Back to Front Page


Share This Article!
Share
የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ በሕግ መነጽር ሲታይ

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ በሕግ መነጽር ሲታይ

 

ባይሳ ዋቅ-ወያ ****

ሰሞኑን በተለያዩ መድረኮች የአዲስ አበባን ባለቤትነት በተመለከተ ዜጎች በጎራ ተከፋፍለው ዱላ ቀረሽ የቃላት ጥይቶች ሲለዋወጡ ተስተውሏል። ክርክሩና እንካ ስላንቲያው በመደማመጥና በመከባበር ወይም ከእርስ በርስ ለመማማር፣ ቀድሞ ያልተረዱትን ሃቆች አሁን ተገንዝቦ አቋም ለመቀየር ሳይሆን፣ የኔ አቋም ብቻ ትክክል ነው በሚል መሪህ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ይህን ጽንፍ የያዘውን ክርክር፣ ጽንፈኞቹ መሰረት አድርገው የሚከራከሩበትን ታሪካዊ ሃቆችንና መረጃዎችን ወደ ጎን ትቼ የማያከራክሩንን የፌዴራሉንና የክልሉን ሕገ መንግሥት ይዘቶች ብቻ በመመርመር አንዳች ዓይነት መግባባት ላይ እንደርሳለን በሚል እምነት ይህንን የግል አስተያየት ለመሰንዘር ወሰንኩ። ታሪካዊ መረጃዎችን ወደ ጎን ትቼ ሕጋዊ መረጃዎች ላይ ያተኮርኩበት ዋናው ምክንያት፣ ሕጋዊ መረጃዎቹ ዛሬ በቀን ተቀን ኑሮአችን የምንጠቀምባቸው ሕያው መረጃዎች በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብለን እስከ ዛሬ ስንጠቀምባቸው የነበረው የጥቂት ትላልቅ ብሄሮችን ገድል ብቻ የሚዘክር እንጂ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ብሄር ታሪክ በተለይም የደቡብን ሕዝብ ታሪክ የማያወሳ በመሆኑ፣ ይህንን አግላይ ታሪካዊ መረጃ ለክርክር መርቻ ዋቢ አድርጎ ማቅረቡን በግሌ ስለማላምንበት ነው።

እንደው ከወዲሁ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ሌላው ነገር፣ የህግ ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን፣ ሁኔታዎችንና ክስተቶችን የማየው በህግ መነጽር ብቻ መሆኑን ነው። በመሆኑም የህገ መንግሥቶቹን ይዘት እንደገባኝ ተርጉሜ አቀርባለሁ። የሰው ልጅ ደግሞ የተለያየ ጭንቅላት ስላለው በአስተሳሰቡም ይለያልና፣ ከኔ በተለየ መንገድ የገባችሁ ካላችሁ፣ ከፖሊቲካ ገለመሌና ግምታዊ ግምገማ ነጻ በሆነ መንገድ ከኔ ጋር የማትግባቡበትን ምክንያት ህገ መንግሥቶቹን ብቻ በመመርኮዝ እንድትሞግቱኝ እሻለሁ። ዋናው አቤቱታዬ፣ ያገራችንን ችግሮች በብሄር መነጽር ብቻ አንይ፣ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በጣም ዝቅ ብለናል፣ እስቲ ራሳችንን ከዚያ ከፍ እናደርግና ውይይታችንን ትንሽ እናዘምን ነው። በሃቅ ላይ የተመሰረተ ጤናማ ውይይት ብቻ ነው ላገራችን የሚበጃት። ነገሮችን ሁሉ በጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ መፈረጅ የለብንም። በመሃሉ ግራጫ ቀለም እንዳለ እንረዳ። ጽንፈኞች አንሁን ማለቴ ነው።

