Back to Front Page


Share This Article!
Share

የአቶ በረከትና የአቶ ታደሰ እስር የፍትህ ጉዳይ ወይስ ጊዜ ሰጠኝ ባሉ የጦር አበጋዞች (War Lords) በመካሄድ ላይ ያለ እገታ (Detention)?

ከምስክር አለነ(18.02.2019)

እንደሚታወቀው አቃቤ ህግም ሆነ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሰውን በሙስና ወንጀል ለመክሰስ ምርመራ ሲጀምሩ ሶስት መሰረታዊ ነገሮችን ማስረዳት ያለባቸው መሆኑን ተረድተው ነው። እነዚህም የህግ ክፍል (Legal Element) ፣ የድርጊት ክፍል (Material Element) እና የሃሳብ ክፍል (Mental Element) ናቸው። እነዚህ ሶስት መሰረታዊ የወንጀል ሃላፊነት ማቋቋሚያ ቅንጣቶች ሊሟሉ እንደማይችሉ ከወዲሁ መረዳት የሚቻልበት ግልፅ የሆነ ነገር ካለ ምርመራውም ክሱም ሳይጀመር ቢቀር ይሻላል። ምክንያቱም የዘመኑ የወነጀል ህግ ስርዓት ዜጎች በሆነ ባልሆነው እንዲሁም በበቀልና በሌሎች መሰረት በሌላቸው ምክንያቶች እንዲሰቃዩ ሳይሆን ተምረውና ታርመው ወደፊት የተሻለ ህይወት ሊኖራቸው እንዲችሉ ማስቻል ነውና። ለማንኛውም የዛሬው ፅሁፍ የሚያተኩረው የወንጀል (ሙስናን ጨምሮ) ማቋቋሚያ ቅንጣቶች ውስጥ አንዱና መሰረታዊ በሆነው የህግ ክፍል (Legal Element) ነው።

Videos From Around The World

ለመጀመር ያህል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ረፑብሊክ መንግስት የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 ንዑስ አንቀፅ 34 በወንጀል ህጉ የመጀመሪያ ታላቅ ክፍል ከአንቀፅ 1 እስከ 237 ያሉት ድንጋጌዎች [አጠቃላይ መርሆዎች] በዚህ አዋጅ ለተመለከቱት የሙስና ወንጀሎችም ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል ይላል። የእንግሊዝኛ ቅጅውም “The Provisions Anicles 1 to 237 of the General Part of the Criminal Code shall be applicable to Corruption Crimes provided for under this Proclamation.” በሚል ይነበባል። የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዝኛው ድንጋጌዎች የሚያሳዩት መሰረታዊ የሆነ ነገር ቢኖር በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ውስጥ ከአንቀፅ 1 እስከ አንቀፅ 237 የተዘረዘሩት መርሆዎች በሙስና ወንጀሎች ላይ ያላቸው ተፈፃሚነት ለማንኛውም የመንግስት አካል ምርጫ የሚተው ሳይሆኑ ይልቁንም አስገዳጅ መሆናቸውን ነወ። ከዚህ መረዳት የሚቻለው እነዚህ መርሆዎችና ድንጋጌዎች በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሚወጣ ህግ ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር ጨምሮ በማንኛውም የመንግስት አካል ሊታለፉ የማይችሉ መሆናቸውን ነው።

ከላይ ከተገለፁት የሙስና ነክ ህግ መርሆዎች ውስጥ ለዚህ ፅሁፍ ርዕስ አስፈላጊ የሆኑት የህጋዊነት መርህ ወይም የህግ ክፍል (Principle of Legality or Legal Element) ድንጋጌዎች አንቀፅ 2 እና 5 እንዲሁም የህገመንግስቱ አንቀፅ 22 እንደ አግባባቸው የሚከተለውን አስፍረዋል።

ፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱ በህግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጥረው እና ቅጣት ሊወስንበት አይችልም። (የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 2 (2))

ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈፀመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈፀሙ ወይም አለመፈፀሙ ወንጀል መሆኑ በህግ ካልተደነገገ በስተቀር ሊቀጣ አይችልም። (የህገመንግስቱ አንቀፅ 22 (1)) የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀፅ አምስትም ቢሆን የወንጀል ህግ ወደኋላ ተመልሶ የማይሰራ መሆኑን ይደነግጋል። (This refers to the nor-retroactive application of Criminal laws)

እነዚህ ከላይ የተገለፁ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉም ይሁን የህገመንግስቱ ድንጋጌዎች አሻሚ ባልሆነ መንገድ የሚያስቀምጡት ማንም ሰው ሙስናን ጨምሮ ወንጀል ተፈፀመ በተባለበት ጊዜ ውስጥ የወንጀል ድርጊቱ ወይም ግድፈቱ በወንጀል ነክ ህጎች ያልተከለከለ ከሆነ በቀር በወንጀ

