Back to Front Page


Share This Article!
Share
ሕገ መንግስትና ጥሰተቹ

ሕገ መንግስትና ጥሰተቹ

 

Ahferom  Nigus  August 13, 2018

 

 

 

 

ዝርዝር

I.   ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች ስልጣን ላይ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና ህገመንግስቱ. 2

II.  የህገመንግስቱ የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት በተመለከተ. 2

III.   ህገመንግስቱ፣ ኢህኣዴግና ኣዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር. 3

IV.   በህገመንግስታዊና ሌሎች ፖለቲካዊ ክርክሮች ሃሳብና ተቃዉሞ የማቅረብ መብት በተመለከተ. 4

V.  የኣዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ህገመንስቱን የጣሰ ተግባር. 5

VI.   ሰላማዊ ለውጥና ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር. 7

 

 

 

I.          ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሎች ስልጣን ላይ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነትና ህገመንግስቱ

ሰሞኑ የዶ/ር ኣቢይ መንግስት በክልልሎች ስልጣን ላይ የሚያደርገው ጣልቃገብነትና በፌደራል መንግስት እንቅስቃሴዎች ዙርያ የሚነሳው የህገምንግስት ጥያቄና ክርክር  በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።

 

II.         የህገመንግስቱ የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት በተመለከተ

የመጀመርያው ህገመንግስቱ በህዝብ ዉይይትና ስምምነት ያልተመሰረተ ስለሆነ ልንገዛለት ኣይገባም የሚለው ሲሆን በዛው ኣቀራረብ ፌደራላዊ መንግስቱ ህገምንግስቱን ቢጥስ ኣያስጨንቀንም፥ ይበለው የሚል መንፈስ ያለበት ነው። በመጀመርያ ደረጃ  ህዝቡ ኣልተወያየበትም የሚለው ሃሳብ እዉነትነት የለዉም። በየደረጃዉና በብዙ ያገራችን ኣካባቢዎች በጣም ሰፊ ሊባል የሚችል የህዝብ ዉይይት የተደረገበት እንደሆነ የህገመንግስቱ የማረቀቅ ሂደት ሰነዶችና  በጊዜው የነበሩ  ብዙ ሰዎች ምስክርነታቸው የሰጡበት ጉዳይ ነው።ሆኖም፦

Ø  ኣማራጭ ሃሳቦች በተሟላና በበቂ ሁኔታ ለህዝቡ ኣልቀረቡም።

Ø  ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኣማራጮቹ ዙርያ ያላቸው ልዩነትና ተቃዉሞ ለህዝቡ እንዲያቀርቡ እድል ኣላገኙም።

Ø  በነበረዉ ዉይይት የቀረቡ የህዝብ ሃሳቦች በተገቢው ኣንዲታዩና እንዲካተቱ ኣልተደረገም።

የተደረገዉን ሙሉ በሙሉ በመካድ ከሚቀርብ ክርክር የነበረዉ ሁኔታ በኣግባቡና በትክክል በመግለጽ  እውነትና ሚዛናዊ ኣቀራረብ መከተሉ  ተገቢ ነው።

ሆኖም ይህ ክርክር በተጨባጭ በኣሁኑ ወቅት ካለንበት ችግርና ወደፊት የኣገራችን ፖለቲካዊ ስርኣት ኣቅጣጫ በተመለከተ ከምንፈልገው  ኣንጻር የታሪክ ግምገማ ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለዉም ። ህገመንግስቱ በህዝብ ውይይትና ስምምነት ቢጸድቅም ባይጸድቅም ወደፊት መገንባት ከምንፈልገው ኣገራዊ ኣንድነትና ሊገጥመን ከሚችለው ፈተና ኣንጻር ህገመንግስቱን ተቀብለንና ኣክብረን መንቀሳቀስና ኣዲሱ የፌደራል መንግስትም በዚህ መንፈስና ኣካሄድ በጥብቅ እንዲሄድ ማድረግ የበለጠ ጥሩ መፍትሄ ነው። ይህም፦  