Videos From Around The World

ፊንፊኔ የአዲስ አበቤዎች ናት ፊንፊኔ የሁሉም ክልሎች ህዝብ ናት ፊንፊኔ የኦሮሞዎች ናት ወዘተ የሚሉትን መፈክሮችን ስሰማ፣ ይህ በሌሎች ክልል ዋና ከተሞች የማይከሰት በኦሮሚያ ዋና ከተማ ላይ ብቻ ያተኮረ የባላቤትነት ጥያቄ ምንጩና ዓላማው ምንድነው? የአሶሳና የጋምቤላ፣ የባህር ዳር ወይም የጂጂጋ የሃዋሳ ወይም የሃረር ባለቤትነት ጥያቄ አንድም ቀን ሳይነሳ ለምን የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ያን ያህል ሊገንን ቻለ? ብዬ ራሴን ደጋግሜ ስጠይቅ መልሱን ለማግኘት ወደ ህገ መንግሥቶቹ አቀናሁ። የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ ህገ መንግሥት፣ አፈጻጸሙ ላይ ችግር ይኖራቸው እንደው እንጂ ቃልና መንፈሳቸው አሉ ከሚባሉ የሌሎች ዲሞክራት አገሮች ህገ መንግሥት ተርታ የሚያሰልፋቸው ስለሆነ ለውዝግቡ መፍትሄ ይሰጣሉ የሚል እምነት አለኝ። ህጎቻችን ግን ፍጹማን ናቸው የሚል ዕብደት አይከጅለኝም። ህገ መንግሥት ግን ከፋም ለማም፣ ዜጎች ተስማምተው የሚበጃቸውን ሌላ ህገ መንግሥት እስከሚያጸድቁ ድረስ፣ ዛሬ ጠቀሜታ ላይ ያሉ ህገ መንግሥቶቻችን ብቸኛ መተዳደርያችን ናቸው። መሻሻል አለባቸው ተብሎ ከታመነበት ደግሞ የህገ መንግሥቱን ድንጋጌ ተከትለን የተሻለ ህገ መንግሥት የማናጸድቅበት ምክንያት የለም። በዚህ ዕውኔታ ላይ ተመሥርቼ ነው እንግዲህ ይህን ጽሁፌን በሙሉ

ለአንባቢያን ምቾት ሲባል ከሁለቱም ህገ መንግሥቶች ለዚህ ሙግታችን ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውንና ለጥያቄዎቻችን ተገቢውን መልስ ይሰጣሉ ብዬ የማምንባቸውን አንዳንድ የክልሉንና የፌዴራሉን ህገ መንግሥት አንቀጾች ለይቼ በማስቀመጥ ሙግቴን ልቀጥልበት።

የፌዴራሉ ህገ መንግሥቱ፣

አንቀጽ 46 የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው።

አንቀጽ 47 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሬፑብሊክ አባላት ዘጠኝ ናቸው።

አንቀጽ 49 የፌዴራሉ መንግሥ ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራሉ መንግሥት ይሆናል።

አንቀጽ 104 አንድ የህገ መንግሥት ማሻሻያ ሃሳብ.. በህዝብ ተወካዮችና የፌዴረሺኑ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛው ድምጽ የደገፈው ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ህዝብና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል።

የክልሉ ህገ መንግሥት፣

አንቀጽ 5 ኦሮሚኛ የክልሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል።

አንቀጽ 6 የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ (ፊንፊኔ) አዲስ አበባ ነው።

አንቀጽ 8 የኦሮሞ ህዝብ የክልሉ መንግሥት የሥልጣን ባለቤት ነው።

አንቀጽ 9 ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ፣ የፖሊቲካ ድርጅት፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባላሥልጣኖቻቸው ይህንን ህገ መንግሥት የማስከበርና ለህገ መንግሥቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው።

አንቀጽ 34 በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች የክልሉን የሥራ ቋንቋ እስካወቁ ድረስ በክልሉ መንግሥታዊ ሥራ ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት፣ እንደማንኛውም የክልሉ ተወላጅ ሰርቶ የመኖር፣ ከስፍራ ስፍራ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማፍራትና የመያዝ መብት አላቸው።

አንቀጽ 39 ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ..በቀለም፣ በዘር፣ በብሄረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖሊቲካ ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት በቀጥታና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካይነት በህዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ ..ዕድሜው አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላ በህጉ መሰረት የመምረጥና የመመረጥ መብት አለው

አንቀጽ 44 በክልሉ ውስጥ በሚያካሄዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግሥት በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ የማዘዋወር መብት አለው።

