Back to Front Page

የውህደት ዓላማ፣ ውጤቱ እና ዕጣ ፈንታው

 

 

የውህደት ዓላማ፣ ውጤቱ እና ዕጣ ፈንታው

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

 

ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ

ህዳር 2011 ዓ.ም

 

ይህ ኣጭር ጽሁፍ በጥድፊያ እየተደረገ ስላለው የኢህኣዴግ የመወሃድ ሂደት እና ውጤቱን ኣስመልክቶ ኣስተያየት ይሰጣል። በግልፅ ስለማይነገረው የውህደቱ ዋና ዓላማ ኣስመልክቶም ኣንዳንድ ጭብጦችን በማጣቀስ የደመደምኩትን ኣካፍላለሁ። በመጨረሻም ውህደቱ ሊፈጥረው ስለሚችለውን ሁኔታ በመጠቆም ይቋጫል። ለመሆኑ መወሃድ ለምን ኣስፈለገ? ዓላማውስ ምን ይሆን? የባህርዳሩን ጉባኤ ተከትሎ ካቀረብኩት ኣንድ ኣጠር ያለ ኣስተያየት የሚከተለውን ይገኝበታል።

'እንደዚህ ኣይነት ሃሳብ [የመወሃድ] የሚያነሱ ሃይሎች ኣገሪቷ በተወሃደ ህብረብሄራዊ ፓርቲ እንድትመራ ካላቸው መልካም ምኞት የመነጨ ሳይሆን በዋናነት ብዙሃነትን ካለመቀበልና ብሄርን መሰረት ኣድርገው የቆሙት የፖለቲካ ድርጅቶችን ህልውና ላማክሰም የታሰበ ዘዴ ነው። ይህ ደግሞ ወዴት እንደሚያመራ መገመት ኣይከብድም። የድርጅቶቹ ህልውና በማክሰም በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ እና ማንነት የተዋቀሩት ክልሎችም በመልክኣ -ምድር እንዲከለሉ መጠየቁ ኣይቀሬ ይሆናል። ይህ ማለት ደግሞ በቀጥታ በብሄር የተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶችን ህልውና ብቻ ሳይሆን በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ የተመሰረቱት የክልሎች ህልውናም የሚፈታተን ይሆናል። በኣጭሩ ህገ መንግስቱና ፌደራላዊ ስርኣቱ ተጥሶ ጉዞ ወደ ኣሃዳዊ ስርኣት መመልስ ይሆናል ይላል (ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ January 2018)።

Videos From Around The World

የድርጅቶች መወሃድ ሃሳብ ዋና ጠንሳሹ ማን እንደሆነ በግልፅ ባይነገርም ኢህኣዴግን የመሰረቱ ኣራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሃሳቡን ተቀብለው ለረጅም ጊዜ ሲወያዩበት እና ሲያጠኑት እንደከረሙ ሁሉም ሲገልጹ ሰምተናል። ሃሳቡ ከየትኛውም ድርጅት መጣ የሚለውን ኣንድ ጉዳይ ሆኖ ካለፈው ኣመት ጀምሮ ጉዳዩን እየገፋበት ያለው ግን ኣሁን ግንባሩን በሊቀ መንበርነት እየመራ ያለው ዶ/ር ኣብይ ኣህመድ እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው። የውህደት ሃሳብ ሲጀምር በቅንነት ኣሊያም ስልጣን ወደ ቤተ መንግስት ለማጋብስ ታስቦ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቢቻልም ኣሁን በጥድፊያ እየተካሄደ ያለው የውህደት ሂደት ግን የብሄር ድርጅቶችን ኣክስሞ በብሄር ድርጅቶች ኣማካኝነት የተፈጠረውን የፌደራል ስርኣት ወደ ኣሃዳዊ ስርኣት መለወጥ እንደ ዓላማ ይዞ የተነሳ እንደሆነ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች ኣሉ።

