Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሀገራዊ ማዕቀፍ አልባ ሀገር!!!

ሀገራዊ ማዕቀፍ አልባ ሀገር!!!

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ 1-23-19

ሀገራዊ ማዕቀፍ ባሕሪያዊ የሰው ልጅ ታሪክ ጠባያዊ ውጤት ነው፡፡ ግላዊ የኾነው ሰው እንዳሻው በግለሰባዊ ማዕቀፍ እንዳይፈነጭ - ገደብ እንዲኖረው ቤተሰባዊ ማዕቀፍ አለ፡፡ ቤተሰቤ ምን ይለኝ ይኾን? ለቤተሰቤ ምን ላድርግ? ይላል፡፡ ራሱን ይገዛል፡፡ ፍላጎቱን በዛ ማዕቀፍ ይገድባል፡፡ ቤተሰብ እንደፈቀደው - እንዳሻው እንዳይኾን ከባቢያዊ ማዕቀፍ አለ፡፡ ከባቢ ምን ይለን ይኾን? ለከባቢ ምን እናድርግ? ይላሉ፡፡ ራሳቸውን ያስገዛሉ፡፡ ፍላጎታቸውን በዛ ማዕቀፍ ይገድባሉ፡፡

ከባቢያውያን እንዳሻቸው እንዳይኾኑ ሀገራዊ ማዕቀፍ አለ፡፡ ሀገር ምን ይለን ይኾን? ለሀገር ምን እናድርግ? ይላሉ፡፡ ሀገራውያን እንዳሻቸው እንዳይኾኑ አኅጉራዊ ማዕቀፍ አለ፡፡ የአኅጉራችን ሀገራት ምን ይሉን ይኾን? ለአኅጉር ምን እናድርግ? ይላሉ፡፡ ለአኅጉራዊ በአንጻሩ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፍ አለ፡፡ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ምን ይሉን ይኾን? ለዓለም ምን እናድርግ? ይላሉ፡፡

Videos From Around The World

እነዚህን የሚያስተሳስሩ ቤተሰባዊ፣ ከባቢያዊ፣ ሀገራዊ፣ አኅጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ሕግጋት፣ ሥርዓታትና ስምምነቶች ይኖራሉ፡፡ ዋነኛ አኹን ባለንበት ክፍለ ዘመን ዓለምን በኹለንተናዊ መልኩ እየመራና እያንቀሳቀሰ ያለ - ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፍ ሲኾን ሀገራዊ ማዕቀፍ ግን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡

የዓለም ሀገራት - በሀገራዊ ማዕቀፍ ነው እየተመሩ ያሉት፡፡ አሜሪካ በአሜሪካዊነት፤ እስራኤል በእስራኤላዊነት፤ እንግሊዝ በእንግሊዛዊነት፤ ጀርመን በጀርመናዊነት፤ ቻይና በቻይናዊነት፤ ሲንጋፖር በሲንጋፖራዊነት ፤ ህንድ በህንዳዊነት፤ ደቡብ ኮሪያ በደቡብ ኮሪያዊነት - - - መሠረትነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ከፖለቲካ፣ ከሐይማኖት፣ ከአካባቢ፣ ከጾታ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከአስተሳሰብና አመለካከቶቻችን - - - ወዘተ ልዩነቶቻችን በላይ የኾነ እኛ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ብቻ በመኾናችን ያለልዩነት በአንድነት፣ በሕብረት የምንቆምበት፣ ብሔራዊ መግባባት የፈጠረ አንዳች ነገር የለንም፡፡ ሕገ መንግሥት፣ ባንዴራ፣ ብሔራዊ መዝሙር፣ ሀገራዊነት፣ ሉዓላዊነት፣ ድህነት፣ ስደት፣ ሽብርተኝነት፣ - - - ወዘተ ብለን ሌሎች ሀገራት ከኹለንተናዊ ልዩነቶቻቸው በላይ አንድ የሚያደርጋቸው ሀገራዊ ማዕቀፍ አለ ብለን እንደምንጠቅሰው - እኛ የለንም፡፡ ሳንነጋገር የምንግባባበት፣ ሳንጠያየቅ በመንፈስ አንድ የሚያደርገን/ያደረገን አንዳች ነገር የለም፡፡ ሲጀመር ሀገራዊ ማዕቀፍ ሳይኖረን እንዴት ይኖረናል?

