Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሀገራዊ አገልግሎት ቢታወጅስ?

ሀገራዊ አገልግሎት ቢታወጅስ?

(ራህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

1-12-19

የዚህ ጽሁፍ ርእስ ብዙዎችን ሊያስገርምም፣ ሊያስደምም፣ ሊያደናግርም፣ ምን ማለቱ ነው? ሊያስብልም፣ እንደሚችል መገመት ሊቅነትን የሚጠይቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ምን ማለቴ እንደሆነ አብራራለሁ፡፡ ምን ዓይነት ሀገራዊ አገልግሎት? የሚለውን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት ግን ይህንን ጥያቄ እንዳነሳ ያደረጉኝን ምክንያቶች ለማስቀደም ወደድሁ፡፡

Videos From Around The World

የኢትዮጵያ ሀገራችንን ዕድሜ ጠገብ ሰነዶች ስናገላብጥ በጎላ መንጎል (ብዕር) ተከትቦ የምናገኘው ታሪክ የፍቅርና የመደመር ታሪክ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ መመንደግን የሚያሳይ፣ ባለጠጋነትን የሚመሰክር አይደለም፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ መላቅን የሚያመላክትም አይደለም፡፡ ጉልሁና ዋነኛ ሆኖ እንደ ዘበት የሚዘከረው ታሪካችን መገዳደል፣ መጫረስ፣ አካል ማጉደል፣ መማረክ፣ መስለብ፣ ማሰር፣ መግረፍ፣ ነው፡፡ ይህንን ታሪካችንን የመርዶ ታሪክ ይለዋል አንድ የታሪክ ምሁር የሆነ ወዳጄ፡፡

በተለምዶ አነጋገር ኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ አላት ይባላል፡፡ ልክ ነው፤ ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በዚህ ሁሉ የዘመናት ሂደት የጦርነት ነጋሪት ያልተጎሰመበት ወቅት ያለ አይመስለኝም፡፡ መላ ህይወቱን በሰላምና በእፎይታ ያሳለፈ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ስለመኖሩ የታሪክ ድርሳናት አጉልተው አያሳዩንም፡፡ የታሪክ ሊቃውንትም አይነግሩንም፡፡ ምሁራን በትምህርት ቤት አያስተምሩንም፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችም ሆኑ የጎሳ መሪዎች አይተርኩልንም፡፡ ወላጆቻችን የቀደምት መሪዎችን ጦረኛነትና ገዳይነት እንጂ ፍቅርና ልማታቸውን አላወጉንም፡፡

ኢትዮጵያ ያልተነካ ሃብት ያላት፤ ድንግል መሬት ያላት ሀገር ናት የሚለውን አባባል ያለ ምንም ማንገራገርና ያለ ምንም ማቅማማት ለመቀበል የምገደደው፤ እድሜ ልኩን ሲዋጋና ሲገዳደል የኖረ ህዝብ ጫካ መንጥሮ፣ ተራራ ንዶ፣ የመስኖ መስመር ዘርግቶ፣ መሬት አርሶና ቆፍሮ የሚያለማበት ጊዜ እንደማይኖረውና ጫካውንም ለሽፍትነት ወይም ለመደበቂያነት እንደሚፈልገው ስለምገነዘብ ነው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት እንደመሆኗ ታላላቅና ታዋቂ ወደቦችና ከተሞች እንደነበሯት ይነገራል፡፡ ግን እነዚያ ከተሞችና ወደቦች፣ እነዚያ የዘመን አሻራ የታተመባቸው ቅርሶች ስማቸውን ብቻ ነው ታሪክ የመዘገባቸው፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት ወድመዋል፡፡ አፈር ትቢያ ሆነዋል፡፡ ፍርስራሻቸው እንኳ የለም፡፡ የገንቢም የአፍራሽም ማንነት ተለይቶ አይታወቅም፡፡ አንዳንዱን ሲሰሙት ተረት ተረት ይመስላል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ፤ ከጂማ እስከ ታጁራ፣ ከቦሳሶ (አሶሳ) እስከ አውሳ፣ ከመሐል አገር እስከ ምፅዋ፣ ከሸዋ እስከ ጂቡቲ፣ እየተባለ በተረት መልክ ይጠቀሳል እንጂ የምርቱ ዓይነት፣ የሸቀጡ ብዛት፣ የሚሄድበት መዳረሻም ሆነ ወደኛ የመጣበት መነሻ አገር በውል አይታወቅም፡፡ ከዘመን ዘመን ያለው እድገትም ሆነ ውድቀት አይታወቅም፡፡

