Back to Front Page


Share This Article!
Share
ዶክተር አቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደሚሆኑ በትንቢት መነገሩ ትርጉሙ ምን ይሆን?

ዶክተር አቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደሚሆኑ በትንቢት መነገሩ ትርጉሙ ምን ይሆን?

 

ከኮሎኔል በቀለ ኃይለ ማርያም፡፡ 1-15-19

bekelehm47@gmail.com

አልፎ አልፎ፣ በተለያዩ ዘመናት እግዚአብሔር የመረጣቸውን የአገር መሪዎች፣ ለነቢያቱ እንደሚገልጽና ነቢያቱም ለሕዝቡ እንደሚነግሩ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ሆኖም፣ ትንቢት የመጣለት መሪ የተመረጠበት ምክንያቱ በክእሎቱ ወይም በመልካም ባሕርይው ነው ማለት አይደለም፡፡ ለሕዝቡም ጥሩ ዘመን ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዱ ትንቢት ስለ ጥሩ ንጉሥ ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ ስለሕዝቡ ክፋት መቀጣጫ የተላከ ዱላ እንደሆን የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳል፡፡ ምሳሌዎች ብንመለከት፡-

ስለ መልካም ንጉሥ የተነገረ ትንቢት፡-

Videos From Around The World

ንጉሥ ዳዊት፣ ገና በአሥራ አራት ዓመቱ ገደማ ማለትም እረኛ በነበረበት ጊዜ፣ ለወደፊቱ የእሥራኤል ንጉሥ እንደሚሆን፣ እግዚአብሔር በነቢዩ ሳሙዔል በኩል የላከው ትንቢት፣ ከ15 ዓመታት በኋላ መፈጸሙ፣ ቀዳማዊ ሳሙዔል ምዕራፍ 16 ውስጥ ተጽፏል፡፡ ዳዊትም መልካም ንጉሥ ብቻ ሳይሆን፣ በባህርዩ ምስጉን እንዲሁም መንፈሳዊ መሆኑ በተግባሩ ስለተረጋገጠ፣ እግዚአብሔር "እንደልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ . . . . . . " ብሎ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 13 መስክሮለታል፡፡

ከክፋቱ አልመለስ ላለ ሕዝብ፣ የመቀጣጫ ዱላ ሆኖ ስለ ተላከ ንጉሥ የተነገረ ትንቢት፡-

የእሥራኤል ሕዝብ ፈጣሪውን ለዘመናት በማሳዘኑና ማስጠንቀቂያዎችንም ሰምቶ ንሥሐ ባለመግባቱ፣ እግዚአብሔር፣ ንጉሥ ናቡከደናጾርን መቀጣጫ አድርጎ ልኮ ለ70 ዓመታት በባርነት እንደሚያስኖረው የላከው ትንቢት፣ በኤርምያስ መጽሐፍ፣ ምዕራፍ 13 እና 14 ተጽፏል፡፡ ስለሆነም፣ የይሁዳን ሰዎች፣ የመጣባቸውን ተቀብለው፣ 70 ዓመታቱን በባርነት እንዲገዙ፣ እንዲወልዱ እንዲዋለዱ፣ እንዲያርሱ መከሩንም እንዲያገቡ፣ ቤት ሠርተው ተደላድለው እንዲኖሩ ኤርምያስ ይነግራቸው ነበር፡፡ ታዲያ የታዘዙት አይሁዶች 70 ዓመታቱ እስኪደርስ በሕይወት ኖረው ወዳገራቸው ሲመለሱ፣ ወይ ለመቆየት የመረጡት እዚያው ሲቀሩ፣ ትንቢቱን ሰምተው ያልታዘዙት፣ ማለትም ያገር ክብር ለማስጠበቅ፣ ናቡከደናጾርን እንዋጋለን፣ ብለው ባገር ፍቅር ወኔ ዘራፍ! እያሉ የተነሱት ሁሉ፣ አገራቸው ምድረበዳ እስክትመስል በሠይፍ አለቁ፣ ንብረታቸውም ወደመ፡፡

ከንጉሥ ናቡከደናጾር ጀምሮ፣ ጸረ ክርስቶስ እስከሚመጣ፣ ብሎም ዘልዓለማዊ ሕይወት እስኪጀመር፣ በዓለም ላይ ስለሚነሱ ዋና ዋና መንግሥታት መሪዎች የተነገሩ ትንቢቶች፡-

በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት የተዘገበውን ታሪክ በአጭሩ ብገልጸው -- አንድ ሌሊት፣ ንጉሥ ናቡከደናጾር ያስገረመው ሕልም ካየ በኋላ፣ ሕልሙን በመርሳቱ በጣም ተረበሸ፡፡ ከዚያም ሕልም ፈቺዎች፣ አስማተኞች፣ መተተኞች እና ጠቢባን ሰብስቦ ሕልሙን ከነትርጉሙ ካልነገሩት፣ እነሱና ቤተሰባቸውን እንደሚያጠፋ፣ ከነገሩት ደግሞ እንደሚሸልማቸው ነገራቸው፡፡ እነሱም ሕልሙን አስታውሶ ከነገራቸው መፍታት እንደሚችሉ፣ የተረሳ ሕልምን ግን ከአማልክት በስተቀር ማንም ሊያውቅ እንደማይችል አስረዱት፡፡ ጠቢቡ ነቢይ ዳንኤል ግን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ የጸሎት ጊዜ ጀመረ፡፡ እግዚአብሔርም የንጉሡን ሕልምና የፍቺውን ምሥጢር በሌሊት ራዕይ ገለጠለት፡፡ ዳንኤልም ናቡከደናጾር ዘንድ ገብቶ፣ ንጉሡ አይቶ የረሳውን ሕልም እስከነ ፍቺው ነገረው፡፡

ሕልሙን ሲያትትለት፡- ንጉሡ በሕልሙ ያየው አንድ የተብለጨለጨ እና መልኩ ግሩም የሆነ ትልቅ የሰው ምስል ነበር ብሎ ጀመረለት፡፡ የምስሉ ራስም የተሠራው ከወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ወገቡ ከናስ፣ ጭኖቹ ከብረት፣ እግሮቹም ከብረት እና ከሸክላ የተሠሩ ነበር አለው፡፡ ይሄም ምስል፣ የማንም እጅ ሳይነካው አንድ ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ እግሮቹን ሲመታው ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ በአንድነት ሲፈጭ፣ የተፈጨውም ተበትኖ በነፋስ ሲወሰድ፣ በመጨረሻም፣ ያ ምስሉን የመታ ድንጋይ፣ ታላቅ ተራራ ሆኖ ምድርን ፈጽሞ እንደሞላ ማየቱን አስታወሰው፡፡

ፍቺውን ሲያስረዳው ደግሞ፡- በምዕራፍ አሥራ አንድ እንደተዘገበው፣ ምስሉ ከራሱ ከንጉሡ ናቡከደናጾር ጀምሮ፣ በተለያዩ ጊዜያት ስለሚነሱ መንግሥታት መሪዎች መሆኑን እንደሚተከለው ገለጸለት፡፡

1)   ከወርቅ የተሠራው የምስሉ ራስ፣ ብርታትና ክብር ከእግዚአብሔር የተሰጠው፣ ንጉሥ እንደሆነ፣ (ናቡከደናጾር እራሱ እንደሆን)

2)   ከብር የተሠሩት ደረትና ክንዶች ደግሞ ከናቡከደናጾር በኋላ የሚነሳው፣ አነስተኛ የሆነ መንግሥት እንደሆን፣ (የፋርስን መንግሥት የሚመራው ቂሮስ / ሳይረስ)

3)   ከናስ የተሠሩት ሆድና ወገብ ደግሞ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሦስተኛው መንግሥት፣ በጦር በጣም ፈጣን በሆነ መሪ እንደሚመራ፣ (የግሪክ መንግሥትን የሚመራው አሌክሳንደር ዘ ግሬት)

4)   ከብረት የተሠሩት ጭኖች ደግሞ፣ ከአሌክሳንደር በኋላ የሚገዛው በአራት የተከፈለ መንግሥት፣ ጨካኝ፣ ኃይለኛ እና ሌሎች መንግሥታትን የሚያደቅቅ እንደሆነ፣ (የቀድሞው የሮማ መንግሥት)

5)   ከብረት እና ከሸክላ የተሠሩት እግሮች ደግሞ፣ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ስለሆኑ መንግሥታት እንደሆነ፣ አሥሮቹ የእግር ጣቶች በአሥር የሚከፈሉ መንግሥታትን እንደሚገልጹ፣ ብረቱ ከሸክላው ተደባልቆ እንዳየ፣ እንዲሁ ከሰው ዘር እንደሚደባለቁ፣ ሆኖም ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፣ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንደማይጣበቁ፣ (ከምዕራብ እና ከምሥራቅ የሮማ ኤምፓየር የተውጣጣው አውሮፓ ማለትም በአሥር የተከፈለው፣ በመጨረሻም፣ ጸረ ክርስቶስን የሚወልደው)

