Back to Front Page


Share This Article!
Share
የለውጡ ባለቤት ማን ነው?

የለውጡ ባለቤት ማን ነው?

(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

2-23-19

ብዙ ጊዜ ታሪክ ራሱን ይደግማል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ሌሎቻችሁም እንደኔው ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ ታሪክ ራሱን የሚደግመው ከታሪክ ከራሱ ተምረን ማስተካከልና ማቆም የሚገባንን ማረምና ማስተካከል ካልቻልን ነው፡፡ ከታሪክ መማር የሚያስፈልገው ስህተትን ላለመድገም ነው፡፡ በኛ ሀገር ግን ታሪክን የመድገም አባዜ ስለተጠናወተን ወይም ታሪክን ለመድገም እንዲያመቸን በዩንቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍልን እስከ መዝጋት እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ሰው ከታሪክ ካልተማረ ከምንም ነገር መማር አይችልም፡፡ ሰው ካለፈ ጥፋቱና ካለፈ ልማቱ ካልተማረ ሊማር የሚችለው ከምርምር ውጤቱ ነው፡፡ መመራመር ደግሞ የሁላችንም ሥራም ፀጋም አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ስልጣን ከያዙበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ አጀንዳ ሆኖ በየሶሻል ሜዲያው መነታረኪያ የሆነው ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ የለም እከሌ ነው የሚለው የለውጥ ባለቤትነትና የአርበኛነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ መነሳቱ የሚጠበቅ ስለሆነ አያስገርምም፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ ግን የለውጡ ባለቤትነት ለምን ተፈለገ? የሚለው ነው፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ በልባችን እንያዝና ለመልሱ ግብዓት የሚሆን ነገር ከታሪክ ስንክሳር ውስጥ እያገላበጥን እንፈልግ፡፡ ከውጪ ሀገር እንጀምር፡፡

Videos From Around The World

በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሁለት አሰርት ዓመታት በሩሲያ የተለያዩ አብዮቶች ተካሂደዋል፡፡ ታላቁ የሩሲያ አብዮት የተካሄደው ግን እ.ኤ.አ በየካቲት 1917 ነበር፡፡ የዚያ አብዮት መነሻ ምክንያቶች ከሆኑት ውስጥ፤ በሩሲያ የነበረው የዛሩ አምባገነናዊ አስተዳደር፣ አንድ ሀገር፣ አንድ መንግስት፣ አንድ ቤተክርስቲያን' በሚል መንፈስ ሁሉንም ጎሣዎች ጨፍልቆ ሩሲያዊ' የማድረግ ዘመቻ፣ ድሃና ሀብታም የሚል ማህበራዊ መደብ መፈጠሩና የኢንዱስትሪ አብዮት የፈጠረው ግፊት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የሚገርመው ነገር ይህ አብዮታዊ እንቅስቃሴ በሚካሄድበት ወቅት ሌኒን ዙሪክ ስዊዘርላንድ ነበር፡፡ ትሮትስኪ ኒውዮርክ አሜሪካ ነበር፡፡ ጆሴፍ ስታሊን ሳይቤሪያ አካባቢ በምትገኝ አችኒስክ የተሰኘች ትንሽዬ ከተማ ግዞት ላይ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎች ዋነኛው የአብዮቱ ግለት በነበረበት ወቅት ግንባር ቀደም መሪ አልነበሩም፡፡ አብዮቱ ተካሂዶ፣ የሞተው ሙቶ፣ የቆሰለው ቆስሎ፣ የዛሩ መንግስት ተገርስሶ የስልጣን ቅርምቱ ሲጀመር ከያሉበት ጎሬ መጥተው የአብዮቱ መሪ እኛ ነን ብለው ስልጣኑን ከህዝቡ ቀሙ፡፡ በመላዋ ሶቭየት ህብረት ለሰባ ዓመታት የዘለቀ የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ ስርዓትም አሰፈኑ፡፡ የአብዮቱ ቀበኞች የሆኑት እነ ሌኒን ሞቶና ቆስሎ ስልጣን ላይ ያወጣቸውን ህዝብ በዘመነ ስልጣናቸው አሰሩት፣ ገረፉት፣ አንገላቱት፡፡

