Back to Front Page


Share This Article!
Share
እነበረከት እንደ “እድለ ቢሶቹ” ልጆች (Like the “Unfortunate Kids”)

እነበረከት እንደ “እድለ ቢሶቹ” ልጆች (Like the “Unfortunate Kids”)

                                                                                                    ምስክር አለነ (29.01.2019)

ሰሞኑን አንድ የእንግሊዝኛ ተከታታይ ፊልም እየተከታተልን ነው። የዚህ ፊልም ርዕስ” The Series of Unfortunate Events” የሚል ነው። እዚህ ላይ ይህን ፊልም ያነሳሁት ስለሱ ትንታኔ ውስጥ ልገባ አይደለም፤ እንዲያው ነገሮች ቢመሳሰሉብኝ እንጅ። ነገሩ እንዲህ ነው። ፊልሙ ውስጥ ቤተሰቦቻቸው በሞት የተለዩአቸው ሶስት ልጆች አሉ። እነዚህ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው በውርስ ያገኙት የትየለሌ ሃብት ባደራ ተቀምጧል። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ይህን የልጆች ሃብት ሰይጣናዊ በሆነ መንገድ የራሱ ለማድረግ የማይፈነቅለው ደንጋይ የሌለው የሩቅ ዘመድ (ከዚህ በኋላ ዘመድ እየተባለ የሚገለፅ ሰው) አላቸው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የልጆቹ አሳዳጊ ሆኖ እንዲሰራ ጥረት አድርጎ ተሳክቶለት ነበር። ይህ ዘመድ ተብየ የልጆቹን የውርስ ገንዘብ መፈለግ ብቻ ሳይሆን የነሱን ጉልበት እንደ ሸንኮራ አገዳ መጥጦታል ማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ልጆቹ አሳዳጊ እስኪያገኙ ድረስ በሞግዚትነት የሚከታተላቸው ሰው አለ።

ልጆቹ የዘመዳቸውን ሰይጣናዊ ድርጊት ስለተገነዘቡ አሳዳጊያቸው እንዳይሆን ለሞግዚታቸው በማስረጃ አስደግፈው በማሳመናቸው ይህ ሞግዚት ሌላ አሳዳጊ እንዲመደብላቸው አድርጓል።  ጉዱ ያለው ግን ይህ ሌላ ሰው የተባለው አሳዳጊ ያው ዘመዳቸው መሆኑ ነው። ዘመድ ተብየው አሳዳጊ ሊሆን ይችል ዘንድ የተሳካለት ራሱን በሰው ሰራሽ ዘዴ ቀይሮ ሌላ ሰው ሆኖ በመቅረቡ ነበር።

Videos From Around The World

ታዲያ ይህ አሳዳጊ አላማው ልጆቹን ችግር ውስጥ አስገብቶ ሃብታቸውን የራሱ ማድረግ ነበርና ራሱ ያስገደለውን አንድ ምስኪን ሰው  እውነተኛው ዘመዳቸው (ራሱ ማለት ነው) እንደሆነ በማስመሰል ልጆቹ እንደገደሉት አድርጎ የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ በማቅረብ ህዝቡን ለማሳመን ቻለ። ። በዚህ ምክንያት እድለ ቢሶቹ ልጆች በመሳደድ ላይ ይገኛሉ። እስኪ እንግዲህ ይህን ፊልም በዘርፍ በዘርፉ አድርገን ከነበረከት ጉዳይ ጋ እያነፃፀርን እንመልከተው።

እነበረከት ከእድለ ቢሶቹ ልጆች አንፃር:

እንደሚታወቀው እነበረከት ከልጅነት እስከእውቀት ከጓደኞቻቸው ጋ በመሆን ኢህዴንን (ብአዴንን) መስርተው አሁን ለደረሰበት ደርጃ ያበቁ ሰዎች ናቸው። በዚህ ሂደት ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውንና ጊዚያቸውን ለአማራ ህዝብ ሰውተዋል። ለዚህም አንዱ ማሳያ የጥረት ኮርፖሬት ከ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተነስቶ በቢሊዮን የሚቆጠር ካፒታል እንዲያፈራ ማድረጋቸው ነው። እዚህ ላይ ግልፅ መሆን ያለበት ፍሬ ነገር በጥረት ሃብት ጉዳይ ላይ በእነበረከትና በከሳሾች መካከል ያለው ልዩነት ካፒታሉ በቢልዮን የሚቆጠር መሆን አለመሆኑ ላይ ሳይሆን ስንት ቢሊዮን ስንት ቢሊዮን ደርሷል በሚል ጉድይ ላይ ነው።

