Back to Front Page


Share This Article!
Share
የሕግ የበላይነት መከበር ወሳኝነት

የሕግ የበላይነት መከበር ወሳኝነት

ይልቃል ፍርዱ 08-07-18

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን ለውጥ ማስቀጠል የሚቻለው መሰረታዊ የሆነው የሕግ የበላይነት በሁሉም መስክ መከበር ሲችል ብቻ ነው፡፡የተጀመረው ለውጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍን አግኝቷል፡፡ ይህንን ታላቅ የሕዝብና የአለም አቀፉን ሕብረተሰብ፤ በውጭ ነዋሪ የሆነውን የዲያስፖራ ድጋፍ ያስገኘ የለውጥ ሂደት ጠብቆ ለማስቀጠል ቁልፉ ጉዳይ የሕግ የበላይነትን መጠበቅና ማስከበር ነው፡፡

ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የበለጠ የሚከበሩት ማንኛውም አይነት የሕብረተሰቡ ጥያቄዎች መፍትሄ የሚያገኙት የሕግ የበላይነት ተከበሮ መቀጠል ሲችል ነው፡፡ያደጉ ሀገራት የሚባሉት ለዛሬ ሀገራዊ ልእልናቸው የበቁት ሕግና ስርአትን ጠብቀውና አስከብረው መዝለቅ በመቻላቸው ነው፡፡የሕግ የበላይነት ከፈረሰ ሀገር ወደማትወጣው ምስቅልቅልና ትርምስ ውስጥ ትገባለች፡፡ሕግና ስርአትን የሚያስከብር አካል ካልኖረም የከፋ ስርአተ አልበኝነት ይነግሳል ፤ የዜጎች መብትና ንብረት ይዘረፋል፤ሕይወታቸውም በጎበዝ አለቆችና በየመንደር ጉልበተኞች እጅ ይወድቃል፤ሴቶች ይደፈራሉ፤ ዜጎች በአደባባይ ይገደላሉ፡፡

ሕግና ስርአት ፈረሰ ማለት ሀገር ጠፋች ወደመች የማንም መፈንጪያ ሆነች ማለት ነው፡፡ ይህ ነው በቀድሞዋ ሶማሊያ፣ በዩጎዝላቪያ፣ በኢራቅ፣ በሶርያ፣ በየመንና በሌሎችም ሀገራት የታየውና የሆነው፡፡ በለውጥ ስም በዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄና የተሻለ ስርአት በመናፈቅ የተነሳውን የሕዝቦች ትግል የጠለፉት የለውጡ ተጻራሪ ኃይሎች የቀሰቀሱት አመጽና ሁከት የስራ ማቆም አድማ፣ የእርስ በእርስ ግጭት በስሜታዊነት በእልህና በከፋ ጥላቻ ታጅቦ እልቂትና ውድመትን ሲያስከትል አይተናል፡፡ በዚህም የየራሳቸውን ሀገር የጥንት ስልጣኔ፣ በዘመናት ሊተኳቸው የማይችሏቸውን ቅርሶች፣ የኢኮኖሚ ልማቶቻቻውን፣ መሰረተ ልማቶችን፣ ድልድዮችን፣ ፋብሪካዎችን፣ የውኃ መስመሮችን የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያዎችን ወዘተ አጥተዋል፡፡ሕዝብ የጠበቀው የተሻለ ለውጥም ሊገኝ አልቻለም፡፡ ይብሱንም ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ቀድሞ ከነበረውም በአጅጉ የከፋ ሁኔታ ተፈጥሮ ሀገራት እስከ መበታተን ደረሱ፡፡

የእነዚህ ሀገራት ቀውስ ለዓለምም ጠንቅ ሆኗል፡፡ ዓለም በተለይም የአውሮፓ ሀገራት የሚመጡባቸውን ስደተኞች ማስተናገድ እስከ ሚያቅታቸው ድረስ ተፈትነዋል፡፡ ሀገራቱ ከገቡበት ቀውስ መውጫው መንገድ ጠፍቷቸው ፈራርሰዋል ፤ ዜጎቻቸውም ለእልቂትና ሞት ተዳርገዋል፡፡ይህ አይነቱ የየሀገራቱ ተቃዋሚዎች የከፋ እብደት፣ ስሜታዊነት፣ ጭፍንነትና ጥላቻ ያስከተለው ጥፋትና ውድመት እንዲህ ነው ተብሎ ሊገመት የሚችል አይደለም ፡፡ያወደሙት የየራሳቸውን ሀገር ነው፤ሞት እልቂትና ስደት ያወጁትም በራሳቸው ሕዝብ ላይ ነው፡፡