ወደ መካከለኛው ምስራቅ እናምራ፡፡ በዓለም ላይ ከሚታወቁ ደም አፋሳሽ አብዮቶች ውስጥ እ.ኤ.አ በ1979 በኢራን የተካሄደው ተጠቃሽ ነው፡፡ የዚህ አብዮት ገፊ ምክንያቶች፤ በኢራኑ የሻህ አምባገነናዊ ስርዓት መማረር፣ የማህበራዊ ፍትህ መጓደል፣ የምዕራብ ኢምፔሪያሊዝም መንሰራፋትና ሌሎችም ሃይማኖታዊ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የሚገርመው ነገር በዚህ የተጋጋለ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ወቅት አያቶላ ኾሚኒ ፈረንሳይ ፓሪስ በግዞት ይኖር ነበር፡፡ አብዮቱ ተካሂዶ የኢራኑ የሻህ መንግስት ሲገረሰስ የድል አጥቢያ አርበኛ የሆነው አያቶላ ኾሚኒ ከፈረንሳይ ወደ ቴህራን ተመለሰና በአውሮፕላን ማረፊያ በሰጠው መግለጫ የአብዮቱ መሪ ማን ነው? ተብሎ በጋዜጠኛ ሲጠየቅ እኔና እኔ ነኝ ነበር ያለው፡፡ የአብዮት ቀበኞችና የድል አጥቢያ አርበኞች ሁኔታ እ.ኤ.አ. በ2011 በፈነዳው የዓረቡ ዓለም የፀደይ አብዮትም በብዛት ተስተውሏል::

ወደ ራሳችን እንመለስ፡፡ በሀገራችን ከ1960ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ማህበረሰባዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የአፄ ኃ/ስላሴን መንግስት ያስጨንቁ ነበር፡፡ በርካታ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ የአመፅ እርምጃዎች ነበሩ፡፡ በጭሰኛነት የተማረሩት የባሌና የጎጃም ገበሬዎች አመፅ፣ የተማሪዎች የመሬት ላራሹ ጥያቄ፣ በፋብሪካዎችና በኩባንዎች ይሰሩ የነበሩ ወዛደሮች የሥራ ማቆም አድማ፣ የሙስሊሞች የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ፣ የሴቶች የእኩልነት መብት የመሳሰሉት እርምጃዎች የአፄውን አልጋ ያነቃነቁ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡

እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለማክሸፍ የኃይል እርምጃ ይወስድ የነበረው መለዮ ለባሹ የራሱን ደመወዝ ከማስጨመር ውጪ ለህዝባዊ እንቅስቃሴው የረባ አስተዋጽዖ አልነበረውም፡፡ ይሁን እንጂ፤ ህዝቡ የአፄውን መንግስት ገዝግዞ፣ ገዝግዞ መውደቂያው ሲቃረብ ደርግ የሚባል የ108 ሰዎች ወታደራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ የህዝቡን የለውጥ ውጤት የቀማው ግን ወታደሩ ነበር፡፡ በዚህም ሂደት ስልጣን ከነ ቀኛዝማች ወደ እነ አስር አለቃ በጉልበት ተሸጋገረ፡፡