የሩቁን ዘመን ትተን ባለፉት አንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት የነበረውን ታሪካችንን ብናይ ጥሩ ምናባዊ ስእል የሚከስትልን ይመስለኛል፡፡ አጤ ቴዎድሮስ በጦርነት መሀል ተወልዶ፣ አድጎና ጎልምሶ በጠመንጃና በጉልበት ዙፋን ላይ ወጣ፡፡ በዘመነ ስልጣኑ ይሄን አረሰ፣ አመረተ፣ ሳይባል በመጣበት ጠመንጃ ተወገደ፡፡ አጤ ዮሐንስ በጠመንጃ ወደ ንጉሰ ነገስትነት ተሸጋገረ፡፡ መተማ ላይ አንገቱን የተቀላው ሁመራ ያለውን የሰሊጥ መሬት ሲጎበኝ አልነበረም፡፡ ባለ ተራው እምዬ ምኒልክ (መጠነኛ የሚቆጠሩ ስራዎች መስራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) ሽፍታ ሆኖ አድጎ፣ ሽፍታና ወራሪ ሲያሳድድ ኖሮ አለፈ፡፡ እያሱ፣ ዘውዲቱ፣ አጤ ኃ/ስላሴ ተከታተሉ ደርግ ጠመንጃ ነክሶ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገባ፤ በጦርነት ወረደ፡፡ ኢህአዴግ በክላሽንኮቭ ስልጣን ያዘ

አሁን ወዳለንበት ወቅት እንሻገር ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል፡፡ አሁን ውጊያው በዲሞትፈር ሳይሆን በኮምፒዩተር ሆኗል - በጣት! (በጣት ምላጭ ከመሳብ ፌስቡክ ላይ በጣት መጠንቆል ይብሳል) በኢንተርኔት እየተዋጋን ነው፡፡ በማህበራዊ ሜዲያ በስድብና በነገር እየተሞሻለቅን ነው፡፡ ተማሪው የከተመው እዚያ ነው፡፡ ምሁሩ ምሽግ የያዘው እዚያ ነው፡፡ ፖለቲከኛው የሚተጋተገው እዚያ ነው፡፡ መንግስት ሀገር እየመራ ያለው በሜዲያ ወጣ ገባ እያለ ነው እንጂ አራት ኪሎ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ ብቻ አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ የሚያገኘው በቴሌቪዥን ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡ በዚህ ወቅት የሁሉም ሰው ትኩረት ፖለቲካ ሆኗል፡፡ ኢኮኖሚው ተረስቷል፡፡ ግብርናው ተዘንግቷል፡፡ መሬቱ አረም ውጦታል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ተሽመድምዶ ወድቋል፡፡ ምርትና ምርታማነት አፈርድሜ ግጧል፡፡

ሁለት አሃዝ (ዲጂት) አደገ ሲባል የነበረው ኢኮኖሚያችን በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው? በስንትና ስንት የዲፕሎማሲ ውትወታ የመጡ የውጭ ሀገር ባለ ሀብቶች ምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት? በብዙ ቢሊዮን ብር የተገነቡ የኢንዱስትሪ መንደሮችና ፓርኮች ምን እየተሰራባቸው ነው? ይህ ሁኔታ ወደ ሌላ ጦርነት ወደ ሌላ ተጨማሪ መበላላትና መጫረስ ካልሆነ ወደ የት ይወስደናል?

