Back to Front Page


Share This Article!
Share
ከሃሳዊ ዴሞክራሲያውያን እንጠበቅ

ከሃሳዊ ዴሞክራሲያውያን እንጠበቅ

አዲስ ቶልቻ 09-03-18

ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የተለያየ የማንነት መገለጫ ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ ሃገር ነች። ይህ እውነት ነው፤ የለም አይደለም ለሚል ድርድር አይጋብዝም፤ የማያከራክር መሬት ላይ ያለ ተጨባጭ እውነት በመሆኑ። ብዝሃ ብሄር ኢትዮጵያ በተለያዩ የመንግስት ስርአት ስር ያለፈች ባለታሪክ ሃገርም ነች። ኢትዮጵያ ካለፈችባቸው ስርአቶች አመለካከቶች (ርዕዮተ ዓለሞች)፣ እንዲሁም ከተለያየ ፍልስፍና የመነጩ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚደግፉና የሚያራምዱ ዜጎች መኖሪያም ነች።

በኢትዮጵያ አሁንም የዘውዳዊውን ስርአት የሚደግፉ የአሃዳዊ ስርአት አመለካከት አራማጆች አሉ። የወታደራዊውን ደርግ የአሃዳዊ ሃገርና ኮምኒስታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ደጋፊዎችና አራማጆችም አሉ። የሃገሪቱ ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ የሚኖሩበትን ፌደራላዊ ስርአትና የልማታዊ መንግስት አስተሳሰብን የሚደግፉና የሚያራምዱም አሉ። የምዕራባውያንን የሊበራል ዴሞክራሲና የሶሻል ዴሞክራሲ አመለካከቶች የሚደግፉና የሚያራምዱም አሉ። ሁሉም በሰላማዊ መነገድ አመለካከታቸውን የማራመድ ህገመንግስታዊ መብት አላቸው።

በዚህች የብሄርና የርዕዮተ ዓለም ብዝሃነት ባላት ሃገር ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። ዘውዳዊው ስርአት የብሄርና የአመለካካት ብዝሃነትን አለመቀበሉ የውድቀቱ ምክንያት ነው። ወታደራዊው ደርግም በተመሳሳይ ለብሄርና ለአመለካካት ብዝሃነት እውቅና የሚሰጥ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑ የውድቀቱ ምክንያት ነው። የወታደራዊው ደርግ ዴሞክራሲያዊ አለመሆን የቀሰቀሰው የብሄራዊ ነጻነትና እኩልነት ጥያቄ ላይ የተመሰረተ እስከ ትጥቅ የዘለቀ ትግል ሃገሪቱን ለመበታተን አደጋ አጋልጧት የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

Videos From Around The World

ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ እንደ ሃገር የመቀጠል ያለመቀጠል እጣ ፈንታዋን የሚወስን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ፣ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ለብሄራዊ ማንነቶችና ለማናቸውም አመለካከቶች እውቅና የሚሰጥ ህገመንግስት ተቀረጸ፤ የኢፌዴሪ ህገመንግስት። በዚህ ህገመንግስት መሰረት ላለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄሮች እስከመገንጠል የደረሰ ራስን በራስ የማሰተዳደር መብታቸው ተረጋግጦላቸው በፍቃዳቸው የኢትዮጵያ አካል ሆነው በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት እየኖሩ ይገኛሉ። በህገመንግስቱ በተረጋገጠው የአመለካከት ነጻነት መሰረት በተለያየ አመለካከት የተደራጁ ፓርቲዎችም ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ፣ በህገመንግስት የተረጋገጠው የዴሞክራሲ ነጻነት ከአተገባበር ረገድ ጉልህ ችግር ታይቶበታል። ህገመንግስቱ በስራ ላይ በዋለባቸው ያለፉ ሁለት አስር ዓመታት የተካሄዱ የፌደራልና የክልል መንግስታት ምርጫዎች ላይ በተለያየ አመለካካት የተደራጁ በርካታ ፓርቲዎች ቢሳተፉም፣ ምርጫው ግን ተአማኒነት የጎደለው መሆኑን ሲናገሩ ቆይተዋል። አመለካከትን በነጻ በማራመድ ረገድም ችግሮች እንደነበሩ ሲነገር ቆይቷል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በመላ ሃገሪቱ ተንቀሳቅሰው የመስራት፣ ደጋፊዎቻቸውን የመሰብሰብ፣ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ የማሰማት ህገመንግስታዊ መብታቸው ታግዶ እንደነበረ በተለያየ ጊዜ ሲያሰሟቸው የነበሩ አቤቱታዎች ያመለክታሉ። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝግ ነበሩ። የህዝቡን ብሶትና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አመለካከትና አቋም ያንጸባርቁ የነበሩ የግል መገናኛ ብዙሃን ላይም በመንግስት ጫና ይደረግ እንደነበረ የሚያመለክቱ ተጨባጭ አስረጂዎች አሉ።

