነ፤ ኮሽታም አልተሰማ!

አዋጁን ያለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አይቀርብም። ከመነሻውም ቢሆን በብሄር ፓለቲካ የተዋቀረው ኢህአዲግ ራሱን በራሱ የሚያጠፋበትን አዋጅ አያፀድቅም። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን ለማስፈን የፍቅርና የመደመር ፍልስፍና በማስፋፋት ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩና "ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው" የሚሉት ኦቦ ለማ መገርሳ ይህን አዋጅ በድፍረት ለማወጅ ያመነታሉ ብየ አላስብም። ሆኖም ግን የሌሎች ብሄር ፓርቲዎች ፈቃደኝነት ለጊዜው ወደ ጎን ትተን እነዚህ ወሳኝ ባለስልጣናት ጠበቅ ያለ የብሄር ፓለቲካ የሚያራምደው እናት ፓርቲያቸው ኦህዴድ/ኦዴፓ ረዥም ገመድ ወገባቸው ላይ ስላሰረባቸው የብሄርን ፓለቲካ ለማገድ አዋጅ እስከማውጣት የሚደርስ ርቀት እንደማይሄዱ እሙን ነው። በየክልሉ ያለ ህዝብም እንደጎርፍ እያሳሰቀ በሚወስደው የብሄር ፓለቲካ እየተዝናና ያለ ይመስላል። እጅግ የሚያሳስበውና የሚያስፈራው የኢትዮጵያ አድራሻ የት ነው ብለው ሲጠይቁ መልሱ "እንጃ" መሆኑ ነው። አገር አለ የሚባለው በተባበሩት መንግስታት ወንበር ስለተሰጠው አይደለም። አገር በሰዎች ፓስፓርት ላይ መፃፉ አይደለም ህልውናው የሚረጋገጠው፤ በስሙ የሚጠራ ቤተ መንግስት፣ ምክር ቤት፣ የውጭ ኤምባሲ፣ ወዘተ ስላለው አይደለም አገር አለ የሚባለው። አገር የሚኖረው ካርታ ላይ ስለተቀመጠ ሳይሆን ወይንም በየሚድያው ስለተሞካሸና ስለተዘፈነለት ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ነኝ በሚለው ሰው ልብ ውስጥ በክብርና በፍቅር ተቀምጦ ሲገኝ ነው። "አገር ማለት ሰው ነው" ተብሏል። አገሬ የሚል ከሌለ አገር ሊኖር አይችልም። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያ የታወቀ አድራሻ አላት የምትባለው። ሰው ሁሉ ብሄራዊ ማንነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ይቀድማል እያለ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ስኳርት ጎማ ካስቀመጠ እየተነፋ እንጂ እየተነፈሰ የማይሄደው ብሄርተኝነት ስኳርት ጎማውን ተፈላጊነት ሳይኖረው ሊያስቀረው ይችላል።  በኢትዮጵያ ውስጥ ሳይታወቀን የብሄርተኝነት ነገር በያንዳንዷ የህይወታችን ቀዳዳ ውስጥ ተመስጓል። ይህን ያህል ከፓለቲካው፣ ከኢኮኖሚው፣ ከማህበራዊ ህይወት ጋር ጠብቆ የተገመደው አስተሳሰብ በአንድ የአዋጅ ምት አፈርሳለሁ ብሎ ማለም አደገኛ ሃሳብ ነው። ተቀምጠው የሰቀሉት ነገር ቆሞ ለማውረድ ስለሚያዳግትና ለማውረድ ተብሎ መልሶ መቀመጥም የባሰ ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ እንግዲህ በመቆምና በመቀመጥ መሃል በመሆን የረቀቀ ሚዛን ጠብቆ መስራት አስፈላጊ ነው።

