Back to Front Page


Share This Article!
Share
ለዉጥ ምንድን ነዉ? ህገመንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርአቱን አስጠብቆና አጠናክሮ መቀጠልንም ይጨምራል!

 

 

ለዉጥ ምንድን ነዉ? ህገመንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርአቱን አስጠብቆና አጠናክሮ መቀጠልንም ይጨምራል!

      የኦሮሚያ ህዝብና መንግስት አዲስ አበባን ዋና ከተማዉ ለማድረግ ቢደነግግ ህግመንግስታዊ ነዉ!

ብርሃኔ በርሄ ተስፋዬ 3-16-19

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ ያደረጋቸዉን ንግግሮች፤ በእርሳቸዉ መሪነት ስራ ላይ እንዲዉሉ የወጡ ህግጋትንና ተቆማዊ አደረጃጀቶች እና እርሳቸዉ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን የተከሰቱ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉሶችና ዉድመቶች በጥሞና ስከታተል ቆይቻለሁ። አብዛኞቹን ክስተቶችና ንግግሮቻቸዉንም ስቃወም ቆይቻለሁ። እርሳቸዉ ስለዚህ ግለሰብ ፀሀፊ ማንነት ለማወቅ የሚያስችል እዚህ ከምገልፀዉ በላይ መረጃ ደርሱዋቸዋል የሚል እምነት ስላለኝ ወደዝርዝሩ አልገባም። ሆኖም ግን ስወቅሳቸዉ የቆየሁትን ያህል ከሰሞኑ ንግግራቸዉ ዉስጥ ደግሞ እንዳከብራቸዉና እንዳመሰግናቸዉ እገደዳለሁ። ስለለዉጥ ስናወራ ትክክል ያልሆነዉን መቃወም ተገቢ የሆነዉን ያህል መልካም ተግባራትንና ንግግሮችን ማድነቅና መደገፍ ደግሞ ፍትሃዊነት ነዉ። ከዚህ አኳያም የፖለቲካ ፓርቲዎች የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፌዴራል እና ከክልል ህገመንግስታት አንፃር ህዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ለጠቆሙት ሀሳብ አድናቆቴን እገልፃለሁ። የኢፌዴሪ ህገመንግስት የደርግ እና የአፄ ሀይለስላሴ ስርአት አቀንቃኞች እንደሚሉት በኢህአዴግ ይሁንታ ብቻ የተመሰረተ አይደለም። ይህ እንዳልሆነ መገንዘብ የሚፈልግ ካለ ከሁለተኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተnማት ድረስ ለስነምግባርና ህገመንግስት ትምህርት የተዘጋጁትን ቴክስቶች ማንበብ ይችላል። ህገመንግስታችን በየደረጃዉ እና በየሴክተሩ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ መድረኮች እና ወቅቶች ባደረቸዉ መጠነ ሰፊ ዉይይቶች ይሁንታ የፀደቀ መሆኑን ለመገንዘብ የተሳታፊ ህብረተሰብ ክፍሎችን ዳታ ጭምር የሚያስገነዝቡትን የመማሪያ ቴክስቶች ማንበቡ ጠቃሚ ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ በዚህ ህገመንግስት ላይ ህዝበ ዉሳኔ ይሰጥ ቢባል አሀዳዊ የመንግስት አወቃቀር ለመመስረት የሚያቀነቅኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚንቀሳቀሱበት የአማራ ክልል ዉጭ ያሉት የኦሮሚያ፣የትግራይ፣የአፋር፣የሶማሌ፣የቤኒሻንጉል፣የጋምቤላ፣የሀረሪ እና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ህዝቦች ከ2/3ኛ በላይ በሆነ ድምፅ ህገመንግስቱ የሉአላዊ ማንነታቸዉ መገለጫ መሆኑን እንደሚያበስሩ ቅንጣት ታህል አልጠራጠርም። ህገመንግስቱን ለማፍረስ እየተሯሯጡ ያሉት የዉስጥና የዉጭ ፖለቲካ ሀይሎች በእርግጥም ይህ ህገመንግስት የህዝብ ድጋፍ የለዉም የሚል መተማመን ካላቸዉ ዝንተ ዓለም ከሚነተርኩንና ህዝብን እያተራመሱ ከሚኖሩ በየክልሎቹ በሰላማዊና ህገመንግስታዊ ስርአት መንገድ ተንቀሳቅሰዉ ህዝበ ዉሳኔ እንዲሰጥበት የሚያስችል ፔቲሽን ማሰባሰብ ይችላሉ። ድጋፍ የሚያገኙ ከሆነ ያን ጊዜ እናያቸዋለን! በአዲስ አበባና በአማራ ክልል እያዉደለደሉ የህዝብ ድጋፍ የለዉም ቢሉን ማንም አይሰማቸዉም። ይህን ማድረግ ካልቻሉ እንዲተዉን እንጠይቃቸዋለን። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህገመንግስቱን አስመልክቶ ያደረጉትን ንግግር ያደነቅኩትን ያህል ከህገመንግስታዊ ስርአቱ ጋር የሚጋጨዉን የወቅቱን ተግባርም ሳልነቅፍ አላልፍም። እንደሰማሁት ከሆነ ህጋዊ ፈቃድ ያላገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች የመግባቢያ ስምምነቱን ፈርመዋል። በበኩሌ የህግ ሰዉነት ያልተሰጠዉን የፖለቲካ ድርጅት የስምምነቱ አካል ማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የህግ የበላይነትንና ህጋዊ ስርአትን እንደመጣስ ይቆጠራል። ወደተነሳሁበት መሰረታዊ ጉዳይ ልመለስ።