በመንግስት የሚደረገውን ጫና ተጋፍተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ህዝብን በተሳሳተ መረጃ በመንግስት ላይ በማነሳሳት፣ በሽብርተኝነትና በመሳሰሉ ወንጀሎች ሲከሰሱ መቆየታቸውን የሚማለክቱ ተጨባጭ አስረጂዎች አሉ። በቀላጤ ትእዛዝና በተለያዩ አሳሪ ህጎች የሚደረገውን ጫና ተጋፍተው የሚሰሩ የግል ፕሬሶች ጋዜጠኞችና አዘጋጆችም ለእስር የሚዳረጉበት ሁኔታ ነበር።

ለዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ የሆኑ ሲቪክ ማህበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የነጻ ፕሬስ እንቅስቃሴን የሚገድቡ አሳሪ ህጎች - የሲቪክ ማህበራትና በጎ አድራጎት ድርጀቶች አዋጅ፣ የመረጃ ነጻነትና የመገናኛ ብዙሃን አሰራር አዋጅ፣ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ወዘተ ጸድቀው ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉም እንደችግር ሲነሳ ቆይቷል። እነዚህ አዋጆች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ነጻው ፕሬስ በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ከማደረጋቸው ባሻገር፣ በርካቶች ህጎችን በመተላለፍ ክስ እንዲመሰረትባቸውና በቅጣት እንዲታሰሩ ምክንያት ሆነዋል። በአጠቃላይ የሃገሪቱ የዴሞክራሲ ሜዳ/ምህዳር ህገመንግስቱ በሚፈቅደው ልክ ሰፊ አልነበረም።

በተገደበው የዴሞክራሲ ሜዳ ውስጥ መንቀሳቀስ ያልቻሉ ፓለቲከኞችና ጋዜጠኞች ሃገሪቱን ለቀው ለመሰደድ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሃገር ለቀው ከወጡት የተወሰኑት በምእራባውያን ሃገራት የተቃውሞ ፖለቲካ አራማጅ በመሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በፖለቲካ ፓርቲነት በመደራጀት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወቃል። በጎረቤት ሃገራት በተለይ በኤርትራ ሸፍተው በትጥቅ ትግል የሥርአት ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ እንደነበሩም እናውቃለን።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ሁኔታዎች ህዘቡ የዴሞክራሲ ጥያቄ አንግቦ ለተቃውሞ እንዲነሳ ምክንያት ሆነዋል። በተለያየ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ጥያቄዎች ሲቀርቡና የተቃውሞ ድምጾች ሲሰሙ ቆይተዋል። በተለይ ከ2008 ዓ/ም መግቢያ ጀምሮ የተካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከረር ያሉ ነበሩ። የዴሞክራሲ ሜዳ ሲጠብ ህዝባዊ እምቢተኝነት ፈንድቶ መውጣቱ አይቀሬ ነው። የ2008ቱን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከተሉ የፖለቲካ ምህዳሩን ህገመንግስቱ በሚፈቅደው ልክ የማስፋት ጉዳይ ችላ ሊባል የማይችል ሆነ።

በዚህ መሰረት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በሃገሪቱ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የዴሞክራሲ ምህዳሩን የማስፋት ዓላማ ያለው ድርድር ለማካሄድ ጥሪ አስተላለፈ። በዚህ ጥሪ መሰረት በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ ምህዳሩን ሊያሰፉ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ መደራደር ጀመሩ። በዚህ ድርድር በተለይ የምርጫ ህጉ ላይ የሚገኙ በርካታ ድንጋጌዎች እንዲሻሻሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከእነዚህ መሃከል የቀላል አብላጫ አሸናፊነት ስርአት፣ የአብላጫና የተመጣጣኝ ውክልና ቅይጥ ሆኖ እንዲሻሻል የተደረሰበት ስምምነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ከምርጫ ህጎች በተጨማሪ የጸረሽብርተኝነት፣ የመረጃ ነጻነትና የሲቪክ ማህበራት አዋጆችንም ለማሻሻል አጀንዳ ይዞ እንደነበረ ይታወሳል። ድርድሩ አሁን አላለቀም፤ በእንጥልጥል ላይ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አካሂዶ በ2010 ዓ/ም አጋማሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ ወንጀል የተከሰሱና የተፈረደባቸው ፖለቲከኞች በይቅርታ እንዲለቀቁ ወሳኔ አሳልፏል። የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በውጭ ሃገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ጥሪ መስተላለፉ ይታወሳል።