እነዚህ ጥያቄዎች በዋዛ ፈዛዛ፣ በሳቅ በፈገግታ የሚታለፉ ሆነው አይታዩኝም፡፡ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ፈተናዎች መሆናቸውም እርግጥ ነው፡፡ እናም፤ እንደ ጥንት እንደ ጧቱ፣ እንደ አያት ቅድመ አያቶቻችን ውጊያ ላይ ነን እንጂ ሥራ ላይ አይደለንም፡፡ የተመረተውን እያጠፋን ነው እንጂ ምርት ላይ አይደለንም፡፡

አለማምረት ብቻ አይደለም፤ ኢንቨስተሮች ተማረው እንዲወጡ እያደረግን ነው፡፡ በተለይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለ ሀብቶች በአዝመራቸው ላይ ከብት ተለቆበት ቡቃያው በመውደሙ፣ የመስኖ ካናሎች በመፍረሳቸው፣ ለዓመታት የተከሏቸው የፍራፍሬ ዛፎች በመቆረጣቸው፣ ትራክተሮችና ኮምባይነሮች በመቃጠላቸው፣ ተማረው እርሻዎቻቸውን ዘግተዋል፡፡ ሰራተኞችን በትነዋል፡፡ (ያለን ሳያንስ ተጨማሪ ስራ ፈት እየተፈጠረ መሆኑን ልብ ይሏል!) በዚህም ምክንያት ቤተሰብ እየተበተነ ነው፡፡

ሆነ ሆኖ መፍትሄውስ ምንድነው? ጥሩ! ወደ መፍትሄው እናምራ! እንደኔ እንደኔ ከዋነኛ መፍትሄዎቹ አንዱ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የሚያስችል ሀገራዊ አገልግሎት ማወጅ ነው፡፡ አራት ነጥብ! ዝርዝሩን እንይ፡፡

በዚህ ወቅት ለተገኘው ሀገራዊ ለውጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበሩት ወጣቶች ናቸው ብል የሚቃወመኝ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ወጣቶች የለውጥ ኃይል ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ወጣቶች የለውጥም የነውጥም (የልማትም የጥፋትም) ኃይል ናቸው፡፡ ወጣት-መራሽ ለውጥ በተደራጀ ኃይል ካልተመራ ወደ ነውጥነት ይሸጋገርና የመጣው ለውጥ ባልተጠበቀ ጉልበተኛ መዳፍ ውስጥ ገብቶ መና ይቀራል፡፡ (በ1966 ወጣቶች ያመጡት ለውጥ በወታደራዊ ደርግ መጠለፉን ልብ ይሏል)

የዚህ ዘመን የሀገራችን ቄሮዎች፣ ፋኖዎች፣ ዘርማዎች፣ ኤጀቶዎች፣ ኮበሌዎች፣ ገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግን በሰልፍና በነውጥ ነቅንቀው ነቅንቀው ከውስጡ ለውጥ መሪ ኃይል እንዲወጣ በማድረጋቸው ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው የስልጣን ሽግግር ተደርጓል፡፡ ይሄ በበጎነት ሊወሰድ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

ወጣቱ ይህንን ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው የስልጣን ሽግግር ወደ ጎን በመተው ወይም ልብ ባለማለት እስከ ታች ያለውን የመንግስት መዋቅር ካልተቆጣጠርኩ በማለቱ፤ ህዝብ በኳስ ሜዳ ተሰብስቦ ከንቲባ እስከ መምረጥ የደረሰበት አስቂኝ ትእይንት ለመታዘብ በቅተናል፡፡ በመንጋ በተሰጠ የጎዳና ላይ ፍርድ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀሙን ሰምተናል፡፡

ብልጭ ድርግም የሚለው ነውጥ በመቀጠሉ በአሁኑ ወቅት በርካታ ት/ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ተዘግተዋል ወይም ትምህርት አቁመዋል፡፡ ከበስተጀርባቸው እነ እከሌ አሉ/የሉም በሚል ውዝግብ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ተስተጓጉለዋል፤ ተዘግተዋል፡፡ የልማት ሥራዎች ተቋርጠዋል፡፡ መሰረተ ልማቶች እየወደሙና እየተበላሹ ነው፡፡ እነዚህና መሰል ተግባራት ደግሞ የለውጡ ሂደት የፈጠራቸው አሉታዊ ክስተቶች ናቸው፡፡