እኛ ያሉን ማዕቀፎች የፖለቲካ ኃይሎች፣ የገዥዎች፣ የከባቢ፣ የሃይማኖት - - - ወዘተ እንጂ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ብቻ በመኾናችን - ዜጋ በመኾናችን ብቻ አንድ ላይ የምንነሣበት፣ እልህ፣ ቁጭት የፈጠርንበት፣ እንቅልፍ ያጣንበት፣ በመንፈስ አንድ የኾንበት እምነት - ዕውቀትና ተግባር የለንም፡፡

ማንኛውም የሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር አሃዳዊም ይኹን ፌደራላዊ የራሱ አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች አሉት፡፡ ለዚህም ነው - ፍጹም የሚባል የሥርዓተ መንግሥት አወቃቀር ባለመኖሩ ሀገራት የተለያየ አወቃቀር የሚጠቀሙት - ለአብነት፡- አሃዳዊ በራሱ ሀገራዊነትን በማዳበር ራስን በራስ ማስተዳደር ላይ የራሱን ተጽዕኖ ሲያሳርፍ፤ ፌደራላዊ በአንጻሩ ራስን በራስ ማስተዳደርን በማዳበር ሀገራዊነት ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡ በመኾኑም የመሪዎች ትልቁ የመሪነት ድርሻ ይህን በመገንዘብና በመረዳት በመረጡት ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የሚኖርን አሉታዊ ገጽታ የመቀነሻና የማጣጣሚያ ዘዴዎችን በጥንቃቄ ማከናወን የተገባ ይኾናል፡፡

በሀገራችንም ከላይ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ነገሮች ከተከሱትባቸው ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ራስን በራስ በማስተዳደርና ሀገራዊነትን /ዜጋነትን/ ከሀገራዊ ማዕቀፍ ጋር አስተሳስሮ ያለመያዝ ችግር ከአስተሳሰብና አመለካከት ጀምሮ ከእምነት፣ ከእውቀትና ከድርጊት አንጻር በግለሰብም ኾነ በቡድን ብሎም በተuም ደረጃ ያለብንን ክፍተት የሚያሳይ ነው፡፡ ጥቅል ይዘትና ጭብጡም ሀገራዊ ማዕቀፍ አልባነት ነው፡፡

በሌላ በኩል በተግባር የሰሜኑ ልማት ለደቡቡ፤ የምዕራቡ ለምስራቁ፤ የደቡቡ ለሰሜኑ፤ የምስራቁ ለምዕራቡ ትርጉም ሊኖረው የሚችለው ሀገራዊ ማዕቀፍ ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ነው - የሰሜኑ የደቡቡ፤ የምዕራቡና የምስራቁ ብሎም የማዕከሉ ልማት ለሌላኛው ኩራትና የባለቤትነት ስሜት ሳይኾን የሐሜት፣ የንቀት፣ የቅናት፣ የፉክክር ምንጭ እንደኾነ - እንዳለ ኑሯችን ማሳያ ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተuማት፣ በአክሲዮን ማህበራት፣ በፖለቲካ ኃይሎች፣ በከባቢያዊነት ላይ መሠረት ያደረጉ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች፣ ከባቢያዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መበራከት፣ የዲያስፖራ እንቅስቃሴ፣ የከባቢያዊነት በከፍተኛ ደረጃ መንሰራፋት - - - የማሳያው አብነቶች ናቸው፡፡

ለአንዱ - የሌላኛው ኹለንተናዊ ኹኔታ ትርጉም የማይሰጠው መኾኑ የጊዜ ጉዳይ ካልኾነ በቀር ሀገራዊ አደጋ ነው፡፡ እያስተዋልን ያለነውም ይህን ነው፡፡ ምናልባትም ፉክክሩ ከዓለም ጋር/አንጻር ሳይኾን ከራስ ጋር እርስ በራስ ነው፡፡

ሀገራዊ ማዕቀፍ ስለሌለን የፖለቲካ ስትራቴጂዎቻችን ግላዊ፣ ቡድናዊ፣ ፓርቲያዊ ማዕቀፍ ይይዛሉ፡፡ ይህም በመኾኑ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ሚና ሳይኖራቸው በውስጥ አልያም በውጭ ኃይል ተጥለው በሌላ ይተካሉ፡፡