ይሄውም በኢህእዴግ ኣባል ድርጅቶችና በግምባሩ ፕሮግራም ኣማካኝነት ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የበቃው ኣብይ ኣህመድ ቢሮ ከገባበት ቀን ጀምሮ ለስልጣን ያበቁትን ድርጅቶችና ፕሮግራም እርግፍ ኣድርጎ በመተው ኣገሪቱን ለመቀራመት ካሰፈሰፉ የወጭ ሃይሎችና በህዝብ ያልተመረጡ እና ኢህኣዴግን በጠላትነት በመፈረጅ በትጥቅ ሳይቀር ሊፋለሙት ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የድርጅት መሪዎች ጋር እጅና ጓንት በመሆን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የማያውቃቸውን ህጎች እስከ ማርቀቅ የደረሰ ግንኙነት ማድረግ መርጠዋል። እንደሚታወቀው ከደርግ ሚኒስትሮች እስከ ጉንበት ሰባት ኣመራሮች፣ ከኤርትራ መንግስት እስከ ኣሜሪካና የዓረብ ኣገሮች ተወዳጅተዋል፤ የእነዚህ ሃይሎች ምክር እየተከተለ እንደሆነም የኣደባባይ ሚስጥር ነው። የተወሳሰበውን የውጮቹን ግንኙነት ትተን ያልተወሳሰበውን የኢትዮጵያውያኑ ግንኙነት ብቻ ለማየት ብንሞክር የጠ/ሚኒስትሩን እንቅስቃሴዎች በግልጽ መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ከደርግ ሚኒስትሮች እና ከግንቦት ሰባት በኣደባባይ የሰጡዋቸው ምክሮችን ዋናዋናዎቹ ለመጥቀስ ያክል፡

የደርጉ ዶ/ር ካሣ ከበደ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጋበዙ የመጀመሪያው እንግዳ ሲሆኑ (በVIP status) ኣዲስ ኣበባ ድረስ በመምጣት ስለ ኣገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታና ኣካሄድ ብስፋት እንደመከሩ በመግለጽ በጠ/ሚኒስትሩ ተስፋ መሰነቃቸው ከጀኖሳይድ ኣቀንቃኙ ሚዲያ (ESAT) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መግለፃቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ኣዲስ ኣበባ በተካሄደው የመጀመሪያው ቪዥን ኢትዮጵያ ባዘጋጀው ስብሰባ ፅሁፍ ያቀረቡት የደርጉ ሺ/ቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ለጠ/ሚኒስትሩ የሚከተሉትን ምክር ለግሰዋል፡ ፓርላማው ያፍርሱ፣ ኣገሪቱ በኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ስር ያስገቡ፣ የሽግግር መንግስት ይቋቋም፣ ህገ መንግስቱ ተጥሎ በኣዲስ ህገ መንግስት ይተካ፣ ኣሁን ያሉት ክልሎች በመልከኣ ምድር ይከለሉ፣ የክልል መንግስታት ወደ ክፍለ ሃገር መስተዳድር ይውረዱ፣ የብሄር ድርጅቶች በህግ ይከልከሉ፣ በየክልሉ ያሉት ልዩ ሃይሎች ይፍረሱ፣ ትጥቅም ይፍቱ ወዘተ በማለት ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኣብይ ኣህመድ መንግስት የሚመራበት ያለው ሮድ-ማፕ እንደሰጠ በኣደባባይ የተናገረው የግንቦት ሰባቱ ኣንዳርጋቸው ፅጌም ኣገሪቱ የገባችበት ኣሳሳቢ ሁኔታና የችግሩ ምንጭ ነው የሚለው ምክንያት በመዘርዘር መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ይወተውታል። ኣንዳርጋቸው በሺ/ቃ ዳዊት የተዘረዘሩት ሁሉ በራሱ ቋንቋ በመድገም ፈራርሳ 20 % ቀራት የሚላትን ኢትዮጵያን ለማዳን ጥሪውን ለመንግስት ያቀርባል። ይህ ይፈጸም ዘንድም ጠ/ሚንስትሩ ወታደራዊ ሃይል ተጠቅመው ክልሎችን ማፍረስ እንደሚኖርባቸው ጎትጎታውን ቀጥሏል። በግንቦት ሰባት (የኣሁኑ ኢዜማ) የሚመራው የኢንተራሃምዌ ESAT ቴሌቪዥን እና ኢትዮጵያዊነት በሚሰብኩና ብዙሃነት በማይቀበሉ ሃይሎች የሚንቀሳቀሱ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሚዲያዎችም ብዙሃነትን እውቅና የሰጠውን የፌደራል ስርኣቱ የሁሉም ችግር ምንጭ ኣድርገው በማቅረብ ህገመንግስታዊ ስርኣቱን ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ በማፍረስ ችግሩን መፍታት እንደሚቻል ሳይታክቱ ጉጎታቸውን ቀጥለዋል።