Videos From Around The World

ስለለዉጥ ምንነት ለመናገር የተራቀቀ እዉቀት ያለዉ ፈላስፋ መሆንን አይጠይቅም። ቀለል ባሉ ምሳሌዎች ለማስረዳት ለዉጥ ማለት-

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ሀገርን መፍጠር

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ የሰዉ ልጆች በህይወት የመኖር መብትን ጨምሮ የሰዉ ልጆች ሰብአዊ መብቶች ይበልጥ የተጠበቀባት ሀገርን መፍጠር

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ አዳዲስ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶችን ነድፎ የሀገር ድህነትንና ስራ አጥነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን መጀመር

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ መጠኑ የጨመረ የዉጭ ምንዛሪ ክምችት መፍጠር

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ የህግ የበላይነት የተጠበቀባትን ሀገር አጠናክሮ ማስቀጠል

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል በተሻለ ደረጃ መተማመን የተፈጠረባትን ሀገር መገንባት

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ በመሪዉ የፖለቲካ ድርጅት መስራች ብሄራዊ ድርጅቶች መካከል የአንድነትና የመተባበር ስሜትን የሚፈጥሩ ፖለቲካዊ አስተሳሰብና የአመራር ሚናን ማሳካት

  ዛሬ ላይ በመሪነት ደረጃ ላይ ሆነን የምንመርቃቸዉ የልማት ፕሮጀክቶች ለ27 ዓመታት ኢህአዴግን ሲመራ የነበረዉ አካል የፖሊሲና የስትራቴጂ ዉጤቶች መሆናቸዉን የሚያደንቅ ፖለቲካዊና ህብረተሰባዊ አስተሳሰብን የሚፈጥር የአመራር ሚና መጫወት

  ቀደም ካሉት ጊዜአት ይልቅ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ህገመንግስታዊ መብትና ጥቅም የሚታገል ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ሰብእና ያለዉ ህብረተሰብን መፍጠር

  ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢፌዴሪ ህገመንግስት እና የክልሎች የራስን እድል በራስ የመወሰን ሉአላዊ ስልጣን ሳይሸራረፍና ሳይደበላለቅ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል የአመራር ሚና መጫወት

የሚሉት ጥቂት መገለጫዎች ሊሆኑ ይችላሉ ። በዚህ መነሻነት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ያለዉን መብት በተመለከተ ባይሳ ዋቅዎያ የተባሉ የህግ ባለሙያ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ በሕግ መነጽር ሲታይ በሚል ርእስ ለአይጋ ፎረም ካቀረቡት ፅሁፍ ዉስጥ አንዲት ሀረግ መዝ የበኩሌን አስተያየት ለመስጠት እንደሁልጊዜዉ ወደ አይጋ ፎረም ጎራ ብያለሁ። ጉዳዩ ከኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 49/5/ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነዉ። አቶ ባይሳ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሊደፍሩት ያልፈለጉትን የንኡስ አንቀፅ 5 ድንጋጌ ይዘት ህዝቡ መገንዘብ ይኖርበታል። አቶ ባይሳ በዚህ ረገድ ሁለት ፅንፎች መኖራቸን ቢገልፁም በበኩሌ አሁን ያለብን ፅንፈኛ ሀይል አንድ ብቻ ነዉ። ይህም የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠረ ብሄር ብሄረሰቦች በራሳቸዉ ፍላጎት ፈቅደዉና አምነዉበት ተከባብረዉ እንዲኖሩ ያስቻላቸዉን ህገመንግስታዊና ፌዴራላዊ ስርአት በማፈራረስ በሽግግር መንግስት ምስረታ ሰበብ ቀጣዩን ምርጫ ለማደናቀፍና ጥለናቸዉ ያለፍናቸዉን ጨnኝ ስርአቶች በግርግር ለመመለስ እየሰራ ያለዉ ቡድን ነዉ። የዚህ ቡድን ማስተር ማይንድ አባላት በኢህአዴግ ዉስጥም እንዳሉ ይሰማኛል። ይህ ፅንፈኛ ሀይል በአዲስ አበባና ኦሮሚያ የጥቅም ግንኙነት ሰበብ አጠቃላይ ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፍረስ የሚያስችል የትርምስ መድረክና የፖለቲካ ሁኔታ እንዲፈጠር የሚፈልግ የአሀዳዊ ስርአት አቀንቃኝ ነዉ። በኦሮሚያ በኩል ያለዉ የአዲስ አበባ ከተማን በዋና ከተማነት የሚጠይቅ ህገመንግስታዊ ድንጋጌም ሆነ አስተሳሰብ በኢፌዴሪ ህገመንግስ ያገኘዉን እውቅና እንጄ ከፅንፈኝነት የመነጨ እንዳልሆነ ቅን ለሆነ የህግም ሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጅ ዜጋ የሚደበቅ ሊሆን አይችልም። የኢፌዴሪ ህገመንገስት አንቀፅ 49/5/ ድንጋጌ አዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ . መሆኑን ይደነግጋል። ይህ ማለት ምን ማለት ነዉ?