Ø  በቀዳሚነት ህገመንግስቱ በተግባር መሰረታዊ የሚባሉ መብቶች ያካተተ በመሆኑ ባለበት ሁኔታ እንኳን በቅንነትና በተሟላ ሁኔታ ስራ ላይ ቢዉልና በጥብቅ ቢተገበር ኣብዛኛው የህዝቡ የመብት ጥያቄ መመልስና ማስከበር የሚችል በመሆኑ።

Ø  በመቀጠል የሚቀር ነገር እየታየ በህዝብ ተሳታፎና በዘርፉ ባለሞያዎች እገዛ ህገመንግስቱ ራሱ በሚያስቀምጠው የማሻሻያ ስርኣት ተከትሎ ሁሉኑም የህዝብ ፍላጎቶች ያካተተ ህዝባዊና ዘመናዊ ህገመንግስት ማድረግ የሚስያስችል ሰላማዊና ህጋዊ መንገድና እድል የሚሰጠን በመሆኑ።

Ø  በተጨማሪ ቁጥራቸው የፈለገ ቢሆንም በዚህ ህገመንግስት እምነት ያላቸው ዜጎችና የፖለቲካ ሃይሎች ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ኣካሄድ ዉጪ የሚደረግ ለውጥና እንቅስቃሴ የሚቃወሙ በመሆናቸው፥ ሲቃወሙ ሊከሰት የሚችል ጥፋትና ዉድመት እሱን ተከትሎ ባገር ህልዉናና ህዝቦች ኣንድነት ሊመጣ የሚችለው ኣደጋና ሁከት ለማስቀረትና የሚመጣው ለውጥ ሰላማዊና ገንቢ እንዲሆን ለማድረግ የሚመች በመሆኑ።

በነዚህ ነጥቦች በመመስረት በሂደትና በዲሚክራሲያዊ ኣግባብ እያሻሻሉ ጉድለቶች በማረምና የበለጠ ሰፊ መሰረትና ተቀባይነት ያለው ህገመንግስት እንዲሆን በማስቻል ወደፊት መንቀሳቀስ ይቻላል። ስለሆነም ህገምንግስቱ ሲጣስ ህጋዊና ሰላማዊ ለውጥ ለማምጣት ያለን እድል ስለሚያበላሽ እንደዛ ኣይነት ኣስተሳሰብና ኣካሄድ ተቀባይነት ሊኖረው ኣይገባም።ፌደራል መንግስትም ሆነ ሌሎች ኣካላት  ህጋዊና ሰላማዊ ለውጥ ለማረጋገጥ በማናቸዉም ጊዜና ሁኔታ ህገመንግስቱን ኣክብሮ መንቀሳቀስ የማይታለፍ ግዴታቸው መሆን ኣለበት።

Videos From Around The World

በዚህ መሰረት ኣዲሱ የፌደራል መንግስት ኣመራር በኢትዮሶማሌ ክልል፣በደቡብ ህዝቦች ክልል።በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይና የህዝብ ተሳትፎ ጥያቄ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ በንግግርና በተግባር የሚያካሂዳቸው ህገመንግስቱን የሚጥሱ ተግባራት እንደ ሃገር ህጋዊና ሰላማዊ ለውጥ ለማካሄድ  ያለው እድል በመዝጋት ኣላስፈላጊና ኣደገኛ ሁኔታ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ሊቆሙ ይገባል። ደጋፊዎችም በዚህ  መንፈስ ህገመንግስቱ በሁሉም ኣካላት እንዲከበር ግፊትና ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል።  