አንቀጽ 98 የዚህ ህገ መንግሥት ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት የቀረበውን የማሻሻያ ሃሳብ የምክር ቤቱ ሶስት አራተኛ አባላት ሲያጸድቁት ነው።

በኔ ግምት፣ የአዲስ አበባን ባላቤትነት አስመልክቶ ዛሬ በመካሄድ ላይ ስላለው መርዛማ ክርክር መንስኤው የፌዴራሉ ህገ መንግሥት አንቀጽ 49 እና የኦሮሚያ ክልል ህገ መንግሥት አንቀጽ 6 አለመጣጣም ነው። ሁለቱም ህገ መንግሥቶች አዲስ አበባን ዋና ከተማዬ ነው ብለው አስቀምጠዋልና! በህገ መንግሥታችን መሰረት ኢትዮጵያ የተዋቀረችዉ በዘጠኝ ክልሎች ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያን ምድር የተከፋፈሏት እነዚህ ዘጠኝ ክልሎች ሲሆኑ ከነዚህ ዘጠኝ ክልሎች ተርፎ ለሌላ ዓላማ የተቀመጠ አንዲት ካሬ ሜትር የኢትዮጵያ ምድር የለም። በመሆኑም፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ ዘጠኙ ክልሎች ከተከፋፈሉት ይዞታ ውጪ ነጻና የራሱ የሆነ ልዩ ክልል ወይም ተከልሎ የተሰጠው ቁራጭ መሬት የለውም። ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ፣ መንግሥታዊ መዋቅርና ቢሮክራሲያዊ አስተዳደር ስናወሳ ስለነዚህ ዘጠኝ ክልሎችና በነዚህ ክልሎች ውስጥ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንጂ በፌዴራሉ ክልል ስለሚኖር ህዝብ አለመሆኑ ግልጽ ነው።

አንድ የፌዴራሉ አባል የሆነ የክልል ዋና ከተማ እንዴት የፌዴራሉም ዋና ከተማ እንደሆነ ባይገባኝም አንድ ከተማ የፌዴራሉም የክልሉም ዋና ከተማ ሊሆን እንደሚችል አውቃለሁ። ስለዚህ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የፌዴራሉ መንግሥት ከተስማሙ አዲስ አበባ የሁለቱም ዋና ከተማ የማትሆንበት ምክንያት አይታየኝም። በተቃራኒው ግን፣ አዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥርያ ቤት ያለበትና የዲፕሎማቲኩ ማህበረሰብ መናኸርያ ስለሆነች የፌዴራሉ መቀመጫ ብቻ መሆን አለባት የሚለውን መሰረተ ቢስ ክስ መቀበል ያዳግታል። የፌዴራል ስዊዘርላንድ መንግሥት መቀመጫው በታሪካዊዋና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቶች መቀመጫ በሆነችው በጄኔቫ ከተማ ሳይሆን ቤርን በምትባል አነስተኛ ከተማ ነውና!

በተለምዶ አዲስ አበባ የፊውዳሊስት ኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስለነበረች ዛሬም ያ አሓዳዊ ሥርዓት ተገርስሶ አገሪቷ በፌዴራሊዝም ሥርዓት መተዳደር ስትጀምርና ኢትዮጵያ በዘጠኝ ራሳቸውን በራሳቸው በሚያስተዳድሩ ክልሎች ስትከፋፈል፣ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነገር አድርገው የሚያዩ ወገኖች አሉ። ቢሆን ጥሩ ነበር፣ ዕውኔታው ግን ከዚህ ለየት ያለ ነው። በ 1995 ዓ/ም ህገ መንግሥቱ ሲረቅቅ ስለነበረው ውይይት የቃለ ጉባኤውን ቅጂ ማግኘት አልቻልንም እንጂ፣ ኢትዮጵያ በዘጠኝ ክልሎች እንዴት እንደ ተከፋፈለች፣ ለምን ለፌዴራሉ መቀመጫ የሚሆን ስንዝር መሬት እንኳ እንዳላስቀሩ፣ ከዚያም ደግሞ በምን ምክንያት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ የፌዴራሉም ዋና ከተማ እንደሆነች ለማወቅ ይቻል ነበር። በሁለቱ ተቋማት መካከል ማለትም በኦሮሚያና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል የተካሄደ አንዳች ዓይነት የምሥጢር ስምምነት ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። አንዳች ዓይነት የሁለትዮሽ ውል ባይኖር ኖሮ ኩርማን መሬት እንኳ የተነፈገውና ግንድ የሌለው የፌዴራሉ መንግሥት አዲስ አበባ ዋና ከተማዬ ናት፣ በመሆኑም እኔ ነኝ የማዝበት ከማለት ባሻገር ለክልሉ ባለቤት ልዩ ጥቅም ጠባቂና አስጠባቂ አይሆንም ነበር። በራሱ ስም የተመዘገበ ስንዝር የምታክል መሬት የሌለው ሰው በራሱ ስም የቤት ካርታ ሲኖረው እንደ ማለት ነው።