6)   ድንጋዩም፣ ከተራራ ተፈንቅሎ ሁሉንም ፈጭቶ የበተነው ደግሞ፣ በሰው እጅ ያልተሠራ፣ የሰማይ አምላክ የሚያስነሳው መንግሥት እንደሆነ እና ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት እንደሚሆን፣ ከወርቁ እስከ ሸክላው ያሉትን መንግሥታት ሁሉ እንደሚፈጫቸውና እንደሚያጠፋቸው፣ ከዚያም ያ መንግሥት፣ በዓለም ሁሉ ለዘላለም የሚቆም እንደሆነ፣ (ድንጋዩ ኢየሱስ ሲሆን፣ መንግሥቱ ዘላለማዊው የእግዚአብሔር መንግሥት ነው፡፡)

ዶክተር አቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደሚሆኑ የተነገረው ትንቢት፡-

ስለ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተነገረውን ትንቢት፣ "ዶክተሩ ሹመቱን ከማግኘታቸው ከስድስት ዓመታት በፊት የተነበይኩት እኔ ነኝ፡፡" በማለት አንዲት የዘመናችን ነቢይት በቴሌቪዥን በተዳጋጋሚ ቢያስነግሩትም፣ ትንቢቱን ያመጡት ሌላ ከገጠር የመጡ ነቢይት ናቸው፡፡ በቴሌቪዥኑ የታየው "ክሊፕም" በኤዲቲንግ ቴክኒክ የተለዋወጠ ነው፡፡ ለማንኛውም፣ ዋናው ጉዳይ ትንቢቱን ማን አመጣው ሳይሆን መምጣቱ ነው፡፡ በእርግጥም ከእግዚአብሔር መጥቷል፡፡ ትንቢት ነው ባይሉትም፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩም፣ ሌሎችም የሳቸውን ወደዚህ ወንበር መድረስ በቅድሚያ ማወቃቸውን ሲያወሩ፡- "መሪ እንደምሆን፣ እናቴ ተናግራ ነበር፡፡" ብለዋል፡፡ ደስ ይላል፡፡ ብዙ እናት ስለልጇ ብዙ ትተነብያለች፡፡ ብዙዎቻችን ምን እየተባልን እንዳደግን እናውቃለን፡፡ እኔን እንኳን እናቴ "እኔኮ ያገርህ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንድትሆን ነው ያዘጋጀሁህ!" ስትለኝ "ምናባቴ ላርግ፣ ይሄ መለስ ዜናዊ ወንበሩን ይዞ አልወርድ አለኝ" እያልኩ እቀልድባት ነበር፡፡ ለማንኛውም፣ ትንቢት የመምጣቱ ምክንያት፣ ያ ዘመን የደስታ ጊዜ ይሆናል ብሎ ለእፎይታ እንድንዘጋጅ ሳይሆን፣ ጉዳዩ ከእግዚአብሔር እንደሆን ተረድተን፣ ትንቢቱን ተቀብለን፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንድንኖር እንደሆን፣ ስለ ንጉሦች ወይም መሪዎች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በአፈታሪክ የተነገሩት ትንቢቶች እና ውጤታቸው ያስተምሩናል፡፡ ስለንጉሥ ዳዊት ስለነ ዖዝያን፣ ሕዝቅያስ፣ ወዘተ መልካም ዘመናት ትንቢት እንደተተነበየ ሁሉ፣ ስለነ ሂትለር፣ ስለነ ኢዲያሚን እንዲሁም ስለ ጸረ ክርስቶስ ተተንብዩዋል፡፡

ታዲያ አሁን የዶክተር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆንን በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር እንዴት እንየው? መልካም ጊዜ ወይስ የጭንቅ ጊዜ?

 

ስለ ዶክተር አቢይ የመጣው ትንቢት፣ ስለ መልካም ዘመን ወይም ተቃራኒውን እንደሚሆን በእርግጠኝነት የምንለየው፣ ከትንቢቱ ጋር ማብራሪያ ቃል ቢተነበይ ነበር፡፡ ከትንቢቱ ጋር የመጣ የመግለጫ ቃል ስለሌለ፣ ጊዜውን መገምገም የምንችለው፣ የሥራቸውን ውጤት በሂደት በማጤን ብቻ ነው፡፡ ይህ ትንቢት መተንበዩ፣ የመልካም ጊዜ መምጣት መስሏቸው፣ በጴንጤ እምነት ውስጥ ያሉ በርካታ አማኞች፣ ከኔም ጭምር፣ ተደስተን ነበር፡፡ የደስታ፣ የሰላም፣ የበረከት ጊዜ የመጣ መስሎን ፈነደቅን፡፡ በየስብሰባችን ለጌታ ምስጋና በመዝሙር፣ በእልልታ እና በሽብሸባ ገለጽን፡፡ እግዚአብሔርን አየኸን ወይ? አልን፡፡ ቤታቸውን ዘግተው ለብቻቸው ተማክረው ገፈቱን (የሥራቸውን መጥፎ ውጤት) በግድ ከሚግቱን ከቀድሞዎቹ መሪዎች ገላገልከን ወይ? አልን፡፡ ጥያቄ ስንጠይቃቸው፣ በቁጣ ከሚያደናግጡን፣ ግንባራቸው ከማይፈታ እና "ጸረ ኢሀደግ" እያሉ ከሚያስፈራሩን መሪዎች ገላገልከን ወይ? አልን፡፡ የፓርቲያቸው ደጋፊ ያልሆነ ዜጋን ከጥቅም ተካፋይ እንዳይሆን ከሚያከላክሉ መሪዎች ገላገልከን ወይ? አልን፡፡ በልሣን የሚናገር መሪ መጣ ብለን ኮራን፡፡