ቀድሞውንም ቢሆን ከዚህ ኣስተሳሰብ ጋር ተዛምዶ የቆየው ጠ/ሚኒስተር ኣብይ ከላይ የተሰጠውን ምክር ይፈጸምለት ዘንድ የመጀምሪያ እርምጃ ኣድርጎ የወሰደው ቀደም ሲል በግምባሩ ኣባላት ይጠናል የተባለውን የውህደት ጉዳይ ነው። በመሆኑም ውህደት የብሄር ድርጅቶችን የማክሰምያ (የማጥፍያ) እጅግ ወሳኝ መሳሪያ ኣድርጎ በመውሰድ ለስኬቱ ተንቀሳቅሰዋል። የብሄር ድርጅቶች በተለይም ህወሓት እንደ ዋና የብሄር ኣቀንቃኝና ለሌሎች ድርጅቶችም እንደ መጥፎ ኣርኣያ ብሎም እንደ ጠላት በመታየቱ ህወሓትን በውህደት ስም ማክሰም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር በወሳኝ መልኩ እንደሚቀይረዋ ታምኖበታል። የዚህ እርምጃ መሳካት ወደ ቀጣይ እርምጃ፣ ማለትም ከላይ የተጠቀሱት ምክሮች ሁሉ ለማስፈፀም ሰፊ ዕድል እንደሚከፍት እርግጠኛ በመሆናቸው በፖለቲካ እምነታቸው እና ኣካሄዳቸው በተቃርኖ የቆሙትን የግምባሩ ኣባላት የድርጅቱን ህገ ደምብ፣ የምርጫ ቦርድ ህግ እና በኣጠቃላይ ህገ መንግስቱ በሚጥስ ኣካሄድ ውህደቱ እንዲፈጸም እየተጣደፉ ይገኛሉ።

በዚህ ሁኔታ የታቀደበት ሴራ የገባው ህወሓትም የዓላማ ኣንድነት እና የሚዋሃዱበት ፕሮግራም በሌለበት ሁኔታ በሚል ውህደቱ እንደማይቀበል ኣስታወቀ። በእርግጥም ኢህኣዴግ በኣባል ድርጅቶች መካከል የዓላማ ኣንድነት፣ እምነት እና የኣሰራር ስምምነት የሌለው ግምባር ሆነዋልና በዚህ ሁኔታ እያሉ ለውህደት መጣደፍ የጤና እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ዶ/ር ኣብይ ኣህመድም ያሰበውን በኣንድ ስብሰባ ይፈጸም ዘንድ የተቻለውን ሁሉ ቢያደርግም ህወሓትን ለማሳመን ባለመቻሉ የተቀሩት ሶስቱን ድርጅቶች ወክለው የመጡትን የሥራ ኣስፈፃሚ ኣባላት ኣብላጫ ያለውን ድምፅ ከጎኑ በማሰለፍ ስብሰባውን ተጠናቅቀዋል። ውጤቱ ከስብሰባው በፊት የታወቀው ቢሆንም በኣንድ በኩል የድል ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት መቻኮል ሲታይ በሌላ በኩል ግን ሊቀመንበሩ የህወሓት መሪዎች ብቻ በመለየት ለማግባባት የድህረ ስብሰባ ሙከራ ማድረጉን ታውቀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢህኣዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ለማድረግ ኣባል ድርጅቶችን ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ህወሓትም በቅርቡ የተደረገው ስብሰባ እና የተወሰደው ውሳኔ የግምባሩ ህገ ደምብ የጣሰ እንደሆነ በመግለጽ በምክርቤቱ ስብሰባ እንደማይገኝ ኣስታውቀዋል። ይልቁን የመወሃድ ጉዳይ በየደረጃው ውይይት ከተደረገበት በኋላ በህወሓት ጉባኤ ባቻ እንደሚወሰን ኣስምሮበታል።

ሂደቱ እስከ ኣሁን ባለው ሲታይ የግምባሩ ህገ ደምብና ሌሎች ተያያዥ ህጎች በመጣስ ውህደቱ ሊፈጸም እንደሚችል መገመት ይቻላል። ዶ/ር ኣብይ በኣንድ ንግግሩ እንዳለው የተወሃደው ድርጅት የኦሮሞ፣ የኣማራ፣ የሶማሊያ፣ የኣፋር፣ የቤንሻንጉል ወዘተ የሚባል ኣይኖርም። የኢትዮጵያ ፓርቲ እንጂ። በእርግጥ የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ ሲባል የሰነበተው በመሰራት ላይ የሚገኘው ስብስብ ሰሞኑን ባወጣው ህገ ደምቡ ላይ ኢትዮጵያ የምትለዋን በመሰረዝ የኣሃዳዊነት ምስሉ እንዳይታይ ሊደብቅ የሞከረ ይመስላል።