ሊጠየቅ አይችልም በሚል ነው። ከላይ ከተቀመጡት ድንጋጌዎች መረዳት የሚቻለው ሌላው ቁም ነገር የወንጀል ድርጊቱ ወይም ግድፈቱ ተፈፅሟል በተባለበት ወቅት ያልነበሩ የወንጀል ነክ ህጎችም ወደ ኋላ ተመልሰው ሊሰሩ የማይችሉ መሆኑን ነው። ይህ ድንጋጌ የሙስና ህግ መርሆዎች አካል የሆነበት ምክንያት ማንኛውም ሰው በወንጀል ህጎች ባልተከለከለ ድርጊቱ ሊጠየቅ አይገባም የሚለውን የወንጀል ህግ መርህ ለማጠናከር ወይም ጉልበት ለመስጠት ታስቦ ነው፡።

የሙስና ወንጀሎችን ለማቋቋም ከሚያስፈልጉ ቅንጣቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የህጋዊነት መርህ (Principle of Legality) ከላይ በተቀመጡት መንገዶች ከተብራራ አሁን ደግሞ በዚሁ መርህ ውስጥ ሆነን የአቶ በረከትንና የአቶ ታደሰን ክስ ጉዳይ እንመልከት። እንደሚታወቀው እነዚህ ሰዎች የጥረትን ሃብትና ንብረት በማባከን ተጠርጥረው አማራ ክልል ባለው የባህር ዳር ወህኒ ቤት ታስረው ይገኛሉ። ጥረት ማለት ደግሞ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ እንደቅደም ተከተላቸው የቦርድ ሰብሳቢና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ሲመሩት የነበረ ተቋም ነው። በጥረት አመሰራረትና ባለቤትነት ዙሩያ ያለውን የብአዴን/ኢህአዴግ ጉድ ለጊዜው ትተን ላሁኑ ጥረትን ህዝባዊ ድርጀት ነው ብለን እንውሰደው።

በህዝባዊ ድርጅቶችና በሰራተኞቻቸው የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶችን በሙስና መመርመርና መክሰስ የተጀመረው ደግሞ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 እና የተሻሻለው የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 883/2007 በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት 2007 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ነው። ይህ ማለት ከ2007 ዓ.ም አጋማሽ በፊት ባለው ጊዜ ሁሉ ህዝባዊ ድርጅቶችም ሆኑ ሰራተኞቻቸው የሙስና ድርጊት ወይም ግድፈት ፈፅማችኋል ተብለው በሙስና ሊከሰሱ የሚችሉበት የህግ መሰረት አልነበረም ማለት ነው። እውነታውን በሚገባ ለመረዳት ይቻል ዘንድ እነዚህ አዋጆች ቃል በቃል ያስቀመጡትን መመልከት ጠቃሚ ነው። በዚህም መሰረት የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 መግቢያ:

"የሙስና ወንጀሎቹ ማካተት የነበረባቸውን ተመሳሳይ ተግባራት በተለይም ከህዝብ የተሰበሰበ ወይም ለህዝብ ተብሎ የተሰበሰበ ሃብት በሚያስተዳድሩ የግል ዘርፍ አካላት የሚፈፀሙ ተመሳሳይ ተግባራትን ባግባቡ ያላካተቱ በመሆናቸው እነዚህኑ ማካተት በማስፈለጉ" በማለት አስቀምጦታል።

የተሻሻለው የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 883/2007 መግቢያ በበኩሉ በሙስና ወንጀሎች አዋጁ የተዘረዘሩ የሙስና ወንጀሎች ለኮሚሽኑ (አሁን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ መሆኑ ነው) የተሰጡ መሆኑን በግልፅ ለማሳየት “ህዝባዊ ድርጅቶች የሚፈፅሟቸውን የሙስና ወንጀሎች የመመርመርና የመክሰስ ስልጣንን ለኮሚሽሽኑ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ" ሲል ደንግጓል።