በፌዴራሉ ህገ መንግሥት በተደተደነገገው መሰረት ዘጠኙ የፌዴራሉ አካላት የየራሳቸው የሆነ የክልላቸው ርዕሰ ከተማ አላቸው። ባቋቋሙት ክልላዊ ፓርላማና፣ ፓርላማዎቹም ባጸደቋቸው ህጎች ተመርተው ያለፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት፣ በርዕሰ ከተሞቻቸው ጭምር፣ ክልላዊ የአስተዳደር መዋቅር ዘርግተው ራሳቸውን ያስተዳድራሉ። የፌዴራሊዝም ዋና መገለጫውም ይኸው ነውና። የአማራው ክልል በባህር ዳር፣ የደቡብ ህዝቦች በሃዋሳ፣ ጉሙዝና ቤኒሻንጉል በአሶሳ እና የትግራይ ክልል ደግሞ በመቀሌ ከተሞች ላይ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተግባር ለመተርጎም የሚረዳ አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግተው የክልላቸውን ነዋሪ ህዝብ መብትና ጥቅም እያስጠበቁ ይገኛሉ። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም የክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ የራሱን አስተዳደራዊ መዋቅር ዘርግቶ የክልሉ ነዋሪዎችን መብትና ጥቅም እያስጠበቀ ነው። በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ያልኩት፣ የክልሉን ዋና ከተማ አዲስ አበባን በተመለከተ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ በሌሎች የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ባግባቡ የተጠቀመበት ስለማይመስለኝ ነው። ለምሳሌ የክልሉ የመሥርያ ቋንቋ የሆነው ኦሮሚኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ የመሥርያ ቋንቋ አልሆነም። በሌሎቹ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች እንደሚያደርገውም፣ በክልሉ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ የራሱን አስተዳደራዊ መዋቅርም በሥነ ሥርዓት አልዘረጋም። ለምን?

ዛሬ በወረቀት ደረጃ ያለው የቃላት ጥይት የመወራወሩ ጉዳይ ነገ ወደ እውነተኛ ጥይት ወይም ዱላ ሊቀየር ይችላል የሚል ሥጋት አለኝ። ችግሩ ደግሞ በጊዜ ካልተፈታ የባሰ አደጋ ሊያመጣ ይችላል። ታዲያ ምን መደረግ አለበት? ለማንኛውም ሰው ሰራሽ ችግር ሰው ሰራሽ መፍትሄ አለው ይላል ኦሮሞ ሲተርት። እኔም በዚህ እስማማለሁ። ችግሮቹን የፈጠርናቸው እኛው ስለሆንን መፍትሄውም በጃችን ነው። የእያንዳንዱ ህብረተሰብ ችግር ደግሞ የየራሱ የሆነ ይዘትና አፈጣጠር ስላለው የሌሎች አገር ተሞክሮዎችን እንዳለ ተውሶ ላገራችን ይሆናል ብሎ ማሰብ ትክክል አይመስለኝም። ለሁሉም ግጭቶች መፍቻ የሆነ አንድ ወጥ ሳይንሳዊ ፎርሙላ ስለሌለ ከዚህ በታች የማቀርበውንም መፍትሄ ከዚያ አንጻር እዩት ለማለት ያህል ነው። ከዚያ በፊት ግን በህገ መንግሥቱ መሰረት ሥራ ላይ መዋል ያለባቸውና በንትርክና ወከባ ሊቀየሩ የማይችሉ ዕውኔታዎችን ላስቀምጥና ወደ መፍትሄዎቹ ልዝለቅ።

