Back to Front Page


Share This Article!
Share
ፖለቲካዊ ርእዮተ-ዓለም ምንድነው?

ፖለቲካዊ ርእዮተ-ዓለም ምንድነው?

በታዲሱ አብርሃ (ፖለቲካል ሳይንስ MA)

1-26-19

የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን ልዩ የሚያደርገው ባህሪ ቢኖር በስሜት ብቻ የሚኖር ሳይሆን ነገሮችን በጥልቀት በመመርመር መልካም አጋጣሚዎችን አስቦና አስልቶ ወደ ጥቅም የመቀየር እውቀትና ችሎታ ያለው እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች ቀድሞ ሊቀርፍበት የሚችል ስትራቴጂና ታክቲክ የሚቀይስ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ በዘፈቀደ ሳይሆን በተደራጀ፣ በተቀናጀና ስርዓት ባለው አግባብ የሚመራ መሆኑም ከሰው ልጅ የእድገት ታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡  የፍልስፍና አባት አርስቶትልም ይህን ታሳቢ በማድረግ የሰው ልጅ “ፖለቲካዊ እንስሳ (Political Animal) ነው” ይላል፡፡ የሰው ልጆች በጋራ የሚኖሩ በመሆናቸውም ፍላጎታቸው ለማርካታት የተለያዩ ተግባራት ማከናወናቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ምክንያትም የስራ ክፍፍል በመፈጠሩ በማህበረሰቡ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መደቦች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ ይህም በሁሉም ስልተ-ምርቶች (Mode of Production) ማለትም በጋርዮሽ፣ በባሪያ ፍንገላ፣ በፊውዳልና በከበርቴ ስርዓቶች በሰዎች መካከል ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየሰፋ መጥቷል፡፡

Videos From Around The World

በአንድ ወቅት የራሱና የማህበረሰቡ የእለት ምግብ ፍላጎት ለማሟላት የእንስሳት አዳኝ የነበረ፤ ከጊዜ በኋላ የባሪያ ጌታና የገበሬ አዛዥ አናዛዥ፤ በአሁን ወቅት ደግሞ የተትረፈረፈ ገንዘብ ባለቤትና በቅንጦት ዓለም የሚኖር የህብረተሰብ ክፍል ወይም በካርል ማርክስ አጠራር “ከበርቴ” ሆነዋል፡፡ ያኔ በጋርዮሽ ስርዓት በምግብ አብሳይነት ወይም በተላላኪነት ደረጃ የነበሩ ሰዎች በቀጣዮቹ ስርዓቶች ባርያዎች ወይም ጭሰኞች ሲሆኑ በአሁኑ ዘመን ጉልበታቸው ሽጠው የሚያድሩ ሰራተኞች ወይም “ላብ አደር ” ሆነዋል፡፡ ያኔ በጥንቱ የየአከባቢው ሰላምና ፀጥታ ለማክበር የዘር ግንድ ወይም ሀይማኖታዊና ባህላዊ እምነት አልያም ጉልበትን መሰረት አድርጎ ይቋቋም የነበረ የመንደር አስተዳደር በጊዜ ሂደት በመልኩ፣ በአደረጃጀቱ፣ በግዝፈቱና በባህሪው እጅግ የተለየ እንዲሁም በአሰራር ስርዓቱ በጣም ያደገና የዘመነ መንግስት መገንባት ተችሏል፡፡

በተለይም በዘመናዊ የሰው ልጅ ታሪክ ያለመንግስት የሀገር ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ፣ የህዝቦች ሉአላዊነት ማክበር፣ የህብረተሰብ መሰረታዊ ፍላጎቶችና አገልግሎቶች ማሟላት የማይቻልበት ደረጀ ተደርሷል፡፡ የመንግስት አስፈላጊነትም ባያጠራጥርም፤ “ምን ዓይነት መንግስት” የሚለው ግን አሁንም በበርካታ የዘርፉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ የተካረረ ልዩነት ይታያል፡፡ መንግስታት ባህሪያቸውና ዓላማቸው የሚለያዩበት በርካታ ቢሆንም ርእዮተ-ዓለም (Political Ideology) ደግሞ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንድ መንግሰት ወይም ፖለቲካ ፓርቲ የሚመዘነው ከሚከተለው ርእዮተ-ዓላማው አንፃር ነው፡፡  በስልጣን ማማ ላይ ያለ አካል ይሁን ወደ ስልጣን ዙፋን ለመምጣት ያለመ አካል ርእዮተ-ዓለሙ ለሰፊው ህዝብ በልዩ ልዩ ዘዴዎችና መገናኛ ብዙኋን የፖለቲካ ቅስቀሳ (Political maneuver) ያካሄዳሉ፡፡ በተለይም በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ርእዮተ-ዓለሙ በህብረተሰብ ያሰረፀና ተቀባይነት ያገኘ አካል ይመረጣል፡፡ መንግስት ያቋቁማል፡፡ ርእዮተ-ዓለማው እውን ለማድረግም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመቅረፅ ለተግባራዊነቱ ይረባረባል፡፡ የተሳካለት ከሆነ ሀገር ይለውጣል፤ ታሪክ ይሰራል፡፡