እኛ እንደ አንድ ትልቅና ታሪካዊ ሕዝብ የሚበጀን ሀገራዊ ሰላማችንንና ደሕንነታችንን እየጠበቅን ጥያቄዎቻችንን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማሰማት የተጀመረው ለውጥ ሳይደናቀፍ ለበለጠ ውጤት መሰራት ብቻ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ለውጥ የሚገኘው ቀድሞ በተሰራው በጎና መልካም ስራ ላይ በጎደለው እያከሉ መሻሻል ያለበትን እያረሙና እያስተካክሉ በመጨመር ከትላንት የበለጠና የተሻለ ስራ ለሀገርና ለወገን በመስራት እንጂ ትላንት በትውልድ ፈረቃ የተገነባውን በማፍረስና በማውደም አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም፡፡

Videos From Around The World

በየትኛውም አካባቢ የተሰሩት የልማት ስራዎች ሁሉ የዚህችው ሀገር ሀብትና ገንዘብ የዜጎችዋ ጉልበት የፈሰሰባቸው ናቸው፡፡ ጠብቆና ተንከባክቦ መያዝ የዜጎችና የትውልዱ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግስት ቢለወጥ ባለበት ቢቀጥል እነዚህ ንብረቶች የሀገር ሀብቶችና የትውልድም ቅርሶች ናቸው፡፡ የተዘረፉ ናቸው ከተባለም በሕግና በስርአት ሕጉ ያስመልሳቸዋል፡፡ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ይውላሉ፡፡ማውደምና ማጥፋት ግን እጅግ ጸረ ልማትና ጸረ ሀገር ስራ ነው የሚሆነው፡፡

ጥንትም የነበሩትን ሆነ በዘመነ ኢሕአዴግ የተሰሩትን ታላላቅ የልማትና የግንባታ ስራዎች ጠብቀን በተሰሩት ላይ እየጨመርን የበለጠ ሀገራችንን በልማት ማሳደግ ነው የሚገባን፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሆን ተብሎ ለውጡን ለማደናቀፍ በሚጫሩ ግርግርና ሁከቶች መንስኤነት አንድም ንብረት ሊወድም በእሳት ሊጋይ አይገባም፡፡ያን ያህል የተረፈንና የሞላን አይደልንም፡፡ ከድሕነት ለመውጣት ታላቅ ትግል በማድረግ ላይ ባለች ሀገር ውስጥ ነገና ከነገ ወዲያም ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅሙ ንብረቶችን ማውደም መልሶ የሚጎዳው ሀገርና ሕዝብን ነው፡፡ ወጣቶቻችን ሀገራዊ ሀብትና ንብረታቸውን መጠበቅና መንከባከብ እንጂ በስሜታዊነት ተውጠው ሊያወድሙ አይገባም፤የራሳቸው ንብረት መሆኑን መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕግና ስርአትን ማክበርም ተገቢጉዳ መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

የነበረንን በስንትና ስንት ልፋትና ድካም የተገነባን መሰረተ ልማት የተገዛን ንብረት እያወደሙ ሀገር እናለማን እናሳድጋለን ማለት አይታሰብም፡፡ለዚህ ነው የሕግና ስርአት መከበር ለሀገርና ለሕዝብ ያለው ጠቀሜታ በእጅጉ የጎላ የሚሆነው፡፡ሕግና ስርአት ሲከበርና ሲኖር ብቻ ነው በሰላም ወጥቶ በሰላም ወደቤት መመለስ የሚቻለው፡፡ሕግና ስርአት ሲከበር ብቻ ነው ዜጎች አስተማማኝ ሰላማዊ ሕይወት ሊኖራቸው የሚችለው፡፡ ለሕግና ስርአት መከበር ሁሉም ዜጋ ጸንቶ መቆም ያለበት የሚገባውም ለዚህ ነው፡፡