የብሄር ፓለቲካን ለማዳከም በደካማ ጎኑ መጀመር ይቻላል። ከነዚህ ደካማ ጎኖቹ አንዱ የብሄር ልዩነትን ተፈጥሯዊ ክስተት አድርጎ ማመኑ ነው። እንኳን የብሄር የአገር ማንነትም ተፈጥሯዊ አይደለም። የዘር ሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት ከሆነ የሰው ፍጡር ሁሉ 99.5 ከመቶ ዘረመሉ (ዲ.ኤን.ኤ) አንድ አይነት ነው። ቀሪው 0.5 በመቶው የፀጉር፣ የአይን፣ የከንፈር፣ የቆዳ ቀለም፣ ወዘተ ልዩነቶችን የሚፈጥሩት ናቸው። ሄዶ ሄዶ የሚደረሰው ከአዳም ወይንም ከሉሲ ነው፣ እንደየ እምነታችን። ሌላው ደካማ ጎኑ "ከእኩሎችም የበለጡ እኩሎች" አሉ የሚለው አባባል የውስጠ-ብሄር የማበላለጥ አስተሳሰብ ነው። የዚህ ዞን ህዝብ ንፁህ ትግሬ፣ ንፁህ ኦሮሞ፣ ንፁህ አማራ ሲባል ሌላውን ያልፀዳ፣ የተቀየጠ፣ ቋንቋው ግርድፍና በትክክል የማይሰማ እየተባለ ጥቂት አካባቢዎች ተጠቃሚ ሌላው የበይ ተመልካችና ክብሩ የተነካ ሁለተኛ ሥስተኛ ደረጃ የብሄር ተወላጅ ሁኖ ይታያል። ይህ የብሄር ስብስቡን አንድነት በገዛ እጁ የሚያላላው ስለሚሆን በተገፉት ላይ የኢትዮጵያዊነትን ስሜት በማስረፅ በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ መርዳት ይቻላል። እንዲህ አይነቱ ችግር ላይ አገራዊ ስሜት የማስረፁ ጥረት ቶሎ ካልደረሰ ከብሄሩ ወዳነሱ ክፍልፋዮች የመውረድ እድል አለው። በተወሰነ ወረዳ ወይንም ዞን የሚነዳው ክልላዊነት ብሶት የወለደው ዞናዊነትና ወረዳዊነት ለአገር ህልውና የበለጠ አደገኛ ነው። ስለዚህ ወደታች ሳይዘቅጥ ወደ አገራዊ ከፍታ ማንሳት ያስፈልጋል። ሦስተኛ አድርጌ የምወስደው ድክመት የብሄር ፓለቲካ ህይወቱን የሚመሰርተው በ"ራስ መቻል" ኢኮኖሚ ነው። የብሄር ክልል በሁሉም የምርት አይነቶች ራሱን ከቻለ ከሌላ ክልል ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርግበት ምክንያት አይኖርም። ስለዚህ ህዝቡ በብሄራዊ ገበያ ላይ ከሌላ ክልል ህዝብ ጋር በነፃ ተቀላቅሎ የሚገበያይበት እድል አይኖረውም። በሰው ሃብት ረገድም ክልል ሁሉ የየራሱ ብሄር ባለሞያ ከተሟላለት ከሌላ ስለማይፈልግ ባለሞያዎችም፣ የወደፊት አገር መሪ ወጣቶችም አይቀላቀሉም፣ አይተዋወቁም። መነጠል የብሄርን ልዩነት እያገነነ የባዳነት ስሜትን ያጎለምሳል። አገር የሚባለው የብሄሮች ደካማ ቅይጥ እንጂ የተጠናከረ ውህድ አይሆንም። ይህም ዞሮ ዞሮ ክልሎችን ክፉኛ ያዳክማቸዋል፤ ከመደጋገፍ ጥንካሬ ይገኝ ስለነበር። ለዚህ መፍትሄ ይሆናል የምለው አገራዊ በምርት ስፔሻላይዜሽን ላይ የተመሰረተ ክልላዊ ወይንም ዞናዊ የስራ ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ ነው። "ኮምፓራቲቭ አድቫቴጅ" በሚለው መርህ መስረት ክልሎች ሆኑ ዞኖች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ነገር ማምረት ሳይሆን በአነስተኛ ወጪ ማምረት በሚችሉት ላይ አተኩረው ቢሰሩና ክልል ለክልል ዞን ለዞን የሸቀጦች ልውውጥ ለመኖር የግድ መደረግ ያለበት እንዲሆን። ይህ ህዝብን ያቀላቅላል የጋራ እሴቶችን በማብዛት በፈቃዱ ውህደቱን የሚያጠናክርበት ዘዴ ይሆናል። አንዱ በሌው ክልል ላይ የተመሠረተ ህይወት ካለው እርስ በርሱ የማይፋቀርበት ምክንያት የለውም። ፌደራል መንግስትም ክልሎችን በአዲስ አበባ በኩል የሚያገናኝ መንገድ ሳይሆን   ለሸቀጦችና ስፔሻላይዝድ አገልግሎቶች ፈጣን ልውውጥ ክልሎችን በቀጥታ የሚያገናኙ አሳላጭ አውራ ጎዳናዎችና ባቡር ሃዲዶችን መገንባት ይኖርበታል። በኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ረገድም ሁሉም አይነት ኢንቨስትመንት በሁሉም ክልል መፍቀድ ጠቃሚ አይደለም። ለክልላዊና ዞናዊ ስፔሻላይዜሽን በሚመች መልኩ መሠራት አለበት። በርግጥ ይህንን ስንተገብር የክልሎች ገቢም ሚዛኑ እንዳይበላሽ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ዮኒቨርሲቲዎችም ሁሉም የትምህርት አይነት ከሚሰጡ እነሱም ስፔሻላይዝ ቢያደርጉ ወጪ ከመቆጠቡም በላይ የወደፊት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚቀላቀሉበትና የሚተዋወቁበት እድል ይፈጥራል።