እስራኤላውያንን፣ አሜሪካውያንን፣ እንግሊዛውያንን፣ ሩስያውያንን፣ ቻይናውያንን፣ ደቡብ ኮርያውያንን፣ ሲንጋፖራውያንን፣ ግብፃውያንን - - - ወዘተ እንቅልፍ የሚነሣቸው ሀገራዊ ማዕቀፍ አለ፡፡ እኛንስ እንቅልፍ የሚነሣን ምንድን ነው? ሕብረተሰቡን እንቅልፍ የሚነሣው ምንድን ነው? ድህነቱ ወይንስ ድህነቱን ለማስወገድ የሚያደርገው ትግል? ተፎካካሪውንና ገዥውን እንቅልፍ የሚነሣው ምንድን ነው? ሥልጣን ወይስ በሥልጣኑ የሚሰራው ሥራ? ምሁሩን እንቅልፍ የሚነሣው የግል ሕይወቱ ወይስ የሀገሩ ኹኔታ? ባለሀብቱን እንቅልፍ የሚነሣው ምንድን ነው? የግል ሀብት ወይስ ሀገራዊ ሀብት? ተማሪውን እንቅልፍ የሚነሣው ምንድን ነው? ሰርተፍኬቱ ወይስ ዕውቀቱ? ሕዝብን እንቅልፍ የሚነሣው ሀገራዊ ራዕይ ሀገራዊ ግብና ሀገራዊ ዓላማ ነውን ወይስ ምንድን ነው? ድሃዎች እን ኾነን ድህነት እንቅልፍ የማይነሣንና ድሃ መኾናችን የማይቆጨን ለምን ይኾን? ስሜትስ የማይሰጠን ለምንድነው?

ሀገራዊ ማዕቀፍ በሌላት ሀገር ቡድናዊና ፓርቲያዊ ብሎም ግላዊ ማዕቀፎች የኹሉ ነገር ማያ መነሻ መሠረተ ሀሳብ ይኾናል፡፡ የሀገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሀገራዊ ማዕቀፍ የኹሉ ነገር ማያ መነሻ መሠረተ ሀሳብ ስለሌለው ልዩነትን መሸከም አይችልም፡፡ ኹሉ ነገር እንደኛ ብቻ፣ እኛ ያልነው ብቻ፣ እንዲኾን እንፈልጋለን፡፡ ከእኛ በላይ የኾነ ሀገራዊ ማዕቀፍ ስለሌለን የኛ ማዕቀፍ - የኛ ፍላጎት ይኾናል፡፡ ሀገር አልያም ሕዝብ የሚባለው እኔና እኛ የሚል ግለሰባዊ፣ ቡድናዊ፣ ከባቢያዊና ፓርቲያዊ ማዕቀፍ ማለት መኾኑ ነው፡፡

ሀገራዊ ማዕቀፍ ያላቸው ሀገራት ዜጎች - እርስ በራሳቸው እንደዜጋ ከፖለቲካ ልዩነቶቻቸው በላይ ይተማመናሉ፡፡ እንደዜጋ አይጠራጠሩም፡፡ ትግላቸው ከሀገር በመለስ ነው፡፡ እኛ ግን ሀገራዊ ማዕቀፍ ስለሌለን እርስ በራሳችን አንተማመንም፡፡ በጥርጣሬ እንተያያለን፡፡ ዜጋ ኾነን ሳለ አንደኛው አልሚ - አንደኛው አጥፊ በመኾን እርስ በራስ በጥርጣሬ ከመተያየት በዘለለ ለመጠፋፋት ከፍተኛ ትግል ይደረጋል፡፡ ይህም ፖለቲካችን በቃላት አጠቃቀም፡- በስድቦች፣ በፍረጃ፣ በዘለፋዎች፣ በአሽሙሮች - - - ወዘተ የተሞላ እንዲኾን አድርጎታል፡፡