እና ምን ይደረግ? በተለያዩ ሀገሮች በእንደዚህ ያለ ወቅት ስልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች የሚወሰዱ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አሉ፡፡ በእኛም ሀገር ተሞክሮ አለ፡፡ በ1966 ዓ.ም አፄ ኃ/ስላሴን ከዙፋናቸው አውርዶ ስልጣን የጨበጠው ጊዜአዊ ወታደራዊ ደርግ በከተሞችና በትምህርት ቤቶች የነበሩ፤ ወታደር ወደ ካምፕ! ህዝባዊ መንግስት አሁን! እያሉ ይቀውጡ የነበሩ ወጣት የለውጥ ኃይሎችን የተገላገለው ዕድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ የሚል አዋጅ አውጆ ወጣት ተማሪዎችንና ምሁራንን ወደ ገጠር በማሰማራት ነበር፡፡

ይህንን የደርግ ተግባር የሚተቹ በርካታ ሰዎች እንዳአሉ አውቃለሁ፡፡ በበኩሌ የደርግ ዓላማ ቢገባኝም፤ በዚያ ወቅት ወደ መላ ሀገሪቱ የዘመቱ መምህራንና ተማሪዎች ለደርግ ዓላማ መጠቀሚያ ከመሆን ባሻገር በርካታ ታሪካዊ ተግባራትን አከናውነዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለምሣሌ፤ መሰረተ ትምህርት በማስተማር አርሶ አደሩን፣ ወዛደሩንና የከተማ ነዋሪውን ፊደል በማስቆጠር በጣት ከመፈረም አላቀውታል፡፡ (ከመሰረተ ትምህርት ተነስተው እስከ ፒ.ኤች.ዲ የደረሱ ሰዎችም ነበሩ)

ለዘመናት መሬት ለአራሹ የሚል መፈክር እየተስተጋባ ትግል የተደረገበትን ሀገራዊ አጀንዳ በመመለስ ረገድ ዘማች ተማሪዎች በገጠር የገበሬ ማህበራትን በማደራጀትና በጥቂት ፊውዳሎች ተይዘው የነበሩ መሬቶችን በማከፋፈል፤ በገዛ መሬቱ ላይ ለዘመናት ጭሰኛ የነበረው አርሶ አደር የመሬት ባለቤት እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዘማች ተማሪዎቹ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መጥተው ተሰበጣጥረው እንዲዘምቱ በመደረጉ የተለያዩ ብሄር ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ትውፊት፣ እንዲተዋወቁ መልካም እድል ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የእርስ በርስ መተዋወቂያና መማማሪያ መድረክም ነበር፡፡

አሁን ያለንበት ወቅት ከ1966ቱ አብዮት ጋር ተመሳሳይ ባህሪያት እንዳሉት አስባለሁ፡፡ ወቅቱ የለውጥ ወቅት ነው፡፡ ወቅቱ የሽግግር ወቅት ነው፡፡ በሽግግር ወቅት ደግሞ ሀገራዊ መመሰቃቀልና ማህበረሰባዊ መተረማመስ መፈጠሩ በብዙ ሀገሮች ታይቷል፡፡ በኛም ሀገር ተመሳሳይ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በመላ ሀገሪቱ (በገጠርም በከተማም) ስልሳ ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተማሪዎች እንደሆኑና በትምህርት ገበታ ላይ እንዳሉ ይታመናል፡፡ ይህ ለውጥ በአንድ ጀንበር እንዲመጣ የሚመኝ ትኩስ ኃይል በስራ ካልተጠመደ በረባ ባልረባው፣ በሰበብ አስባቡ፣ ምክንያት እየፈጠረ ሁከትና ብጥብጥ መቀስቀሱ አይቀሬና የሚጠበቅ ነው ብየ አስባለሁ፡፡

እንደኔ እንደኔ መንግስት በዚህ ወቅት መውሰድ ከሚገባው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ቀዳሚ መሆን ያለበት የወጣቶች ሀገራዊ አገልግሎትን ማወጅ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እዚህ ላይ እኔ እያልኩ ያለሁት ሀገራዊ አገልግሎት በደርግ ጊዜ ከነበረው ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑን ልብ ይሏል!