ሌላው ብሄረተኝነትን በማኮሰስ የብሄር ፓለቲካን የሚያዳክመው አገርን ማወቅ ነው። "የማያውቁት አገር አይናፍቅም" እኮ ይባላል። የአሁኑ ትውልድ ክልሉን ቢያውቅ እንጂ ቀሪው ኢትዮጵያ ምን እንደሆነ የሚያውቀው ነገር የለም። ይህ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። "ሶሻል ሳይንስን ማንም ይሰራዋል፤ የኢትዮጵያ ልጆች የሚያስፈልጋቸው የተፈጥሮ ሳይንስና ምህንድስና ነው የሚል አስተሳሰብ ገነነና 70 ከመቶው ተማሪ ማህበራዊ ህይወት ምን እንደሆነ የማይገባው በቴክኒክ እውቀት ብቻ የተሞላ ሮቦት ሆነ። ይህ አስተሳሰብ ከባድ ጉዳት ያስከተለው የኢትዮጵያን ጂኦግራፊ ትምህርትን ከከፍተኛ ትምህርት ኮርስነት በመወገዱ ነበር። እንደየመንግስታቱ ስሜት ሲቀያየር የብሄር ብሄረሰቦች ስሜትን ሲያበላሽ የኖረው የኢትዮጵያ ታሪክን እንኳ ለመመለስ ትግል ሲደረግ በማንም መንግስት አቋም ሆነ ስሜት ሊቀያየር የማይችለው የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ ግን ችላ እንደተባለ ነው። የተለያዮ ክልሎች ስነምድር፣ የአየር ሁኔታ፣ አፈሩ፣ እፅፕዋቱን፣ የውሃ አካላቱን፣ ዱር አራዊቱን ማሳወቅ በተማሪዎቹ አይምሮ ውስጥ አድናቆትንና ሄዶ የማየትን ጉጉት በመጨመር የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከመጨመር በስተቀር ምን ጉዳት አለው? መሃንዲሱ ኦሮሞ ስለ ዳሎል በቂ እውቀት ቢያገኝ ሄዶ በአይኑ ለማየት ይጓጓል። ከሄደም ከአፋሮች ጋር ይገናኛል። ከተገናኘም ደግነታቸው ማርኮት መንገድ ሊሰራላቸው ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። እነሱም ወደውት ልጃቸውን ሊድሩለት ይችላሉ። እንዲህ እያለ ነው ህዝብ የሚዋሃደው።

የብሄር ፓለቲካን አዳክሞ አገራዊ ፓለቲካን ለማጎልመስ ወሳኙ ህዝብ ቢሆንም የአመራር የማስተባበርና ማቀነባበር ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የብሄር ፓርቲዎች በአገር ሃላፊነት ስሜት በፍላጎት እየተቀላቀሉ አገራዊ ፓርቲዎች ቢፈጥሩ ጠቃሚ ነው። ለብሄሮች መብት ተቆርቋሪ የሚሆነው የዛ ብሄር ተወላጅ ብቻ ሳይሆን የሌላው ብሄር ተወላጅም በእኩል ደረጃ ዋስ ጠበቃ የሚሆንበት ቱባ የባህል እሴት ማዳበር ያስፈልግናል። እንዲህ አይነት ባህል ውስጥ አድገው አይደል ማይክል ጃክሰን ከነጓደኞቹ ጋር በመሆን "እኛ አለም ነን" ብለው ዘፍነው ባገኙት ገንዘብ ከድርቅ አደጋ የታደጉን። በአገራዊ ፓርቲነት ተሰባስቦ ውስጡ የተወሰነ ብሄር ጥቅም የሚያንፀባርቅ ከሆነ ግን የባሰ ችግር ያስከትላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህብረብሄር ፓርቲዎች የተውሰነ ብሄር ዝንባሌ እንዳላቸው ይነገራል። መኢአድና ብአዴን የተቅያየሩበት የፓለቲካ ድራማ ብዙ ያልፀዳ ነገር እንዳለን ያመለክታል። የአማራ ብሄር ፓርቲ ከነበረው መአህድ አባላቱን እንደያዘ አገራዊ ፓርቲ ሲሆን አገራዊ ፓርቲ የነበረው ኢህዴን ህብረ ብሄር አባላቱን በከፊል እንደያዘ ወደ ብሄር ፓርቲ ተቀየረ። ኖሮ ኖሮ በሌላ ብሄር አባላት ንፁህ አማራነቱ የቆሽሸ መስሎ ሲስማው "በካዮቹን" አንድ በአንድ እየለቀመና እያዋረደ አራገፋቸው። ለጠንካራ ኢትዮጵያዊነት የሚያስፈልገን አደረጃጀት በግል፣ ቡድንና ፓርቲ ፍቅር ሳይሆን ያልተከፈለ ንፁህ የአገር ፍቅር ነው።

 

Back to Front Page