ራስን ማሞኘት - ጆሮ እያለን ማናዳምጥ፣ ዐይን እያለን የማናስተውል፣ ስሜት እያለን ስሜት አልባ፣ ልብና ህሊና እያለን - ልብና ህሊና አልባ፣ አርቆ አሳቢ አለመኾን - መኾን ካልኾነ በስተቀር የትኛው የአዳማ ወጣት ነው - በመቐለ ከተማ ኹለንተናዊ ኹኔታ የሚኮራው? የትኛው የባህር ዳር ወጣት ነው - በጅጅጋ ከተማ የሚኮራው? የትኛው የአዲስ አበባ ወጣት ነው - በሰመራ የሚኮራው? የትኛው የሐረር ወጣት ነው - በጋምቤላ የሚኮራው? የትኛው የድሬዳዋ ወጣት ነው - በአሶሳ የሚኮራው? የትኛው የአዋሳ ወጣት ነው - በአዲግራት ከተማ የሚኮራው? ምን ተሰራና? ምን ተደረገና? የአንደኛው አካባቢ ልማት ለሌላኛው አካባቢ የኩራት፣ የእኔነት፣ የባለቤትነት ስሜት - - - ወዘተ በሚሰጥ መልኩ አይደለም ያለው፡፡

የአንድ ሀገር ዜጎች ኾነን ሳለ የነሱ' - የኛ' - የነዛ' ነው የምንለው፡፡ ሀገራችን ከማለት ይልቅ ሀገራችሁ'፤ አካባቢያችን ከማለት ይልቅ አካባቢያችሁ' ነው የምንለው፡፡ እርስ በራስ መተማመን የለንም፤ ከእኛ ይልቅ የእኔነት፤ ከሀገራዊነት ይልቅ ከባቢያዊነት ይበዛል፡፡

ሀገራዊ ማዕቀፍ ማበጀት ብንችል የመቐለ ልማት ለአዲስ አበባው፤ የባህር ዳር ልማት ለጅማው፤ የአዳማ ልማት ለሰመራው፤ የድሬዳዋ ልማት ለአሶሳው፤ የሐረር ልማት ለአZሱሙ፤ የአዋሳ ልማት ለጅጅጋው፤ የጋምቤላው ልማት ለጎንደሩ ትርጉም የሚሰጠው፤ የሚኮራበት፣ የጋራ ዕሴት በኾነ አልነበር? ኹለንተናዊ ነገሮችን በባለቤትነት፣ በእኔነት፣ በእኛነት ስሜት ማየት በተቻለ አልነበር? ብሔራዊ መነሣሣት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ብሔራዊ አንድነት፣ ብሔራዊ ሕብረት፣ ብሔራዊ የመንፈስ አንድነት ይኖር አልነበርን?

የአZሱም ጺዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን እጅጉን ትርጉም የምትሰጠው የደቡብ ኢትዮጵያ ክርስቲያን - አZሱም ከተማና ኹለንተናዊ ኹኔታዋ ትርጉም አትሰጠውም፤ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ትርጉም የሚሰጠው የምስራቁ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ - ፍቼ ከተማና ኹለንተናዊ ኹኔታዋ ትርጉም አትሰጠውም፤ ጊሸን ማርያም እጅጉን ትርጉም የምትሰጠው የምዕራብ ኢትዮጵያ ክርስቲያን - አማራ ክልልና ኹለንተናዊ ኹኔታዋ ትርጉም አትሰጠውም፤- - -

- - - ላሊበላ ትርጉም የሚሰጠው የደቡቡ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ - አማራ ክልልና ኹለንተናዊ ኹኔታዋ ትርጉም አትሰጠውም፤ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ /ዝuላ/ ገዳም፣ የቁልቢ ገብርኤል እጅጉን ትርጉም የሚሰጠው የሰሜኑ ክርስቲያን የኦሮሚያ ክልልና - ድሬዳዋ ከተማ ኹለንተናዊ ኹኔታቸው ትርጉም አይሰጠውም፤ የአልነጃሺ መስጂድ እጅጉን ትርጉም የሚሰጠው የሱማሌውና የአርሲው ሙስሊም - የትግራይ ክልልና ውቅሮ ከተማ ግን ትርጉም አትሰጠውም፤- - -

- - - የሐረር ቅዱስ የእስልምና መናገሻነት ትርጉም የምትሰጠው የሰሜኑ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም - ሐረር ከተማና ኹለንተናዊ ኹኔታዋ ግን ትርጉም አትሰጠውም፤ ቀዳሚ ከኾኑ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት አንዷ የኾነችው በኢሮብ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትርጉም የምትሰጠው በአዲስ አበባ የሚገኝ ካቶሊካዊ - ኢሮብና ትግራይ ግን ትርጉም ባለው መልኩ ትርጉም አትሰጠውም፤