ደርግ ስልጣንን ከህዝብ ቀምቶ መውሰዱ ሳያንስ ስልጣን ከጨበጠበት እለት ጀምሮ በወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ምክንያት በህዝብ የተጠላ መንግስት ነበር፡፡ እናም ስልጣን ከጨበጠበት እለት ጀምሮ ለ17 ዓመታት በግልፅም በስውርም የሚካሄዱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ህዝቡ የትጥቅ ትግል ለሚያደርጉ ኃይሎች መጠጊያና መጠለያ ብቻ ሳይሆን ልጆቹ ትጥቅ ትግሉን እንዲቀላቀሉ መርቆ ልኳል፡፡ ለታጋዮቹ የሚበላውን አካፍሏል፡፡ የትጥቅ ትግሉ እየተጠናከረ ወደ መሀል ሀገር በመጣበት ወቅት ህዝቡ ለታጋዮቹ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርግላቸው ነበር፡፡ በህዝቡ ሁለገብ ትግልና እገዛ ደርግ በ1983 ሲገረሰስ፤ ወያኔ ትግሉን በዋናነት የመራሁት እኔ ነኝ፣ አሁንም ሀገሪቱን መምራት የሚገባኝ እኔ ነኝ በሚል መንፈስ የህዝቡን የትግል ውጤት ጠቅልላ ወሰደቺው፡፡ ከታሪክ ባለመማራችን ለሁለተኛ ጊዜ የህዝብ ትግል ውጤት አብዮተኞች ነን በሚሉ የህዝብ አብዮት ቀበኞች መዳፍ ስር ወደቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ስልጣን ከእነ አስር አለቃ ወደ እነ ተጋዳላይ በጉልበት ተሸጋገረ፡፡

ወያኔ የትጥቅ ትግሉ ግንባር ቀደም ፈላሚ፣ የትግሉ መሪና ፊት አውራሪ እኔ ስለሆንኩ እኔ ያልኩት መፈጸም አለበት በማለት የፖለቲካ ፕሮግራሟን የሀገሪቱ ህገ መንግስት አካል እንዲሆን አደረገች፡፡ ከዚያ በኋላ፤ በዚያ ህገ መንግስት እየማለችና እየተገዘተች የህወሓትን የበላትነት አንግሳ 27 ዓመታት ብትቆይም ዛሬ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከታሪክ ባለመማራችን በአገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ላይ አደገኛ ሁኔታ እያንዣበበ መሆኑ ይስተዋላል፡፡ ዛሬም የአብዮት ቀበኞች ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን አለብኝ በሚል ውዝግብ የማህበራዊ ሜዲያውን አምድ እያጨናነቁት ነው፡፡ ለመሆኑ አሁን የተገኘው ለውጥ የትግል እንቅስቃሴ መቼ ነበር የጀመረው? ባለቤቱስ ማን ነው? ቀጥለን እንየው፡፡

የለውጡ እንቅስቃሴ መቼ ተጀመረ?

አንዳንድ ሰዎች የዚህ ለውጥ አቀጣጣዮችና ባለቤቶች በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን ህዝባዊ ማዕበል ያቀጣጠሉት ቄሮዎች፣ ፋኖዎች፣ (ወጣቶች) ይመስሏቸዋል፡፡ ይህ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ አበው ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ እንዲሉ ከወያኔ ስልጣን መያዝ ጀምሮ የነበረውን የለውጥ ትግልና የሕዝብ እንቅስቃሴ በአጭሩ እንይ፡፡

ወያኔ መራሹ ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ደርግን ከገረሰሰ በኋላ ለአንድ ወር የቆየ ጊዜያዊ መንግስት አቋቋመ፡፡ ከአንድ ወር በኋላ (በሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ) የሽግግር መንግስት መመስረቻ ኮንፈረንስ አካሄደና ከጊዜያዊነት ወደ ሽግግር መንግስት ተሸጋገረ፡፡ ለ17 ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ትግል የተካሄደው ይህንኑ ለማድረግ ነበርና ይሄ ባልከፋ! የከፋው ነገር በሽግግር ጉባዔው እንዲሳተፉ የተጠሩት ከኢህአዴግ ጋር ለመብረር የሚችሉ ተመሳሳይ ላባ ያላቸው መፎች ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ፣ የፖለቲካ አጀንዳ የነበራቸው፣ ለዚህም 17 ዓመታት ደርግን በትጥቅ ትግል ሲታገሉ የነበሩትን ጭምር ያገለለው የሽግግር ኮንፈረንስ የለውጥ ኃይሎችን ውጪ አድርጎ የተካሄደ በመሆኑ ቀጣዩ ከወያኔ ጋር የሚደረግ ትግል የተጀመረው እዚያው የጉባዔው አዳራሽ ውስጥ ነበር፡፡