ከዚህ በመነሳትም ርእዮተ-ዓለም የሚል ቃል በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ዘንድ ተደጋግሞ ከሚነሱ ቃላቶች መካከል በቀዳምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ሆኖም ግን የፅንሰ-ሀሳቡ ይዘትና ምንነት በቅጡ ካለመረዳት የተነሳ፤ በርካታ ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ርእዮተ-ዓለም ከተለያዩ ፅንሰ-ሀሳቦች ጋር በመቀያየርና በመቀላቀል (Interchangeably) ሲጠቀሙበት ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ርእዮተ-ዓለም ከፖለቲካ ንድፈ-ሀሳብ ወይም ፍልስፍና (Political theory/Philosophy) ጋር እንደተመሳሳይነት ትርጉም ሲወስዱት ሌሎች ደግሞ ከድርጅት ፕሮግራም ያውና አንድ ፍቺ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ የዚህ አጭር ፅሁፍ መነሻም በርእዮተ-ዓለም ፅንሰ-ሀሳብ ምንነት ዙርያ የሚታዩ ብዥታዎች በተወሰነ መልክ ለመቅረፍ ያለመ ነው፡፡

ከፍ ሲል እንደተገለፀው ርእዮተ-ዓለም ለአንድ ፖለቲካዊ ፓርቲ ወይም መንግስት ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በርካታ ምሁራን የፅንሰ-ሀሳቡ ምንነት ለመተርጎምና ለመግለፅ በስፋት ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ ፅሁፍ ይዘትና ዓላማ አንፃር የተለያዩ ምሁራን ብያኔ በማነፃፀር ከመጠቀም ይልቅ የዶ/ር ባል ትሬስ (2014) የርእዮተ-ዓለም ፍች፤ በይዘቱና በምሉእነቱ ከሌሎች ምሁራን ብያኔዎች በተሻለ ሁኔታ ተመራጭ ሆኖ በመገኘቱ፤ እንደመሳሪያ ትርጉም (working definition) ተወስዷል፡፡ በዚህ መሰረትም ርእየተ-ዓለም ማለት “የህብረተሰብ ነባራዊ ሁኔታ ለመተንተንና ለመገምገም፣ ህዝቦች በማህበረሰቡ ላይ ያላቸው ደረጃ ለመገንዘብ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግባራት በፕሮግራም መልክ ለመቅረፅ የሚያስችሉ በግልፅና ቅደም ተከተል ባለው አኳሀን (fairly coherent)፣ ሁሉን አቀፍ በሆነ አግባብ (comprehensive) የተደራጁ ሀሳቦች ስብስብ (set of ideas) ነው፡፡ ይልቁንም ሰዎች ርእዮተ-ዓለም የሚከተሉት አራት መሰረታዊ ጥቅሞች ማለትም ነገሮችን ለመተንተን፣ ለመገምገም፣ መለያ እምነትና መገለጫ ለመለየት እንዲሁም ፕሮግራማቸው ለመቅረፅ ስለሚያስቸላቸው ነው” ይላል የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ባል ትሬስ (2014፡4-5)፡፡