በአጭር ጊዜ ግን፣ ሁኔታዎችን የሚያጠያይቅ ጊዜ መጣ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከልክ ያለፈ ስሜታዊ መሆናቸው፣ ማለትም ደስ ሲላቸው፣ ቸኮላት እንደተሰጠው የሰባት ዓመት ልጅ ሲፍለቀለቁ እና አንዱን ሲያቅፉ አንዱን ሲስሙ፣ አንዱን ምሥጢር የሚያወራ መስለው በጆሮው ሲያንሾካሽኩ፣ አንዱን እንደ ትንሽ ልጅ እጁን ይዘው እያሳሳቁ ሲሄዱ፣ መምሬ ወልደ ሕጻንን ያስታውስ ጀመር፡፡ ሲያዝኑ ሊሰበር የሚደርስ ዕቃ ይመስላሉ፣ ሲከፋቸው ደግሞ፣ የፊታቸው መለዋወጥ እና የንዴታቸው መግለጫ ቃላቶች፣ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቀርቶ ከአነስተኛ ደረጃ ኃላፊ የማይጠበቅ በመሆኑ፣ ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ በሚሄድ የስሜት ዥዋዥዌ የሚኖሩ አስመሰላቸው፡፡ አሁን የሚያንቋሽሹትን፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስኪሆኑ ድረስ ግን በኩራት በሚኒስቴርነት ደረጃ ሲያገለግሉት የነበረውን የገዛ ፓርቲያቸውን፣ በድንገት ገልበጥ ብለው ከድተው የፓርቲውን መሪዎች ማጣጣል ብቻ ሳይሆን፣ ለማጥቃት እንዲመቻቸው፣ የወሰዱት እርምጃ ያሳፍራል፡፡ "ኦፖርችዩኒስት" መሆንን ያመላክታል፡፡ የ"ኢንቴግሪቲ" ያለህ!!! ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጸረ ትግራይ ኃይሎችን አስደስት ብለው፣ "ሕጻኑ የታጠበበትን ቆሻሻ ውሃ፣ እስከነሕጻኑ ደፉት" እንዲሁም፣ ኢሀደግ ቨርስስ ኢሀደግ ሆነ፡፡ "እርስ በርሱ የተከፋፈለ ቤት! ታዲያ ያ ሁሉ የተተነተነው ኃጢአት እና በአርቲስቶች ተቀናብሮ በቲቪ የታየው ድራማ እውነት ከሆነ፣ እንዴት ዝም ብለው ቀድሞ በደህንነት በኋላም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርነቱን ለዓመታት ቀጠሉበት? እንዴትስ ችግሩን ያስተዋሉ ጊዜ፣ ቀፏቸው አሻፈረኝ፣ የዚህ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ አልሆንም ብለው በቆራጥነት አልወጡም ነበር? ለምን ዝም ብለው ቆዩ? በእንግሊዝኛ courage በአማርኛ "ችግርን የማይፈራ የድፍረት ጠባይ" አላከበቱም? ለክህደት አመቺ ደቂቃ ነበር የጠበቁት? የክርስቲያን ባሕሪ ያለህ!!! ወይስ የጥላቻ ፖለቲካ በማራመድ ጸረ ትግራይ ወዳጆቻቸውን ለማስደሰት የተቀናበረ የሐሰት ድራማ ነው፡፡ 'በነባር የህወሃት መሪዎች ላይ "ቬንዴታ" አላቸው በተለይም ከጌታቸው አሰፋ ጋር በደህንነት ውስጥ ሲሠሩ' የሚባለው፣ ሐሜት መስሎን ያለፍነው ወሬ ሁሉ፣ እውነት ይሆን? የደም መላሽ ያለህ!!! በሠፈሩበት ቁና መሠፈር ካልቀረ ደግሞ፣ ለወደፊት እሳቸውንም በተመሳሳይ ልብ ወለድ ውንጀላዎች የሚፈርጃቸው መንግሥት ሲመጣ ድራማው ይቀጥላል፡፡ ባልና ሚስት ለዘመናት ተፋቅረው ኖረው እና ልጆች አሳድገው፣ ለመፋታት ሲወስኑ፣ ሽማግሌዎች ዘንድ ሄደው እርስ በርስ ሲወነጃጀሉና ስም ሲጠፋፉ፣ ሁለቱም፣ ለተመልካች የሚቀፉትን አስታወሰኝ፡፡ ለብዙዎቻችን፣ የፓለቲካ ሞያ የሚቀፈው፣ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት የሚመጣው መከዳዳት ነው?