ሀ) አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት። ከተማዋን ለማስተዳደርም ሆነ የወደፊት ዕጣዋን ለመወሰን የሚችለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ የኦሮሞ ሕዝብና በክልሉ በህጋዊነት የሚኖሩ ዜጎች ብቻ ነው። በሃዋሳና በመቀሌ ወይም በአሶሳና በባህር ዳር አስተዳደራዊ መዋቅርና የወደፊት ዕጣ ሌሎችን ክልል እንደማያገባቸው ሁሉ፣ በአዲስ አበባም ጉዳይ ሌሎችን ክልሎች የሚያገባቸው ሊኖር አይችልም ማለት ነው። ለ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚያካሄዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸውን ሰዎች ሁሉ በመንግሥቱ በቂ ዕርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ ማዘዋወሩ ፍጹም ህጋዊ ነው። በመሆኑም፣ የክልሉ መንግሥት፣ ተፈናቃይ የክልሉን ህዝቦች አዲስ አበባ አካባቢ ወይም በራሱ በአዲስ አበባ መሃል ከተማ ማስፈር ህጋዊ ነው። የተፈናቀሉ ዜጎችን በተለያዩ የክልሉ አካል የማስፈር ግዴታ፣ አያድርስና ከአዲስ አበባም ሰዎች ቢፈናቀሉ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ተፈናቃዮቹን ወደ አምቦ ወይም ሻሸመኔ ወስዶ የማስፈር መብትም ግዴታም አለበት ማለት ነው። አለበለዚያ ግን፣ ባንድ በኩል የኢትዮጵያውያንን በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በነጻ ተዘዋወረው የመሥራትና የመኖር መብት እንዲጠበቅላቸው እየተሟገትን፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የጎረቤት አገር ዜጎችን ያሰፈረ ይመስል ይህንንን ሰብዓዊ ድርጊት ለመኮነን መሞከር፣ ወይ የምንፈልገውን የማናውቅና ሰላምና መረጋጋት የሚረብሸን ፣ አለበለዚያ ደግሞ ሌላ ስውር የሆነ የፖሊቲካ ዓላማ ያለን ቡድኖች ነን።

ሐ) የአዲስ አበባን አስተዳደራዊ መዋቅርንና የክልሉ መሥርያ ቋንቋ የሆነውን ኦሮሚኛና በከተማው ጠቀሜታ ላይ አለማዋል ብስለት ያለው አካሄድ ይመስለኛል። በከተማው ያለው ኗሪ ህዝብ ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆነው ኦሮሚኛ ተናጋሪ አይደለምና! ለወደፊቱም በሚደረገው ድርድር፣ በከተማው የክልል መሥርያ ቤቶች ኦሮሚኛን የመሥርያ ቋንቋ አድርጎ አማርኛ ቋንቋን ደግሞ በፌዴራሉ ተቋማት የሥራ ቋንቋ ማድረግ የማንንም ዜጋ መብት የማይጥስ ትክክለኛ ውሳኔ ይመስለኛል።

መ) አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ስለሆነች በህገ መንግሥቱ 34 እና 39 መሰረት፣ የክልሉ መንግሥት፣ ለከተማዋ አስተዳደር፣ ከንቲባውንም ጨምሮ፣ ለቦታው ብቁ ነው/ናት ብሉ የሚያስበውን የክልሉን ኗሪ ከየትም የክልሉ አካል አምጥቶ ሊሾም ይችላል። ማንኛውም የክልሉ ህጋዊ ኗሪም ቶለሳም ሆነ ከፍያለው፣ ሃጎስም ሆነ ሄሌቦ የክልሉን የመሥርያ ቋንቋ ኦሮሚኛን እስካወቁ ድረስ፣ ተመርጠው ወይም ተመድበው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

ታዲያ መፍትሄው ምን ይሆን?