ከዶ/ር ባል ትሬስ ትርጉም በመነሳትም ስለ ርእዮተ-ዓለም ምንነት በርካታ ቁም ነገሮች መረዳት ይቻላል፡፡ አንደኛው ርእየተ-ዓለም ከፖለቲካ ንድፈ-ሀሳብ ወይም ፍልስፍና እንዲሁም ከድርጅት ፕሮግራም ጋር ያውና አንድ አለመሆኑንና የደረጃ ልዩነት እንዳላቸው ይጠቁማል፡፡ ፓርቲዎች ወይም መንግስታት የርእዮተ-ዓለማቸው ይዘትና ምንነት ለህብረተሰቡ ለማስረዳት፣ ለመመርመር፣ ከሌሎች ተቃራኒ አካላት ያላቸው ልዩነት ለማጉላት ፖለቲካዊ ንድፈ-ሃሳቦችን እንደመነሻ ሊጠቀሙ እንዲሁም ሳይንሳዊ ዘዴ ሊያላብሱት ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ርእዮተ-ዓለም እንደ ፖለቲካዊ ንድፈ-ሃሳብ እጅግ ረቂቅና ውስብስብ፣ ትኩረቱ በጉዳዮች ላይ በጥልቀት መራቀቅና መፈላሰፍ ሳይሆን ሀሳቦችን፣ አስተሳሰቦችንና እምነቶችን ከተግባር ጋር የሚያገናኝ ወይም ነገሮችን ለህዝቡ በቀለለ መንገድ እንዴት ተግባራዊ መሆን እንደሚችሉ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ እንዲሁም ለተግባር የሚያነቃቃ ፅንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም አንዳንድ ሰዎች እንደሚጠቀሙበት የድርጅት ፕሮግራም ከርእዮተ-ዓለም ጋር ተመሳሳይ እንደምታና ይዘት ያለው ሳይሆን በቀጣይ በዝርዝር ለመግለፅ ጥረት እንደተደረገው ፕሮግራም የርእዮተ-ዓለም አንድ መገለጫ አካል ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ከባል ትሬስ ትርጉም መገንዘብ የሚቻለው፤ አንድ ፅንሰ-ሀሳብ እንደ ርእዮተ-ዓለም ለመውሰድ አራት መሰረታዊ ጉዳዮችን ማከናወን የሚያስችል መሆኑ ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑ ያመላክታል፡፡ ይህም ርእዮተ-ዓለም በቀዳሚነት ማህበራዊ መሰረቶች አሁን ባሉበት ነባራዊ ሁኔታ ለምን እንዳሉ መተንተን የሚያስችል ሲሆን በቀጣይም ነባራዊ ሁኔታዎች በጥልቀት መገምገም ይኖርበታል፡፡ ሌለኛውም ርእዮተ-ዓለሙ ለህብረተሰቡ እንዴት እንደሚጠቅም ማስገንዘብ ያለበት ሲሆን በመጨረሻም ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባር በፕሮግራም ደረጃ በዝርዝር ለመቅረፅ የሚያስችሉ ታሳቢዎች ያቀፈ ነው፡፡ በድምሩ አንድ ርእዮተ-ዓለም ርእዮተ-ዓለም ነው ለማለት እንዲቻል ቀደም ሲሉ በተጠቀሱ አራት ጉዳዮች መሰረት ለምሳሌ የሰው ልጅ ተፈጥሮና ነፃነት (Human Nature and Freedom) በተለየ አቅጣጫ መተንተንና መገምገም፣ ልዩ ልዩ መለያ እምነቶችና መገለጫዎች ማስቀመጥ፣ ከመለያ እምነቶች የሚመመነጭና ወደ ተግባር ሊተረጎም የሚችል ፕሮግራም መቅረፅ የሚያስችል መሆኑ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም የርእዮተ-ዓለም ምንነት፣ አስፈላጊነትና ይዘት እንዲሁም አንዱ ከሌላው የሚለይበት ባህሪ በተሻለ አግባብ ለማስረዳት አራት ርእዮተ-ዓለሞች ማለትም ሊበራሊዝም፣ ኮንዘርቫቲዝም፣ ሶሺሊዝና ፋሺዝም በሰው ልጅ ተፈጥሮና ነፃነት ላይ ያላቸው እይታ ከሚያቀርቡት ትንተና፣ ከሚያካሄዱት ግምገማ፣ ከሚያቀርቡት መለያ እምነትና መገለጫ እንዲሁም ከሚቀርፁት የፕሮግራም ይዘት አንፃር እንደሚከተለው በቅደም ተከተል ተዘርዝረው ቀርበዋል፡፡