የደርግ ዘመን ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ስሙ እንደሚያመለክተው ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ከወያኔ ጋር መዋጋት ነበር፡፡ እኔ አሁን ምክረ ሃሳብ እያቀረብኩበት ያለው ሀገራዊ አገልግሎት ግን መደበኛ ወታደራዊ አገልግሎትን ሳይጨምር በሚከተሉት ተግባራት ላይ እንዲያተኩር የታለመ ነው፡፡ ይኸውም፡- በስልጠና ረገድ፤ መጠነኛ ወታደራዊ/ስፖርታዊ ስልጠና መውሰድ፣ በሀገሪቷና በህዝቧ ታሪክ፣ ባህልና ማንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መውሰድ፣ በዘማቾች መካከል የቋንቋና የባህል ልውውጥ መድረኮችን በመፍጠር ለአብሮነታችን የሚበጁ ግብረ ገባዊ እሴቶችን አንጥሮ ማውጣት፡፡ ስለ ዴሞክራሲና ስለ ሰብአዊ መብት መሰረታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና ውይይት ማድረግ፡፡

እነዚህ ተግባራት ከተከናወኑ በኋላ ዘማች ተማሪዎችን አሰበጣጥሮ በቡድን በቡድን በመደልደል በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ መመደብ፡፡ ዘማቾች በየተመደቡበት የዘመቻ ጣቢያ ላሉ ማህበረሰቦች በመሰረተ ትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ ወዘተ. በስልጠና ያገኙትን ትምህርት ማስተማር፡፡ በየተመደቡበት የዘመቻ ጣቢያ ላሉ ማህበረሰቦች ነፃ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የህዝብ አለኝታና የሥራ ኃይል መሆናቸውን ማሳየት፡፡ እግረ መንገዳቸውን የሥራ ባህል ማዳበር፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ሰላምና አንድነት፣ ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ ህገ መንግስት፣ ስለ መብትና ግዴታ፣ በማስተማር ህዝብን ማረጋጋት፡፡ ባህላዊ ማህበራዊ ፍትህ እንዲጎለብት ማገዝ፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ የሰላምና የእርቅ መድረኮችን በማደራጀት አገራዊ መግባባትን መፍጠር ዋነኛ ተግባር አድርጎ የመስራት ተልእኮ መስጠት አስፈላጊ መሆኑም ይታየኛል፡፡

በዘመቻው ላይ እነማን ይሳተፉ? የሚለው አከራካሪ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ አንዳንዶች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና መምህራኖቻቸው ቢሳተፉ የሚል ሃሳብ ሲያቀርቡ እሰማለሁ፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ የዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች የአንድ ዓመት ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ቢደረግ ይሻላል ይላሉ፡፡

እንደኔ እንደኔ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ የሀገራዊ ዘመቻው ተሳታፊዎች አካላዊ ብቃት ያላቸው፣ እድሜያቸው ከ18 - 30 ያሉ ዜጎች ቢሆኑ ይመረጣል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ የቆይታ ጊዜውም ከሁለት ዓመት ባይበልጥ ይመረጣል እላለሁ፡፡ ይሁን እንጂ፤ እነዚህ ተግባራት በዚህ ወቅት ይጀመሩ እንጂ ለወደፊት ህይወታችንም ጠቃሚ ስለሆኑ በሚመለከታቸው አካላትና በዩኒቨርስቲዎች አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ፣ ህግና ስርዓት ተዘጋጅቶ፣ ከሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ በቀጣይ ትውልዶች ተግባራዊ እንዲደረግ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ይህን መሰሉ ሀገራዊ አገልግሎት አላስፈላጊ ማህበረሰባዊ ግጭትን ለመቋቋም፣ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና የህዝቡን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽዖ ይኖረዋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ!

ጸሐፊውን በ Email: ahayder2000@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

 

Back to Front Page