III.        ህገመንግስቱ፣ ኢህኣዴግና ኣዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር

ሁለተኛው ደግሞ ህገመንግስቱን በማረቀቅና በማጽደቅ ዋናዉን ሚና የተወጣዉና የርሱን ፍላጎቶች ሙሉ በሙሉ በማካተት በተግባር የህገመንግስቱ ባለቤት የሆነው ህወሃት/ኢሕአዴግና መሪዎቹ ህገመንስቱን ባለማክበርና በተደጋጋሚ በመጣስ ከስራ ዉጪ ያደረጉት በመሆኑ ኣክብሩት ለማለት ተገቢ ብቃት የላቸዉም ሌሎችም ቢሆን ባለቤቱ ያላከበረው ህገመንግስት  የማክበር ግዴታ የለባቸዉም የሚለው ክርክርና ሃሳብ ነው።

ኢሕአዴግና መሪዎቹ ህገመንግስቱን በብዙ መልኩና በሰፊው ከቃል የዘለለ በተግባር ሲያከብሩት እንዳልነበር የአደባባይ እዉነት ነው። እነሱም በግምገማቸው ኣምነው የተቀበሉት ሃቅ ነው። ሆኖም እንሱን የሚተችና ለውጥ የሚፈልግ ኣካል ራሱ በዚህ ምክንያት ህገመንግስቱን ባለማክበርና በመጣስ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ከነሱ ጋር ያለው የተግባር ኣንድነት ከማረጋገጥ ያለፈ የለውጥ ሃይልና ህግ ኣክባሪ ኣስተዳደር ሊሆን ኣይችልም። ስለዚህ ከነሱ የተለየ ኣይደለምና ኢህአዲግን ህግ ባለማክበሩ የተቃወመ ኣካል ኣዲሱ ሃይል ተመሳሳይ ተግባር ሲፈጽም ሊደግፈዉና ሊከራከርለት ኣይገባም።

ኣዲሱ የለዉጥ ሃይል የተለየና የተሻለ ከሆነ ከሱ በፊት ከነበሩት የኢሕአዴግ ኣመራሮች ሲጥሱት ስለነበረ እኔም በዛው መንገድ የምፈልገዉን ማድረግ እችላለሁ በማለት ሳይሆን  በተለየ ሁኔታ ህገመንግስቱን ከምንምና ከማንም በላይ በማክበርና በማስከበር ማሳየትና ማረጋገጥ ኣለበት።ለራሱ የሚመቸው ብቻ መርጦ እየለወጠና የማይመቸው መስሎ የታየዉን በጎን  እያለፈ የሚጥስ ከሆነ እውነተኛ የለውጥ ሃይል ሊሆን ኣይችልም።ተከታዮቹና ደገፊዎቹም ህገመንግስቱ እንዲከበር እንጂ ለጊዚያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል በግፋበለው ስሜት ህገመንግስቱን የሚጥስ ተግባር መደገፍ የለባቸዉም።

ከዚህ በፊት በነበረው ኣስተዳደርም ሆነ ኣሁን ባለው ኣመራር ህጉን ወደጎን በመተው ከፖለቲካዊ ድጋፍና ተቃዉሞ ኣንጻር ብቻ እያየን የምንደግፍና የምንቃወም ከሆነ እንደ ሃገር እውነተኛ የለውጥ ሃይል መገንባትና ማስቀጠል ኣንችልም። ስለሆነም ኣስተማማኝ፣ እውነተኛና ህጋዊ  መሰረት ያለው ለውጥ የምንፈልግና የምንደግፍ  ከሆነ ኣዲሱ የፌደራል መንግስት በተመለከተ ከባለፈው ሁኔታና ከፖለቲካዊ ትርፍ ኣንጻር ሳይሆን ከመርህና ከህጋዊነት ኣንጻር እየመዝን ድጋፍና ትችት ተቃዉሞና ሙገሳ ልናደርግለት ይገባል።