የሊበራሊዝም ወይም የከበርቴ ርእዮተ-ዓለም የትንተናው ማጠንጠኛ ግለሰብ ሲሆን ማንኛው ማህበራዊ ሁኔታም የግለሰቦች የአማራጭና የተግባር ውጤት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ነገሮች ጥሩ ወይም መጥፎ ተብለው የሚገመገምበት መስፈርትም የሌሎች መብት ሳይጋፉ የግለሰቦችን ነፃነትና አማራጭ ፍላጎታቸው ይገድባል ወይስ አይገድብም በሚል ይሆናል፡፡ በግለሰቦች መካከልም እኩል የነፃነት እድል ያስፈልጋልም ይላሉ፡፡ እንደመለያ እምነታቸውም ግለሰቦች ምክንያታዊና የግላቸውን ጥቅም አሳልፈው የማይሰጡ ናቸው የሚል ታሳቢ አላቸው፡፡ የሰው ልጅ ነፃነትም መታየት ያለበት በቡድን ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ በመሆኑም እንደ ፕሮግራም የሰው ልጅ አማራጭና ነፃነት ቅድሚያ መስጠት እና ለነዚህ ተግዳሮቶች ሊሆኑ የሚችሉ ማንኛው መንግስታዊና ልምዳዊ ስርዓቶች ለማስወገድ የሚያስችል ይሆናል፡፡ ለማጠቃለል ያህልም የሊበራሊዝም ትኩረት ግለሰብ እንደሆነ፣ የግለሰቦች አማራጭ የሚገድቡ ህጎች፣ ልምዶችና የተለያዩ ሁኔታዎች ለማስወደግ ትግል የሚያካሄድና ሰዎች እንደመረጡት መኖር አለባቸው የሚል ዓላማ ያነገበ ርእዮት ነው፡፡

የኮንዘርቫቲዝም ወይም የወግአጥባቂነት ርእዮተ-ዓለም የትንተናው ማእከል እንደ ሊበራሊዝም በግለሰዎች ሳይሆን በሰው ልጆች እንከን (human imperfection) ላይ ነው፡፡ ነገሮችም መከወን ያለባቸው በጥንቃቄና ቀስ በቀስ መሆን ይኖርበታል ይላል፡፡ ማህበራዊ ሁኔታም የሚገመገመው ከሚያስከትለው ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ መለያ እምነታቸውም እያንዳንዱ ግለሰው የአብይ ግንዱ (greater whole) አካል ነው፤ የእያንዳንዱ ግለሰብ ተግባር የአጠቃላይ ማህበረሰብ ጠቀሜታ የሚያሳካ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢና አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ይከተላል፡፡ የሚቀረፀው ፕሮግራምም በአሁን ወቅት ያሉ ፀጋዎች የሚያቅብ፣ የሚያስቀጥልና ደህንነታቸው የሚያረጋገጥ እንዲሁም የሚፈጠር ለውጥ በእርጋታና በጥንቃቄ መመራት ይኖርበታል ይላል፡፡ በአጠቃላይ ወግ አጥባቂ ርእዮተ-ዓለም ለግለሰቦች ትስስርና መስተጋብር ትኩረት የሚሰጥ፣ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ልዩ ትኩረት የሚያደርግ፤ መሰረታዊ ለውጦች፣ ፈጠራዎችና ፍላጎቶች መገደብ አለባቸው የሚል እሳቤ ያለው፤ ፕሮግራሙ በህብረተሰቡ መካከል ስርዓት፣ መረጋጋት፣ መቻቻልና ቀጣይነት ለማስፈን የሚቀርፅ ነው፡፡

ሶሻሊዝም ማህበራዊ ሁኔታን የሚተነትነው ከኢኮኖሚያዊና ከመደብ ግንኙነት አንፃር ነው፡፡  የማህበረሰቡ ሁኔታ የሚወሰነውም ግለሰቦች በሚሰሩት ተግባር ወይም በፍላጎታቸው ሳይሆን በሚገኙበት መደብ ነው የሚል መከራከሪያ ነጥብ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ሶሻሊስቶች “Men make their own history, but they do not make it just as they please” በግርድፉ “የሰው ልጅ ታሪክ ይሰራል እንጂ እንደፈለገው አይሆንም” የሚል የካርል ማርክስ ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ በዚህ ርእዮት እንደመገምገሚያ ነጥብ የሚወሰድም በመደቦች መካከል የሚኖር የመደብ ልዩነት ወይም የቅራኔ መጠን ነው፡፡ የርእዮቱ መለያ እምነትም የእያንዳንዱ ሰው ማንነት የሚወሰነው አሁን ባለው መደብ ነው፤ ላብ አደሩ ከግልብ ንቃተ-ህልና “False Consciousness” እንዲወጣ ሁሉም ነገርም ከመደቡ አንፃር መቃኘት ይኖርበታል የሚል ነው፡፡ የርእዮተ-ዓለሙ ፕሮግራምም የመደብ ልዩነት የሌለው ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል ማንኛውም ነገር አስፈላጊ ሲሆንም አብዮታዊ እርምጃ  ጭምር ለማካሄድ የሚያስችል ይሆናል፡፡ በድምሩ የሶሻሊዝም ትኩረት ላብአደሩ ላይ ሲሆን የመደብ፣ የኢኮኖሚና የአማራጭ እድል ልዩነት እንዲሁም ግልብ ንቃተ-ህልና በመቅረፍ የሰው ልጅ እኩል ሰብእና እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚጥር ነው፡፡