 

ይህ ድንጋጌ የሚነግረን የኦሮሚያ ክልል የአዲስ አበባን ምድር ዋና ከተማ የማድረግ መብት ያለዉ መሆኑን ነዉ። ይህ መብት ባይኖረዉ ኖሮ የአዲስ አበባ መልከአምድራዊ አቀማመጥ የኦሮሚያ ክልል ስለመሆኑና የኦሮሞያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ የአስተዳደራዊ፤ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሊኖረዉ እንደሚችል መደንገጉ ባላስፈለገም፤ ትክክል ባልሆነም ነበር። መብትና ተጠቃሚነት ከባዶ ሜዳ አይገኝም። የኦሮሚያ ክልል እየጠየቀ ያለዉ መብት ከክልሉ መልከአምድራዊ ዉጭ ባለ በባህርዳር ወይንም በመቀሌ ወይንም በሀዋሳ ከተማ ሳይሆን በህገመንግስት እዉቅና ከተሰጠዉ በራሱ መልከአምድር ዉስጥ ባለ ቦታ ላይ ነዉ። በህገመንግስታችን መሰረት ኢትዮጵያ የተዋቀረችዉ በ 9 ክልሎች መሆኑ ትክክል ቢሆንም የኦሮሚያ ክልል ደግሞ አዲስ አበባን እንደሚያካትት በግልፅ ተደንግል። ይህ ከሆነ ዘንዳ የኦሮሚያ መንግስት የክልሌ አካል የሆነችዉን አዲስ አበባን ዋና ከተማዬ አደርጋለሁ በማለት በህገመንግስቱ ዉስጥ ቢያሰፍር ህገመንግስታዊ ነዉ። የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ አያስነሳም! ስለዚህም ከህገመንግስት አንፃር ሲመዘን ሁለት ጎራ የለም። የኦሮሚያ ክልል እስከአሁንም ከኢፌዴሪ ህገመንግስት ድንጋጌና አስተሳሰብ አላፈነገጠም። አዲስና የህዝቦችን ህገመንግስታዊ መብት በመፃረር ፅንፈኛ አስተሳሰብ ይዘዉ ጎራ እና ጭቅጭቅ እየፈጠሩ ያሉት የዚህችን አገር ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአት ለማፈራረስና ህዝብን ከጎናቸዉ ለማሰለፍ እንቅልፍ አጥተዉ ዉለዉ የሚያድሩት ናቸዉ። ፌዴራላዊና ህገመንግስታዊ ስርአቱን ለማፈራረስና ህዝቦችን ለማነሳሳት የአዲስ አበባን ጉዳይ በዋነኛ ስልትነት የሚጠቀሙት አፍራሽ ሀይሎች መንገድ ለዚህች አገር አያዋጣትም። የሚያዋጣዉ በህገመንግስቱ መሰረት ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ሰላማዊና የተባበረ መፍትሄ መፍጠር ብቻ ነዉ። የለዉጥ ጎዳና ሲባልም በህገመንግስቱ የተቀመጡትን የህዝቦችን መብትና ጥቅሞች ከምንጊዜዉም በላይ ተግባራዊ በማድረግ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ሀገርን መፍጠር እንጂ የሁዋልዮሽ የሚያስኬዱንን የነዉጥና የማፈራረስ መንገዶች መከተል ማለት አይደለም። ስለሆነም በእርግጥም ህግን በአግባቡና በቅንነት የመተርጎም ፍላጎት ካለን የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባን በዋና ከተማነት በህገመንግስቱ ዉስጥ የማስፈር ጉዳይ በኢፌዴሪ ህገመንግስት አንቀፅ 49/5/ ያገኘዉ እዉቅና እንጂ በፅንፈኝነት አስተሳብ ያሰፈረዉ አይደለም። የህገመንግስት ትርጉም ጥያቄ አያስነሳም። ህገመንግስታዊ ነዉ!

Back to Front Page