ደግሞም፣ በሰከነ መንፈስ ሳያጤኑት፣ ከብልሆች ሳይማከሩበት፣ ምንም ዓይነት ስምምነት ሳይደረግ፣ ባስቸኳይ ከኤርትራ ጋር እርቅ አድርገው፣ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ፍቅሩንና ፍሰስ ተፋሰስ ግብዣዎችን አቀለጡ? እነ መለስ፣ ናቅፋን አንቀበልም ሲሏቸው፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በንዴት መንፈስ፣ ቦምብ የረፈረፉባቸው የአይደር ሕጻናት፣ ሁኔታውን በቲቪ ሲያዩ ምን ብለው ይሆን? ኧረ ያቺ ሸበሎቿን ያስረከበች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ እናት ምን አለች? ያ የኢትዮጵያ ነጋዴስ፣ በአሰብ ወደብ በኩል የንግድ ዕቃዎቹን ሲያስመጣ፣ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ትእዛዝ ወደ አሥመራ የተወሰደበት ምን አለ? ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ እንደገና እንደነዚህ ዓይነት ተግባሮችን እንደማይደግሟቸው፣ የገቡት ቃል ሳይኖር ወደ ግብዣ ጠረጴዛ እንዴት ተሄደ?

እንደዚሁም፣ ኤርትራን ፍቅር እያሳዩ፣ ትግራይን መስደብ እና መጥላት የመጣው፣ ጸረ ትግራይ ኃይሎችን ለማስደሰት ነው? ወይስ፣ እነኢማይሬትስ ቃል የገቡትን ቢልየንስ ከማሰላሰል የመነጨ ነው? ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንደኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 6 ቁጥር 10 ውስጥ እንዲህ ይላል፡- "ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ፡፡ አንተ ግን፣ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፣ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል፡፡" የጥላቻቸው ምክንያቱ ምንም ቢሆንም፣ አማራ ወይ ትግሬ ያልሆነውን፣ ጥላቻውን ተካፋይ ያልሆነውን ሕዝብ ሊያሳስበው እንደሚችል መሪው አልገመቱም፡፡ የኢሳያስ ፍቅርስ ለማን በጀ? መጨረሻው የባሕር ሰለባ እንደሚያደርግ አልተገነዘቡም? ከትግራይ ኢሳያስ ተሻላቸው?

ከሁሉም ነገር በላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሪነት ችሎታ ላይ እምነቴ የተሸረሸረው፣ ዴሞክራሲን የሚያከብሩ መሪ ለመባል፣ ቅድመ ዝግጅት ወይም ሕጋዊ አቋም ሳይደረግ፣ ከተቃራኒ ፓርቲዎች ጋር በጽሑፍ ስምምነት ሳይገባ፣ በስሜት ግፊት የተደረገው የ"አገር ግቡ" ጥሪ፣ ከዚያም ሽፍንፍን እርቅ፣ ግብዣ፣ ሠልፍ እና ፉከራ፣ ዛሬ በምታለቅሰዋ የኦሮሚያ እናት መነጽር እያየሁት፣ አልዋጥ አለኝ፡፡ መረረኝ፣ አንገፈገፈኝ፡፡ በስሜት የተጠነሰሰው፣ ብስለት የጎደለው፣ ጥሩ መሪ ለመባል የተደረገው እሽቅድድም፣ "ሲሮጡ ታጥቀውት፣ ሲሮጡ ተፈትቶ፣ ግቢ ነፍስ፣ ውጪ ነፍስ" ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ፣ ኢትዮጵያን ባየር ደበደበ??? ያገር ያለህ! የወገን ያለህ!!! ስሜት የፈጠረው ውዥንብር!!! ምን ይደረግ? ጠቅላይ ሚኒስቴራችን፣ ምነው ከዘጠኙ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ አንዱ የሆነውን ራስን የመግዛት ባሕርይን ሳይለማመዱ ነው ወደ አገር መሪነት የገቡት? ታዲያ የራሱን ስሜት ያላስተዳደረ፣ ሌላን ሊያስተዳድር ይችላል? በኦሮምያም በትግራይም በተወሰደው ጥበብ ጎደለሽ እርምጃ ውጤት፣ ኢትዮጵያ ትሸራረፍ ይሆን? የሚለው ስጋት ለመጀመሪያ ጊዜ በልቤ አገባ፡፡ በልሣን ከሚናገር አማኝ ያልጠበቅሁት ባሕሪ፣ ልቤን ከመስበሩ ሌላ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትን ማሰልሰሉን ስላስተዋልኩ፣ እኔንም እንደሌላው "የምህለላ ጸሎት ስብሰባ! ና ወዲህ በለኝ!" ካስባለኝ ጥቂት ወራት ሊሆን ነው፡፡