በርግጥ በሁለቱ ህገ መንግሥቶች መካከል የሚጻረሩ አንቀጾች ተካተዋል፣ ይህ በሁለቱ ተቋማት መካከል በውይይት መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው። በበኩሌ የህጎቹን ቃልና መንፈስ ስመረምር፣ ቁራጭ መሬት የሌለው የፌዴራሉ መንግሥት አዲስ አበባ የምትባል ዋና ከተማ አለው ብዬ ለመፍረድ ያዳግተኛል። አዎ የፌዴራሉ መንግሥት የግድ መቀመጫ ያስፈልገዋል፣ ለዚህ ተብሎ ግን ተከልሎ የተቀመጠ ወይም የተመደበ ቁራጭ የኢትዮጵያ ምድር የለም፣ ስለዚህ ዘጠኙም የፊዴራሉ አባላት ተስማምተው በአስቸኳይ አንዳች ዓይነት ውሳኔ ላይ መድረስ አለባቸው ባይ ነኝ። የተለየ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያላቸው መብት እንደተጠበቀ ሆኖ በበኩሌ ግን የሚከተሉትን አማራጮች ላቀርብ እወዳለሁ፣

ሀ) ክልሎቹ በየግላቸው ለፌዴራሉ መቀመጫ የሚሆን የተወሰነ መሬት ከክልላቸው ላይ ቆርሰው መስጠት ይችላሉ። ይህም ማለት የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ አማራ ወይም ጋምቤላ ክልል ውስጥ ሊሆን ይችላል ማለት ነው።

ለ) ክልሎች በጋራ ተስማማተው ለፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ የሚሆን የተወሰነ መሬት ቆርጠው ሊሰጡ ይችላሉ። የቪርጂኒያና ሜሪላንድ ስቴቶች የተወሰነ ስኩዌር ኪሜ ከራሳቸው ላይ ቀንሰው ዛሬ ዋሺንግተን ዲሲ ተብሎ የሚጠራውን ቦታ ለፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ እንዲሆን በስጦታ መልክ እንደሰጡ ማለት ነው።

ሐ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማውን አዲስ አበባን ለፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ ሆኖ እንዲያገለግል ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ልዩ ውል ሊፈራረም ይችላል። አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማና የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ የክልሉ መንግሥት የበላይ ሥልጣን ባለቤትነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፌዴራሉ መንግሥት በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅለት (ለምሳሌ መሬት ያለ ሊዝ እንዲወስድ፣ የውሃና የመብራት እንዳይከፍል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በፌዴራል መሥርያ ቤቶች የመሥርያ ቋንቋው አማርኛ እንዲሆን ወዘተ) ሊዋዋል ይችላል። ሁለቱም ጎን ለጎን ይኖራሉ ማለት ነው።

መደምደሚያ፣

የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ባገራችን ሲነሱ ከነበሩና እየተነሱ ካሉ የፖሊቲካ ጥያቄዎች በጣም ለየት ያለ ነው። በመጀመርያ ደረጃ፣ የኢትዮጵያን መሬት በግል ሃብትነት መያዝ እንደማይቻል እየታወቀ አዲስ አበባን የኔ ነው የኛ ነው የአዲስ አበቤዎች ወይም የሁሉም ብሄር ተወላጆች ነው ብሎ መሞገት ጉንጭ አልፋ ክርክር ይመስለኛል። አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ መሆኗ እየታወቀና የኦሮሞሕዝብና ሌሎች የክልሉ ህጋዊ ኗሪዎች ደግሞ የክልሉ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ በህገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ ተነድፎ እያለ፣ አዲስ አበባ ከዘጠኙ የፌዴራሉ ክልል አባላት በአንዳቸውም ያልተጠቃለለች እንደው በአየር ላይ የተንጠለጠለችና ከክልሎች አስተዳደራዊ መዋቅር ውጪ እንዳለች አስመስሎ ማቅረብና የተለየ ባለቤትነትን መጠየቅ ህገ መንግሥቱን መገዳደር ነው። አዎ፣ ህገ መንግሥቱ የህዝቡን ጥቅም አያስጠብቅም ተብሎ ከታመነበት ህጉን ተከትሎ የማይቀየርበት ምክንያት የለም። ይህ ደግሞ ህጋዊ ነው። ከሚቀጥለው የፓርላማ ምርጫ በኋላ ለሚሰየመው የህዝብ ተወካዮች ጉባኤ ላይ አቅርቦና አወያይቶ ህጋዊ በሆነ መንገድ ማስቀየር ብቻ ነው። እስከዚያ ድረስ ግን ወደድነውም ጠላነው፣ በህገ መንግሥቱ መሰረት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት። የክልሉ የሥልጣን ባለቤት ደግሞ የኦሮሞ ህዝብና በህጋዊነት በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች ነው፣ አራት ነጥብ!