አሁን ላይ ደግሞ ልክ እድለ ቢሶቹ ልጆች በዘመዳቸው የናጠጡ ሃብታሞች ተደርገው እንደሚወሰዱት ሁሉ እነረከትም በብአዴን (አዴፓ) አመራሮች ከፍተኛ የሃብት ምንጭ ተደርገው ነው እየተቆጠሩ ያሉት። እዚህ ላይ ስለሃብት ምንጭነት ሲወራ እየተነሳ ያለው ስለገንዘብና ንብረት አይደለም፤ የመራጮችን ድምፅ መግዛት ስለሚያስችል የፖለቲካ ትርፍ እንጅ። ይህም ማለት ለረጅም ዘመናት ብአዴን ውስጥም ሆነ ከውጭ እነበረከት አማራ አይደሉም እንዲያውም ፀረ አማራ ናቸው በሚል በጎጥ ጭቃ በተጨማለቀ ጅራፍ ሲገረፉ ቆይተዋል።  ይህ በነበረከት ላይ የተፈፀመና አሁንም እየተፈፀመ ያለ የጎጥ ጅራፍ ግርፋትም ሰፊ የጥላቻ ጠባሳ አሳርፎባቸዋል። ስለዚህ አሁን ላይ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች  እነበረከትን ፀረ አማራና ሙሰኞች ናቸው በሚል አሳልፈን ብንሰጣቸው  ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ትርፍ እናገኝባቸዋለን ወይም የምርጫ ካርድ እንገዛባቸዋለን የሚል ተስፋ የሰነቁ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች ከዘመድ ተብዬው አንፃር፡

እንደሚታወቀው የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች እነበረከትን ከማንም በላይ ላባቸውን አንጠፍጥፈው እንዲሰሩ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል እነበረከት በአፈር፣ ውሃና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በሰላምና ፀጥታ፣ እንዲሁም በሌሎች የልማት ስራወች በርካታ አስተዋፅዖ አብርክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በረከት ካንተ በተሻለ ሊሰራው የሚችል ሰው የለም እየተባለ አብዛኛውን የብአዴን ስራ ተሸክሞ የኖረና በጀግንነቱ የታወቀ ታጋይ እንደነበር አሁን ያሰሩት “ባለጊዜዎች” በደንብ ይገነዘቡታል። በረከት አሁን አነሱ እንደሚሉት ፀረ አማራና ሙሰኛ ከነበረ ከዛሬ አንድ አመት በፊት መልቀቂያ ጠይቆ ከድርጅቱ ሲወጣ ለምነውና ተለማምጠው ወደ ድርጅቱ እንዲመለስ አያደርጉትም ነበር። ባጠቃላይም የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች ልክ የእድለ ቢሶቹ ልጆች ዘመድ እንዳደረገው ሁሉ የነበረከትን ጉልበት ጋጥ አድርገው በልተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።  

አሁን ያለንበትን ወቅት ስናይ ደግሞ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች የህዝቡን በተለይም የወጣቱን ጥያቄዎች እየመለሱ ስላልሆነ ከተወሰኑ ወራት በፊት ተችሯቸው የነበረው ሞቅ ሞቅ ያለው ድጋፍ እየተቀዛቀዘ መጥቷል። በተለይ ወጣቱ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አንፃር የሚያነሳው ጥያቄ እየተመለሰለት ስላልሆነ ለአዴፓ አመርሮች ጀርባውን እየሰጣቸው  እንዳለ በግልፅ የሚታይ ሃቅ ነው። በዚያ ላይ አማራ ብሄራዊ ንቅናቄ -አብን (National Movement of Amhara-NMA) ብሎ ራሱን የሚጠራ አዲስ የፖሊቲካ ፓርቲ ተመስርቷል። ይህ ፓርቲ ፅንፈኝኛ የሆነ የብሄርትተኝነት ጥያቄ በማራመድና የአዴፓ አመራሮችን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ድክመቶች በመንቀስ በህዝቡ በተለይም በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አያገኝ እንዳለ እየታየ ነው። በነዚህ ምክንያቶች የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች በሚቀጥለው ምርጫ ስልጣናችንን እናጣ ይሆናል የሚል ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀዋል።  ስለዚህ ልክ የእድለ ቢሶቹ ዘመድ የልጆቹን የውርስ ሃብት የራሱ ለማድረግ ሰው ገድለዋል በሚል በህዝቡ እንዲሳደዱ እንዳደረገው ሁሉ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮችም ፀረ አማራ የሚሏቸውን እነበረከትን ሙሰኞች ናቸው የሚል የፈጠራ ክስ መስርተው እጅግ በጣም ርካሽ የሆነ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየጣሩ ነው። እውነት እንነጋገርና ኢህአዴግ ውስጥ ቀርቶ ብአዴንን ብቻ ወስደን በከፍተኛ አመራሩ ውስጥ ያሉ ሙሰኞች ይሰለፉ ቢባል በረከት ሲሆን ሲሆን ሰልፉን አይቀላቀልም፡ ካልሆነም ደግሞ አቶ ጌታቸው አረዳ እንዳለው የመጨረሻው ተሰላፊ ነበር የሚሆነው። በዚህ ላይ በቂም በቀል ተነሳስተው እነበረክትን መቀመቅ ለማውረድ የሚታትሩ የአዴፓ አመራሮች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች ብዙ ናቸው።  