IV.        በህገመንግስታዊና ሌሎች ፖለቲካዊ ክርክሮች ሃሳብና ተቃዉሞ የማቅረብ መብት በተመለከተ

ሃሳብም ሆነ ተቃዉሞ  ማቅረብ በተመለከተም ህገመንግስቱን ያላከበረ የመንግስትና የኢሕአዴግ ኣካል በህግ መሰረት መጠየቅ ካለበትና በሌላ መልኩ መማር ካለበት እንደተጠበቀ ሆኖ ህገመንግስቱ ሲጣስ ይከበር ብሎ የመናገርና የመቃወም መብቱ ሊገፈፍ ኣይገባም።ኣንተ ኣላከበርክምና ኣንዲከበር መናገር የለብህም ወይም ኣትችልም የሚል ኣካሄድ ተገቢና ገንቢ ኣይደለም ብቻ ሳይሆን መርህና ህግ የሚጻረር የደካማ ክርክር ሂደት ነው።ኣይደለም በፖለቲካ ዉይይትና እንቅስቃሴ በወንጀል የተጠረጠረም ሆነ የተፈረደበት ሰው እንኳን፥ የሚያቀርበው ክርክርና የመብት ጥያቄ ከእውነትና ከህግ ኣንጻር እንጂ ኣንተ ወንጀለኛ ወይም ተጠርጣሪ ስልሆንክ በሚል ሃሳቡና ጥያቄው ዉድቅ ኣይደረግም። የጉዳዩ እዉነትነትና ህጋዊነት ኣንጂ የተናጋሪው ማንነትና ድህረ ታሪክ ኣስፈላጊና ወሳኝ መሆን የለበትም።  

ከዚህ ጋር በተመሳሳይ  በሌሎች ዜጎችም ላይ እስካሁን  በነበረው ህገመንግስታዊ ጥሰት ምንም ተቃዉሞ ስላልተንፈሳቹ ከኣሁን በኋላ በሚደረገው ህገወጥ ተግባር ተቃዉሞና ትችት ማቅረብ ኣትችሉም የሚለው ነው።በመጀመርያ ደረጃ ተቃዉሞ ማድረግና ኣለማድረግ የዜጎች መብት ነው። ይህንን መብት መቼና በምን ኣይነት ሁኔታ ጥቅም ላይ ይዉላል የሚለዉም እንደዚሁ ለራስቸው ለዜጎቹ የተተወ ነው።

ስለዚህ ይህ መብት በመጠቀምም ሆነ ባለመጠቀም የሚገኝ ተጨማሪ ኣዲስ መብትም ሆነ የሚሰረዝ ቋሚ መብት የለም። ስለሆነም ባለፈው ጊዜ ህግ ሲጣስ ያልተቃወሙ ዜጎች ኣሁን ተቃዉሞኣቸዉን በፈለጉት መንገድና ኣግባብ ማቅረብ የሚከላክላቸው ኣንዳችም የመርህም የህግም ሁኔታ የለም። ባለፈው ያልተቃወሙት ዜጎች ኣንደ ወኔ ቢስና የባልፈው ስርኣት የጥቅም ተጋሪ ኣድርጎ በማቅረብ በማሽማቀቅና ከጨዋታ ዉጪ በማድረግ ለውጡን በስህተት ጎዳና እንዲገፋበት ከማድረግ ዉጪ እዉነተኛና ገንቢ ለውጥ ማረጋገጥ ኣይቻልም። በድጋፊ ብዛትና የፕሮፓጋንዳ የበላይነት እነሱ እንዳይቃወሙ ግፊትና ጫና ፈጥሮ ጸጥ በማሰኘት፥ ህገወጥ ተግባርና ሃሰት የሆነዉን ነገር  በቀለም ቅብ በማስዋብ እዉነትና  ህጋዊ ማድረግ ኣይቻለም።ይልቁንም በማናቸዉም ጊዜ ህግ እንዲከበር የሚያደርጉት ተሳትፎ በራሱ ብቻ እንዲቀጥል ሊበረታታና ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል።