በዚያ ጉባዔ ላይ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህራንን ወክለው የተገኙት እውቁ ቀዳጅ ሐኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ከወያኔ/ኢህአዴግ መንግስት ጋር የሚደረገውን ትግል እዚያው አዳራሽ ውስጥ ለኩሰውት ወጡ፡፡ ያኔ የተጀመረው የተቃውሞ ትግል አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ እያለ እስከ 1997 ድረስ ዘልቋል፡፡ በዚህም ጊዜ ትግሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ መምህራንን፣ የሰራተኛ ማህበር አባላትን፣ ተማሪዎችንና ወጣቶችን ማገዶ አድርጓል፡፡ ወላፈኑም ህዝቡን በአስከፊ ሁኔታ ለብልቧል፡፡

በ1997 ተቃዋሚዎች ህዝቡን ለማንቀሳቀስ ባደረጉት ጥረት የለውጡ የትግል ግለት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከታሪክ ባለመማር ተቃዋሚዎች ውጤቱ በእጃቸው ሳይገባ የድሉ ባለቤት እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ በሚል ሽኩቻና ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ወያኔ/ኢህአዴግ የህዝቡን ድምፅ በመዝረፍ ዳግም የለውጡን ውጤት በመቀማት የፓርቲዎች አውራ ነኝ ወደሚልበት ደረጃ ተሸጋገረ፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ የተቃዋሚው ጎራ የለውጥ እንቅስቃሴ በተስፋ መቁረጥ የተሞላና የተቀዛቀዘ ቢመስልም የተዳፈነው የህዝብ ትግል ከሞርታር ወደ ኮምፒዩተር፣ ከጥይት ወደ ወረቀት በመሸጋገር ማህበራዊ ሜዲያንና ኢንተርኔትን የማቀጣጠያ ምድጃ አድርጎ የተዳፈነው እሳት እየተገላለጠ መቀጣጠል ጀመረ፡፡ ይሄኛውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ለየት ያደረገው ትግሉ በወያኔ/ኢህአዴግ ጓዳ ውስጥ ጭምር መካሄዱ ነው፡፡

ቄሮና፣ ፋኖ (ሌሎችም ወጣት የለውጥ ኃይሎች) የመጨረሻዎቹን የትግል ዙሮች በፈጣን እርምጃ በመራመድ ክሯን በጠሱ፡፡ ወጣቶቹ የመጨረሻውን ዙር እንዲያከሩ በቴሌቪዥንም፣ በጋዜጣም፣ በሬዲዮም፣ በኢንተርኔትም፣ በፌስቡክም፣ በሌሎችም የማህበራዊ ሜዲያ አውታሮች የተሰለፉ የግፊት ኃይሎች (አክቲቪስቶች) በሞራል አነቃቂነት በማጨብጨብ የትግሉ ግለት ከፍ እንዲል አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም ለውጡ ስልጣንን ከተሸናፊ ወደ አሸናፊ ሳይሆን አሸናፊም ኢህአዴግ ተሸናፊም ኢህአዴግ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው ኢህአዴግ ነው፡፡ ዛሬም እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው፡፡ ልዩነቱ ኢህአዴግ መሆኑ ላይ ሳይሆን ኢህአዴግን የሚመሩት ግለሰቦች መቀያየራቸው ላይ ነው፡፡ በርግጥ የተቀየሩት ግለሰቦች አዳዲስ አስተሳሰቦችንና አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎቻችን ወቅቱ ከአምባገነናዊ አስተዳደር ወደተሻለ የዴሞክራሲ ስርዓት የምንሸጋገርበት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ አዲሱ የኢህአዴግ አመራር የጀመራቸውን የለውጥ እርምጃዎች ማገዝና ማጠናከር ይገባናል የሚል እምነት ያደረብን፡፡

