Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሰዉ ወደ ልቡ እየተመለሰ ያለ ይመስላል

ሰዉ ወደ ልቡ እየተመለሰ ያለ ይመስላል

ዶር. ዮሃንስ አበራ አየለ 2-24-19

"አሳድሬ ልናገር" የሚል አባባል አለ፤ ምክንያቱም ሲያድር ነገር ሆነ ምግብ በረድ ማለቱ ስለማይቀር። ምግብ ሲያድር ቀዝቀዝ ይልና ምላስ አይፈጅም። ነገርም ቢሆን ሲያሳድሩት ጉዳቱና ጥቅሙን ለማንሰላሰል ጊዜ ይሰጣል። ለዚህ ነው ስሜቱ እንደገነፈለ ወዲያው በመናገር የሰው ስሜት የሚጎዳውን ሰው "ሲናገር ለነገ አይልም" ተብሎ የሚተቸው። እንኳንና አገርና ህዝብን ያህል ነገር ላይ ጉዳት የሚያደርስ ንግግር ይቅርና አንድን ሰው እንኳን ስሜት የሚነካ ነገር መናገር አስቦ አውጥቶ አውርዶ ጊዜ ሰጥቶ መሆን ይኖርበታል።

Videos From Around The World

ከዛ በፊት በየሰፈሩ ሲደረግ የኖረውን ትተን ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ትግሬን መሳደብ እንደ ፓለቲካ ሊቅነት፤ ከዛም ወረድ ሲል እንደፋሽን፣ አሁንም ወረድ ሲል እንደሞኝ ለቅሶ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ክስተት የእንቆቅልሾች ሁሉ እናት እንዲሆን ያደረገው የዚህ ሁሉ የስድብ መአት ዋና መፈልፈያ ከተሰዳቢው ጋር እጅግ ቅርብና ጥብቅ የሆነ የሃይማኖት፣ የባህልና፣ የታሪክ ቁርኝት ያለው ህዝብ መሆኑ ነው። መሪዎቹና ገዢዎቹ እርስበርስ ሲጣሉና ስልጣን ሲቀማሙ ህዝቡን ሲያገዳድሉት ከመኖራቸው ውጪ የትግራይና የአማራ ህዝብን የሚያጣላና ለመሰዳደብ የሚያበቃ ምንም ምክንያት ኖሮት አያውቅም። በያሉበት ሆነው ደካማ የሆነችውን የእርሻ መሬታቸውን እየቧጠጡ የድህነት ኑሮ ከመግፋት በስተቀር "ከእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" ከሆነ ለቃላትና ለመሳርያ ፍጥጫ የሚያደርሳቸው ነገር የለም። ይልቅስ የሚበጀውና ለዘለቄታው የሚያስደስተው ተደጋግፎ ድህነትን ማጥፋት ነው። ድህነት ሊያጣላ ይችላል። ፈረንጃች " የራበው ሰው ቁጡ ነው" ይላሉ። መፍትሄው የሚሆነው መንስኤውን (ድህነትን/ረሃብን) ተባብሮ ማጥፋት እንጂ ውጤቱን (ፀብን) ማጋጋል አይደለም። ወባውን በመድሃኒት ካላስወገድን ትኩሳቱ እንደሚገድለን ምን ጥርጥር አለው። ፀብ ፀብን እንጂ ሰላምና ብልፅግናን ወልዶ አያውቅም። ሳይዘሩት በቀለ የሚባለው ስድብ ላይ ብቻ ነው።