ይህ ውሳኔ በኢህአዴግ ውስጥ በተካሄደው በጥልቀት የመታደስ እርምጃ ወደሃላፊነት በመጡት የግንባሩ ሊቀመነበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህ መሰረት ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩና የተፈረደባቸው በርካታ ፖለቲከኞች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲሁም ብይቅርታ ክእስር እንዲለቀቁ ተደረጓል። በውጭ ሃገራት ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት ጭምር፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያራምዱ የነበሩ ግለሰቦችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የተቃውሞ እንቅስሴ ልሳን የነበሩ ሚዲያዎች ወደሃገር ቤት እየገቡ ይገኛሉ። ተቃዋሚዎቹን ወደሃገር ቤት እንዲገቡ ያደረጋቸው መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያለው ቁርተኝነትና በተጨባጭ የሚታየው መሆኑ ነው።

አሁን የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ህገመንግስቱ በሚያዘው ልክ ይሰፋል የሚል እምነትና ተስፋ ተፈጥሯል፤ በዜጎችም በፖለቲከኞችም ዘንድ። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ይህ ሃገራዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደረጉትን ወጣቶች ሽፋን በማደረግ አልፎ አልፎም መንግስት ባደረገው ጥሪና በሰጠው ምህረት መሰረት ወደሃገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሽፋን በማደረግ ኢዴሞክራሲያዊና ህገወጥ ድርጊቶች እየተከናወኑ ነው። በኦሮሚያ በቄሮና በኦነግ ሽፋን፣ በአማራ ፋኖ የመል ስያሜ በተሰጠው የህዝባዊ እንቅስቀሴ አራማጅ ቡድን ሽፋን የሚፈጸሙት ወንጀሎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የዚህ ማሳያዎች ናቸው።

በኦሮሚያ የለወጡ ሃይል በሆነው ቄሮ ስም ዘረፋና ግድያ ከመፈጸሙ ባሻገር የመንግስት መዋቅሮች ሰራ እንዳይሰሩ እየተደረገ ይገኛል። በአማራ ክልልም የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት በመጣስ ግድያዎች እየተፈሙ መሆኑ ይታወቃል። የዜጎች የፈቀዱበት ቦታ የመኖር፣ የመስራትና የመዘዋወር ሰብአዊ መብትና ነጻነትም በገሃድ እየተጣሰ ነው። የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴም እየተስተጓጎለ ነው። ሰዎች በብሄራዊ ማንነታቸው ብቻ ሰብአዊ ክብራቸው እየተነካ ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ የብሄር ጥላቻ ቅስቀሳዎች እየተካሄዱ ነው። የኢትዮጵያ አንድነት ደጋፊ ነን በሚል ሽፋን ብሄር የሚለውን ቃል የሚጠሩ ዜጎች ጸረ መደመር በሚል ፍረጃ የሚዋከቡበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ወከባ የሚያድነው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ብሄር አባል መሆን ብቻ ነው። ከጥቃት የሚከልለው  ህግ ሳይሆን ብዙ ቁጥር ያለው ብሄር አባል መሆን እየሆነ ነው። ይህ በተግባር እየታየ ነው። መከባበር ሳይሆን መፈራራት የበላይነት እየያዘ ነው።

እንግዲህ፣ ዴሞክራሲ የሌሎችን መበቶቸና ነፃነቶች፣ ሰብአዊ ክብርን መንካትን አያጠቃልልም። የህግ የበላይነትን ችላ በሎ ወይም የህግ የበላይነት እንዳይከበር እንቅፋት በመፍጠር የሚከናወን የመብትና የነጻነት ጥሰት ዴሞክራሲ ሳይሆን ስርአተ አልበኝነት ነው። አሁን በሃገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የስርአተ አልበኝነት አዝማማያዎች እየታዩ ነው። ይህ ስርአተ አልበኝነት በዚህ ከቀጠለ የዴሞክራሲው ሜዳ መጥበብ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ መጥፋቱ አይቀሬ ነው። አሁን የተፈጠረው የሃገሪቱ የዴሞክራሲ ሜዳ ህገመንግስቱ በሚፈቀደው ልክ ይሰፋል የሚለው ተስፋ መና ሆኖ ለመቅረት አደጋ ተጋልጧል። እናም በዴሞክራሲያዊነት ሽፋን ተስፋ የፈነጠቀውን የሃገሪቱን ዴሞክራሲ ለማጨለም ከሚንቀሳቀሱ ሃሳዊ ዴሞክራሲያውያን መጠበቅ አለብን።

  

Back to Front Page