ኹሉም እንደየዕምነቱ የሚኮራበት ነገር በሌላኛው የሀገሩ ክፍል የሚገኝ ቢኾንም እንደሀገራዊነቱ፣ የአንድ ሀገር ዜጋ እንደመኾኑ ሰፋ አድርጎ ማየትና መተንተን ባለመቻላችን - ከዕምነቱና ከዕምነቱ ታሪክ ባሻገር በሀገራዊነቱ በቦታውና በቦታው አካባቢ ያሉ ቦታዎች ዕምነቱ የሚሰጡትን የኔነት፣ የኛነት፣ የባለቤትነት ስሜትና ኩራት፤ ታሪኩን የተሸከሙት ቦታዎች አይሰጡትም፡፡ አይሰማውም፡፡ እንዲሰጠውና እንዲሰማው ትርጉም ያለው ሥራ አልተሰራበትም፡፡ በዕምነቱ ባለቤት የኾነበትን፤ በዜጋነቱባለቤት መኾን አልቻለም፡፡ ዜጋነት ላይ ትርጉም ያለው ሥራ አልተሰራም፡፡

በአንድ የሀገራችን ክፍል የሚገኝን ባህል፣uu፣ ልማድ፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ዕሴት፣ ዕድገት፣ ልማት፣ ብልጽግና፣ ገጠመኝ፣ ሐዘን፣ ደስታ፣ ችግር፣ ጉዳት፣ መከራና ሰቆቃ - - - እንደሀገር ዜጋነታችን ባህላችን፣uuችን፣ ልማዳችን፣ ወጋችን፣ ታሪካችን፣ ዕሴታችን፣ ዕድገታችን፣ ልማታችን፣ ብልጽግናችን፣ ገጠመኛችን፣ ሐዘናችን፣ ደስታችን፣ ችግራችን፣ ጉዳታችን፣ መከራችንና ሰቆቃችን - - - ማለት የሚያስችል እኛነት ወደ ያዘ ሀገራዊ ማዕቀፍ መሻገርና ማሻገር አልቻልንም፡፡

ለሀገራዊ ማዕቀፍ እጅግ በጣም ጠቃሚና በምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ሊገኝ የማይችል ትርጉም ያለው ታሪክና የታሪክ አሻራ ማንነት መገለጫችንን - አርቆ በማሰብ፤ ለሀገራዊ መንፈስ አንድነት መጠቀም ሲገባን - እዛው ባለንበት አለን፡፡ ሀገራዊ ማዕቀፍ አልባ ሀገር የመኾናችን አንዱ ማሳያ ይኸው ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን እንዳንቀላፉ ናቸው፡፡ ሀገራዊነት ገና ትርጉም ባለው መልኩ የገባቸው አይመስሉም፡፡

እንደሌለንም ያለንበት ነባራዊ ኹኔታ በተለይም ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንˆ ሲመረጡ ከባቢያዊ ኮታን መሰርት ያደረጉ መኾናቸው፤ አቅምና ብቃት የሌላቸውና እንደሌላቸው ለዓመታት ያስመሰከሩ ግለሰቦች በተደጋጋሚ መሾማቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተuማት ቦርድ አመራሮችና ፕሬዝደንቶች ራሳቸው በከባቢያዊነት ላይ ተመስርተው የሚመረጡ መኾናቸው፤ በሀገራችን ከባቢያዊነትን መሰረት ያደረጉ የፋይናንስ ተuማትና አክስዮን ማኅበራት መበራከታቸው - - -