V.         የኣዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ህገመንስቱን የጣሰ ተግባር

ኣቶ መለስና በሁሉም ደርጃ የነበሩት የኢህኣዴግ ኣመራር ኣባላት የዜጎች መሰረታዊ መብቶች በመጣስም ሆነ የክልሎች ስልጣን በመጋፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፈጸሙት ተግባር በሙሉ ሕገመንግስቱን የሚጻረርና የሚወገዝ ተግባር ነው። በተመሳሳይ መልክ ዶ/ር ኣቢይም ሆነ ከርሱ ጋር ያሉ ኣመራሮች የግለስብ መብቶችን በተመለከተ ይሁን የክልል ስልጣን በመጋፋት የሚያደርጉት ማናቸዉም ተግባር ሊወገዝ ይገባል። ኣሳቻና ኮስማና ምክንያት እየተፈለገ፣ ከፖለቲካዊ ድጋፍና ተቃዉሞ ኣንጻር እየተመዘነ፣ በግልጽ ህገመንግስቱን ጥሰው የሚፈጽሙት ህገወጥ ተግባር እንዲገፉበት  መደገፍና ማበረታት ተቀባይነት ሊኖረው ኣይገባም።

ስለሆነም ኣዲሱ የፌደራል መንግስት በተለያዩ ኣጋጣሚዎች የሚሰጠው ዲስኩርና የሚወስዳቸው እርምጃዎች፣በደቡብ ህዝቦች ክልል ድርጅታዊና ፌደራላዊ ስልጣን በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ ማባባያ፣ጫናና ማስፈራርያ  በማሳደር የተደረገው ሹምሽር፣በሱማሌ ክልል ቂም በቀል ባዘለ ሁኔታ በቀጥታና በሃይል እየተደረገ ያለው ጣልቃገብነት እና ሌሎችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ህገመንግስቱን ኣከብራለሁ ብሎ ምሎ ስልጣን ከተቀበለ ኣመራር የሚጠበቅ ኣይደለም።

የክልሎች ስልጣንና የክልል ኣመራር በተመለከተ ፌደራሉ መንግስት የሚፈልገው ለዉጥ ካለ በጉልበትና በማስፈራራት ዘው ብሎ መፈትፈት ሳይሆን ህጉ የሚያስቀምጠዉን ኣካሂድና ኣሰራር በጥብቅ ተከትሎ የሚፈጸም መሆን ኣለበት።የሱማሌ ክልል ኣመራር የፈጸመው ጥፋት ካለ በዚህ ጥፋት መሰረት ሊደርግ የሚገባውና ህጉ የሚፈቅደው እርምጃ ህጉን ተከትሎ መዉሰድና ለህዝቡ ስለሂደቱና ስለምክንያቱ በተገቢውና በዝርዝር  ማሰውቅ  ይገባል።

ከዚህ ዉጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ እዚህም እዚያም ደጋፊ በማስቀመጥ ስልጣን ይዞ ለመቀጠል በሚደረገው ጥረት ትንሽ ፋታ ይሰጥ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ሰላምና ስርዓት ከማስጠበቅ ኣንጻር ጎጂ የሆነ ሚና እንድሚኖረው ኣያጠያይቅም።

ኣቶ መለስ ስልጣኑን ለማስጠበቅና ተቃዋሚዎች ለመመንጠር የፌድራልና የክልል ኣመራሮችን እንዳሻው ያወርድና ይሾም ኣንድነበረ የሚታወቅ ነው። ዶ/ር ኣቢይም በተመሳሳይ ይህንኑ ተግባር እንዳለ ስራ ላይ እያዋለው መሆኑ እየታየ ነው።በዚህ ነጥብ ሁለቱም ኣንድና ተመሳሳይ መሆናቸው ማየት ይቻላል። ያዉም ኣቶ መለስ ብስልትና በጥበብ እንዲሁም በድብቅ ሲያስፈጽመው ዶ/ር ኣቢይ ግን በግላጭ፣በሃይልና በትእቢት  የክልል መንግስታትን ለመቀየር ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።