እነዚህ አዋጆች በማያሻማ መንገድ ያስቀመጡት አብይ ጉዳይ ቢኖር ህዝባዊ ድርጅቶችና ሰራተኞቻቸው በሙስና ወንጀል ሊከሰሱ የሚችሉት ድርጊቱን ወይም ግድፈቱን የፈፀሙት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከሆነ ብቻ ነው። ከላይ ከተጠቀሰው ቀን በፊት የሙስና ወንጀል ፈፅመሃል ወይም ገድፈሃል ብሎ ክስ የሚያቀርብ የትኛውም ምድራዊ ሃይል ካለ ግን በራሱ ጡንቻ ህግ ጥሶ እንጅ ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት እንደሌለው ሊገነዘብ ይገባል። ስለዚህ አቶ በረከትና ታደሰ የተባለውን የጥረት ሃብትና ንብረት አባክነዋል ቢባል እንኳ ከ2007 ዓ.ም በፊት ለተፈፀመ ድርጊት ወይም ግድፈት በሙስና ተጠያቂ የሚሆኑበት ህጋዊ መሰረት የለም። ምክንያቱም ከ2007 ዓ.ም በፊት ተፈፀመ የሚባል ድርጊት ወይም ግድፈት ካለም በሙስና የወንጀል ነክ ህጎች የተክለከለ ባለመሆኑ ነው። አቶ በረከትንና አቶ ታደሰን ለማሰርና ለመክሰስ በማቀድ ከ2007 አጋማሽ ጀምሮ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ስራ ላይ የዋሉትን የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 እና የተሻሻለውን የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 883/2007 ወደኋላ መልሰን እንዲሰሩ እናደርጋቸዋለን የሚል አካል በዚህ ፅሁፍ ከፍ ብለው የተገለፁትን የህገመንግስቱን አንቀፅ 22፣ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን አንቀፅ 2 እና 5 እየጣሰ መሆኑን ሊረዳ ይገባል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው አቶ በረከትንና አቶ ታደስን እስከ 2007 ዓ.ም ተፈፀመ ለሚባል ድርጊት ወይም ግድፈት ተጠያቂ የሚያደርጓቸው የሙስና ወንጀል ነክ ህጎች ከሌሉ ከዚያ በኋላ ባሉት 3 አመታት ውስጥ በተፈፀመ የሙስና ወንጀል ድርጊት ወይም ግድፈትስ በሙስና ሊጠየቁ የሚችሉበት ሁኔታ አለ ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳት አግባብነት አለው። በነዚህ 3 አመታት ማለትም ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ጊዚያት ውስጥ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተገለፀ እንዳለው የሙስና ድርጊት ወይም ግድፈት ፈፅመው ከሆነ በሙስና ሊጠየቁ የሚችሉበት የህግ አግባብ አለ ማለት ይቻላል። ይህ የህግ አግባብም በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 እና በተሻሻለው የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 883/2007 በግልፅ ሰፍሯል። በነዚህ አዋጆች መሰረት ከ2007 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እነ አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ ጥረትን እስከለቀቁበት 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የፈፀሙት የሙስና ድርጊት ወይም ግድፈት ካለ ጥረት ኮርፖሬት ህዝባዊ ድርጅት ነውና ሊጠየቁ የሚችሉበት አግባብ አለ።

እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ አቶ በረከትና አቶ ታደስ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል የሚለውን ጥርጣሬ ብንቀበል እንኳ በነዚህ ህዝባዊ ድርጅቶች የሚፈፀሙ የሙስና ወንጀል ድርጊቶችን ወይም ግድፈቶችን የመመርመርና የመክሰስ ስልጣን የተሰጠው አካል የትኛው ነው የሚለው ነው። በተሻሻለው የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 433/1997 አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ከባድ ተብለው የሚገመቱ የሙስና ወንጀሎችን የመመርመር ስላጣን የተሰጠው ለፌዴራል መንግስቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን (አሁን ደግሞ የጠቅላይ አቃቢ ህግ) ነው። ከባድ ሙስና ወንጀሎች ተብለው በተሻሻለው የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 883/2007 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 1 ከተጠቀሱት መካከል ደግሞ "…ከአንድ ክልል በላይ በሆኑ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ [የፌዴራልም ይሁኑ የክልል] ህዝባዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈፀሙ ከፍተኛ የገንዘብ መጠንን ያካተቱ የሙስና ወንጀሎች" ይገኙበታል።

በዚህ ድንጋጌ መሰረት ጥረት ከአንድ ክልል በላይ በሆኑ ክልሎች የሚንቀሳቀስ ህዝባዊ ድርጅት በመሆኑ በዚህ ድርጅት ውስጥ ተፈፅመዋል የተባሉ የሙስና ወንጀሎችን ሁሉ የመመርመር ስልጣን የተሰጠው ለፌዴራል መንግስቱ ነው። ምንም እንኳ የፌዴራል መንግስቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን/ጠቅላይ አቃቢ ህግ በመርህ ደረጃ የመመርመር ስልጣኑን ለክልሎች ወይም ለሌሎች አግባብ ላላቸው አካላት ማስተላለፍ የሚችል ቢሆንም ከባድ የሆኑ የሙስና ወንጀሎችን መመርመር ያለበት ግን ራሱ ነው። በሌላ አነጋገር የፌደራል መንግስት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከባድ የሙስና ወንጀሎችን ክልሎች ወይም ሌሎች አግባብ ያላቸው አካላት እንዲመረምሩለት ውክልና ይሰጣል የሚል ህግ በግልፅ አልተቀመጠም። በዚህ ረገድ ህጉ የሚያስቀምጠው ነገር ቢኖር የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንደማንኛውም ክልል ሁሉ በፌዴራል መንግስቱ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የስልጣን ወሰን ያለ ማንኛውም አይነት የሙስና ወንጀል እንደተፈፀመ በራሱ መንገድ ጥቆማ ሲደርሰው ምርመራ መጀመር የሚችል መሆኑን ነው። ክልሉ በዚህ መንገድ ሄዶ በነአቶ በረከትና አቶ ታደሰ ላይ የጀመረውን የምርመራ ሂደት ወዲያውኑ ለፌዴራል መንግስቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበተም ህጉ ይደነግጋል። ይሁን እንጅ የፌዴራል መንግስቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በነአቶ በረከትና አቶ ታደሰ ላይ ስለተጀመረ የሙስና ወንጀል ምርመራ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በቃል አቀባዩ በኩል ገልጿል። ከዚህ በመነሳት የአማራ ክልል ፀር ሙስና ኮሚሽን ከህግ ውጭ እየተንቀሳቀሰ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