- - - እንˆንስ እንደሀገር ሀገራዊ ማዕቀፍ ሊኖረን ይቅርና - ሀገራዊ ፓርቲዎች ብቻ ሳይኾኑ ገዥው ፓርቲ ራሱ ከሩብ ክፍለ ዘመን ቆይታው በኃላ እንˆ ገና ከግንባርነት ያልወጣ መኾኑ፤ በግንባርነቱም ቢኾን ዕውን ነባርና አንጋፋዎቹ መስራቾችና አመራሮች በተፈጥሮ፣ በእድሜና በአስገዳጅ ኹኔታዎች ዘወር ቢሉ አብዛኛው መካከለኛ አመራር እርስ በራሱ በመንፈስ ተግባብቶና አንድ ኾኖ ሊሰራ ይችላልን; የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ጎልተው በመታየት ላይ መኾናቸው፤ ገዥው ፓርቲ ራሱ ለሀገር የሚጠቅሙ አመራሮች ብሎ አመራሮችን ከመምረጥ ይልቅ በኮታና በውክልና መምረጡ - - -

- - - በዚህም በገዥው ፓርቲ አመራርና አባሎች ዘንድ ያለ አለመተማመን ይህም በአባል ድርጅቶች አመራሮችና አባሎች ዘንድ እርስ በራሳቸው በነጠላ የሚያነሡትና የሚያሙትን ሌሎች ሲመጡ ለማንሣት አለመድፈር፤ ከጥቂቶች በቀር የገዥው ፓርቲ አመራሮች እንደተወካይ እንጂ ትርጉም ባለው መልኩ እንደሀገር መሪ የማይታዩ መኾናቸው፤ የገዢው ፓርቲ አባሎች አፋቸውን ሞልተው በምክንያትና በዕውቀት ላይ ተመስርተው 'መሪዎቻችን' የሚሏቸው አመራሮች በብዛት አለመኖር ምክንያቱም አብዛኛዎቹ አመራሮች በብቃትና ችሎታቸው ሳይኾን በከባቢ አመጣጣቸው የተመረጡ የውክልና ሹመኞች በመኾናቸው እንˆንስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሕዝብ መሪዎቻችን ሊላቸው ይቅርና የገዛ አባሎቻቸው እንˆ በአደባባይ መሪዎቻችን ብለው አፋቸውን ሞልተው በምክንያት ስለስብዕናቸውና ብቃታቸው ሊከራከሩላቸው የሚችሏቸው አለመኾኑ - - -

- - - ገዥው ፓርቲ ኹሉን ነገር የመቆጣጠር - በአንድ አመለካከት ስር እንደቧንቧ ለመቆጣጠር መሻት፤ በዲያስፖራ ያለው ከፍተኛ የከባቢያዊነት እንቅስቃሴ፤ የታሪካዊ መጻሕፍት የከባቢያዊነት ንትርክ፤ የሃይማኖት ተuማት በከባቢያዊነት መታመስ፤ ባህልን መሰረት ያደረገ ሥርዓት አለመኖር፤ የሚዲያዎች የርስ በራስ መናቆርና መናናቅ፤ የምሁራን ስደት፤ የባለሀብቱ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ መበራከት፤ በሀሳብ ላይ የተመሠረቱ የውይይት - የምክክር - የክርክር መድረኮች አለመበራከት፤- - - ትላልቅ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል የሰሜኑ ለደቡቡ፤ የምዕራቡ ለምስራቁ፤ የማዕከሉ ኹለንተናዊ ኹኔታ እንዲሁ ለሌላው የኩራት ምንጭ በኾነ ነበር፡፡

በዓለም ላይ አንድስ እንˆ ያለ ሀገራዊ ማዕቀፍ ስር ነቀል ለውጥ ያመጣ ሀገር የለም፡፡ በመሠረተ ሀሳብ ደረጃም ሊኖር አይችልም፡፡ ከውክልና ሹመት ፖለቲካና ከቲፎዞ ፖለቲካ ወደ ትርጉም ያለው በዕውቀትና በምክንያት ላይ ወደ ተመሠረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ካልገባን በቀር ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡ ለዚህም እስከዛሬ ከተዝንበት የተሳሳተ መንገድ ባሻገር - የሌሎች ሀገራት ስኬት ለዚህ ማሳያ ነው፡፡

ጃፓን፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ኩባ - - - ወዘተ ታሪካቸውን የተመለከትን እንደኾነ ስር ከሰደደ ድህነት መውጣት የቻሉት በሆድ ልማት ሳይኾን በጭንቅላት ልማት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በሀገራዊ ማዕቀፍ - ሀገራዊነት ላይ ተመስርተው ነው፡፡ አንዳቸውም ሀገራዊነትን ትርጉም ባለው መልኩ ሳያቀነቅኑ፤ ሀገራዊ ማዕቀፋቸውን መሰረት በማድረግ ሀገራዊ ቁጭትና እልህ ሳይፈጥሩ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለደረሱበት ደረጃ መድረስ አልቻሉም፡፡