ስለዚህ ኣቶ መለስን በዚህ ጉዳይ የተቃወሙ ሰዎች ኣሁን ዶ/ር ኣቢይን ቢደግፉ መርህና እውነት ረግጠው በመጨፍለቅ ለፖለቲካ ትርፍ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው በቀላሉ ማየት ይቻላል። ኣንድ ተግባር የተለያዩ ሰዎች ስለፈጸሙት ብቻ በኣንድ ጊዜ ትክክል በሌላው ጊዜ ስህተት ሊሆን ኣይችልም።

ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ኣገራችን ስልጣን ላይ ያለው ሰው ከመቀየር በዘለለ፥ ደጋፊን ህገወጥ በሆነ መንገድ ስልጣንና ጥቅም እንዲያገኝ ማድረግ፣ ተቃዋሚን በሰበብ ባስባቡ መደፍጠጥ፣ በሚለው የኣምባገነኖችና ህገወጦች የስልጣን ኣዙሪት እንደቀጠለች ነው የሚያሰየው። በዚህ ኣካሄድ ያው ኣሁን የሚገፋውና የሚገለለው ወገን ደሞ ጊዜ ጠብቆ ወንበሩን ይረከብና በተራው ኣዙሪቱን ተከትሎ ስልጣኑን ይጠቀማል። ስለዚህ ከዚህ ዓይነት ኣዙሪት በመውጣት እውነተኛ የለውጥ ሃይልና ሽግግር እንዲካሄድ የሚደግፍ ሰው ከኣንድ መጽሃፍ የተቀዱ ግን በተለያዩ ሰዎች ጥቅም ላይ የዋሉ ጉዳዮችን ከመርህና ከህግ ኣንጻር መቃወምና ማስቆም እንጂ ማጨብጨቡ ለማንም ኣይበጅም።

ማንኛዉም ዜጋ እንዲዚህ ኣይነቱ ኣይን ያወጣና በግላጭ የሚደረግ ህገወጥ ተግባር ለመቃወምና ለማወገዝ ከድሮ ጀምሮ የነበረ የተቃዋሚነት ልምድና ታሪክ ማቅረብ ኣያስፈልገውም። ጣልገብነቱና ሌላው የፌደራል መንግስቱ ተግባር  እውነት ስለመሆኑና ህገወጥ ስለመሆኑ በቅንነት ያመነ ማንኛዉም ዜጋ ሁሉ ለመቃወምና ለማዉገዝ የተሟላ መብት ኣንዳለው የተርገጋገጠ ነው። ጉዳዩ እውነት ካልሆነ በማስረጃ ማስተባበል፣ እዉነት ከሆነ በሚያሳምን ሁኔታ ማስረዳት፣ስህተት ከሆነ ማረምና ይቅርታ መጠየቅ የመንግስት ተግባርና ግዴታ ነው።

ከዚህ ዉጪ ትናንት የት ነበርክ ወይ ምን ብለህ ነበር በሚል ከጭብጡ ጋር ተያያዥነት በሌለው ኣፍ ማስያዣ ሙግት የተቃዋሚ ኣስተያትና የተቃዉሞ ድምጽ እንዲታፈን በማድረግ ጉዳዩን እዉነትና ህጋዊ ማድረግ ኣይቻልም።እንዲያዉም እንዲዚህ ኣይነት የማስመሰል፣የማስፈራራትና የማፈን ኣካሄድ የመረረ ስሜትና ጥላቻ እየፈጠረ ወደማንወጣበት ኣዘቅት የሚከተን ኣደገኛ ኣካሄድ ነው። ስለሆነም ጊዜው ሳይረፍድ መታረምና ገንቢ በሆነ እውነትና ህግን መሰረት ባደርገ የክርክር፣የድጋፍና ተቃዉሞ ስርኣት መተካት ኣለበት።