የፌዴራል መንግስቱ ከእድለ ቢሶቹ ልጆች ሞግዚት አንፃር፡

በረከት ለረጅም አመታት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራር ሆኖ የሰራ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት የፌዴራል መንግስቱ ህግ በሚፈቅቅደው መሰረት ጥበቃ የማድረግ ግዴታ አለበት። ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ፌዴራል መንግስቱ አሁንም ህጉ በሚፈቅደው መሰረት የበረከትን ጥቅማ ጥቅሞች የማስከበር ሃላፊነት አለበት። ይሁንና ልክ የእድለ ቢሶቹ ልጆች ሞግዚት ልጆቹ ሰው ገድለዋል በሚል ስግብግቡ ዘመዳቸው የለጠፈባቸውን ውንጀላ አምኖ የራሳችሁ ጉዳይ እንዳላቸው ሁሉ ፌዴራል መንግስቱም በረከትን ሜዳ ላይ ጥሎታል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አንዱ ጉዳይ  እስካሁን ድረስ ስንትና ስንት የፈጠራ ዘመቻ ሲካሄድበትና ደብረማርቆስና ሌሎች አከባቢዎች በአካል ተገኝቶ ቢሆን ኖሮ በህይወት በመኖር መብቱ ላይ አደጋ ሊያደርሱ ይችሉ የነበሩ እጅግ በጣም ነውረኛ ድርጊቶች ሲፈፀሙ የኮነነ አንድም የፌዴራል መንግስት አካል የለም። ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ በቅርቡ የአማራ ክልላዊ መንግስት ፖሊሶች ጠለፋ በሚመስል መንገድ በረከትን ወደ ባህር ዳር ወስደው እስር ቤት ሲያስገቡት የሱ እስር ጉዳይ በፌዴራል መንግስት የተያዘ አይደለም የሚል መልስ ከመስጠት ውጭ ፌዴራል መንግስቱ ስለበረከት ደህንነት መጨነቁን የሚያሳይ አንድም ምልክት አልታየም።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ቁም ነገር የፌዴራል መንግስቱ በረከትን ሊያግዘው ያልፈለገበት ምክኒያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። አንደኛው ምክንያት በረከት በቆራጥንነትና በግልፅነት እንዲሁም  ለአገርና ለህዝብ ካለው ተቆርቋሪነት በመነሳት በመንግስት ላይ ሲያቀርብ የነበረው ትችት ሊሆን ይችላል። በሁለተኛ ደረጃም ቢሆን  የጅምላና ጎራን የደበላለቀ መደመር አይገባኝም የሚል አቋም በመያዙ ቅሬታ አልፈጠረም ብሎ መገመት የዋህነት ነው።

ፊልሙ ውስጥ ያለው ህዝብ ከአማራ ክልልል ህዝብ አንፃር፡

ፊልሙ ውስጥ ያለው ህዝብ በዘመድ ተብየውና አጋሮቹ መሰሪ ተንኮሎች በተቀነባበረ የፈጠራ ወሬ ተደናግሮ ልጆቹ ሰው ገዳይ እንደሆኑ አምኗል። በመሆኑም በየሄዱበት እያሳደዳቸው ይገኛል። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የአማራ ህዝብም ቢሆን በተለይ ደግሞ ወጣቱ በአዴፓ አመራሮችና የሰይጣን ስራ በተጠናወታቸው ኢሳትን በመሳሰሉ የብዙሃን መገናኛ ተቋማት ነን ባይ የውሸት ቋቶች ድጋፍ እንዲሁም በፌስቡክ ሰራዊቱ የፈጠራ ወሬ ግራ ተጋብቶ እነበረከትን በማሳደድ ላይ ይገኛል። በነገራችን ላይ ኢሳት በታቀደና በተደራጀ አኳኋን የበረከትን ስም እያጠፋ መሆኑን ለማሳየት ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ መጥቀስ በቂ ነው።