ከአመራር ለውጡ በፊት የነበረው የጋዜጠኝነት ስነምግባር ከጎደላቸው "ጋዜጠኞችና" መረን ከተለቀቀው የማህበራዊ ሚድያ ሰራዊት የሚያንከባልለው ግብታዊ የሆነ የስድብ ናዳ ነበር። የስርአት ለውጥ ሳይሆን የአመራር ለውጥ ከመጣ በኋላ ግን ስድቡ በመሪዎች የተደገፈና ህጋዊ የሆነ የመሰለበት ደረጃ ላይ ደረሰ። እንኳንና ህዝብን ግለሰብን ቢሆን መስደብ ፍርድ ቤት የሚያስቀርብ ወንጀል ነው። ለነገሩ በለውጥ ስም ቤት፣ መኪና፣ ፋብሪካ ሲያቃጥሉ፣ ሰላማዊ ሰው ሲገድሉ፣ ሲያጎሳቁሉና ሲያባርሩ የነበሩ ሁሉ እንደ ጀግኖች በተቆጠሩበት አገር ህዝብን ተሳደበ ብሎ የሚከታተልና ለፍርድ የሚያቀርብ የትኛው የፓሊስ አርበኛ ነው? ታክሲ ላይ፣ ምግብና መጠጥ ቤት ውስጥ አውራ ጎዳና ላይ ትግርኛ ሲነገር ልክ ሸለምጥማጥ እንደመጣባቸው ዶሮዎች የሚያደናግጥ ሲሆን ክርስቶስ እንዳለው "የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" ከማለት በስተቀር ምን ይባላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአምላክ ቀድሞ የቀረበ ህዝብ የደረሰበትን ስድብና ውርደት አምላክ ጀሮ ዘንድ የደረሰ ይመስላል። ይህ አስገራሚ ለውጥ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመገመት በስተቀር እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ያ ሁሉ የስድብ ናዳ ረብ ያለ ይመስላል። አሁን አሁን በትግርኛ ቋንቋ የሚደነግጥ ሰው ያለ አይመስልም፤ እንዳያውም ባልተለመደ ሁኔታ የትግርኛ ዘፈኖች ተወዳጅ እየሆኑ መጠዋል። ከሁሉም በላይ ማህበራዊ ሚድያውም የእረኛ ስድቡን ጨርሶ ባያቆምም "ተመስገን" የሚያሰኝ ያህል በጣም ቀንሷል። ብልግናን በብልግና መመለስ መጥፎ እንደሆነ እየታወቀ ከትግራይ በኩል አንዳንድ ግለሰቦች አስፀያፊ ስድብ ሲሰነዝሩ እንደቆዩ ይታወቃል። ከነዚህ ጥቂት አረሞች በስተቀር የትግራይ ህዝብ ያሳየው ትእግስትና አስተዋይነት ታላቅነቱን የሚያስመሰክር ሆኖ ቆይቷል።

አስተውለን እንደሆነ ሰዎች በአንድ ነገር ከተጣሉ በኋላ ወደ ዱላ መሰናዘር የሚያመሩት መሰዳደብ ሲጀምሩ እንጂ መጀመሪያ በተጣሉበት ነገር አይደለም።  በግሪኮች ዘንድ ስድብ ከአካላዊ ጉዳት የከፋ እንደሆነ የሚያስተምር  ተረት አለ። አንበሳ አንድ ህፃን ልጅ ጫካ ውስጥ ወድቆ ያገኛል። ህፃኑን እንደልጁ ተንከባክቦ ያሳድገዋል፣ ጎበዝ አዳኝም ይሆናል። ከእለታት በአንዱ ቀን አንበሳ ያሳደገው ሰውየ ሌላ ሰው ጋር ይገናኝና ከኣበሳው ብዙም ሳይርቁ ወሬ ይጀምራሉ። ጥያቄ፦"እዚህ ከማን ጋር ነው የምትኖረው?"  መልስ፦ "ከአንበሳው ጋር።" ጥያቄ፦"እንዴት ቻልከው?" መልስ፦ "የብብቱ ሽታ ያስቸግረኛል እንጂ ሌላ ችግር የለም።" ውይይቱ አብቅቶ ወደ አንበሳው ተመልሶ ሲሄድ አንበሳው አንድ ልመና ያቀርብለታል፣ እንዲህ ብሎ፦ "በጦር ውጋኝ።"፣ መልስ፦"አባቴን በጦር?" እንደገና ልመና፦"የምትወደኝ መሆንህን የማረጋግጠው ስትወጋኝ ብቻ ነው።" እንደታዘዘው አንበሳውን በጦር ወጋውና አንበሳው ቆሰለ። አንበሳው ከቆሰለ በኋላ እንዲህ አለ፦"ይችን ቁስል አክመህ አድናት።" ልጅ ቁስሏን አክሞ አዳነ። ቁስሉ ደርቆ ሲጠፋ አበሳው እንዲህ ብሎ የማይረሳ ነገር ነገረው፦ "ቁስሏ ዳነች ጠፋች፤ እንደቁስሏ ደርቃ የማትጠፋው ግን ከሰውየው ጋር ሆነህ ስለኔ የተናገርካት አስፀያፊ ቃል ናት"።

Back to Front Page