ችግሩ፣ ለብዙዎች የመደንገጥ እና የሐዘን ድባብ መፍጠሩ፣ በየቤተክርስቲያኑ በለቅሶ የሕብረት ንሥሐ መግባት መጀመሩ ምስክር ነው፡፡ ያ "ጊዜው የኛ ነው!" ብሎ ኮርቶ የነበረው ጴንጤ ሁሉ፣ እንደ ደርግ ዘመን፣ በቅጽበት "ጌታ ሆይ! ኃጢአታችን በዝቶ፣ አስቀይመንህ ነው፣ ይቅር በለን!" የሚል የምህለላ ፕሮግራሞች፣ ማለትም የአዳር ጸሎት፣ ወይም የጥሞና ጊዜ ለመውሰድ እየተደራጁ ለጾም ለጸሎት "ምሽግ መግባት" መጣ፡፡ አንዳንዱም ነቢይ፣ "አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ ተነስቶ፣ በኢትዮጵያ ደርሶ የማያውቅ የደም ጎርፍ ባገሪቱ ሲጎርፍ ጌታ አሳየኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ጩሁ፣ አልቅሱ" እያለ ራሱም እያለቀሰ መጸለይ ጀመረ፡፡ ከብዙዎቹ አንዱን ለምሳሌ ያህል በሚቀጥለው የድህረ ገጽ አድራሻ ማየት ይቻላል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=DMBXCY8iLBI

እኔም የዘመን መለወጫ ቀን፣ እንደሌላው ዓመት በዓል፣ በደስታ ከማሳለፍ ይልቅ፣ በተመሳሳይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከምእመኑ ጋር በምህለላ እየዬ በማለት አሳለፍኩት፡፡ አሁንማ ፍርሃት ያደረባቸው ወላጆች፣ እንደ ደርግ ዘመን፣ ጎረምሳና ኮረዳ ልጆቻቸውን በምን ዘዴ ካገር ውጪ ሰደው እንደሚያስተምሩ መመካከር ጀምረዋል፡፡ ሌላ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች፣ በወገኖቻቸው የደረሰውን በማየት እና ለልጆቻቸው በመሳሳት፣ ሥራና ቤታቸውን ጥለው ወደ ትግራይ ስለሚሄዱ፣ ወደመቀሌ የሚበረው የየቀኑ አውሮፕላን ብዛት መጨመር፣ ከሌላ ክልል ብንሆንም፣ የጥላቻው ተካፋይ ላልሆነው የእፍረት ምንጭ ሆኗል፡፡

እንደዚሁም፣ ከአዲስ አበባ ውጭ ብዙ ትምህርት ቤቶች እና ኮሌጆች ተዘግተዋል፤ በርካታ ከክልል ወደ ክልል የሚሄዱ መንገዶች ተዘግተዋል፡፡ ከአማራ ወደ ትግራይ የሚሄደው መንገድ ከተዘጋ ሰባት ወር እንዳለፈው ሰሞኑን ይፋ ሆኗል፡፡ ከትላንት ወዲያ፣ በጎንደር እና በቅማንት መሃል በነበረው ያለመግባባት ዜጎች ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ ባገር ሁሉ ተጧጡፎ የነበረው የሕንጻ ግንባታ ሥራ፣ ታሪክ ሆኗል፡፡ የንግድ ሕብረሰቡን ከሁሉ አንገብጋቢ ሆኖ የታየው፣ ሰዉ ገንዘብ አያወጣም፣ ገበያ የለም፤ የመርካቶ ነጋዴ ትርፍ ማግኘት ቀርቶ፣ ቤት ኪራዩን መክፈል ተስኖታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ስለሌለ፣ ንግዶች መካሄድ ተስኗቸዋል፣ የዕቃ ውድነት ብሩን ቅጠል አስመስሎታል ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ የሕዝብ ጭንቀት ውስጥ፣ ዶክተር አቢይ የነገሩን አሳሳቢነት ወይም ግዙፍነቱን የተረዱት አይመስሉም፡፡ ወደ ላይ እያዩ በማልቀሻቸው ሰዓት፣ መፍለቅለቁ ቀጥሏል፡፡ ወይስ ከእንቅልፋቸው ያልነቁት / ያልተቀሰቀሱት አውቀው ተኝተው ነው?