እንግዲያውስ በዚህ ሁኔታ የተወሃዱት ድርጅቶች በውህደቱ ማግስት የነበራቸው የብሄር ውክልና በኣዋጅ መሰረዛቸው ለህዝቡ ግልፅ ሊሆንለት ይገባል። ውህደቱ በሃሳብ የተስማሙ የግለ ሰቦች ስብስብ ብቻ ነው። በኣጭሩ በውህደት የተሰባሰቡት ግለ ሰቦች ኣገሪቱ ያላት ብዝሃነት የማያምኑና ብሄርን የሚጠየፉ፣ የክልሎች ውስጣዊ ሉዓላዊነት የማይቀበሉ፣ የክልሎችን መብት በሚፃረር ሁኔታ ህገ መንግስቱ በወሳኝ መልኩ መቀየር የሚፈልጉ፣ ኣከላልል ኣሁን ካለበት ወደ መልክኣ ምድር መለወጥ የሚፈልጉ፣ የብሄር ብሄረ ሰቦች ራስን የማስተዳደር ፖለቲካዊ መብት ወደ የባህል እና ሲቪላዊ መብት እንዲወሰን የሚፈልጉ ስብስብ እንደሆኑ በተግባር ኣረጋግጠውልናል። እነ ዶ/ር ኣብይ እንደሚሉን ሳይሆን ከላይ የተሰጠው ምክርና እሱም ከልብ የሚያምነበት ለመፈጸም የሚደረግ ውህደት እንደሆነ ግልፅ ሊሆንል ይገባል። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ቢኖር ውህደቱ የግምባሩ ኣባል ድርጅቶች የማፍረስ መብት የሌለው መሆኑን ነው። ፈቃደኛ የሆኑትን ግን የየድርጅቶቻቸው ህገ ደምብ በመከተልና የብሄር ድርጅታቸውን በማክሰም ከሚመሰላቸው ጋር የመወሃድ የማይነካ ሙሉ መብት ኣላቸው።

እንግዲህ የተጠየፉትን የብሄር ፖለቲካና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ በመሸሽ እንወክለሃለን ከሚሉት ህዝብ ፊት መቆም የሚቻል ኣይደልም። በተለይም በየክልሉ እየተንቀሳቀሱ የሚገኝትን የብሄር ድርጅቶች ሁኔታውን በኣገባቡ ከተጠቀሙበት ለእነሱ የሚሆን ዕድል መከፈቱ ኣይቀርም። በተለይም ጠ/ሚኒስትር ኣብይ ኣህመድ የኣጼዎቹና የለየለት የኣሃዳዊ ስርኣት ኣቀንቃኝ መሆኑን በተግባር ያሳየ በመሆኑ ድርጅቱ ኦዴፓ በብቸኝነት ይዞት የቆየው የኦሮሞ ህዝብ ውክልና በኦነግ፣ በኦሮሞ ፌዳራሊስት ኮንግረስ እና ኦሮሚያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ሌሎች የኦሮሞ ብሄር ድርጅቶች መነጠቁ ኣይቀሬ ነው። ከኣንጋፋ ድርጅት ወደ ውታፍ - ነቃይነት የተሸጋገረው መርህ ኣልባው ኣዴፓም በስርኣት ኣልበኝነት የታመሰው ክልሉን ይዞ በስልጣን የመቆየት ዕድሉን ጠባብ በመሆኑ ከመወሃድ ውጭ ሌላ ኣማራጭ እንደሌለው የተገነዘበ ይመስላል። እንደዛ ካላደረገ ሳውይወድ ክልሉን ለኣብን እና ለኣንዳንድ ኣማራ ነክ ድርጅቶች መልቀቁ ኣይቀሬ ነው።

በመጭረሻም በኢትዮጵያ የመንግስትነት ታሪክ ሁለንተናዊ መብታቸው ተነጥቀው ከሰው በታች ተደርገው ሲታዩ የነበሩት ኣሁን በኣጋር ድርጅቶች የሚመሩ ህዝቦች ኣንድ ክ/ዘመን የቆየወን የጨካኞች ኣገዛዝ ላይመለስ ከተገረሰሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው 27 ኣመታት ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር እና የልማቱ ተቋዳሽ ለመሆን እንደበቁ ዓለም የሚመሰክረው ነው። ሆኖም ኣሁን በተፈጠረው የክህደት መንገድ ከሚነገራቸው የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳና ያልተጨበጠ ተስፋ በመነሳት እስከ ኣሁን የተጎናፀፉትን ድል ሁሉ በማራክስ ውህደቱ ይዞላቸው የመጣውን ለመቋደስ የቸኮሉ ይመስላሉ። እንግዲህ ከኣሁን በፊት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ማግኘት ያልቻላችሁት የኢህኣዴግ ኣባል ባለመሆናቹሁ ስለሆነ ውህደቱ ለዚህ ያባቃቹሃል የሚለውን ቅጥፈት የቆጡን ኣወርድ ብላ የብብቷን ጣላች እንደሚሉት ሆኖባቸው ክልላቸውም ጭምር እንዳያጡ ስጋት ኣለኝ። ለማነኛውም የሚሆነውን ጊዜ እስኪያሳየን ድረስ ኣብረን እንጠብቅ።

 

ቸር ይግጠመን።

 

 

 

 

Back to Front Page