የተጀመረወን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ ፈርጀ ብዙ ሴራዎች መልካቸውን እየለዋወጡ በመከሰት ላይ መሆናቸውን ሕዝቡ እያስተዋለ ነው፡፡ ሕዝብን ስሜታዊ በማድረግ ሀገራዊ ትርምስና ሁከት እንዲፈጠር፣ ሕግና ስርአት እንዲፈርስ፣ ስርአተ አልበኝንት እንዲነግስና ሀገራችን ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ እንድትነጉድ ለማድረግ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፤አብዛኛዎቹ ግን በሕዝቡ አርቆ አሳቢነት ከሽፈዋል፡፡

የለውጡን ሂደት ለማጨናገፍ ሆን ተብሎ እየተሰራ ያለው ስራ መልኩን እየቀያየረ ቢከሰትም አልተሳካም፡፡እስከአሁን ሕዝቡና ወጣቱ በታላቅ አስተዋይነትና ትእግስት ስሜታዊነትን በማስወገድ የከፋ ችግር እንዳይከሰት አድርጓል፡፡ይህ የበሰለና በአስተዋይነት የተሞላ ትእግስት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ መንግስትም እንደ መንግስት የራሱን መንግስታዊ ኃላፊነት በመወጣት ለችግሮች ሁሉ እልባት እየሰጠ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡ ለሕግ የበላይነት መከበር ትልቁ ድርሻ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ነው፡፡የሰላሙ የልማቱ ተጠቃሚ የእድገቱና የሀገሩም ባለቤት ሕዝብ ነውና፡፡ የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ለድርድር የማይቀርብ ሌላ አማራጭ የሌለው ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ነው፡፡

ዜጎች በማንኛውም አይነት ሁኔታ ድጋፋቸውን ማሰማት፤ተቃውሞአቸውንም መግለጽ የሚችሉት ፍጹም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ረብሻ ሁከት ድንጋይ ውርወራ ንብረት ማውደምና ማቃጠል በዜጎች ሕይወት ላይ አደጋ ማድረስ ስርአተ አልበኝነትን ይፈጥራል፡፡የሕግ የበላይነትን ይጻረራል፡ እንዲህ አይነቱ እንቅስቃሴና እርምጃ የለውጡን ሂደት ሆን ተብሎ ለማሰናከል የሚደረግ ሴራ አካል ከመሆኑም አልፎ ሙሉ በሙሉ የሥርዓተ አልበኝነት መገለጫ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ሕዝብና መንግስት ሊታገሱት አይገባም፡፡

የለውጡ ሂደት ያስመዘገባቸውን ተጨባጭ ውጤቶች በመደግፍ ስም በአንዳንድ አካባቢዎች የተደረጉ ሰልፎች መሰረታዊ አላማቸውን ስተው በለውጡ መደመር ስምና ሽፋን በአመራሮችና ሕጋዊ ተቋማት ላይ ጥቃት የመፈፀም፣መንገዶችን የመዝጋት፣ የግለሰቦችንና የመንግሥት ንብረቶችን የማውደም ተግባራት ሲፈጸሙ በተጨባጭ ታይተዋል፡፡ይህ ድርጊት የስርአተ አልበኝነት መገለጫ እንጂ በምንም መልኩ የመደመር ለውጥ አካል ሊሆን አይችልም፡፡

የመደመር ለውጥ ከጥላቻ ከቂም በቀል ከትላንት ቁስል በመውጣት ፍቅርን፣ መቻቻል፣ መከባበርን ፣ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም ዘብ መቆምን፣ ይቅርባይነትንና በአዲስ አስተሳሰብ ለአዲስ ለውጥ መነሳትን የሚጠይቅ እንጂ ጥፋትና ውድመትን የሚደግፍ አይደለም፡፡ የለውጡን መሰረታዊ አላማና ግብ በውል መረዳትንም ይጠይቃል፡፡

ዛሬም ሀገራችንን ለረዥም ዘመናት ደፍቋት በኖረው ኋላቀር አስተሳሰብ ውስጥ የምንዋኝ ከሆነ የለውጡ አጋዥ ኃይል መሆን አይቻልም፡፡ይህንን አስተሳሰብ ይዘን ከለውጡ ጎራ መቀላቀል አይቻለንምና የመደመሩን እሳቤ በውሉ ተረድተን የየድርሻችንን በመወጣት የሀገራችንንና የህዝባችንን ተስፋ ማለምለም ይኖርብናል፡፡

 

Back to Front Page