የመክሰስ ስልጣን በተመለከተም ህጉ የሚለው አለው። ይሀውም ከአንድ በላይ ባሉ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፌዴራልም ይሁኑ የክልል ህዝባዊ ድርጅቶች ውስጥ ወንጀል ተፈፅሟል የሚል ጥርጣሬ ካለ የመክሰስ ስልጣን የተሰጠው ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ደግሞ ይህን ስልጣኑን ለክልሎች ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች ወይም አግባብ ላላቸው ሌሎች ተቋማት በውክልና ማሳለፍ እንደሚችል ተደንግጓል። ይህ ማለት ደግሞ የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ በረከትንና አቶ ታደሰን ጠረጠርኳቸው ባለው የሙስና ወንጀሎች መክሰስ የሚችለው የፌዴራል አቃቤ ህግ የውክልና ስልጣን ሲሰጠው ብቻ ነው። ይሁን እንጅ የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ በረከትንና አቶ ታደሰን መክሰስ ይችል ዘንድ ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተሰጠው የውክልና ስልጣን አለመኖሩን ከላይ ምርመራውን በተመለከተ የጠቅላይ አቃቤ ህጉ ቃል አቀባይ ከሰጡት መልስ መረዳት ይቻላል። ከዚህ አንፃር የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ በረከትንና አቶ ታደስን እከሳለሁ ብሎ ሲነሳ ከህግ ውጭ እየተንቀሳቀሰ እንዳለ መረዳት ይቻላል።

ከዚሁ ከነአቶ በረከትና አቶ ታደሰ የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ጋ ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሌላው ጥያቄ የጥረት ኮርፖሬት ከነሃሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስር እንዲተዳደር ተደርጓል መባሉ በምርመራውና በክሱ ላይ ምን እንደምታ ይኖረዋል የሚለው ነው። በነገራችን ላይ ይህ ተቋም በክልሉ መንግስት ስር እንዲተዳደር ያደረገው ገፊ ምክንያት ምን እንደሆነ እስከአሁን የሚታወቅ ነገር የለም። አንዳንዶቹ አቶ በረከትንና አቶ ታደሰን ለመክሰስ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የተደረገ ሴራ ነው ብለው ያምናሉ። የዚህ አይነት ውሳኔ የተወሰነው በየትኛው የክልሉ መንግስት አዋጅ ወይም ደንብ እንደሆነም እስካሁን በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም። ወጣም ወረደ ይህ ተቋም ከነሃሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ መንግስት ስር እንዲተዳደር መደረጉ በአቶ በረከትና አቶ ታደሰ የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ላይ የሚያስከትለው አዲስ ነገር የለም። ምክንያቱም አቶ በረከትና አቶ ታደሰ የተጠረጠሩበትን የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉት ጥረት ኮርፖሬት ህዝባዊ ድርጅት ሆኖ በግል ካምፓኒነት ሲንቀሳቀስ በነበረበት ከነሃሴ 2010 በፊት ባሉት ጊዚያት እንጅ በአማራ ክልላዊ መንግስት ስር መተዳደር ጀምሯል ከተባለበት ነሃሴ 2010 ዓ.ም በኋላ አይደለም።

በአጠቃላይ ሲታይ የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን እያደረኩት ነው የሚለው ምርመራና እሱንም ተከትሎ እመሰርተዋለሁ የሚለው ክስ ከህግ ውጭ የሆነ በማን አለብኝነት የሚደረግ ሽምጥ ግልቢያ መሆኑን ለመረዳት የግድ የህግ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም። ለዚህም ነው የአቶ በረከትና የአቶ ታደሰ እስር የፍትህ ጉዳይ ወይስ ጊዜ ሰጠኝ ባሉ የጦር አበጋዞች (War Lords) እየተካሄደ ያለ እገታ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አስገዳጅ የሆነው።

 

Back to Front Page