የፋሺዝም ርእዮተ-ዓለም የትንተና ማእከሉ ከፍ ሲሉ እንደተገፁት በግለሰቦች አልያም በመደብ ሳይሆን ሰዎች በሚኖሩበት ሀገር ወይም ዘር ነው፡፡ መነሻ የሚያደርገውም ህዝቡ ወደ ጋራ አስተሳሰብ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን በመምዘዝ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሁኔታ የሚመዘነውም ህዝቡ በአንድ ማእበል የማሰልፍ አቅምና የሀገሪቱ አንድነትና ጥንካሬ ከማረጋገጥ አንፃር ይሆናል፡፡ የዚህ ርእዮት መለያ እምነትም ግለሰቦች በአጠቃላይ የሀገሪቱ ዜጋ ወይም የዘር ግንድ ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ የፕሮግራሙ ይዘትም ከእያንዳንዱ ግለሰብ በርእዮተ-ዓለሙ ማመን፣ መታዘዝ፣ መታገልና መሪውን መከታል ነው፡፡ በአጠቃላይ የፋሺዝም ትኩረት ሀገር (nation-state) ሲሆን ዜጎች ከግለሰባዊነት፣ ከቡድነኝነትና ከመደብ ልዩነት መታቀብ ይኖርባቸዋል፤ ለሀገሪቱ ሀያልነትና ክብር አስፈላጊው ሁሉ ለመከፈል የሚያስችል ፕሮግራም ይቀርፃሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል፤ የዚህ ፅሁፍ ትኩረት የተለያዩ ርእዮተ-ዓለሞች ምንነት ለመትንተንና ለማስረዳት አይደለም፡፡ ይልቁንም የፅሁፉ ዓላማ የርእዮተ-ዓለም ፅንሰ-ሃሳብ ምንነት በወፍ በረር ቅኝት በመዳሰስ ተደራሲያኑ ይበልጥ በርእሰ-ጉዳዩ ላይ እንዲያነቡ ለመጋበዝ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተመኮረው፤ ርእዮተ-ዓለም ማለት አንድ መንግስት ወይም ፖለቲካ ፓርቲ አልያም ፖለቲከኛ ነገሮችን የሚያይበት፣ የሚተነትንበትና የሚገመግምበት መነፅር፤ የሚመራበት የእምነት መመሪያና የልዩ ባህሪው መገለጫ፤ የማህበራዊ መሰረቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚቀረፀውን ፕሮግራም መሰረት የሚደርግበት አስተሳሰቦች፣ ሀሳቦችንና እምነቶችን በተደራጀ አግባበ ያቀፈ ፅንሰ-ሀሳብ ነው፡፡ ርእዮተ-ዓለም ከሌሎች ፅንሰ-ሀሳቦች ለመለየትም በአራት መስፈርቶች መገምገም አስፈላጊ መሆኑ ባል ትሬስ ይመክራል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ቀደም ሲል የሰው ልጅ ተፈጥሮና ነጻነት መነሻ በማድረግ የርእዮተ-ዓለሞች ምንነት ለመገምገም ጥረት በተደረገው አግባብ ልክ ለምሳሌ ዲሞክራሲ፣ ልማትና ብሔርተኝነት ወዘተ… ታሳቢ በማድረግ ነገሮችን በመተንተን ፖለቲካዊ ብቃታችንን ማጎልበት ብሎም የርእዮተ-ዓለም ምንነት ይበልጥ መረዳትና መመርመር እንችላለን፡፡ ይህም በሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ጤነኛ እንዲሆን የጎላ እገዛ እንዲኖረው ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ምንጭ

·        Ball, Terence (2014) Political Ideologies and the Democratic Ideal (ninth edition) Terence Ball, Arizona State University, Richard Dagger, University of Richmond With the assistance of Daniel I. O’Neill University of Florida

 

Back to Front Page