ደቡብ ኮርያውያን በመላው ዓለም የሚገኙ ኮርያውያንን አስተባብረው ነው - ታላቅ ደረጃ መድረስ የቻሉት፡፡ ከፖለቲካ ልዩነቶቻቸው በላይ ኮርያዊ ቁጭት ታላቅ ደረጃ አደረሳቸው፡፡ የቅኝ ገዥያቸው ጃፓን ሀገራዊ ዕድገት መነሻ የኾነው ጃፓናዊ ቁጭት - ታላቅ ደረጃ እንዳደረሳቸው ያውቃሉና እነሱም ኮርያዊ ቁጭትን - በሀገራቸው መፍጠር ቻሉ፡፡ መሪዎቻቸው ታላቅ ናቸው - ከራሳቸው በላይ ስለሀገራቸው የሚጨነቁና እንቅልፍ የሚነሣቸው - ታላላቅ ትርጉም ያለው ሀሳብ የገባቸው - የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ የገባቸው - የሀገራዊ ማዕቀፍ ምሥጢር የገባቸው ታላላቆች ናቸውና ታላቅ ሥራ ሰሩ፡፡ እኛስ?

እኛ ባለችን አቅም የረዳናቸው ኮርያውያንን የመሳሰሉ ሀገራት ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መኾን ሲችሉ - እኛ ግን ገና ባለንበት እንረግጣለን፡፡ ኮርያውያን በዓለም ቀዳሚና ተወዳዳሪ ለመኾን 33 ዓመታት ሲወስድባቸው - እኛ ገና አኹን ያለንበትን ሥርዓት እንˆ ብንወስድ - ይኸው ሩብ ክፍለ ዘመን ሞላ ለውጥ መኖሩ ባይካድም መሠረታዊ (ስር ነቀል) ለውጥ ግን እስካሁን የለም፡፡

ደቡብ ኮርያውያን በኮርያዊነት ማዕቀፍ፤ ጃፓናውያን በጃፓናዊነት ማዕቀፍ፤ ሲንጋፖር በሲንጋፖራዊነት ማዕቀፍ፤ ቻይናውያን በቻይናዊነት ማዕቀፍ፤ እንግሊዛውያን በእንግሊዛዊነት ማዕቀፍ፤ ጀርመናውያን በጀርመናዊነት ማዕቀፍ፤ እስራኤላውያን በእስራኤላዊነት ማዕቀፍ፤ ኩባውያን በኩባዊነት ማዕቀፍ፤ - - - ቀን ከለሊት ሲተጉ እኛ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ መትጋት አልቻልንማ! ሥር ነቀል ለውጥ እንዴት ብሎ ይምጣ? ሰው እኮ የዘራውን ነው የሚያጭደው፡፡ የአንድ ሥርዓት ምንነት በሥራው ይታወቃል፡፡

የሀገራችን ሕዝብ ብዛት መበራከት በራሱ ከባቢያዊነትን አጥፍቶ ህልውናችንን ይፈታተናል፡፡ እንዲያውም ከባቢያዊነት - ንዑስ ከባቢያዊነት እንዲያፈርሰው - ከዚያ በታች ንዑሳት ከባቢያት ሲበራከት የከባቢ - ከባቢ - ከባቢ ትግሉ ለሕዝብና ለሀገር አይበጅም፡፡

በሀገራችን ፖለቲካችን ከባቢያዊነትን መሠረት ያደረገ በመኾኑ ከባቢያዊ ማዕቀፍ ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳል፡፡ ይህም በከባቢያዊነት በተuuሙ የፖለቲካ ኃይሎች ብቻ ሳይኾን ሀገራዊነትን ጭምር የሚያቀነቅኑ ኃይሎች በከባቢያዊነት ላይ የቆሙና የሚቆሙ ናቸው፡፡ ይህም ማለት በሀገራዊነታቸው ውስጥ በግልጽም ኾነ በውስጠ ታዋቂነት ከባቢያዊነት ይኖራቸዋል፡፡ ይህም የኾነው ሀገራዊ ማዕቀፍ የሌለን በመኾኑ ነው፡፡