VI.        ሰላማዊ ለውጥና ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር

ኣዲሱ ፌደራላዊ መንግስት በፍቅርና በይቅርታ እንደመር በሚል እስረኞችን በመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን ሊያሰፉ የሚችሉ እርምጃዎች በመዉሰድ ሰፊ የፖለቲካ ለውጥ በማደርግ ላይ ይገኛል።ይህ ለውጥ እንደሚባለው ሰላም የሚያሰፍንና የምር ወደ ዲሞክራሲ የሚወስድ ሽግግር እዉን ማደርግ ይችላልን? ብለን ስንጠይቅ ካለፈው ታሪካችን ልምድና ባለፉት ሶስት ወራት ያየነው ኣካሄድ ከፍ ያለ ጥርጣሬና ጥያቄ የሚያስነሱ ኣያሌ ተግባራት እየተፈጸሙ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።።

ደርግ የሃይለስላሴ መንግስት ገርስሶ ስልጣን ሲይዝ ``ኢትዮጵያ ትቅደም ያለ ምንም ደም`` በማለት በእስር ላይ የነበሩ የንጉሱ ተቃዋዎች በመፍታትና የፖለቲካ ፓርቲዎች  እንዲመሰረቱና እንዲንቀሳቀሱ በመፍቀድ  የጀምረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በራሱ ላይ ተቃዉሞ ሲነሳበት በፍጥነት ወደ ማሰርና መግደል በመግባት የፖለቲካ ድርጅቶችንም ከጨዋታ ዉጪ እንዳደረገ የቅርብ ጊዜ የታሪክ ትዝታ ነው።

በተመሳሳይ ኢህኣዴግም ደርግን ጥሎ ስልጣን ሲይዝ የደርግ ተቃዋሚዎች በመፍታትና ካሁን በኋላ  ሰላም ኣንጂ ጦርነት ቦታ የለዉም በማለት ሰፊ የዲሚክራሲ ስርኣት ግንባታ እንደጀመረ ይታወቃል።ቆይቶ ግን በራሱ ላይ የተነሱት ተቃዋሚዎች በማሰርና መብት በመገደብ ስልጣኑን በማጠናከር ዙርያ እንደተጠመደ ኣይተናል።

ኣሁንም ኣዲሱ የፌደራል መንግስት ከሱ በፊት የነበረው መንግስት ተቃዉመው ለእስር የተዳረጉት ሁሉ በመፍታት የፍቅርና የይቅርታ ዲስኩር እያሰማ ይገኛል።ሆኖም እዛው በዛው ለውጥ ኣደናቃፊና ሌሎች ስያሜዎች እየለጠፈ የማግለልና የመበቀል እንቅስቃሴ  እያደረገ ሲሆን ኣልፎ ኣልፎም የሚቃወሙትንና በግል የተጣሉትን ሳይቀር የማሰርና በፖለቲካዊ ስልት የመድፈቅ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየታዝብን እንገኛለን። በዚህም የፍቅርና የይቅርታ ንግግሮችና በተግባር የሚካሄደው የፌደራሉ መንግስት እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየተለያዩ መሄዳቸዉን በግልጽ ማስተዋል ይቻላል።

እውነትኛ የይቅርታ፣የሰላምና የዲሚክራሲ መንገድ በራስ ስልጣን ላይ የተናሳና የሚቀርብ ተቃዉሞ በይቅርታና በፍቅር በማስተናገድ የሚገነባ እንጂ ያለፈው ስርኣት የተቃወሙትን በማቀፍና በመሳም የሚፈጸምና የሚወሰድ የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰብያ  ሁኔታ ኣይደለም።ይህንንማ ሁሉም ያለፉት መንግስታት ኣድረገዉታል።ስለዚህ ኣሁንም ለውጡ በተለመደው የባለጊዜና የኣሸናፊነት መንፈስ ስልጣን ይዞ ለመቀጠል የሚደረግ ኣዙሪት ከመሆን የሚዘል ኣይመስልም። 

 

Back to Front Page