በበኩሌ አሁን የተገኘውን ለውጥ ወደ ሌላ ከፍ ያለ ለውጥ የሚያሸጋግረን ለውጥ እንጂ በራሱ የተሟላ ለውጥ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ለውጥ የተሟላ ለውጥ ሊሆን የሚችለው አሁን በተገኘው ለውጥ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ተጠቅመን በመጪው ምርጫ ህዝቡ ስልጣኑን የተሻለ ለሚለው የፖለቲካ ኃይል የሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት በህዝብ ትግል የተገኘውን ለውጥ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት ወቅት ነው፡፡

የለውጡ ባለቤት ማን ነው?

ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው አሁን የተገኘው ለውጥ ባለቤት አንድ የፖለቲካ ቡድን ወይም አክቲቪስት ወይም ጋዜጠኛ ወይም ግለሰብ አይደለም፡፡ ፌስቡክም፣ ቴሌቪዥንም፣ ሬዲዮም፣ ኢንተርኔትም፣ ሶሻል ሜዲያም አይደለም፡፡ አሁን የተገኘው ለውጥ አንድ ብቸኛ ባለቤት የለውም፡፡ ባለቤቱ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ የለውጥ ኃይሎችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ደርግ እኔ ነኝ ንጉሡን የገረሰስኩት፣ ባለ ውለታችሁ ነኝ ብሎ 17 ዓመት ገዛን፡፡ ወያኔ በጠመንጃ ታግየ ደርግን የጣልኩት እኔ ስለሆንኩ ለሰራሁት ውለታ ሀገር የመምራት ስልጣን ሊሰጠኝ ይገባል ብሎ 27 ዓመት ገዛን፡፡ አሁንም ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ ባዩ በዝቷል፡፡ ከንግዲህ ታሪክ ራሱን ሊደግም አይገባልም፡፡ እናም የለውጡ ባለቤት እኔ ነኝና ቀይ ምንጣፍ አንጥፉልኝ፣ የለውጡ አንቀሳቃሽ ሞተር እኔ ነበርኩና ሹመት ይሰጠኝ፣ የህዝባዊ ማዕበሉ መሪና ታጋይ እኔ ነበርኩና መሬት ይሰጠኝ፣ እውቅና ይሰጠኝ የሚሉ መዝሙሮች መቆም አለባቸው፡፡ ሁላችንም የታገልነው ማንም አስገድዶን፣ ለማንም ብለን አልነበረም፣ አይደለምም፡፡ በመሆኑም ለትግል ውለታችን ስልጣንም ገንዘብም ሌላም የምንጠይቀው ነገር ሊኖር አይገባም፡፡

በ1966 እነ ቀኛዝማች በእነ አስር አለቃ ተቀየሩ፣ በ1983 እነ አስር አለቃ በተጋዳላይ ተቀየሩ፡፡ ሁለቱ የመንግስት ለውጦች የአስተዳደራዊ ስርዓት (change of governance) ለውጦች አልነበሩም፡፡ አሁን ሀገሪቱ የስርዓት ለውጥ ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዢዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ተገዢዎችም (ህዝቡ) የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ህዝብ ከሌለ ለውጡ የተሟላ ለውጥ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ባህላችን በአስተሳሰብ አብዮት የታጀበ፣ ላቅ ያለ ደረጃ ያለው (ራዲካል) ለውጥ ሊደረግበት ይገባል፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ሸምሰዲንና ገብረመድን እኩል ስላልነበሩ ነው ለውጥ ያስፈለገው፡፡ አሁንም በዚያው መስመር እንሂድ ብለን ሙሣና ቶሎሣ የሚል የልዩነት ጉዞ ከጀመርን ዘፋኙ በ17 መርፌ እንዳለው ነው የሚሆነው፡፡ እናም ታሪክ ራሱን እንዳይደግም!

 

ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.comማግኘት ይቻላል፡፡

Back to Front Page