በሌላ በኩል ደግሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ስለገቡ ያሳዝኑኛል፡፡ በአገሪቱ በየክልሉ ሰላም መጥፋቱ እና ጥላቻ መብዛቱ፣ መንፈሳዊ ሰዓቱ ይሆን እላለሁ፡፡ በሌላም እንቆቅልሽ የሆነብኝን ሳስበው፣ ለጠቅላይ ሚኒስቴርነቱ ያበቋቸው እነሱ መሆናቸውን የአማራ ክልል መሪዎች ገልጸውታል፡፡ ታዲያ እነሱን ማስደሰቱ ግድ ስለሚላቸው ይሆን፣ ትግራይን ለማጥቃት የወሰኑት እላለሁ፡፡ ምነው የአማራ ክልል መሪዎችስ ይሄን 200 ዓመታት ተዘፍቀንበት፣ መልካም ውጤት ያላመጣውን ጥላቻ ቢተዉት! ምናለ ምሳሌ ቢሆኑ! እላለሁ፡፡ አንዳንዴም፡- ህወሃትን የእጃቸውን ሰጣቸው፡፡ እነሱ ኃይል በጨበጡ ጊዜ፣ ተመልካች እስኪሰለቸው ድረስ አሁን እነ ዶክተር አቢይ እና የአማራ ክልል መሪዎች በቲቪ የሚያደርጉትን ያደርጉት አልነበረ? እንዲያውም የትግራይ ምሑራን "ስድቡን ተዉት" ሲሏቸው እንኳን ሊሰሙ፣ በማግሥቱ በእልህ መንፈስ፣ "ነፍጠኛ! ትምክህተኛ!" ሲሉ አልነበር? "ብድር በምድር" እላለሁ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ፣ በጌታ ቃል መነጽር ላየው እመርጥና፣ ዶክተር አቢይ የሰውን ጊዜያዊ ጠባይ ትተው፣ የሚያምኑትን የፍቅር አምላክ ትምህርትን ተከትለው፡-

አንደኛ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች መሃል ለዘመናት ሲካሄድ በኖረው የመቀያየም እሳት ውስጥ ቤንዚን ከሚያርከፈክፉ፣

ሁለተኛ፣ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በመታረቅ የሚመጣውን $$$ በማሰብ፣ ለትግራይ ሕዝብ ደንታ እንደሌላቸው የሚመስል ጠባይ ከሚያንጸባርቁ፣

በሁለቱም ሁኔታዎች፣ ፍቅርን መሥራች ቢሆኑ ኖሮ፣ ምን ዓይነት የፖለቲካ እና የታሪክ ድል ይሆንላቸው ነበር! እላለሁ፡፡ Missed opportunity የሚባለው እንዲህ ነው፡፡

መዝጊያ፡-

የዶክተር አቢይ ወደ መሪነት የመምጣት ትንቢት፣ ምንም እንኳን ከፈጣሪ የመጣ ነው ብዬ ባምንም፣ ለመልካም ጊዜ ነው ወይስ ለጭንቅ ዘመን? ለሚለው ጥያቄ፣ እኔ በበኩሌ፣ መልሱ ወደአሉታው የሚያመዝን ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ግምጋሜ ያደረሱኝን፣ ከላይ የጻፍኩትን እና ከዚህ በታች የዘረዘርኩትን ምክንያቶቼን በማንበብ፣ የመጣው ትንቢት፣ ስለ ጥሩ መሪና ስለ ጥሩ ዘመን መሆኑን ወይም አለመሆኑን፣ እስቲ አንባቢ ይፍረድ!

 

(1) ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ኃይል ከያዙ ጀምሮ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምዕራብ እና በምሥራቅ ሰላም የለም፡፡ በብሔር ግጭት የሞቱት ሰዎች ብዛት ይዘገንናል፤

(2) በዓለም ተወዳዳሪው ሌላ አንድ አገር ብቻ የሆነ፣ የተፈናቀለ ሕዝብ ብዛት፤ እንዲሁም አብሮ የሚመጣው በሽታና ሞት ያስለቅሳል፤

(3) ንግድ መቀዝቀዙ፣ ዶላር መጥፋቱ እና ዕቃ መወደዱ ያሳስባል፤

(4) ዓይኑን አፍጦ በግላጭ፣ ፊት ለፊት የመጣ ጎሳን መሠረት ያደረገ ጥላቻ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ስድቦች እና ዘፈኖች እየተለመዱ መምጣታቸው፣ መጥፎ ጊዜያትን ያመለክታል፤