አንደኛው የኢሳት ነጭ ውሸት የሚጀምረው በብ/ጀኔራል መላኩ ሽፈራው የፈጠራ ወሬ አመንጭነትና   በሃብታሙ አያሌውና ምናላቸው ስማቸው አራጋቢነት በረከት ታጋይ ሙሉአለም አበበን እንዲገደል አድርጓል ከሚል ውንጀላው ነው። ኢሳት ያልተረዳው ነገር ግን በረከት ሙሉአለምን  እንደ ልጁ የሚሳሳለት ውድ የትግል ጓዱና የባሌቤቱ እህት ባል የነበረ መሆኑን ነው።  ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ የታማኝ ወንድም በሆነው ተወልደ በየነ የተባለ ጋዜጠኛ ነኝ ተብየ ቆርጦ ቀጥል በኩል የሚቀርበው “በረከት ወደ ፌዴራል መንግስት ከመዛወሩ በፊት አማራ ክልል ይሰራ በነበረበት ወቅት የዘር ማጥፋት የሚመስል ስራ ሰርቷል” ብሎ የሚያቀርበው ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት ውንጀላው ነው። ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት ውንጀላ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በረከት ከደርግ ውድቀት ጀምሮ አዲስ አበባ እንጅ አማራ ክልል ተመድቦ ያማያቅ በመሆኑ ነው። እንዲያው ተወልደ እንዳለው በረከት አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት አማራ ክልል ነበር እንኳን ቢባል ዘር ማጥፋት የሚመስል ወንጀል መስራቱን የሚያሳይ አንድ ቅንጣት እንኳን ማስረጃ ማቅረብ አይችልም። ከዚህ ስንነሳ ኢሳትና በዙሪያው ያሉ ጋዜጠኛ ተብየዎች ምን ያህል የውሸት ፋብሪካ እንደሆኑና  ሚድያውን ያለተጠያቂነት የጠሉትን ሰው የሚበቀሉበት መሳሪያ አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

በማጠቃለል ሲታይ የሆነ ሰው ወይም ቡድን በበቀል ወይም የሆነ አይነት ጥቅምን/ትርፍን መሰረት አድርጎ ሌላውን ሰው ወይም ቡድን ለማጥቃት መንቀሳቀሱ በአለም ላይ አዲስ ክስተት ባይሆንም የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች ክፋት፣ የቅጥፈት ውንጀላና የሴራ መንገድ ግን በጣም ጥርሱን አግጥጦ የወጣ ነው። የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች ሴረኛ ባይሆኑ ኖሮ ከአንድ አመት በፊት ከድርጅቱ መልቀቂያ ጠይቆ ከወጣ በኋላ ለምነው እንዲመለስ ያደረጉትን ሰው ማለትም በረከት ፀረ አማራና ሙሰኛ ብለው አይወነጅሉትም ነበር። የሚገርመው ነገር ደግሞ እነዚህ የአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች እነበርከትን ለመክሰስ ሲሉ ጥረት ኮርፖሬትን በክልሉ መንግስት ስር ከማድረግ ጀምሮ ሌሎችንም ሁኔታዎች እስከማመቻቸት ደርሰዋል። ወጣም ወረደ ግን  ባብዛኛው እውነት ዘግይታም ቢሆን ራሷን መግለጧ ስለማይቀር በእደለ ቢሶቹ ልጆችና በነበረከት ጉዳይም እውነታው ወጥቶ ማን ጥፋተና ማን አባይ/ቀጣፊ እንደሆነ ለማየት እንበቃ ይሆናል።

ከሁሉ የሚያሳዝነው ግን በረከት በቋንቋ፣ በባህልና በስነልቦና እቆራኘዋለሁ ከሚለውና እድሜ ልኩን አፈር ድሜ ግጦ ከሰራለት አማራ ህዝብ ፀረ አማራና ሙሰኛ ነው በሚል በፈጠራ የተቀነባበረ የሴራና ጎጠኛ የጥቃት ምክንያቶች እንዲገለል (Ostracised) መደረጉ፤ ትግርኛ መናገር የሚችል እንጅ የትግራይ ተወላጅ  አለመሆኑ፣ የኤርትራም ይሁን የሌላ አገር ዜግነት የሌለው መሆኑ፤ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ደረቱን ነፍቶ እየተናገረ እያለም በመንግስት በኩል ያንን የሚያሳይ ነገር እየታየ አለመሆኑ ባጠቃላይም መንግስት አልባ ሰው (Stateless Person) ተደርጎ መቆጠሩ ነው። ለዚህ መቶ ዓመት እንኳን ሞልቶ መኖር ለማይቻልበት አለም እንዲህ አይነት የክፋት፣ የሴራና የተንኮል ጥቃት ለመሰንዘር መጣደፍ ደግሞ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ዘግናኝም ነው።

 

እስከዚያው ግን ቸር ያቆየን!!!

Back to Front Page