በኔ ግምት፣ አዲስ አበባ የሁለቱም ዋና ከተማ በመሆኗ በውስጧ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊም ሆነ ሀጋዊ መብቶች አልተጣሱም። ይህ እንግዲህ የኔ እይታ ነው። ኦሮሞ ስለሆንኩ ሙላትን እንጂ ጉድለትን ሳላይ ቀርቼ ሊሆን ይችላል። ያልተገለጡልኝን ደግሞ አጥርቶ የማቅረብ ኃላፊነቱ የናንተ ተቃራኒ አስተሳሰብ የምታስተናግዱ ወገኖቼ ፈንታ ነው። በተረፈ ግን አፍቃሬ ግጭቶች የሚያናፍሱትን ወሬ ወደ ጎን ትተን በክልሉ ህገ መንግሥት ውስጥ የተካተተውንና የህጉም መንፈስ ወደ ተግባር ተተርጉሞ ስናየው፣ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ህጋዊ መኖርያ ያላቸውና የክልሉን መሥርያ ቋንቋ የሚችሉ የሌላ ብሄር ተወላጆች ከዞን ከወረዳና ከክልል ባላሥልጣንነት አልፈው በፌዴራል ደረጃ በኦፒዲኦ/ኦዴፓ አባልነታቸው ሚንስትርና ፕሬዚዴንትነት ሆነው ሲሾሙ ባይናችን በብረቱ እያየን ነው። የሚፈለገውና በየክልሎቹም ህገ መንግሥት የተደነገገው ይኸው ነው።

ውድ ወገኖቼ፣

ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ጉዳይ ቅድሚያ እንስጥ። የታዘብነው የሰብዓዊና ህገ መንግሥታዊ መብት ጥሰት ሳይኖር ዛሬ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄን ማንሳት፣ ከባዱን አገራዊ ችግር ለመጋፈጥ ፈርተን፣ ሌላ ጊዜ በሰላም ሊፈታ የሚቻለውን እዚህ ግባ በማይባል ጉዳይ ላይ ማተኮርና ህዝብን ማነሳሳት ቅንነት የጎደለው ይመስለኛል። እንዲያውም ዘንቦብሽ አሉ አበው! በብሄርና በኃይማኖት በመከፋፈላችን ብሄራዊ አገር (Nation State) መፍጠር አቅቷት እየተንገዳገደች ያለችና ለስምንት ሚሊዮን ሥራ አጥ ወጣት የሥራ ዕድል ለመክፈት አቅቷት ውጥረት ላይ ላለች አገር፣ በሁለት ጎረቤት አገሮች መካከል የተነሳ የድንበር ጥያቄ ይመስል የአዲስ አበባን ባለቤትነት ጥያቄ አንስቶ በየሚዲያው ላይ አንጋፋ ዜና አድርጎ ማቅረብና አዲስ አበቤዎችንና ያካባቢውን ወጣት ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ ለማይኖረው ግጭት ለማነሳሳት መሞከር ወንጀል ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ስምንት ሚሊዮን፣ ሊፈነዳ ጊዜውን እየጠበቀ ያለውን ቦምብ ወደ ጎን ትቶ ተከድኖ ቢቀመጥ በማይጎዳ ወይም ሌላ ጊዜ በውይይት ሊፈታ በሚችለው ጉዳይ ላይ ጊዜን ማጥፋት፣ አነሰ ቢባል ከኃላፊነት መሸሽ ነው። ስለዚህ በጥብቅ እናስብበት፣ አገራዊ ችግሮቻችንን እንደ አንገብጋቢነታቸው በቅደም ተከተል እንደርድርና እነሱን ለመፍታት ጉልበታችንን እናስተባብር። ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛልን።

 

***** አዲስ አበባ፣ ማርች 10 ቀን 2019 ዓ/ም Wakwoya2016@gmail.com

Back to Front Page