አሜሪካውያን በዋሽንግተን ከተማቸው ያለልዩነት በከተማው ተወልደው ካደጉት በማይተናነስ መልኩ በሌላው ግዛት የሚኖሩ ዜጎች በዋሽንግተን ከተማ ይኮራሉ፡፡ የእኔነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ከተማችን እያሉ ያወራሉ፡፡ ከተማቸው እንደኾነች ያምናሉ፣ ያውቃሉ፣ ማመናቸውንም፣ ማወቃቸውንም በኹለንተናዊ ድርጊት ይገልጻሉ፡፡

በተመሳሳይ መልኩ እስራኤላውያን፣ ጃፓናውያን፣ እንግሊዛውያን፣ ጀርመናውያን፣ ደቡብ ኮርያውያን፣ ሜክሲውያን፣ ሲንጋፖራውያን፣ ህንዳውያን፣ ሩስያውያን፣ ቻይናውያን፣ ግብጻውያን - - - ወዘተ ተመሳሳይ ተርዕዮ ያሳያሉ፡፡ ታሪካቸው የአንዱ አካባቢ ለሌላው ትርጉም ባለው መልኩ በእኔነት ይመለከቱታል፡፡

ትልቁ ነጥብ በእኔነትና በእኛነት መመልከታቸው ብቻ አይደለም፡፡ እንደዛ እንዲሉ ያደረጋቸው ሀገራዊና ሕዝባዊ የተስፋ ዕምነት፣ ዕውቀትና ድርጊት አለ፡፡ የዚህ ምንጭ የኾነ ሀገራዊ ማዕቀፍ እንዲሁ ለሀገራዊ ማዕቀፋቸው ደግሞ ምሰሶ የኾነ ሀገራዊ ራዕይ፣ ሀገራዊ ግብ፣ ሀገራዊ ተልዕኮ እና ሀገራዊ ዓላማ አለ፡፡ ይህንን የሚያዳብሩ ግለሰባዊ፣ ቡድናዊና ተuማዊ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ፡፡ እኛ ግን በታሪክ ንትርክ ውስጥ የእኛ፣ የእነሱ፣ የእነከሌ፣ የነእከሊት እንላለን፡፡ እንደአንድ የሀገር ዜጋነታችን - የአንደኛችን ታሪክ የሌላኛችን ታሪክ መኾኑ አልገባንም፡፡ እንዲገባን ሥራ አልሰራንም፡፡

በህንድ - ህንዳውያን "ከፖለቲከኞች ይልቅ ሥርዓቱን (the system) የሚደግፉ ናቸው፡፡" ዜጎች በሥርዓቱ (system) ላይ እምነት አላቸው፡፡ በሥርዓቱ አንቀሳቃሾች ላይ ካላቸው እምነት ይልቅ በሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት የላቀ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ታዳጊ ሀገራት ግን በአንቀሳቃሾች ላይ ብቻ ሳይኾን በሥርዓት ላይ ራሱ እምነት የሌለን መኾኑ ያሉብንን ችግሮች እጅጉን አወሳስቦት ይገኛል፡፡ ሀገራዊ ማዕቀፍ ሳይኖር በሥርዓት ላይ እምነትና ተስፋ ማሳደር አይቻልም፡፡

ሀገራዊ ማዕቀፍ በሌለበት ሀገር ውስጥ ከባሕሪያዊና ጠባያዊ 'የእኔነት' ስሜት እጅጉን ከፍ ያለና 'ለኔ' ከማለት አልፎ 'ለእኔ ብቻ' የሚል እምነት፣ ዕውቀትና ድርጊት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ በአንጻሩ ሀገራዊ ማዕቀፍ ባላቸው ሀገሮች 'የኛነት' ስሜት በእምነት፣ በዕውቀትና በድርጊት ደረጃ በእጅጉ የሚዳብር በመኾኑ 'እኛነት' ከፍ ብሎ 'ለሌላው ዋጋ መክፈልን' ጭምር የሚይዝ ይኾናል፡፡(ከሸክም የበዛበት ትውልድ 2009 ዓ.ም - ገጽ 138 149 የተወሰደ) ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Back to Front Page