(5) በሳቸው ጊዜ የመጡት ችግሮች ከባድ በመሆናቸው፣ ተበደልን የሚሉ ክልሎች፣ መፍትሔ ፍለጋ ለመገንጠል እንዳይወስኑ የሚፈራበት ጊዜ፣ የጥሩ ዘመናት ምልክት አይደለም፤

(6) የእርስ በርስ ውጊያ በኦሮሚያ መጀመሩ ያደብናል፡፡ ያንቀጠቅጣል፡፡ ይመራል፡፡ ያንገሸግሻል፡፡ ከሳቸው ችኩል የ"አገር ግቡ" ጥሪ ውጤት መሆኑ ያሳፍራል፣ ያናድዳል፤

(7) ብዙ ሰላማዊ ሰው ከገበሬው ጭምር መሣሪያ ታጥቋል፡፡ ዶክተር አቢይን ለወንበራቸው ካበቁት አንዱ አቶ ገዱም፣ የገበሬውን መታጠቅ በኩራት ማመናቸው፣ ለጭንቅ ዘመን የሚያዘጋጁን ይመስላል፡፡ ለበረከት እና ለብልጽግና ዘመን ሰው ለመገዳደጋል አይዘጋጅም፤

(8) የሚቀጥለው ጦር ሜዳ መቀሌ ይሆን? ወይስ ኦሮሚያ ውስጥ በመፍሰስ ላይ ያለው የሕዝብ እንባና ደም፣ ጦርነትን እንዳይመርጡ ያረጋቸው ይሆን? ያሰኛል፡፡ "ኧረ ቲም ለማ፣ ኧረ አቶ ገዱ! ምንድነው ጉዱ?"

 

"እግዚአብሔር ሆይ!

       ዶክተር አቢይን፣ ችኩልነትን አርቅላቸው፡፡ የሰከነ መንፈስ ስጣቸው! እያልኩ እጸልያለሁ፡፡ እናንተስ?

       ጌታ ሆይ፣ ጸሎታቸውን በመንፈስ ቅዱስህ አስተካክል! ማስተዋልን፣ ዕውቀትን እና ጥበብን ሰጥተህ፣ ራሳቸውን እና የሥራቸውን ውጤት ተገንዝበው፣ ራሳቸው ትክክሉን እርምጃ እንዲወስዱ እርዳቸው!

       እስከዚያው፣ በዕድሜም በጥበብም በሳል የሆኑ በጎ መካሪዎችን በአካባቢያቸው አብዛላቸው!

       እሳቸውንም በትሕትና የሚሰማ ልብ ስጣቸው!

       ለፌደራል ሚሊታሪው አስተዋይነትን እና ታጋሽነት አብዛለት!

       እንደ ርዋንዳ፣ ሱማሌ ወይም ሊቢያ እንዳንሆን እንድንጸልይ በነቢያቶችህ በነገርከን መሠረት የምንጸልየውን ጸሎት ስማን!

       የትግራይ ሕዝብ ጦርነትን እንዳይመርጥ፣ ያልታሰበ አዲስ መፍትሔን እንዲፈጥር እርዳው!

       ለዘመናት የኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ደም የፈሰሰው ይብቃ! በቃችሁ በለን!

       በኦሮሚያ የተነሣው ጦርነት በቶሎ ይቁም! የልጆቻችን ደም አይፍሰስ! በቃችሁ በለን!

       ሌላ የኦሮሚያ እናት አታልቅስ! በቃችሁ በለን!

       ታሪክ የምትቀለብስ አምላክ ሆይ! ካሁን በኋላ የአንድ ሰው ደም አይፍሰስ! ከቀያቸው የተፈናቀሉት አንድ ተኩል ሚልዮን ወገኖቻችን ወደየቤታቸው ይግቡ! የጦርነት ወሬ ይጥፋ! ችግር ይጥፋ!

       ብር፣ ዶላር፣ ዩሮ እና ዬን እየተጠራሩ አገራችን ይግቡ! ባንኮቻችን በውጭ ምንዛሪ እጭቅ ይበሉ!

ኢንቬስተሮች ይረባረቡብን!

       ባገራችን ሰላም ይሁን!

       አሜን፣ ኬር፣ ኬር ይሁን ኬር፣ ኬር ይሁን ኬር፣ ኬር ይሁን ኬር፣ ኬር ኬር ኬር . . . . . .

 

በዩ ትዩብ የምትገኘውን "ኬር ትሁን ኢትዮጵያ፣ ይሁን ይሁን አሜን ይሁን" የምትለውን ሙዚቃ ጋበዣችኋለሁ፡፡

https://www.youtube.com/watch?reload=9&v=P6O7cv9pP9E

 

Back to Front Page